Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የግብር አስፈላጊነት

0 1,975

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የግብር አስፈላጊነት

                                                      ታዬ ከበደ

በየትኛውም አገር ውስጥ የሚገኝ መንግስት ለህዝቡ የተሟላ አገልግሎት መስጠት  እንዲችል ግብር መሰብሰቡ የግድ ነው። ከልማት የገቢ ምንጮች ውስጥ ዋነኛው በአገር ውስጥ የሚሰበሰብ ግብር መሆኑ እርግጥ ነው።

ግብር ከሌለ መንግስት ተግባሩን በሚፈለገው ሁኔታ ሊወጣ ካለመቻሉም በላይ አስፋጊነቱም ጥያቄ ውስጥ ይገባል። በሌላ በኩልም ህዝቡ መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን አያገኝም። መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማያገኝ ህዝብ ደግሞ እርካታ አይኖረውም። የየትኛውም ወገን አመኔታ ሊኖረው አይችልም።

አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር መክፈልን እንደ እዳ ይመለከቱታል። ይህ አስተሳሰብ እጅግ የተሳሳተ ነው። አስተሳሰቡን ለማረቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ያስፈልጋል። ግብር መክፈል ህጋዊ ብቻ አይደለም። የዜጎች ኩራትም ጭምር ነው።

ግብር ከፋይ ዜጋ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመረጠውን መንግስት አገልግሎት አሰጣጡን በተገቢው መንገድ ሊጠይቅ ይችላል። “እኔ እኮ ግብር ከፋይ ነኝ” ብሎ ማናቸውንም ግልጋሎት የማግኘት መብቱንም ይጎናፀፋል።

ሆኖም እንደ እኛ ባለ አገር ውስጥ ግብር መክፈል የአገርን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት፣ ኢኮኖሚው ጠንካራ እንዲሆንና ለህዝብ የሚሰራ መንግስት እንዲኖር ያደርጋል። እናም ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር መክፈል የዜግነት ክብር ማረጋገጫ እንጂ ግዴታ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለዜጎቿ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የተጋረጠባትን የድህነት ፈተና ለመሻገር ብርቱ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ይህምን ጥረቷን እውን ለማድረግም በቂ በጀት ያስፈልጋታል። ይህ በጀት ደግሞ ከየትም የሚመጣ አይደለም።

ህዝቡ ለመንግስት ከሚከፍለው ግብር መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ሀገራችን ውስጥ ያለው መንግስት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንደመሆኑ መጠን፤ የግሉ ባለሃብት በቂ ሁኔታ ሊፈፅማቸው የማይችላቸውን ጉዳዩች መንግስት በተመረ አኳኋን ጣልቃ ገብቶ ይፈፅማል። ታዲያ ይህን ተግባር ለመከወን መንግስት ገንዘብ ያስፈልገዋል። የግሉ ባለሃብት በማይሰማራባቸው፣ ነገር ግን አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ የገጠር ልማቶችን ለመተግበር መንግስት በጀት ሊኖረው ይገባል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ይህን የግብርን አስፈላጊነት ካለመገንዘብ በቀን ገቢ ግምት አወሳሰን ዙሪያ ችግር ፈጠሩ ይታወቃል። ዳሩ ግን ምንጊዜም ቢሆን አንድ አዲስ አሰራር ሲጀመር ከግንዛቤ እጥረት፣ ከአንዳንድ የአፈፃጸም ስህተቶች፣ ከህግ ማዕቀፍ ልልነት እንዲሁም ከግል ጥቅምና ስሜታዊነት ተግዳሮቶች መኖራቸው ነባራዊ ነው። የሰሞኑን የግብር ቅሬታ ከዚህ አኳያ መመልከት ጠቀሜታ ይኖረዋል።

ከዚህ ውጪ አንዳንድ ወገኖች ይህን ሁኔታ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ አብዛኛው ነጋዴ በሀገሩ መስራት እንዳልቻለ ሲያስወሩ ይደመጣል። በእውነቱ ይህ ሃላፊነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው። በምንም ዓይነት መስፈርት ከግብር አከፋፈሉ ጋር የተያያዘ አይደለም።

እርግጥም ግብር አለመክፈል ራስን መልሶ መበደል ነው። ለራስ የሚሰጥን አገልግሎት በራስ ፈቃድ መከልከል ነው። በነጋዴው በኩል የሚነሱት ቅሬታዎች የሚፈቱበት ህጋዊ አሰራር የተዘረጋ በመሆኑ በእነዚህ ወገኖች የተሳሳተ እሳቤ መመራት የሚገባ አይመስለኝም።

በእርግጥ ትክክለኛና ለህዝብ የሚቆረቆር አካል የህዝቡን ችግር ተገንዝቦ ለመፍትሔው ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ይሰራል እንጂ ውዥንብር በመንዛት አገርን ለመጉዳት አይንቀሳቀስም። ለአገር የሚያስብ ወገን ግበርን መክፈል የአገርንና የህዝብን ደህንነት እንደሚያስጠብቅ፣ ልማትን እንደሚያፋጥን፣ እድገትን እንደሚያመጣና ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል በአያሌው እንደሚደግፍ ይገነዘባል።

ለአገርና ለወገን የሚያስብ ህዝብ ግብር መክፈልን እንደ እዳ ሳይሆን እንደ መብት ይቆጥራል። በመሆኑም ስለ ግብር መክፈል ሲወሳ እነዚህ ጉዳዩች ሁሉ ከግምት ውስጥ ገብተው ከህዝብ ተጠቃሚነት አኳያ መመዘን ይኖርባቸዋል።

ሁሉም እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ውስጥ ናት። መሰረተ ልማቶች፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችና ሌሎች የመንግስትና የህዝብ ወጪዎች የሚሸፈኑት በግብር ነው። መንግስት መልሶ ለህዝቡ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያውላቸው እንጂ የትም የሚሄዱ አይደሉም። በመሆኑም የቀን ገቢ ግብር ተመን እነዚህን እውነታዎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

እርግጥ ግምቱ በተካሄደበት ወቅት ገማቾቹ ሰዎች ናቸውና የመብዛት አሊያም የመቀነስ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ፍትሃዊም ላይሆን ይችላል። ለዚህ ደግሞ አንዳንድ ግብር ከፋዩች ዕቃ በማሸሽ፣ የንግድ ቦታን በመዝጋት፣ መረጃን አሳንሶ በመስጠትና መሰል ችግሮችን በመፍጠር ግምቱ ሙሉ በሙሉ ፍትሃዊ እንዳይሆን የበከኩላቸውን ድርሻ እንዳበረከቱ አይዘነጋም።

ያም ሆኖ በቀን ግብረ ገቢ አወሳሰን ላይ ፍትሃዊነትን ለማንገስ መንግስት በየወረዳው የቅሬታ ሰሚ በማቋቋም የህብረተሰቡን ቅሬታ እየተቀበለ ነው። በቅሬታውም ትክክል ያልሆነን አወሳሰን በማስተካከል፣ ከገቢው በታች የሆነውንም የማረም ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ቀደም ሲል ግብር ሳይከፍሉ ይነግዱ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለምን ግብር ከፈልን ማለት ያለባቸው አይመስለኝም። በዓለም ላይ ግብር የማይከፈልበት ስራ የለም። በየትኛውም ሀገር ውስጥ ስራ የሚሰራ ሰው

ታዲያ ሃቁ እንኳንስ በምድራዊ አሰራር ቀር በሃይማኖታዊም የሚታወቅ ነው። ምክንያቱም ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮቶች ውስጥ አንዱ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የኢየሱስን ለኢየሱስ” ተብሎ ስለተገለፀ ነው። እናም ግብር መክፈል ከምድራዊ አስተሳሰቡ ባሻገር ሃይማኖታዊ ተቀባይነትም ያለው ነው።

ያም ሆኖ የቀን ገቢ አወሳሰኑ በነጋዴው ላይ ተጨማሪ ግብር ለመጣል አይደለም። ይልቁንም በየትኛውም ዓለም እንደሚሰራበት በመረጃ ላይ የተመሰረተ የግብር ስርዓት ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። እናም የንግዱ ማህበረሰብ ይህን እውነታ ሊገነዘብ ይገባል።

እናም በአንዳንድ ወገኖች ስለ ግበር አከፋፈልና ነጋዴዎች “ወስደውታል” እየተባለ ስለሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን የንግዱ ማህበረሰብ መረዳት አለበት። የቀን ገቢ ግብር ግምቱ መነሻው ምንም አይደለም። ዋነኛ ማጠንጠኛው የአገርን ልማት በማፋጠን ድህነትን ለመቅረፍ ነው። በመሆኑም የግብር ፋይዳና አስፈላጊነትን ከዚህ አኳያ መመዘኑ ተገቢ ነው። እንዲያውም ግብር ካለተከፈለ ስለ መንግስት ተግባሮች፣ ስለ አገር እድገትና ስልጣኔ እንዲሁም ስለ ግልም ይሁን ስለ ጋራ ተጠቃሚነት ማውሳት ፈፅሞ የሚቻል አይመስለኝም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy