Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማፈጠን

0 425

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማፈጠን

ሰለሞን ሽፈራው

የዛሬዋ ኢትዮጵያ በፈጣን የዕድገትና የብልጽግና ግስጋሴ ላይ ካሉ ጥቂት የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ስለ መሆኗ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጭምር አምኖ የመቀበሉን ያህል ይሄን የማይስተባበል ጥሬ ሀቅ የሚያደበዝዝ አሉታዊ ጫና ሲፈጥሩብን የሚስተዋሉ ፈተናዎች መኖራቸው የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡

ይህን ስንልም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ መላ ህዝቦቿን አስተባብራ በመነሳት ስር ከሰደደው ድህነትና ኋላ ቀርነት ጋር የሞት ሽረት ትግል የገጠመችበት የፈጣን ልማት ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ባያከራክርም፤ ግን ደግሞ ከትናንቱ ታሪካችን የወረስናቸው ፈርጀ ብዙ ችግሮች አሁንም ድረስ ሲፈታተኑን የሚስተዋሉበት አግባብ እንዳለ የማይታበይ ሀቅ ነው ፡፡ በተለይም ደግሞ ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቀውስ ጋር ተያያዥነት እንደሚኖረው በሚነገርለት የዝናብ እጥረት ምክንያት የሚከሰተው ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋና እርሱን ተከትሎ የሚያጋጥም የምግብ እህል እጥረት የዛሬዋ ኢትዮጵያ የምትገለጽበትን በጎ ገጽታ ክፉኛ ሲፈታተነው የሚስተዋል አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ እንዳልቀረ መገመት አያዳግትም፡፡

እንዲሁም ሕገ ወጥ ስደት ሌላው በኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ላይ የተጋረጠ ፈተና እንደሆነ ይታመናል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋነኛ መገለጫ በፈጣን የእድገትና የብልጽግና ጎዳና ላይ እየተራመደች የምትገኝ ሀገር ናት የሚለውን የዓለም ማህበረሰብ ምስክርነት የሚያረጋግጥ እንጂ በተጠቀሱት ችግሮቻችን ምክንያት ሊደበዝዝ የሚችል አይደለም፡፡

ለዚህ አስተያየቴ የተሻለ ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ዕድገትና ብልጽግና መገለጫዎችን እንደ አብነት ማቅረብ ይቻላል የሚል እምነትም ነው ያለኝ፡፡ ከዚህ አኳያም ሀገራችን ለዘመናት ያህል በኋላ ቀር የግብርና ስራ ላይ ተወስኖ የቆየውን ኢኮኖሚዋን ወደ ኢንዱስትሪ መርነት ለማሸጋገር ስትል በነደፈችው የመዋቅራዊ ሽግግግር መርሃ ግብር አማካኝነት ብዙ ርቀት የተጓዘች ስለመሆኗ ከአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ጀምሮ በተደረገ ጥረት የተገኙ አመርቂ ውጤትችን ማውሳት ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡

ይልቁንም ደግሞ የሀገራችንን ምጣኔ ሀብታዊ መሰረት ከኋላ ቀሩ የግብርና ስልት አላቀን ወደ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ መር ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ሲባል የኢፌድሪ መንግስት የቀየሰውን የመዋቅራዊ ለውጥ መርሃ ግብር (የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ) የማስፈጸሙ ጥረት በሁለተኛው አምስት ዓመት የትግበራ ዘመን ካስመዘገባቸው አመርቂ ውጤትች መካከል ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠውን የሀዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክን ለመጣጥፌ ርዕሰ ጉዳይ ዓይነተኛ ማጣቀሻ አድርጌ አቀርበው ዘንድ ጠቃሚ መስሎ ይሰማኛል፡፡ ይህን የምልበት ዋነኛ ምክንያትም ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት መቀመጫ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ተገንብቶ አሁን ላይ በርካታ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ወደ ማምረት ተግባር እንዲገቡ ማድረግ የቻለው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ልማት መንደር፤ በብዙ መልኩ ሀገራችን ለተያያዘችው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ሂደት ተጨባጭ ማሳያ ይሆናል ብዬ ስለማምን ነው፡፡

እንግዲያውስ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለመገንባት አቅዳ ከተቀመጠላቸው ጊዜ እጅግ በጣም ባጠረ መልኩ ካሳካቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠውን የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሌሎች መሰል የልማት ተቋማት በርካታ ጠቃሚ ልምዶችን የሚያስተላልፍ የሚያደርገው ምክንያት ምን እንደሆነ ለማመላከት የሚረዱንን ጥቂት ጠቃሚ ነጥቦች ብቻ ለአብነት ያህል አነሳለሁ፡፡ እናም ለዚሁ መሰረተ ሃሳብ የተሻለ ማጠናከሪያ ይሆናል የምለው በሃዋሳው የኢንዱስትሪ ልማት መንደር ዙሪያ ከሰሞኑ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡትን ወቅታዊ መረጃ ነው፡፡ ስለሆነም፤ ረቡዕ ሰኔ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ “በሃዋሳው የኢንዱስትሪ ፓርክ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቅ የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ ነው” በሚል ርዕስ የቀረበውን ዜና አስቀድማለሁ፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ረቡዕ ሰኔ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ገጽ ሰባት ላይ ሰፋ ባለ መልኩ የተጻፋው ትንታኔ ዜና (ሪፖርታዥ) ማየት እንደሚቻለው ሁሉ፤ በተለይም የሐዋሳው የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የተፈጠረው የልማት አብዮት፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ከስራ አጥነት ችግር እየታደገ እንደሚገኝም ጭምር ነው ዘገባው ያተተው፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ “አርቪንድ ሊሚትድ” በመባል የሚታወቀው የህንድ ኩባንያ አካል የሆነው “አርቪንድ ኤንቪሶል” የተሰኘ ሌላ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገነቡ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርታማነት ፋይዳው እጅግ የላቀ እንደሚሆን የታመነበትንና የአካባቢ ብክለትን የሚያስቀርም ጭምር የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ለመተግበር የሚያስችለውን የመግባቢዘያ ሰነድ ከኢፌድሪ መንግስት ጋር ስለመፈራረሙ በዝርዝር የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ፤ የሀዋሳው ኢንዱስትሪ መንደር በርካታ የውጪ ኢንቨስተሮችን እያማለለ እንደሚገኝ አክሎ ገልጸዋል፡፡

30 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚጠይቅ የተነገረለትን የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ በተመለከተ ዜናው ሲያብራራም ፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙበትን የፍሳሽ አገልግሎት ከመለቀቁ በፊት እያጣራ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ እውነታ፤ የሐዋሳው እንዱስትሪ መንደር ውስጥ ከተገነቡት የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች መካከል 16ቱ ስራ መጀመራቸውን የጠቆመው የሪፖርተር ጋዜጣ፤ የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂውን እየተገበረ ያለው የህንድ ኩባንያ ራሱ እዚያው ግቢ ውስጥ የገነባቸው ተጨማሪ ሰባት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ማምረት ሲጀምሩ ደግሞ፤ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል ተብሎ እንደሚታመን ነው ምንጭ ጠቅሶ የፃፈው ጋዜጣው፡፡

እስካሁን ድረስ የማምረት ተግባር የጀመሩት በሃዋሳው የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የሚገኙ የጨርቃጨርቅ እና ሌሎችም ፋብሪካዎች ከ50 ሺህ እስከ 60 ሺህ በሚደርሱ ዜጎቻችን የሥራ እድል እንደፈጠሩ ይታወቃል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መቐለን፤ ባህርዳርንና አዳማን በመሳሰሉት ሌሎች የክልል ከተሞች ውስጥ የተጀመረው የኢንዱስትሪ ልማት መንደር ግንባታ ሂደት እጅግ በተፋጠነ መልኩ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሰሞኑን ከተደመጡ የሀገር ቤት መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች መረዳት ይቻላል፡፡

እናም መንግስት በሃዋሳው የኢንዱስትሪ ልማት መንደር ፈጣን የግንባታ ሒደት የተገኘውን ጠቃሚ ልምድ ወደ ሌሎች የክልል መስተዳደር ከተሞች የማስፋት ተግባርን እንደ ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ እየወሰደው መሆኑን የሚያመላክቱት መረጃዎቹ፤ ዘርፉ የሀገራችንን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ አንዲያመጣ ከማድረግም ባሻገር፤ የሥራ አጥ ዜጎችን ቁጥር በእጅጉ የሚቀንስ አዳዲስ ዕድል በመፍጠር ረገድም ቀዳሚ ስፍራ ይይዛል ብሎ ማጠቃለል እንደሚቻል ነው የሚያስረዱት፡፡ በእርግጥም ደግሞ የሐዋሳውን ዓይነት ግዙፍ የኢንዱስትሪ መንደር በእያንዳንዱ የክልል ከተማ መገንባት ከተቻለ የሀገራችንን ወጣት የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች ብቻም ሳይሆን፤ ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ ያስመረረውን የገጠሪቷ ኢትዮጵያ ነዋሪ ህብረተሰብ ጭምር ከስራ አጥነት ችግር የሚታደግ የልማት መስክ የማንፈጥርበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡

ስለዚህ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ለማፋጠን ሲባል በተነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አማካኝነት እየተደረገ ያለው ፈርጀ ብዙ ጥረት የሃዋሳውን ዓይነት ግዙፍ የኢንዱስትሪ ልማት መንደሮችን ለመገንባት ተግባር ቅድሚያ ይሰጥ ዘንድ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ ለማንኛውም ግን፤ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በሃዋሳው የኢንዱስትሪ መንደር ተገኝተው ካሰሙት ንግግር ጠቅሼ ጽሑፌን አጠቃልላለሁ፡፡ በዚህ መሰረትም “እንደዚህ ዓይነቶቹን ስርዓት ባለው የብቃት ደረጃ የተሟሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመላ ሀገሪቱ እየገነባን ኢኮኖሚያችንን ከኋላ ቀሩ የግብርና ዘዴ ጥገኝነት ለማላቀቅ እንችል ዘንድ የውጪ ባለሃብቶች በእጅጉ ያስፈልጉናል፤፤” ሲሉ ተደምጠዋል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ፡፡ ለሁሉም ግን ያሉብንን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጥል ይገባቸዋል መልዕክቴ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy