የጥላቻን መርዝ የሚያረክስ ሸንጎ
ብ. ነጋሽ
ኢትዮጵያ የተለያየ ብሄራዊ ማንነት (ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ልማድ፣ ታሪክ)፣ ሃይማኖት ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ ሃገር ነች። በዚህ ብዝሃነት ውስጥ በህዝቦች መሃከል የእርስ በርስ ግጭት የተፈጠረበት የታሪክ አጋጣሚ የለም። የሃገሪቱ መሪዎች – ነገሥታት ወሰናቸውን ለማስፋት ጦርነት ያወጁበት፣ የስልጣናቸውን አይነኬነት ለማረጋጋጥ ሃይማኖትን እንደርዕዮተ ዓለም የዘው የአንድ ሃይማኖት የበላይነትን የሰበኩበት፣ አንድ ብሄራዊ ማንነት የኢትዮጵያዊነት መግለጫ እንዲሆን ያወጁበት ሁኔታ ግን አለ። ይህ የነገስታቱ እርምጃ በህዝቦች መሃከል የሃይማኖትና የብሄር ግጭት መንስኤ ሆኖ ግን አያውቅም።
የዘውዳዊው ስርአት ነገሥታትና በኋላም ወታደራዊው መንግስት የብሄራዊ ነጻነት ጥያቄዎችን ለመድፈቅ፣ ማንነትን የማንኳሰስና የማጥፋት ስትራቴጂ ነድፈው ተንቀሳቅሰዋል። የብሄራዊ ነጻነት ጥያቄ ባነሱ ላይ አፈና፣ እስርና ግድያ ፈጽመዋል። አንዱ ብሄር በሌላው፣ አንዱ ሃይማኖት በሌላው ላይ ተነስቶ አያውቅም፣ በብሄሮችና ሃይማኖቶች መሃከል በጥርጣሬ የመተያያት መቀያየም ተፈጥሮ አያውቅም። አንዱ ሌላው ከመኖሪያ አካባቢው እንዲወጣ የዘር ማጥራት እርምጃ አውጆ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ የጋራ ጠላታቸው በሆኑት የውጭ ወራሪዎች፣ ዘውዳዊና ወታደራዊ ስርአቶች ላይ በጋራ ተነስተዋል።
የውጭ ወራሪዎችን ለመመከት የተካሄዱትን ውጊያዎች፣ ዘውዳዊውን ስርአት በመቃወም ከተካሄደው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከ ጸረ ደረግ የትጥቅ ትግል ወቅት የነበረውን ሁኔታ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። በተለይ ኢህአዴግ ያካሄደው የፀረ ደርግ ትግል ዋነኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በፀረ ደርግ ትግል ውስጥ የትግራይ፣ የኩናማ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች . . . አባላት በኢህአዴግ ስር በአንድ ግንባር ተሰልፈው ተዋግተዋል። መስዋዕትነት ከፍለው በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች በአንድ ግንባር ተሰልፈው መስዋዕትነት የከፈሉት የሁሉም ብሄራዊ ማንነት እኩልነት የተረጋገጠባት የጋራ ሃገር ለመመስረት ነበር። በዚህ የጋራ ትግልና መስዋጽትነት በመከባበር፣ በእኩልነትና በመቻቻል ከሚያምኑ ሌሎች የሃገሪቱ ሃይሎች ጋር በመሆን ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነትና በመከባባር ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የሚኖሩበትን ፌዴራላዊ ስርአት መገንባት ችለዋል። የኢፌዴሪ የመንግስት ስርአት።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነትና በመከባባር ላይ በተመሰረተ አንድነት ለመኖር በህገመንግስት ቃልኪዳን አስረው የኢፌዴሪ መንግስትን ከመሰረቱ በኋላ፣ አልፎ አልፎ የእርስ በርስ ጥላቻና ግጭት የሚመስሉ ሁኔታዎች ታይተዋል።
በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጉራ ፈርዳ፤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እንዲሁም ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር ገደማ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ይህ ሁኔታ ታይቷል። በደቡብና ቤኒሻንጉል ክልሎች የአማራ ብሄር ተወላጆችን የማባረር፣ በአማራ ክልለ ሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ የትግራይ ብሄር ተወላጆችን የማባረር ሙከራ ተደርጓል።
አንዳንድ ወገኖች ይህን ሁኔታ በብሄሮች መሃከል ካለ የእርስ በርስ ጥላቻ የመነጨ አድርገው ሲያቀርቡት ይደመጣል። ፌደራላዊ ስርአቱ የፈጠረው አስመስለው የሚያቀርቡትም አሉ። በመሰረቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች በጭቆና ውስጥ በነበሩበት ዘመን፣ አንዱ ከፍ ሌላው ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ የሚያደርግ ፖሊሲና ህግ በነበረበት ዘመን፣ እንደ ህዝብ አንዱ ሌላውን አልጠላም። አንዱ ሌላው ላይ አልተነሳም።
በእነዚህ የብሄራዊ ጭቆና ዘመናት አንዱ በሌላው አካባቢ የሚኖርበት ሁኔታ ነበር። አማሮች በኦሮሞ፣ ትግራዮች በአማራ፣ አማሮች በትግራይ መሃከል ይኖሩ ነበር። ታዲያ ያኔ በጭቆናው ዘመን አንዱ ሌላው ላይ ሳይነሳ አሁን ራስን በራስ የማስተዳደርና የእኩልነት መብታቸው በህገመንግስት ሲረጋገጥ ወደመጠላላት፣ በጥርጣሬ ወደመተያየትና ማባረር የሚያደርሳቸው ምን ምክንያት ተፈጠረ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ነገሩ ወዲህ ነው። ቀደም ሲል በናሙናነት የጠቀስኳቸው አካባቢዎች በብሄሮች መሃከል ጥላቻና ባለጋራነት አልተፈጠረም። ጥላቻና ባለጋራነት የተፈጠረ የሚያስመስለውን ሁኔታ የፈጠሩት ትምክህተኞችና ጠባብ ብሄረተኞች ናቸው። ትምክህተኞችና ጠባቦች ለህዝብ መብትና ነጻነት ግድ ኖሯቸው አያውቅም። ለትምክህተኞችና ጠባቦች ህዝብ እነርሱን ወደስልጣን ሊያወጣ የሚችል መሳሪያ ከመሆን ውጭ በራሱ ፍላጎት፣ መብትና ነጻነት ያለው አካል አይደለም። ለዚህ ዓላማቸው ማሳኪያ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የችግርና የጭቆና ምንጭ ሌላኛው ብሄር ወይም ብሄረሰብ እንደሆነ በመቀስቀስ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያይ፣ እንዲጋጭ፣ አንዱ ሌላውን በባለጋራነት ፈርጆ እንዲያባርር ወዘተ ያደርጋሉ። በኢትዮጵያ ትምክህተኞችና ጠባቦች ስፍራ ባጡበት ባለፉ ዓመታት የተደረገው ይህ ነው።
እነዚህ ትምክህተኞችና ጠባቦች በውጭ ሃገራት መሽገው፣ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የገነቡትን ፌደራላዊ ስርአት ለማፍረስ ብሄሮች እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ አንዱ ሌላውን በጥላቻ እንዲመለከት፣ እንዲሁም አጋጣሚ ጠብቆ አንዱ ሌላውን በማባረር የዘር ማጥራት እርምጃ እንዲወስድ እየቀሰቀሱ ይገኛሉ።
የእነዚህን ትምክህተኞችና ጽንፈኞች ሚዲያዎችና ማህበራዊ ሚዲያዎች መመልከት ለዚህ በቂ አስረጂ ነው። አንዴም የብሄር ጥላቻ ከመቀስቀስ፣ የጥላቻ ንግግር ከማሰራጨት ተቆጥበው አያውቁም። በተለይ ባለፈው ዓመት በሰሜን ጎንደር በትግራይ ብሄር ተወላጆች ላይ የተሞከረው የዘር ማጥራት እርምጃ የዚህ የትምክህተኞች ቅስቀሳ ውጤት ነው።
ይህን በብሄሮች መሃከል የሚቀሰቀስ ጥላቻና ግጭት የሚመለከት ጉዳይ እንዳነሳ የቀሰቀሰኝ በቅርቡ በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መቀሌ ከተማ የተካሄደው የአማራና የትግራይ የሃገር ሽማግሌዎች የሰላም ሸንጎ ነው። ይህ ሸንጎ በተለይ ባለፈው ዓመት ልክ በዚህ ወቅት – ሃምሌና ነሃሴ 2008 ዓ/ም በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጎንደር በአካባቢው ለዓመታት ከጎንደሬዎች ጋር አብረው የኖሩ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ላይ ተቀስቅሶ የነበረው ጥላቻና በተወሰነ ደረጃ የተወሰደው የዘር ማጥራት ባህሪ ያለውን አሳዛኝ ክስተት አስታወሰኝ።
የአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ከትግራይ ክልል ጋር ይዋሰናል። በዚህ ምክንያት እንደማንኛውም ተዋሳኝ ክልል የአንዱ ብሄር አባላት በሌኛው ውስጥ በብዛት የሚኖሩበት ሁኔታ አለ። በዚህ ሁኔታ ለዘመናት አብረው ኖረዋል። አብሮነታቸው በጋብቻና በአበልጅ የዝምድና ትስስር፣ በጉርብትና፣ እድርና እቁብን በመሳሰሉ ማህበራዊ ተቋማት የጠነከረና በመተሳሰብና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ነው። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ይህ አብሮነት የቀደሙት ስርአቶች አንዱን የራሳቸው አስመስለው ሌላውን በሚገፉበትና ለብሄራዊ ጭቆና በዳረጉባቸው ጊዜያት እንኳን በጥርጣሬ ወደመተያያትና ጥላቻ አልተለወጠም። ጽኑና ጠንካራ ህብረት ነበራቸው።
ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትምክህተኞች በሁለቱ ብሄሮች ተወላጆች መሃከል ለዘመናት የጸናውን ጠንካራ አብሮነት፣ መከባበርና መቻቻል ለማዛል ያለማሰለስ የጥላቻ ቅስቀሳ ሲነዙ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህ ለዓመታት የተነዛ የጥላቻ ቅስቀሳ አምና ህይወት የዘራ የመሰለበትን ሁኔታ አስተውለናል።
ለዘመናት ከአካባቢው ህዝብ ጋር ተሳስረው የኖሩ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ተሞክሯል፤ ከመኖሪያቸው አፈናቅለው ለማባረር የተሞከረበት ሁኔታም ነበር። ይህ ከጥላቻ የመነጨ የዘር ማጥራት ባህሪ ያለው እርምጃ በምልዓተ ህዘቡ የተካሄደ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ትምክህተኞች በነዙት የጥላቻ ቅስቀሳ የተመረዙ በእድሜም በአመለካከትም ያልበሰሉ ጥቂት ወጣቶችና ትምክህተኞቹ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተባብረው የዘር ማጥራት ተልዕኮ ሰጥተው ባዘመቷቸው ግለሰቦች የተካሄደ ነው። ሳይሳካ የቀረው ለዚህ ነው። ይህን የኢትዮጵያ ጠላቶችና የትምክህተኞች ተልዕኮ ያከሸፈው ህዝቡ ራሱ ነው። ይሁን እንጂ ሃገር ተረካቢ ወጣት ውስጥ የተሰራጨው የጥላቻ መርዝ በግዜ እንዲረክስ መደረግ አለበት።
ታዲያ ሰሞኑን በትግራይ ክልል የተካሄደው የአማራና የትግራይ የሃገር ሽማግሌዎች የሰላም ሸንጎ ይህ ትምክህተኞችና በኢትዮጵያ ጠላቶች አዝማችነት በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ለዘመናት የነበረውን የእምነት፣ በጋብቻ፣ የጋራ ጠላትን በአንድ ግንባር ተሰልፎ ከመከላከል ታሪክ ወዘተ የመነጨ ወዳጀነትና መከባበር ለማበላሸት የነዙትን የጥላቻ መርዝ የሚያረክስ ነው። ከ1200 በላይ የሁለቱ ብሄር የሃገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት በትግራይ መቀሌ የተካሄደ የሰላም ሸንጎ ዓላማ የሁለቱን ህዝቦች የዘመናት ስር የሰደደ ወዳጅነት ማደስና ማጠናከር ነው።
በሰላም ሸንጎው ላይ የተሳተፉት የሃገር ሽማግሌዎች በውስጣቸው የሁለቱን ክልል ህዝቦች ግንኙነት የሚያበላሽ አንድም ችግር አለመኖሩን ገልጸዋል። የአማራና የትግራይ ህዝብ የውጭ ወራሪን ለመከላከል፣ ወታደራዊውን ደርግ ለመደምሰስ በጋራ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ያስታወሱት የሃገር ሽማግሌዎቹ፣ በህዝቡ መካከል ምንም የጥላቻ መንፈስ እንደሌለ አረጋግጠዋል። የሁለቱ ክልል ሕዝቦች ለዓመታት የገነቡትን አብሮነት በቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።
በተለይ ባለፈው ዓመት በሰሜን ጎንደር ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረውን የመጠላላት ባህሪ የነበረውን ሁኔታ ያስታወሱት የሃገር ሽማግሌዎች ይህ በህዝቡ የተፈጠረ አለመሆኑን መስክረዋል። ለዘመናት በደምና በሥጋ የተገነባው የሕዝቦች አንድነት በፀረ ሰላም ሃይሎች ሴራ እንደማይናጋም ያላቸውን እምነትና ምኞት ገልጸዋል። ህዝቡን ሰላም ለመንሳት የሞከሩትና አሁንም ከዚህ ያልታቀቡት ቡድኖች የኢትዮጵያን እድገት የማይመኙ የውጭ ኃይሎችና የጠባብነት፣ ትምክህትና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በመቀሌ ከተማ የተካሄደው የሰላም ሸንጎ በሁለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ግንኙነት ዳግም ለማደስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በመቀሌ የተካሄደው የአማራና የትግራይ የሃገር ሽማግሌዎች ሸንጎ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ትምክህተኞችና የሃገሪቱ የውጭ ጠላቶች ጥምረት ፈጥረው የነዙትን የጥላቻ መርዝ ሳይስፋፋ በማርከስ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ለዘመናት የዘለቀውን ጠንካራ ወዳጅነት የሚያድስ ነው።