Artcles

የድንበር ችግሮችን የሚፈታ ስርዓት

By Admin

July 20, 2017

የድንበር ችግሮችን የሚፈታ ስርዓት

ዳዊት ምትኩ

አገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ የድንበር ውዝግቦችን የመፍታት ስርዓትና አቅም ያለው ነው። ስርዓቱ ብህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ባለፉት ስርዓቶች ይነሱ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት እየፈታ ዛሬ ላይ ደርሷል። በቅርቡም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልል ብሎም በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የነበሩ የድንበር ችግሮችን በሰከነ ሁኔታ እየፈታ ነው።

ይህ በመስተዳድሮቹና ህዝቡ የጋራ ጥረት በመከናወን ላይ የሚገኘው የድንበር ችግሮችን የመፍታት ጉዳይ በስርዓቱ መሰረት የህግ አግባብን ተመርኩዞ የሚከናወን ነው። ከላይ ለአብነት በቀረቡት ክልሎች መካከል የተካሄደው የድንበር ማካለል ችግሮችን እልባት የመስጠት ተግባር  ወደፊትም ከድንበር ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮች ካሉ ስርዓቱ ባለው አሰራር መሰረት የሚፈታው መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታም ስርዓቱ ማናቸውንም ችግሮች በራሱ የአሰራር ስርዓት የመፍታት ብቃትና አቅም መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

እንደሚታወቀው ታዲያ ይህ እኩይ ተግባራቸውም የሚያመላክተው ነገር፤ ልክ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ታሪክ ራሱን በመድገም እነዚህ ኃይሎች የሥርዓቱን እመርታ ቁጭት በተንሸዋረረው  የተገለበጠ መነፅር እየተመለከቱ ለማደናገር መሞከራቸውን ነው።

እርግጥ የማምታታትና የማደናገር ሙከራቸው ምንም ውጤት ሊያስገኝላቸው አልቻለም። መላው የሀገሪቱ ህዝቦች በደማቸው የፃፉት ህገ መንግሥት ፀድቆ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም በአንድነት ተሳስረው የእድገት ጉዟቸውን ተያይዘውታል። ሆኖም አላዛኞችም የሚደልቁት የቆርጦ ቀጥልነት አታሞም ሰሚ አጥቷል።

አንዳንዶቹ ጭራሹኑ በግጦሽ ቦታና በውኃ ምክንያት በአንዳንድ የሀገራችን ብሔረሰቦች መካከል ለዘመናት ሲከሰቱ የኖሩ ግጭቶች መኖራቸውን እንዲሁም አማርኛ ተናጋሪዎች ከአንዳንድ አካባቢዎች ተባረሩ እስከማለት መድረሳቸው ይታወቃል። ሆኖም ስርዓቱ ማናቸውንም ችግሮች የመፍታት አቅምና ብቃት እንዳለው እያሳየ መሆኑን ሊመለከቱ አይሹም። ሃቁ ግን ከላይ ለአብነት እንደጠቀስኩት የስርዓቱ ችግሮችን የመፍታት ብቃት ከፍተኛ ነው።

በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን እያውቁም ወይም ቢያውቁም ለመናገር የሚደፍሩ አይደሉም። ምክንያቱም ለእነርሱ ጥላሸት የመቀባት ሥራ ይህ ሀቅ ምንም ስለማይጠቅማቸው ነው። ሆኖም እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባ እና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ በሥልጣኔ በበለፀጉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ አይቀርም።

ይህ ብቻ አይደለም። ሰው ከራሱ፣ በአቅራቢያው ካለውና ከተፈጥሮ ጋር መጋጨቱም አይቀሬ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዓለማችን ላይ ያለው የተፈጥሮ ሀብት እጥረት ነው። ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየች አይደለችም፤ እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሀብት እጥረት አለባት። እናም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ ነው። ያም ሆኖ ግን የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት እነዚህን ነባራዊ ችግሮች ሳይቀሩ የመፍታት አቅም አለው።

እናም ስርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን እየለወጠ ነው። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሃብታቸው እንዲሆን ማድረግ እየቻለ ነው።

ይህም ሆኖ ያለፉት ስርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም፤ ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ። ስርዓቱ ነባራዊ ችግሮችን በመፍታት የሀገሪቱን ህዝቦች በአንድነት በማስተሳሰር ከሰሃራ በታች ጠንካራ ምጣኔ ሃብት መገንባት የቻለና ህዝቡንም በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ሆኗል። ስለሆነም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ታሪክ እየተገነባ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተገነባ ያለው ስርዓት ራሱን በራሱ እያረመና እያስተካከለ የሚሄድ ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የተገነባ አይደለም። ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። እናም በሂደቱ ውስጥ ጥቃቅን ስንክሳሮች ሊያጋጥሙት ይችላል። ዋናው ነገር እነዚህ ጊዜያዊ ችግሮች በብቃት እየተፈቱ የመሄዳቸው ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ የደረሰ መሆኑ ነው። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ የድንበር ችግሮችን በመፍታት ሁሉም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ስርዓት እየፈጠረ ነው።

እንደሚታወቀው ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፈቃድ ውጭ የመሰረቱት የሃይል አንድነት ነበር ሰፍኖ የቆየው፡፡ በገዥዎች አፈሙዝ እንጂ በሕዝቦች ፍላጎትና በመፈቃቀድ  ላይ ያልተመሰረተን አንድነት እውነትኛ ተብሎ ሊታሰብ አይችልም። እውነተኛ ሊሆን የሚችለው የትኛውም ህዝብ የራሱን እድል በራስ የመወሰን መብቱን ተጠቅሞ የሚመሰርተውና  ሊመሰርት የሚችለው ዴሞክራያዊ ስርዓት እንደሆነ መገንዘብ ያሻል።

ባለፉት ስርዓቶች መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተነፍገው ከነበሩ መብቶቻቸው መካከል የራስን ዕድል በራስ መወሰን አንዱ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ቻርተርና በሌሎች ዓለም አቀፍ ዶኩመንቶች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕውቅና እግኝቶ የነበረ ቢሆንም ያለፉት የኢትዮጵያ ገዥ መደቦች ይህንን መብት አፍነውት ኖረዋል።

በተለይም ተገልለውና ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና  ሕዝቦች ጋር ሆነው በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በእኩልነት የመሳተፍ መብት አልነበራቸውም። ይህ ሁኔታ በህገ መንግስቱ ተለውጧል። ዛሬ በድንበር ጉዳይ የሚከሰተቱ ችግሮችም ለህዝቦች የተሰጠው መብት መገለጫ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ባለፉት ስርዓቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲጨፈለቁ የነበሩባቸው መሆኑን ለመመልከት ተችሏል። ይህንን ሁኔታ ግን መላው ህዝቦች በመስዋእትነታቸው እውን ባደረጉት የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ለዘመናት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለማግኘት  የበቁበት ድልን ተጎናፅፈዋል።

ዛሬ መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ህገ መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን መብት ተጠቅመው ራሳቸውንም ይሁን ሀገራቸውን እየጠቀሙ ይገኛሉ። በዚህም በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥና እድገት እያስመዘገቡ ናቸው። ይህ ደግሞ ግለቱን ጠብቆ በመቀጠል ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ለመሰለፍ የሚያስችላቸው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ነድፈው ለሁለተኛ ጊዜ እየተረባበቡ ነው። እንደ ድንበር ችግሮች ዓይነት የጋራ ችግሮቻቸውን እየፈቱ እዚህ ደርሰዋል። ይህም የመሰረቱት ስርዓት ምን ያህል ችግሮችን የመፍታት ብቃት ያለው ያሳያል።