Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የድርቅ አደጋን በዘላቂነት ለመቋቋም

0 365

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የድርቅ አደጋን በዘላቂነት ለመቋቋም

                                                            ታዬ ከበደ

በአሁኑ ወቅትም ለድርቅ አደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ መንግስት ማናቸውንም ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል። መንግስት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት አስቀድሞ በመገንዘብ የተፈጠረውን ሁኔታ ለመቋቋም በዜጎችና በኢኮኖሚው  ላይ ሊደርስ የሚችለውን  ጉዳት ለማስቀረት የሚያስችል አቅጣጫ ቀይሶ ተግባራዊ እያደረገ ነው።

እርግጥ በተፈጥሮ የአየር መዛባት ምክንያት በሀገራችን የድርቅ አደጋ ሲከሰት አዲስ ነገር አይደለም። ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰት ጉዳይ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም። ሆኖም ይህ በየጊዜው ሀገራችንን የሚጎበኛት የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብነት እንዳይቀየር መንግስት ብርቱ ጥረት አድርጓል።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የመንግስት ትኩረት ምንም ዓይነት የአየር ንብረት መዛባትና ድርቅ  ቢያጋጥምም፤ ህዝባችን  የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ ቆመቆየቱ አይዘነጋም። የኤልኒኖ አደጋ በተከሰተበት ወቅትም አደጋውን በመቀልበስ የልማት አጋር ሀገራትን ድጋፍ እምብዛም ሳያገኝ ችግሩ ወደ ረሃብነት ሳይቀየር መቋቋሙ ይህን ጥረቱን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይመስለኝም።

በእኔ እምነት መንግስት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረግ እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ  በሆነ አኳሃን ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉ ለዜጎቹ ያለውን የኃላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ ስሜትንና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ለእርሻ የሚውል ሰፊ መሬት አላት። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችውም መሬት ቢሆን የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። አመራረቱም እጅግ ኋላ ቀር ሆኖ ቆይቷል።

ይህን ዕውነታ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አነስተኛ የአርሶ አደሮችን ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሯል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖችን አፍ ማስያዝ የቻለ ትክክለኛ መስመርን በመከተል ውጤት ማምጣት ችሏል።

በአርብቶ አደሩም አካባቢ ተመሳሳይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመቅረፅና ቀደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ ድርቅ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ በአያሌው መቀነስ ተችሏል። ከእነዚህ መንግስታዊ ጥረቶች ውስጥ የአርብቶ አደር የልማት ፓኬጆችን በመቅረፅ፤ አርብቶ አደሩ ከልማዳዊ የአኗኗር ባህል ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ህይወት እንዲቀየር፣ ከአርብቶ አደሩ ጋር በመነጋገር ድርቅን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመስኖ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እንዲሸጋገር ብሎም ምርጥ ዝርያዎችን አግኝቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃዎችን በአግባቡ የማሰባሰብ ስራዎችን እንዲያጠናክር እየተደረገ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የመሰረተ ልማትና የሌሎች የልማት ዘርፎች ተቃሚ ይሆን ዘንድ በፍፁም ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሰፈራ ፕሮግራምን እንዲቀበል፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከርና በዚህም ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የማድረግ ስራዎችን ማከናወኑና በማከናወን ላይ መሆኑ ጥቂት ተጠቃሽ ምሳሌዎች ናቸው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ባለፉት ዓመታት የመንግስት ትኩረት ምንም ዓይነት  የአየር ንብረት  መዛባትና ድርቅ ቢያጋጥምም፤ ህዝባችን የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ ቆይቷል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን ድርቅ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረጉ  እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ በሆነ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል የክትትል አሰራርን መከተሉ አሁን ላለበት አቅም ያበቁት ይመስለኛል።

ዳሩ ግን አንዳንድ ወገኖች ይህን የመንግስትን የዕድገት ውጤት የሆነውን ችግርን በራስ አቅም የመቋቋም አቅምን ሊያኮሰምኑት ይፈልጋሉ። ይህ እሳቤያቸው ፈፅሞ ከእውነታው ያፈነገጠ ነው።

እንደሚታወቀው በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት የምትመራው ሀገራችን ላለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት ባስመዘገበችው ዕድገት ችግሮችን እየተቋቋመች መጥታለች። በእነዚህ ዓመታቶች ውስጥ ዓመንግስት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥናት ለማስወገድ በመሞከርና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ክንዋኔዎችን በመስራት፣ ያሉትን ውስን ሃብቶች መሠረታዊ ችግሮችን በሚፈቱበት የልማት ስራዎች ላይ በማዋል፣ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እና የግል ኢንቨስትመንት በማበረታታት ፈጣን ቀጣይነትና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበራዊ ልማት ለማምጣት ተችሏል።

ይህም ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ማህበራዊ ልማት በአሁኑ ወቅትም ገቢራዊ እየሆነ ላለው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መንደርደሪያ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ መንደርደሪያነትም በአሁኑ ወቅት ድርቅን በህዝባዊ ሃላፊነት መንፈስ ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው። አጥጋቢ ውጤትም ተገኝቶበታል ማለት ይቻላል።

እዚህ ላይ አቅም ስለገነባን የለጋሽ ሀገራት ድጋፍ አያስፈልገንም’ እያልኩ አይደለም። ሙሉ ለሙሉ በሁለት እግራችን እስንቆም ድረስ የለጋሽ ሀገራት ድጋፍ ይጠቅመናል። እያንዳንዷ ሽርፍራፊ ሳንቲም ለልማታችንም ይሁን ለችግራችን ፋይዳ እስካላት ድረስ ጠቃሚያችን ናት። በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋልም ይኖርባታል። ከዚህ አኳያ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል ከለጋሽ ሀገራት እገዛና ድጋፍ በመጠኑም ቢሆን ተገኝቷል።

ሆኖም መንግስት ህዝባዊ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ እንደተለመደው ችግሩን ከህዝቡ ጋር በመሆን ይወጣዋል። ይህን ለማድረግም ቀደም ሲል የጠቀስኩት የመንግስት አቅም ምላሽ ይሰጣል፤ እየሰጠም ነው።

በአጠቃላይ መንግስት የተከተለው ልማታዊ መስመር ድርቅን በተገቢው ሁኔታ እየተቋቋመ ነው። በአሁኑ ወቅትም በዝናብ እጥረት ሳቢያ በደቡብና በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው የድርቅ አደጋን ለመከላከል፣ ያለፉትን ተሞክሮዎች በመቀመርና ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ በመለየት ህዝባዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ተግባሩን መቀጠሉ አይቀሬ ነው። አቅም የፈጠረ በመሆኑም አሁንም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው።

በመሆኑም ተረጅውም ሆነ አጠቃላይ ህዝቡ ይህን የመንግስትን አቅምና ህዝባዊ ሃላፊነት ሊገነዘበው ይገባል። የኢትዮጵያ መንግስት ከሁሉም ተግባሮቹ በፊት የሚያስቀድመው የህዝቡን ተጠቃሚነት ነው። ህብረተሰቡ መንግስት የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የሚያደርጋቸውን ጥረት በመገንዘብ ከእርሱም የሚጠበቁትን ድጋፎች እንደ ወትሮው ማከናወን ይኖርበታል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy