Artcles

የፅንፈኞች ህልም እና ተግባር

By Admin

July 27, 2017

የፅንፈኞች ህልም እና ተግባር

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ጽንፈኝነት የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍልን የጋራ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ሁሉም በህብረት ሊታገለው ይገባል። ሁሉም ሠላሙን ይፈልጋልና። ሁሉም ልማትን ይሻልና። ለእነዚህ ዐቢይ ጉዳዮች ሲባል ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ የግድ ነው።   

 

ዛሬ አገራችን ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ ናት። እነዚህን በጎ ተግባራት ለማኮላሸት ብሎም ለማጣጣል የሚንቀሳቀሱ አጥፊ ኃይሎችን ታዝበናል። ተገቢ ያልሆኑና የተዛቡ አስተያየቶችን ሲሰጡም አድምጠናል።

 

ምን ይህ ብቻ! የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት የሚፈታተኑ አቋም ሲያራምዱም ተመልክተናል። ከአገሪቱ የውጭ ጠላቶች ጋር አብረው የተሳሳተ ጎዳና ላይ ቆመው ሲንገላወዱም አይተናል። ታሪካዊ ስህተት ሲፈፅሙም አስተውለናል።

 

በቀደሙት ዓመታት በአገሪቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ነን ባዮች በሚያራምዷቸው ህጋዊነት የጎደላቸው ተግባራት ምክንያት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ጥያቄ ያስነሱ እንደነበር ይታወሳል።

 

ዜጎች በፈለጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለተጽዕኖ ተደራጅተው እንዲሳተፉ ሙሉ ነጻነት ያጎናፀፋቸው የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነውን ህገ መንግሥት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመናድ አልመው ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል።

 

የዜጎችን መብትና እኩልነት ያረጋገጠውን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በነጻነት የአገሪቱን ህገ መንግሥት አክብረው በመንቀሳቀስ የፖለቲካ  አጀንዳቸውን በሕዝብ  ዘንድ በማስረፅ  በምርጫ  አሸንፈው  ወደ  ኃላፊነት  መምጣት የሚያስችላቸውን  ቀና  መንገድ  መከተል ይገባቸዋል።

 

ከዚህ ይልቅ  ግን ይህ ነው  የሚባል አጀንዳ ሳይኖራቸው በሕዝቡ መካከል ሁከትና ትርምስን በመፍጠር በግርግር ለመጠቀም በማለም ተፎካካሪ  የፖለቲካ  ድርጅቶቹ ህገ መንግሥቱን ሲተላለፉም አይተናል።

 

ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ አምስት አገራዊ ምርጫዎች ላይ እነዚህ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የነበራቸው ተሳትፎ የጎላ ነበር። ይሁንና አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገሪቱ ህገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት የህዝቡን ይሁንታና ድጋፍ ለማግኘት እየጣሩ እንዳሉ ቢታወቅም በተቃራኒው አንዳንዶች ደግሞ በህጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ስም ህገ መንግሥቱን ሲተላለፉ ይታያሉ።

 

በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከተዘረጋ ሀያ አምስት ዓመታት አልፈዋል። በአገሪቱ በተፈጠረው ምቹና ሰፊ  የፖለቲካ  ምህዳር  በመጠቀም ቁጥራችው ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመሥርተው የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላሉ።   

 

ታዲያ በውጭ አገራት ሆነው ገንዘብ በመላክና ህዝቡን በማታለል ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ወጣቶች፣ ሴቶችና አባቶች በማያውቁት ነገር ገብተው ለወንጀልና ለጥፋት እንዲዳረጉ ማድረግ አገርን ልመራ ዝግጁ ነኝ ከሚል ተፎካካሪ ፓርቲ ሆነ አመራር  የሚጠበቅ አይደለም።

 

አንዳንዶቹ ለኃይማኖታቸው ካላቸው ቀናኢነት አንጻር እየተታለሉ ከኃይማኖት ጋር ተቀላቅሎ የቀረበን ጉዳይ ኃይማኖታዊ ጥያቄና ተልዕኮ ያዘለ መስሏቸው ባላወቁት ጉዳይ ለፖለቲከኞች ህቡዕ አጀንዳ መፈፀሚያ መሣሪያ ሆነው ሲቀርቡ አይተናል።  

 

ቤተክርስቲያኖችንና መስጊዶችን ሲያቃጥሉ አይተናል። የኃይማኖት መምህራንና አባቶችን ሲገድሉ ተመልክተናል።የተለያዩ ወንጀሎችን በተለያዩ የእምነት ተከታዮች ላይ ሲፈጽሙም ታዝበናል። የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን መንግሥት የፈፀማቸው አስመስለው ፍትሃዊነት በጎደላቸውና ፅንፈኞቹ በሚመሩት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በማስተጋባት መንግሥትን ከእምነት ተከታዮች ጋር የማቆራቆስ ሥልትን በመከተል ሠላምን ለማደፍረስ ሲጥሩም ምስክር ሆነናል።  

 

የተለያዩ እምነት ተከታዮችን ከመንግሥት ጋር ለማጣላት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሲቀጥል ተመልክተናል። ይህ ሁኔታ በተለይ በእስልምና ኃይማኖት ጫፍ የወጣበት ደረጃ ላይም ተገኝተናል። ይህ ሁሉ ሲሆን እነሱም አሉ፤ እኛም ነበርን፤ አለን።

 

ያም ሆነ ይህ በኃይማኖታዊ መቻቻል ለዓለም ተምሣሌት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በኃይማኖት መካከል መቃቃርን ለመፍጠር የተደረገውን ይህን ክፉ ጥረት አክሽፎታል።

 

በአገሪቱ ለዘመናት የዘለቀው መቻቻል በቀላሉ በጥቂት ጽንፈኞች ፍላጎት ሊበጣጠስ እንደማይችል ለዓለም ሕዝብ አስመስክሯል። ዛሬ በኢትዮጵያ ለዚያውም የኃይማኖት እኩልነት በተረጋገጠባት አገር ኃይማኖታዊ ጦርነትን ለማቀጣጠል የሚያመች መሠረት እንደሌለም ለዓለም አሳይቷል።

በተለያዩ የኃይማኖት አማኞች መካከል መቋጫ የለሽ ሁከትና ሽብር ለመፍጠር የተሞከረው ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ ውኃ ባለመቋጠሩ ፅንፈኞቹ ሌላ ዘዬ መፈየድ ግድ ሆኖባቸውም ቆይቷል። አቅጣጫቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ እስልምና ኃይማኖት በማዞር በህዝበ ሙስሊሙ መካከል የእርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር አቅደውም ተንቀሳቅሰው ኖሯል።   

 

የእስልምና ኃይማኖት አማኞች እርስ በርሳቸው ተጋግዘው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። በመካከላቸው ያለው የአብሮነት ገመድም ጠንካራ ነው፤ በቀላሉ የማይበጠስ። ከሌላ እምነት ተከታዮች ጋር ያላቸው ቁርኝትም እንዲሁ እንደ ብረት የጠነከረ ነው፤ በቀላሉ የማፈረካከስ። በመሆኑም ፅንፈኞቹ የፈለጉትን ውጤት ማግኘት አልቻሉም።  

 

ፅንፈኞቹ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚኖሩ ንጹኃን ዜጎች ላይ ጉዳትን አድርሰዋል። በተለያዩ አካባቢዎች አንዱን ብሔር በሌላው ላይ አነሳስተዋል።

 

ለአብነት፤ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በጋምቤላ ክልሎች ከሌላ ክልል ሄደው በሚኖሩና በክልሉ ተወላጆች መካከል ግጭትን ፈጥረዋል። በዚህም የንጹኃን ዜጎች ደም ፈስሷል።  በፈፀሟቸው የሽብር ተግባራት ተጎጂ የሆኑ ዜጎች መንግሥትን አማርረዋል።  

 

ለሰዎች ህይወት የማይሳሱት የሽብር ቡድኖች በአንዳንድ አካባቢዎች ጅምላ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። በህዝብ መገልገያ ትራንስፖርቶች ላይ ጥቃትን ፈጽመዋል። ከዚህም አልፈው በገበያ ቦታዎችና በህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተቀነባብረዋል። ቤተክርስቲያኖች፣ መስጊዶችና ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ  ተቃጥለዋል።

 

ከዚህ የተነሳም ፅንፈኞቹ የቀቢፀ ተስፋ ርምጃዎችን መውሰድ ተያያዘዋል። ሰዎች በፍርሃት የተባሉትን ሁሉ ይቀበላሉ የሚል እምነት ይዞ መጓዝን መርጠዋል።    ጽንፈኞቹ የመረጡት ይህ መስመር የተለያየ እምነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያንን ሆነ በተመሳሳይ እምነት የሚኖሩ ዜጎችን ማነጣጠል በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እንደማይታሰብ ዘንግተውታል።

 

በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የማይፈረካከስ ቁርኝትና የማይፈርስ አንድነት አለ። ከዚህ የኃይማኖት ልዩነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ወይም ሊፈጠር የሚችል ክፍተት የለም። በዚህም ምክንያት በአገሪቱ የኃይማኖት እኩልነት ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ የኃይማኖት ጦርነት ማስነሳት ሆነ የዐረብ አገራቱን ዓይነት አመጽ ማነሳሳት አይቻልም።