Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወጣቱና የባለ ሃብቱ ትስስር— ለአገራዊ ዕድገት

0 361

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወጣቱና የባለ ሃብቱ ትስስር— ለአገራዊ ዕድገት

                                                          ታዬ ከበደ

በሀገራችን እየተካሄደ ባለው ኢንቨስትመንት ስራ ውስጥ ባለ ሃብቱ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው። ባለ ሃብቱ ወጣቱ የልማቱ አካል እንዲሆን በስራው ላይ ግብዓቶችን እንዲያቀርብ ማድረጉ ለተጀመረው አገራዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በሁለቱ አገር ገንቢ አካላት መካከል ያለው ይህ ትስስር አገራችን እውን ለማድረግ ለወጠነችው የልማት ዕቅድ ወሳኝ ነው።

እርግጥ ባለፉት ሥርዓቶች የወጡና የግሉን ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚገቱ ህጎችና ደንቦች በአሁኑ ወቅት ተወግደዋል፡፡ በዚህም ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ በመለወጥ መንግሥት በየጊዜው የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡

በየጊዜው ከታዩ ልምዶች ትምህርት በመውሰድ ጥንካሬዎቹን የማጎልበት ድክመቶቹን የማረም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩም መምጣታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ የሚፈለገው ዓይነት ፈጣን ዕድገት ደግሞ ልቅ በሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ብቻ ሊረጋገጥ የማይችል በመሆኑ ካለፈው ትምህርት መውሰዱ ተገቢ ይሆናል።

ልቅ የሆነ የገበያ ሥርዓት ዘላቂና ሰፊ መሰረት ያለው ዕድገት የማምጣት አቅም እንደሌለው እና ይልቁንም የህዝብንና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሰማሩ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም በሂደት መንግሥት የማይተካ ልማታዊ ሚና የሚጫወትበት የነፃ ገበያ ሥርዓት መከተል እንደሚገባ ታምኖበት በመስራት ላይ ይገኛል።

መንግሥት የግሉና የመንግሥት የዘርፎች ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች በመከተል ላይ ይገኛል።

መንግሥት የገበያ ጉድለቶችንና ተያያዥ የኪራይ ምንጮችን ለመዝጋት በመሰረተ ልማት እና በሰው ሃብት ልማት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል። ከዚህ አንፃር የፌዴራል መንግሥት የ2005 ዓመት የበጀት ድልድልን መጥቀሱ ብቻ በቂ ይመስለኛል።

ድልድሉ 27 ነጥብ 01 በመቶ ለመንገድ፣ 22 ነጥብ 32 በመቶ ደግሞ ለትምህርት በድምሩ የፌዴራለ መንግሥት ከጠቀላላ በጀቱ ወደ 50 በመቶ የሚጠጋ ለእነዚህ ሁለት ዘርፎች የተመደበ ነው። ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለቴሌኮምና ለባቡር መስመር ዝርጋታ በልማት ድርጅቶቹ አማካይነት ሰፋፊ ኢንቨስትመንት በማካሄድ ላይ መሆኑም ይታወቃል።

ታዲያ እዚህ ላይ የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል የሚካሄድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል።

ይህ ሁኔታም እንደ መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን የግሉ ባለሃብት በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል።

እርግጥ ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።

ይሁንና አሁንም ቢሆን ከዕድገት ደረጃችን ጋር ተያይዞ ከሚኖረው የገበያ ጉድለት እና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዞ ሊከሰትና ፈጣን ዕድገቱን ሊያስተጓጉል የሚችለው አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። አደጋውን ለማስቀረት አስቀድሞ የተለየና መፍትሔም የተቀመጠለት ጉዳይ ሆኗል።

በመሆኑም የመሬትና የባንክ አስተዳደር ሥርዓቶቹ እንደታቀደው ልማትን በሚያፋጥንና የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተሟላ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው መንግሥት በጽኑ ያምናል።

ማመን ብቻም አይደለም። የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱም ፍትሃዊ ውድድርን የሚያሰፍንና ህጋዊ ያልሆነ ጥቅምን የሚዘጋ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ማከናወኑንም ቀጥሏል። በዚህም የመንግሥት ተሳትፎ የባለሃብቱን ልማታዊ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ መሆኑም በገሃድ እየታየ ነው።

ባለፉት 26 ዓመታት መንግሥት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥበብ በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ሂደት ውስጥ ውስን ሃብቱን መሰረታዊ ችግሮችን በሚፈቱ የልማት ሥራዎች ላይ አውሏል። የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እና የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትንና ማህበራዊ ልማትን ማረጋገጥ ችሏል።

ከዚህ ጎን ለጎንም መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተውባቸዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት የተመዘገበው አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገት መመዝገቡ ለሀገራችን መፃዒ ዕድል ትልቅ ብስራት ነው። በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከበፊቱ የተሻለ ጥረት ለማድረግ የሚመለከተው አካል ሁሉ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ይገኛል።

ከዚህ አኳያ የመንግሥት ደጋፊ ተቋማት አቅም ለማሳደግ የፋብሪካዎች የቴክኖሎጂና የማኔጅመንት አቅም ካደገ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከባለሃብቱ ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውና ለመፍትሔውም በጋራ መሰለፋቸው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው እሙን ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ልማትን በማስፋፋት የተፋጠነ ልማትን ለማረጋገጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ይገኛል። በመሆኑም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዋና ዋና ዘርፎች፣ በተለይም በግብርና ልማት እንዲሁም በኢንዱስትሪ መር አቅጣጫን በቀዳሚነት የገቢ ምርት መተካት ላይ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።

ታዲያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ውጤታማ ሆኗል ሲባል፤ ለውጭ ንግዱ መልካም አፈጻጸም እንዲሁም ለግብርና ምርቶች የተፈጠረው የዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው መገንዘብ ይቻላል። ለምን ቢባል፤በዕቅድ ዘመኑ የሆልቲካልቸር ምርትንና ኤክስፖርትን ለማሳደግ ብሎም መሬትን ለማስፋፋት፣ የምርታማነትንና የግብይት ሥርዓትን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራቶች በመከናወናቸው ነው።

በዚህም ሳቢያ ከአበባ እንዲሁም ከቁም እንስሳት የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ በምሳሌነት ከቀደምት ዓመታት ጋር ስናነፃፅረው አበረታች ዕድገት ተመዝግቧል። በመሆኑም አበባ የሦስት በመቶ ዕድገት ሲያስመዘግብ፣ የቁም እንስሳት ደግሞ 148 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ አስገኝተዋል። ይህም የ63 በመቶ ጭማሪን ያስመዘገበ ነው።

በእነዚህን በሌሎች የኢንቨስትመንት ውጤቶቹ የተበረታታው መንግሥት ሀገሪቱ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን በርካታ ተግባራትን ከውኗል። ቀደም ሲል የተጀመረውን ሥራ በማስቀጠል  በድርጅቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ ቡድንም ልኳል።

አገራችን በዓለም ንግድ ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሚ እንድትሆን እንዲሁም ተሰፋፊ የገበያ ዕድሎችና የኢንቨስትመንት ፍሰቶች እንዲያድጉ ለማድረግ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ብሎም ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚደረገውን የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነት የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ፈፅሟል። እነዚህ በሁኔታዎች ደግሞ በአሁኑ ወቅት የግሉ ባለሃብትና ወጣቱን አስተሳስረውታል። የሁለቱ የአገር ዋልታ አካላት ትስስር ለአገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ነው። እናም ይህ ትስስር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy