NEWS

የኦሮሚያ ክልል በቀን ገቢ ግመታ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲቀርቡ አሳሰበ

By Admin

July 17, 2017

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከእለት ገቢ ግመታ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲቀርቡ  አሳሰበ።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ቅሬታ ያለው ማንኛውም አካል ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይችላል ብለዋል።

የክልሉ መንግስትም የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች በመመልከት እየፈታ እንደሚገኝ አቶ አዲሱ ገልፀዋል።

ከገቢ ግመታው ጋር ተያይዞ የተነሳውን ቅሬታ ምክንያት በማድረግና ሌላ ዓላማን በማንገብ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሞከር ግን ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ይህንን ህገ ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱ ነጋዴዎች ላይም አስፈላጊ የሆነ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ነው አቶ አዲሱ ያስታወቁት።

በዛሬው እለትም ከእለት ገቢ ግመታ ውጤት ጋር ተያይዞ የተነሳን ቅሬታ ምክንያት በማድረግ በአምቦ እና በወሊሲ ከተሞች የንግድ ተቋማት መዘጋታቸውን ገልጸዋል።

እንዲህ አይነት አካሄድም የከተማዋን የንግድ ማህበረሰብ እና ነዋሪዎችን የሚጎዳ እንጂ የሚያስገኝላቸው ጥቅም እንደሌለ ጠቅሰዋል።

ከግብር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ህጋዊ በሆነ መንገድ አቅርቦ መፍትሄ ማግኘት እየተቻለ ለአመጽ ማነሳሳት ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

አቶ አዲሱ አያይዘውም በሌሎች የክልሉ ከተሞች እና ወረዳዎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴው ሰላማዊ በሆነ መልኩ ቀጥሎ መዋሉን ገልጸዋል።

በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና ወረዳዎች ውስጥ የሚገኘው የንግዱ ማህበረሰብም ቅሬታውን ህጋዊ በሆነ መልኩ እያቀረበ ምላሽ እያገኘ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ በርካታ የልማት ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው ያሉት አቶ አዲሱ፥ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት ደግሞ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የክልሉ የበጀት ፍላጎት ከ56 ቢሊየን ብር በላይ ደርሷል፤ ከግብር የሚገኘው ገቢ ግን ከ10 ቢሊየን ብር እንደማይበልጥ ነው አቶ አዲሱ የገለጹት።

በመሆኑም የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር ህጋዊ በሆነ መልኩ ወቅቱን ጠብቆ እንዲከፍል ጥሪ አቅርበዋል።