Artcles

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከልማት ዕቅዱ አኳያ

By Admin

July 21, 2017

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከልማት ዕቅዱ አኳያ

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአፍሪካ ማዕከል ለመሆን እየሰራች ነው። በተለይም አሁን በያዝነው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በመገንባት ላይ ትገኛለች። ዕቅዱ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ቢሆነውም፤ እየታዩ ያሉት መንግስታዊ ጥረቶች የተፈለገውን ግብ የሚያሳኩ ናቸው። የፓርኮቹ ልማት ለህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲሁም ለሀገራችን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ግኝት ያላቸውን ናቸው።

በአሁኑ ሰዓት ስራው ተጠናቅቆ አገልግሎት ላይ የዋለው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአካባቢው ህዝቦች ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር፤ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይታመናል። በቅርቡ የተመረቁት የመቀሌና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በተመሳሳይ የአካባቢውን ህብረተሰብ የመጥቀም ሚና ይኖራቸዋል። ባለሃብቶች ሲገቡባቸውም የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ናቸው።

የልማት ፓርኮቹ ውስጥ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙባቸው የጋራ መገልገያዎች፣ መጋዘን፣ የብክለት ማጣሪያና ማስወገጃ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የቢሮ መገልገያ ህንፃዎች፣ የሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ መዝናኛዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያገለግሉ መሰል ተቋማትን የሚያካትቱ አገልግሎት መስጫዎች ይኖራቸዋል። ይህ በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው። ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ለማግኘትም በመንግስት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ከሃዋሳው የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት በተጨማሪ የመቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ ማስጀመር መቻሉን መረጃዎች ያስረዳሉ። የቦሌ ለሚ ሁለትና ቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የዲዛይን ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውም እንዲሁ። የድሬዳዋ፣ የአዳማ፣ የባህርዳርና የጅማ ኢንዱሰትሪ ፓርኮች አብዛኛው የቅድመ ዝግጅት ስራዎቻቸው የተጠናቀቁ ሲሆን፤ አንዳንዶቹም ወደ ተግባራዊ የግንባታ ስራ እንደገቡ ተገልጿል።

ይህ በሀገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። ርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። ይህም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ ሰፊ ዕድልን ይፈጥራል። ለዚህም በምሳሌነት ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ብንመለከት፤ ፓርኩ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች መያዙንና የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችም በስራ ሂደት የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባርን እንደሚከውኑ ይጠበቃል።

እዚህ ላይ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ አንድ ግንዛቤ መያዝ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይኸውም ከመጀመሪያው የአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ አንድና ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን ብንመለከት እንኳን፤ ፓርኮቹን ለማልማት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር 346 አባዎራዎች የተሟላ መሰረተ ልማት ያለው ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው የተደረገ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን በማህበር አደራጅተው እንዲያቋቁሙ ለማድረግም በእንስሳትና በእንስሳት ተዋፅኦ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠረላቸው መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ። ከመቀሌ፣ ከኮምቦልቻ፣ ከድሬዳዋ፣ ከአዳማና ሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች በልማት የሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን እስካሁን በተገኙት ተሞክሮዎችን በመቀመርና በተሻለ ውጤት በማስፋት የመልሶ ማስፈሩ ስራ እየተሳለጠ ነው፤ ይሳለጣልም።

እንግዲህ እነዚህ ተግባራት የሚያመላክቱት ነገር ቢኖ፤ር ለልማት የሚነሱ ዜጎች ተመጣጣኝና ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው ሁኔታ ተገቢው ምትክና ካሳ በመንግስት በኩል ተፈፃሚ እየሆነላቸውና እንደሚሆንላቸው ነው። ይህ ሁኔታም ዜጎች ለልማት ተነሺ ቢሆኑም፣ ልማገቱ ዞሮ…ዞሮ ሀገራቸውንና እነርሱንም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው እንደሆነ ታምኖበት የሚከናወን ተግባር መሆኑን ያሳያል።

ያም ሆኖ ግን ከሀገራችን የልማቱ ጀማሪነትና ስራው ከሚጠይቀው በጀት አኳያ ዘርፉ የተወሰኑ ተግዳሮቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ አያጠራጥርም። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከዘርፉ ተግዳሮቶች ውስጥ፤ ልማቱን ለማረጋገጥ ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግርና ግንባር ቀደም ባለሃብቶች በስፋት መሳብ የሚያስችል አቅም አለመኖሩ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ሆኖም እነዚህ ችግሮች በመንግስትና በህዝቡ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ጥረት የሚፈቱ ናቸው። ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል። ያለ ህዝብ ጥረት መንግስት ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም። ተግባሩንም በተገቢው ሁናቴ አይወጣም። እናም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል።

ችግሮችን ለመፍታት የተሻለ አቅም በመፍጠር፣ የገንዘብ ምንጮችን በማፈላለግና ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እገዛ ማድረግ ያለበት ይመስለኛል። በዚህ ድምር ውጤትም የፓርኮቹ ልማት የሀገራችን ህዝቦች የስራ ዕድል አግኝተው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እንዲሁም ሀገራችን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የልማት ስትራቴጂ እንድታድግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው።

በመሆኑም መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ፓርኮቹን ለማልማት እያደረገ ያለው ጥረት በሀገራችን ውስጥ በምጣኔ ሃብት ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑን በመገንዘብ የፓርኮቹን ነባራዊ ችግር መፍታት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድርሻ ነው። እናም ሁሉም በያለበት ቦታ ሁሉ የመንግስትን ተግባር በመደገፍ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የተጀመሩት ስራዎችን መደገፍ አገራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት።