Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢንዱስትሪ ጉዞውን ለማሳለጥ…

0 352

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢንዱስትሪ ጉዞውን ለማሳለጥ…

አባ መላኩ

የኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲቀረፅ ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣትና አገሪቱን ከበለፀጉት አገራት ጎን በማሰለፍ ለልማታዊ ባለሀብቱ ቀጥተኛ ድጋፍ በመስጠት የኢኮኖሚ ልማቱ ዋና ሞተር እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡

የግብርና ግብዓቶችንና ጉልበትን በሰፊው በሚጠቀሙ፣ ከፍተኛ እሴት በሚጨምሩና ለኢንዱስትሪ ሽግግር ሁነኛ አስተዋጽኦ የማድረግ አቅም ባላቸው ቀላል ኢንዱስትሪዎች ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው። በዚህም ባለፉት ዓመታት መንግሥት በአግሮ ፕሮሰሲንግ መስክ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ከፍተኛ ድጋፍ  በማድረግ ላይ ነው።

የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ትኩረት በወጪ ንግድና ስትራተጂ ገቢ ምርቶችን በመተካት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ ተግባር እየተከናወነ ነው። የወጪ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲኖራቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተሻለ የካፒታል አቅም እንዲኖራቸው ብድር የማመቻቸት፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውና በዘመናዊ የማኔጅመንት አመራር አቅማቸው እንዲያድግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡

የኢንዱስትሪዎቹን የገበያ ሁኔታ በማመቻቸት ረገድም የኢንዱስትሪ መንደሮች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ አንዳንድ ፓርኮች ወደ ሥራ መግባት ጀምረዋል። ሌሎች ደግሞ በተለያዩ የግንባታ ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ። አስፈላጊ መሠረተ ልማት በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማሟላት መንግሥት ከፍተኛ በጀት መድቧል።

ለኢንዱስትሪ ልማት ትልቁን ሚና የሚጫወተው የኤሌክትሪክ ኃይል ነው። በዚህ ረገድ አገሪቱ ባለፉት 26 ዓመታት ጉዞ እመርታዊ ለውጥ ከተመዘገበባቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች መካከል ቀዳሚው  ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ የሚዘልቅ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ የዜጎችን ህይወት ለመቀየርና የአኗኗር ዘይቤን ለማዘመን፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ምርት ለማቅረብ እጅግ ወሣኝ  ነገር ነው።

 

በኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከ370 ሜጋ ዋት ያልበለጠ ነበር። በዚህ ምክንያት ትንንሽ ከተሞችና ገጠሮች ቀርቶ ዋና ዋና ከተሞችም ቢሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በተሟላ መልኩ ማዳረስ የማይታሰብ ነበር። ይህም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በአሁኑ ወቅት ጊቤ ሦስት 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ጨምሮ የሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ የአገሪቱ የኃይል አቅርቦት  ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ይደርሳል። ይህ ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ልማት የምታደርገውን ጥረት የሚያሳካ ይሆናል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፉ ከሚገኙት መሠረተ ልማቶች  መካከል የትራንስፖርት መስኩ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለትራንስፖርት መሠረተ ልማት የተመዘገበው ስኬት መንግሥት አገሪቱን በትራንስፖርት መረብ በማስተሳሰር አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ በመንገድ፣ በአየር፣ በባቡርና በመርከብ ትራንስፖርት ልማት በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ ነው።

 

ሌላው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ ረገድ በስፋት እየተሰራበት ያለውን ሁኔታ ማየት ይቻላል። በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በመካከለኛ ደረጀ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማግኘት የሚከብድ አይደለም። የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥር ከሁለት ወደ 34 ማደጉና ለኢንዱስትሪ ልማት ቀጣይነት ወሣኝ የሆነ የሣይንስና የኢንጂነሪንግ ባለሙያ የሰው ሀብት ማፍራት የሚያስችል አሠራር 70 በ30 መርሃ ግብር ተግባር ላይ መዋሉ ተጠቃሽ ርምጃዎች ናቸው፡፡ ምርትንና ምርታማነትን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳደግ እንዲሁም ሠራተኛን በማሰልጠን ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንዲቻል ለግሉ ዘርፍ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት በየንዑስ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በማደራጀት ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

መንግሥት በቀየሰው ትክክለኛ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሯል። የኢንዱስትሪው ዘርፍ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ማዕከል አድርጎ፣ የግብርና ምርትን በስፋት በግብዓትነት በሚጠቀሙ፣ ሰፊ ሰው ኃይል ሊሸከሙ በሚችሉ፣ የአገሪቱን የቴክኖሎጂ አቅም ግምት ውስጥ ባስገቡና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ በሆኑ ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት በመደረጉ ተጨባጭ ለውጦች በመታየት ላይ ናቸው።  

ወደኋላ መለስ ብለን እንመልከት። በመጀመሪያው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ዘርፉን ከ10 ነጥብ 6 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ወደ 21 ነጥብ 4 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ነበር። ሆኖም በነበረው አፈፃፀም የ20 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል። በተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ምርቶችም በ2003 ዓ.ም ከነበረበት 52 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር 87 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረግ ተችሏል። የኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ከመቻላቸው በላይ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ይገቡ የነበሩ ምርቶችንም መተካት ጀምረዋል። ይህ እሰየው የሚያስብል ውጤት ነው።

መንግሥት በትክክለኛ አገር በቀል ፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ እየተመራ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤቶች ማስመዝገብ መጀመሩ የአገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር ትክክለኛ ጉዞ ያመላክታል። የኢንዱስትሪው ዘርፍ የበለጠ ሊጎለብት የሚችለው ቀጣይ ርብርብ ሲደረግበት ነውና የግል ባለሀብቱ በተለይ የአገር ውስጡ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ያለው ተሳትፎ ማሳደግ ይኖርበታል።

 

የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲቀረፅ ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት፣ ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር  አገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ማሰለፍ ነው። እነዚህን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መከተል ያስፈለገበት ምክንያት ኢንዱስትሪዎች የአገሪቱን ዕድገት ያማከሉ እንዲሆኑና በእቅድ የሚመሩ ለማድረግ ነው።

በዚሁ መሠረትም የኢንዱስትሪ ልማቱን የሚደግፉ ፖሊሲዎች፣ ህግና ደንቦች፣ አደረጃጀትና አሠራሮች ተፈጥሯል፡፡ የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ ሥራዎችን ማጠናከሩ በአንድ በኩል ኢንዱስትሪዎቹ የሚያስፈልጓቸውን ድጋፎች በተማከለ ሁኔታ እንዲያገኙ በሌላ በኩል ደግሞ እርስ በርስ የሚኖራቸውን ግንኙነት በማጠናከር ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። የኢንዱስትሪዎቹን የገበያ ሁኔታ በማመቻቸት ረገድም የኢንዱስትሪ መንደሮች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። በእስካሁን አፈፃፀማም አንዳንድ መንደሮች ወደ ሥራ መግባት ጀምረዋል። ሌሎች ደግሞ በተለያዩ የግንባታ ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ። በቀጣይም የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታው ተጠናክሮ በመቀጠል የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ጉዞ ለማሳለጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በአገሪቱ እየተስፋፉ ያሉት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ናቸው። መንግሥት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ትልቅ ሚና ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሟላት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ይገኛል። በቅርቡም ወደ ሥራ የሚገቡ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ይቀረፋሉ። ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መስፋፋት የኤሌክትሪክ ኃይል እጅግ ወሣኝ ሚና ይኖረዋል። በተመሳሳይ መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲስፋፉ የተመረጡት አካባቢዎች ለምርትና አቅርቦት አመቺነታቸው ተጠንቶ ነው።

በዚህም አገሪቱን ከወደብ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከማዕከል የሚያገናኙ ትላልቅ አውራ ጎዳናዎች እንዲሁም የባቡር መስመር ተዘርግቷል። ይህ ሁኔታም የትራንስፖርት ወጪን መቀነስ  የሚያስችል በመሆኑ ምርቶቻችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በመሆኑም መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማልማት በእቅድ የተያዙ አካባቢዎች ሁሉ በባቡር መስመር እንዲያያዙ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በአገሪቱ ሰፊ የሰው ኃይል የሚያስፈልጋቸውን ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል። በመሆኑም ቅድሚያ የሚሰጠው ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቢሆን የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል።

 

በአገሪቱ በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት በሚፈለገው ፍጥነት ዕድገት ባያሳይም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መጥቷል። በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ሳያካትት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሁለት ዓመታት በፊት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዘልሏል።   

መንግሥት በቀየሰው ትክክለኛ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ለአገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የተመቻቸ ሁኔታ የተፈጠረበትን የኢንዱስትሪ ልማት ግንባታ የበለጠ በማጠናከር የአገሪቱን ህዳሴ እውን ማድረግ ተገቢ ይሆናል። መንግሥት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ልማትን ሊያፋጥኑ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተመረጡ አካባቢዎች በማቋቋም የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ማሸጋገሪያ  ድልድይ መሆኑን በማመን መንግሥት የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል።

መንግሥት ኢንዱስትሪዎች በአገሪቱ እንዲስፋፉ ለማድረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚገነባና የሚያስተዳድር የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን የተሰኘ ተቋም በ2007 ዓ.ም በአዋጅ አቋቁሟል። ይህ ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ያለማል፣ ያከራያል ወይም ይሸጣል። በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር በመተባበር ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ያለማል። መንግሥት ለዚህ ተቋም በሰጠው ትኩረት ተቋሙ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ደረጃ እንዲመራ አድርጓል።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy