Artcles

የግድቡ ፍትሐዊነት

By Admin

July 21, 2017

የግድቡ ፍትሐዊነት

                                                          ታዬ ከበደ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጣናውን በኢኮኖሚ ከማስተሳሰር ባለፈ፣ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ፍትሐዊ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ግድቡ ኢትዮጵያዊያን የትኛውንም አካል ሳይጎዱ በፍትሐዊ አስተሳሰብ እንደሚመሩ ዋነኛ ማስረጃ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት እያደገ በመሄድ ላይ በሚገኘው ምጣኔ ሃብታችን ሳቢያ፣ ግብርና የመሪነት ሚናውን በሂደት ለኢንዱስትሪው ሲያስረክብ ለሚፈጠረው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ነው።

ለግብፅ ጭምር ኤሌክትሪክ በመሸጥም የውጭ ምንዛሪ አቅማችን እንዲጎለብት ማድረጉ አይቀሬ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግስት የነደፈውና ተፈፃሚ በመሆን ላይ የሚገኘው ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በማሳካት የሀገራችን ህዳሴ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ በማድረግ የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

የኢፌዴሪ መንግስትም ሀገራዊ የፀረ ድህነት ትግሉን በማቀጣጠል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራን ይፋ የማድረጉ ምክንያትም ይኸው ይመስለኛል። እርግጥ የግድቡ ግንባታ ለዘመናት የዘለቀውን የድህነትና የኋላቀርነት ታሪካችንን የመቀየርና ያለመቀየር ጉዳይ አንዱ ምክንያት በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳነቱ ሊያጠያይቅ አይችልም።

በመሆኑም የግድቡን ግንባታ የማሳካቱ ጉዳይ የአሁኑን ትውልድ ህይወት የመለወጥና ያለ መለወጥ ጥያቄና ውሳኔ ብቻ አይሆንም— የቀጣዩን ትውልድ ህልውና የማረጋገጥና ያለማረጋገጥ ብሎም ሀገራዊ ህልውናን የማስቀጠል ሀገራዊ ፋይዳ ያለውም አንድ ማሳያ በመሆኑም ጭምር እንጂ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም—የጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ጭምር መሆኑ በሀገራችን በተደጋጋሚ ተገልጿል።

እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ላለባቸው እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ለቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ ይሆናል።

አገራችን ከምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አኳያ ሌሎችን የመጉዳት አስተሳሰብን ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ አታራምድም። ይልቁንም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የምታምንና ይህንንም በተግባር እያረጋገጠች የምትገኝ መሆኗን በተለያዩ መድረኮች ማስመስከር ችላለች።

ለአብነት ያህልም የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የኢንቴቤው ስምምነት በማሳያነት ማቅረብ የሚቻል ይመስለኛል። ይህን ስምምነት ከዳር ለማድረስ ከአስራ ሶስት ዓመታት በላይ መፍጀቱ ጉዳዩ ምን ያህል ጥረት እንደጠየቀ ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም። ምክንያቱም ስምምነቱ በዓባይ ተፋሰስ የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የነበረው አስተሳሰብን መቀየሩ እንዲሁም ሀገራችን ከምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር እንዲመጋገብ የማድረጉን ዕውነታ ስለሚያሳይ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ መኖርን፣ ማደግንና መበልጸግን ከማንም በላይ የምንቀበልና የማንነታችን መገለጫም ነው። ልክ እንደ ሌሎች “ለብቻችን” ብለን አናውቅም። እናም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታችን ትኩረትም ማንንም ለመጉዳት ያለመ እንዳልሆነ ማንኛውም አካል ሊያውቅ ይገባል፡፡ አብሮ መብላትና ተያይዞ ማደግ የቆየ ኢትዮጵያዊ እሴት መለያ ባህሪ እንደሆነም ጭምር፡፡

ሀገራችን በተፈጥሯዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ዓለም አቀፋዊው የእኩልነትና የፍትሃዊነት መርህን መሰረት ላደረገው የኢንቴቤው የስምምነት ማዕቀፍ ተግባራዊነት በግምባር ቀደምትነት የተሰለፈችውም ለዚሁ ነው።

መላው ዜጎቿም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን እያበረከቱ የሚገኙት ደግሞ ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን ሙሉ ለሙሉ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጥንቅቀው ስለሚያውቁ ነው።

ግድቡ ለእኛ የላቀ ፋይዳ ስላለው ትናንት የነበረው አቋማችን ዛሬም ሊንጋደድ አይችልም። አቋማችን የትናንቱ ነው። ግድቡ ሀገራችን የተያያዘችውን የፀረ- ድህነት ትግል ከግብ በማድረስ ለህዳሴው ጉዞ ስኬት የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ አያጠያይቅም። የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የኤሌትሪክ ሽፋን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ፤ ለዘመናት መብራት እንደ ገነት ለራቀው የገጠሩ ህዝባችን ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ይህም ለከፍተኛው የደንና የመሬት መራቆት ችግር እንዲሁም ሊከሰት የሚችለውን የአየር መዛባትና የሚያስከትለውን የድርቅ አደጋ የሚያስቀር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከሃይል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለሚደርሰው የጤና ችግር እልባት ይሰጣል፤ መሳ ለመሳም ለህክምና የሚወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ይህም ፋይዳውን ድርብ ድርብርብ ያደርገዋል።

የዘመናት የድህነት ታሪካችንን ለመቀየርና ከተጫነን ድህነት ለመውጣት በምናደርገው ትግል ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት በግድቡ ግንባታ ስፍራ ላይ የመሰረት ድንጋይ ካኖረበት ጊዜ ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት ስኬታማነቱን ዕውን ለማድረግና በራሳችን ተነሳሽነት ማናቸውንም ጉዳዮች ለመከወን ቃል ገብተናል። በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝብ የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት በአዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ተደርጓል።

በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል። ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ ከፍተኛ ነው።

እርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብሔራዊ መግባባት መንፈስ ግድቡን ካለአንዳች ልዩነት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለመገንባት ሲነሱ ተርፏቸው አይደለም። በድህነት አለንጋ መገረፉ ማብቃት እንዳለበት ስለሚያምኑ ብቻ ነው።

ያም ሆነ ይህ ግን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገራችን የምትከተለውን የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተመስርቶ በመገንባት ላይ የሚገኝ ህዝባዊ ልማት ነው።

ይህ በራስ አቅም የመልማት ስራችን ሀገራችን ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት አንድ ማሳያ እንጂ የማንንም ጥቅም ለመጉዳት ታስቦ የሚከናወን አይደለም። ግድቡ ግብፅን ጨምሮ ለጎረቤቶቻችን ህዝቦች የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታ መድህን በመሆን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንጂ የየትኛውንም ሀገር ህዝብ ጥቅም አይፃረርም። ይህም የሀገራችንን ህዝቦችና የመንግስትን ፍትሐዊ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ ነው።