የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢንዱስትሪ አብዮት
ኢብሳ ነመራ
የህብረተሰብ የኢኮኖሚ እድገት ታሪክ ከግብርና ወደየማምረቻ ኢንዱስትሪ የተደረገ ነው። አሁን የበለጸገ የኢኮኖሚ አቅም ባለቤት የሆኑት የአውሮፓ ሃገራት የማምረቻ ኢንዱስትሪ በኢኮኖሚያቸው ውስጥ የበላይነት መያዝ የጀመረው ከ2 መቶ ዓመት በፊት ነበር፤ በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በተከሰተ የኢንዱስትሪ አብዮት። የዚህ የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ዋነኛ መለያ የማምረቻ ኢንዱስትሪ በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ መያዝ ነው፤ በካፒታል፣ በሰው ሃይል፣ በገበያ፣ በቴክኖሎጂ . . . ። እናም ከ18ኛው ክፈለ ዘመን አጋማሽ በኋላ በአወሮፓ ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ መሪ ለመሆን በቃ።
የአምራች ኢንዱስትሪ በድንገት የዚህ አይነት እመርታዊ ለውጥ እንዲያሳይ ማድረግ ያስቻለው በዋነኝነት በሃይል ቴክኖሎጂ የታየው እድገት ነበር። በውሃ በእንፋሎት ሃይል የሚሰራ ሞተር (steam ingine) መፈጠር ቀዳሚው የኢንዱስትሪ አብዮት ገፊ ነበር። የእንፋሎት ሃይል፣ የእጅ መሳሪያዎችን በሞተር ሃይል በሚሰሩ ማሽኖች መተካት አስቻለ። ይህም በተበታተነ ዎርክሾፕ ይመረት የነበረውን ምርት በርካታ ሰራተኞች በተሰማሩበት አንድ የፋብሪካ ስርአት ማምረት የሚቻልበትን ሁኔታ ፈጠረ። እናም የጨርቃጨርቅ፣ የብረታብረት፣ የኬሚካል አምራች ፋብሪካዎች ተፈጠሩ። ምርት በገፍ ይመረት ጀመር። በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ጎልቶ የወጣው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ነበር።
ከአንድ መቶ አመት በኋላ በ1850 ዎቹ የእንፋሎት ሃይል ለፋብሪካ ሞተር ከመዋል አልፎ ለትራንስፖርት – ለመርከብና ባቡር ትራንስፖርት ሃይል ምንጭ ጥቅም ላይ መዋል ደግሞ ንግድን በማስፋፋት የኢንዱስትሪ እድገት ሁለተኛውን እመርታዊ እድገት እንዲያሳይ አድርጓል። የኢንዱስትሪ አብዮት በሰዎች ኑሮም ላይ መሻሻል አምጥቷል። የህዝብ ገቢ እንዲያድግ በማድረግ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል አድርጓል።
የማምረቻ ኢንዱስትሪ ወደተቀሩት አህጉሮች – ወደደቡብ አሜሪካ፣ ኢስያ፣ አፍሪካ መሻገር የጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ነው። እርግጥ በኢሲያ ጃፓን ይህን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ በመጀመር ቀዳሚዋ የኢሲያ ሃገር ነች። በተለይ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሸ በኋላ ግን የደቡብ ምስራቅ ኢሲያ ሃገራት የራሳቸውን የኢንዱስትሪ አብዮት አካሂደዋል። አሁን የዓለም 2ኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ በዚህ ወቅት የተፈጠሩ ባለኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሃገራት ናቸው።
የማምረቻ ኢንዱስትሪ ወደአፍሪካ ያደረገው ጉዞ እጅግ ቀርፋፋ ነው። አፍሪካን በቅኝ ግዛትነት ተቀራመተው የነበሩት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ የአውሮፓ ሃገራትም ቢሆኑ ኢንዱስትሪያቸውን ወደአፍሪካ አላመጡም። ከዚያ ይልቅ ሃገራቸው ይገኙ ለነበሩ ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ የሚያቀርቡ የማዕድን ማውጣትና ሰፋፊ እርሻዎች ላይ ነበር ያተኮሩት። በቅኝ ገዢዎች የማምረቻ ኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ የገነባ ሃገር የለም።
አፍሪካ አሁንም በማምረቻ ኢንዱስትሪ የጨለማ ዘመን ውስጥ ነው የምትገኘው። አፍሪካ አሁንም የኢንዱስትሪ አብዮቷን አላካሄደችም። የአፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ አቅም፣ የህዝባቸው አጠቃላይ የኑሮ ደረጃም በግማሽ ክፍለዘመን ያህል ግዜ ውስጥ ይህ ነው ሊባል የሚችል መሻሻል አላሳየም። አፍሪካውያን አሁንም ትግላቸው መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ከማሟላት ጋር ነው። ኢትዮጵያም አንዷ ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋር ተራርቃ የቆየች ሃገር ነች።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ባለፉ ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ከዘመናት የማሽቆልቆል ጉዞ ወጥታ የእድገትን ጉዞ ዳዴ ጀምራለች። የእድገት ጉዞዋን የጀመረችው በዘመናት የማሽቆልቆል ጉዞ ከወደቀችበት አዘቅት ነው። የእድገት ዳዴዋን የጀመረችው ዜጓቿን በቀን ሶስቴ እንዲመገቡ የማስቻልን ግብ አስቀምጣ ነበር፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት። ይህን፤ በተለይ 85 በመቶ ገደማ የሚሆነውን የሃገሪቱን ህዝብ የሚወከለውን አርሶ አደር በቀን ሶስቴ በወጉ እንዲመገብ የማድረግ ግብ በግብርናው ዘርፍ በተመዘገበው እድገት ተሳክቷል። አሁን ኢትዮጵያ እንደሃገር የምግብ ፍላጎቷን ማሟላት መቻሏ በገለልተኛ አካል ጭምር ተረጋግጧል። ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስቴ መመገብ የቻለበት ደረጃ መደረሱ ሊካድ የማይችል መሆኑን ያመለክታል። በድርቅ ምክንያት የተወሰኑ አካባቢዎች የምግብ እጥረት ቢከሰት እንኳን በራስ አቅም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማቅረብ የተቻለበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን በምግብ መቻል ያቃታቸው ቤተሰቦችም በሴፍቲኔት ፕሮግራም ራሳቸውን የሚችሉበት ስርአት ተዘርግቷል። ይህ በገጠር የጀመረው የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም በያዘነው ዓመት በከተሞችም ተጀምሯል።
ይህ በቀን ሶስቴ ከመመገብ የጀመረው የኢኮኖሚ እድገት ዳዴ አርሶ አደሩ ትርፍ አምርቶ ገቢውን ማሳደግ ወደቻለበት ደረጃ ደርሷል። የአርሶ አደሩ ገቢ ማደግ ለንግዱ፣ ለአገልግሎቱና አምራች ዘርፎ ከፍተኛ የገበያ አቅም በመፍጠር ሃገራዊ የካፒታል ክምችት ፈጥሯል። ይህ በንግድ፣ በአገልግሎትና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ዘንድ በትርፍነት (profit) ተሰብስቦ የተከማቸ ካፒታል የኢንቨስትመንት አቅም እየፈጠረ ነው። በሃገሪቱ ከተሞች ውስጥ እየታየ ያለው የኮንስትራክሽንና የአገልግሎት ዘርፍ እድገት የዚህ የኢንቨስትመንት አቅም መዳበር ውጤት ነው። የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ግን አሁንም ሃገር በቀል ባለሃብቱን በሚፈለገው መልክ እየሳበ አይደለም። የዚህ ምክንያት ዘርፉ የሚጠይቀው የቴክኒክና የማኔጅመንት እውቀትና ክህሎት እጥረት ሊሆን ይችላል።
ያም ሆነ ይህ፣ ኢትዮጵያ የራስዋን የአምራች ኢንዱስትሪ አብዮት ለማካሄድ አቅዳ እየተጋች ትገኛለች። ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የአምራች ኢንዱስትሪው በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የበላይነት እንዲኖረው የማደረግ የኢንዱስትሪ አብዮት ዕቅድ ነው።
የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ተግባራዊ በሆነባቸው አምስት ዓመታት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ 10 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ በየዓመቱ በአማካይ 6 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት የተመዘገበ ሲሆን፤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ 20 በመቶ እድገት ተመዝግቧል። በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ የ10 ነጥብ 7 በመቶ አማካይ ዕድገት ነበር የተመዘገበው። በዚህ እድገት የኢንዱስትሪው ዘርፍ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ በ2003 ከነበረበት 10 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 14 ነጥብ 3 በመቶ አድጓል። በዚህ ረገድ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከኢኮኖሚው የሚኖረውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ቢሆንም፤ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና ውጤታማ ለውጥ ለማምጣት የተለየ ትኩረት መደረግ እንዳለበት የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ሪፖርት ላይ ተገልጿል።
ሁለተኛው የእደገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ከተጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። አጠቃላይ የእቅዱን ስኬት መጠን ለመናገር ጊዜው ገና ቢሆንም፣ አምራች ኢንዱስትሪው እድገት እያሳየ ለመገኘቱ በርካታ ተጨባጭ አስረጂዎችን መጠቀስ ይቻላል። ኢትዮጵያ በተለይ በ2ኛው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ዘመን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እድገቱ የታቀደለትን ግብ እንዲመታ ከተከተለቻቸው ስልቶች መሃከል የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
እንግዲህ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ወደኢንዱስትሪ መር በማሸጋጋር በ2017 ዓ/ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍን ግብ አድርጋ እየሰራች ትገኛለች። የህ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ የመሰለፍ እቅድ እውን የሚሆነው ኢኮኖሚው ወደአምራች ኢንዱስትሪ ሲሸጋጋር ነው። ለዚህ ስኬት ከያዝነው ዓመት መግቢያ ጀመሮ አስር የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው። በ250 ሚሊየን ዶላር ተገንብቶ በቅርቡ ወደስራ ከገባው በጨርቃጨርቅ የወጪ ንግድ ምርት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎችን ከያዘው የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በተጨማሪ የመቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ግንባታቸው በወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የጠበቃል።።
የቂሊንጦ፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ጂማ፣ ባህርዳርና አረርቲ ምንጃር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታም ተጀምሯል። ፓርኮቹ በልዩ ስራ ላይ ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንዲሰማሩባቸው ታስበው ነው የሚገነቡት። ለምሳሌ የቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ በህክምና መሳሪያዎች ማምረት፣ የደብረብርሃን በግብርና ማቀነባበሪያዎች፣ የአዳማ በጨርቃ ጨርቅና ማምረቻ ዘርፍ፣ የመቀሌና ኮምቦልቻ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ድሬዳዋ በከባድ ማሽኖችና ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች፣ አረርቲ በግንባታ እንዲሁም በቤትና ቢሮ እቃ ማምረት ላይ ትኩረት አድርገው የሚገነቡ ናቸው።
የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን እድገት የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግሩ እቅድ በሚጠይቀው ልክ የማሳደጉን ሂደት በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል። የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ፋብሪካዎች ወደምርት ስራ ለመግባትና ወደገበያ ለመወጣት የሚያስፈልጓቸው መሰረተ ልማቶች፤ መንገድ፣ ሃይል፣ ቴሌኮም፣ የፍሳሽ ማሰወገጃ ስርአት፤ የመጋዘን አገልግሎት፣ የገንዘብ ተቋማት አገልግሎት፣ የመኖሪያ ቤቶችና ሌሎች የሰራተኞች አገልግሎቶች ወዘተ የተሟሉለት ሰፊ መንደር ነው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭም ሆኑ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች፣ በተናጥል የየራሳቸውን ፋብሪካ ለመገንባት የሚገጠማቸውን ውጣ ወረድና ጊዜ ያቃልላሉ። አንድ ባለሃብት በአንድ የምርት ዘርፍ ፋብሪካ ለማቋቋም የኢንቨስትመንት ፍቃድ ካገኘ በኋላ ወደመሬት ፍፈለጋ ይሸጋገራል። የመንገድ፣ የሃይል፣ የቴሌኮም፣ . . . መሰረተ ልማት የተሟላበት ቦታ ማገኘት አስቸጋሪ ስለሆነ መሬት ካገኘ በኋላ ቀጣይ ስራው እነዚህን የመሰረ ልማቶች ማሟላት ነው። የመሰረተ ልማቶቹን ለማሟላት በየተቋማቱ ማመልከት ይኖረበታል። ተቋማቱ የአንድ ባለሃብትን ፍላጎት የማሟላት ስራ ከአጠቃላይ በሃገሪቱን የመሰረተ ልማት የማስፋፋት እቅዳቸው አፈጻጸም ጋር ላይጣጣምላቸው ስለሚችል የጎንዮሽ ስራ ይሆንባቸዋል። ይህም የሚፈለገውን ያህል ትኩረት እንዳይሰጡት ያደርጋል። በብዙ ውትወታ ተኩረት ቢሰጡት እንኳን የተናጠል የመሰረተ ለማት ዝርጋታው ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ይሆናል። ይህን ወጪ ባለሃብቱ እንዲሸፍን የሚጠየቅበት ሁኔታም የተለመደ ነው።
እነዚህ ሁኔታዎች የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ሳቢ እንዳይሆን አድርገውት ቆይተዋል። ይህ ደግሞ የሃገሪቱን የማምረቻ ኢንዱስትሪ በሚፈለገው መጠን ማደግ እንዳይችል ያደረገ ጎታች ሆኖ ቆይቷል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይህን የሃገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት መሰናክል ሆኖ የቆየን ችግር የሚያቃለሉ ናቸው። አሁን በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች የሚጠብቃቸው ጥቂት ስራ ነው። መሰረተ ልማት ተዘርግቶለት በተዘጋጀው የኢንዱስትሪ ፓርክ ማሽኖቻቸውን ተክለው፣ ጽህፈት ቤታቸውን አደራጅተው፣ ሰራተኞች ቀጥረው ወደስራ መግባት ብቻ። የመሬት ጥያቄ፣ የተለያየ መሰረተ ልማት መገንባት ወዘተ የባለሃብቱ ራስ ምታት መሆናቸው በኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ አብቅቷል።
ባለፈው ዓመት ሃምሌ ወር ላይ ግንባታው ተጠናቆ የተመረቀው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገበተው አንድ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ወደምርት ስራ የተሸጋጋሩ ፋብሪካዎች ለዚህ ማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ድሮ ቢሆን የአነዚህ ፋብሪካዎች ባለሃብቶች ገና ከመሬት ጥየቃ ሂደት እንኳን ማለፍ አይችሉም ነበር። በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያ በእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅድ ላቀደችው የራስዋ የኢንዱስትሪ አብዮት ስኬት ምርኩዞች ናቸው።