Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፍላጎት ናዳው እጅግ በርክቷል

0 295

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፍላጎት ናዳው እጅግ በርክቷል

አባ መላኩ

 

ሁሉንም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዕለቱን መቅረፍ ባይቻልም በተሃድሶ ወቅት የተለዩ አንዳንድ ጥያቄዎች ምላሽ በማግኘት ላይ ናቸው።  የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን አሰራር በመዘርጋት መቀነስ  ይቻላል።  ይህ አሰራርም ውጤታማ የሚሆነው የመንግስትንና የህብረተሰቡን የቅርብ ክትትል ሲኖር ነው። ፈጣን የማህበራዊም ሆነ የኢኮኖሚያዊ ለውጦች  እስካሉ ድረስ  የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር  ችግሮች መኖራቸው የማይቀር ጉዳይ ነው።  የአገራችን  የዴሞክራሲ ስርዓት  ገና መጎልበት የሚፈልግ ጅምር በመሆኑ ሳቢያ  ህብረተሰቡን ሊያማርሩ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊገጥሙት  ይችላሉ።  

የዴሞክራሲ ስርዓትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ተመሳሳይነት የላቸውም ባይባልም በመሰረታዊ ጉዳዮች ግን እጅግ የተለያዩ ናችው። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ዕኩልነትን አረጋግገጧል። ይሁንና አንዳንድ አካላት በግለሰብ ደረጃ የሚፈጸሙ  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደአጠቃላይ  የዴሞክራሲ ስርዓቱ መገለጫ አድርገው  ማቅረባቸው  አግባብነት የጎደለው ፍረጃ ይመስለኛል። እንዲህ ያለ ፈጣን ልማት እየተመዘገበ ባለበት አገር ፍላጎቶች ስለሚበዙ  የሁሉን ፍላጎት ማሟላት ከባድ  ነው። በአገራችን ፈጣን ልማት ሳቢያ እየተመለከትናቸው ያሉ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየሰማንና እየተመለከትን ነው።

 

በዘንድሮው ዓመት ብቻ በአገራችን ከሙያ ማሰልጠኛዎች  እስከ ዩኒቨርሲቲ  ተመራቂዎች ድረስ  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች  ይመረቃሉ።  በየዓመቱ ይህን  ያህል ቁጥር ያለው አዳዲስ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችን እየፈጥርን ባለንበት ሁኔታ  ሩጫችን ምን ያህል መፍጠን እንዳለበት  መገመት የሚከብድ አይመስለኝም። የፍላጎት ናዳው እጅግ ፈጣን ነው። ይህ ሊመለስ የሚችለው በመንግስትና ህዝብ በመቀራረብ መስራት ብቻ ነው። ካልሆነ ግን እሳቱ ሁሉንም በየደረጃው የሚለበልበው ይሆናል።  

 

ትናንት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሰራለት ይጠይቅ የነበረ የገጠር የህብረተሰብ ክፍል፣ ዛሬ የሁለተኛ ደረጃ የጨረሱ ልጆቻችን ለምን ከእኛ ርቀው ይሄዳሉ በአቅራቢያችን  የሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ወይም ኮሌጅ ይከፈት ባይ ሆነዋል፤ ትላንት የበጋ መንገድ ይሰራልኝ ይል የነበረው ህዝብ፤ ዛሬ የአስፋልት መንገድ አልተሰራልኝም ብሎ የሚጠይቅ ሆኗል። ጥያቄው በርክቷል፣ ሩጫው እየከረረ መጥቷል። ይህ ልማት የፈጠረው ጥያቄ ነው። የፍላጎት ናዳው በርክቷል።

 

ገዥው ፓርቲ እና መንግስት የሚመዘኑት የህዝቡን ፍላጎቶች  በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍና ፈጣን ልማትን በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት በማረጋገጥ ላይ ሆኗል። የህብረተሰቡ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች እየተፈቱ ባለበት ፍጥነትና ስፋት የመልካም አስተዳደር  ጥያቄዎች እየተፈቱ እንዳልሆነ  እየተመለከትን ነው። የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ወሳኝ  ከሆኑ የህብረተሰቡ የዕለት ከለት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው መንግስትን ለማማረር በጣም ቅርብ ናቸው። በተሃድሶ ወቅት መመልከት እንደቻልነው  የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተብለው ከተለዩት መካከል በርካታዎቹ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱ በራሱ ይዟቸው የመጣው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ መመልከት ተችሏል። የልማት እንቅስቃሴ አዳዲስ ፍላጎቶችን እየፈጠረ መጥቷል።

 

ትናንት የአርሶ አደር አባቱን ህይወት ተቀብሎ ለማደር ዘግጁ የነበረው የአርሶ አደሩ ልጅ፤ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሲወጣ ከአባቱ የተሻለ ህይወት የሚፈልግ ሰው ይሆናል። በዘንድሮው ዓመት ብቻ ከ150 ሺህ በላይ ወጣት ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ በሆነ መዕረግ ተመርቋል። ይህ ሃይል የተሻለ ኑሮ ፈላጊ ነው። ይህን ሃይል በአግባብ መጠቀም የሚቻል ከሆነ አገራችን የጀመረችውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚቻል በእርግጠኝኘነት መናገር ይቻላል። ይህ ካልሆነ  ተቃራኒ ገጽታም እንደሚፈጥር መታሰብ ይኖርበታል።     

የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት እንደሆነ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም። የአገራችን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ህብረተሰቡ የመንግስትን አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ  ማግኘት አለመቻሉ አንዱ ነው። የልማት ፈለጋ በራሱ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ተመልክተናል።   ይሁንና  የአገራችን የዴሞክራሲ  ስርዓት አሁንም በሂደት ላይ ቢሆንም በርካታ ስኬቶችን በተጨባጭ አስገኝቷል። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዲኮሩ ሆነዋል፣ ድምጽ በሰጧቸው ይወክሉናል በሚሉት አካል እየተዳደሩ ናቸው፣ በቋንቋቸው መማርና መዳኘት ችለዋል፣ በፌዴራል መንግስቱ ተገቢውን ውክልና አገኝተው በጋራ አገራዊ ጉዳያቸውም  ከሌሎች ጋር  እኩል  ይመክራሉ እንዲሁም አካባቢያቸውን በሚፈልጉት መልኩ  ማልማትና መለወጥም ችለዋል።

በአዲሲቷ  ኢትዮጵያ የትኛውም ብሄር የበላይ እንዲሁም ሌላው የበታች  እንዳይሆን ተደርጓል።  የኢፌዴሪ  ህገመንግስት የበላይም ይሁን የበታች ብሄር ወይም ብሄረሰብ  እንዳይኖር የመጨረሻ  እልባት ሰጥቶታል። አገራችን በየዘርፉ ተጫባጭ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ ነች። ይሁንና እንደእኔ አገራችን ያስመዘገበችውን ኢኮኖሚ ዕድገት ያህል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት አድርጋለች የሚል እምነት የለኝም።    

 

የአሁኑን የአገራችን ሁኔታ  ከሁለት አስርት ዓመታት ጋር  በንጽጽር ማቅረቡ   የከፋ ነገር ባይኖረውም ለመለወጥ የምናደርገውን  ጥረት  እንዳያዘገይብን ግን ስጋት አለኝ።  ህብረተሰቡ የድሮውንና የአሁኑን ሁኔታ በነጻነቱ፣ በገቢው በአጠቃላይ በአኗኗሩ  አሳምሮ ያውቀዋል። መንገር የሚያስፈልገው አይመስለኘም። የአሁኑንና የደርግ ስርዓትን ማነጻጸር ማለት ጭለማንና ብረሃንን እንደማወዳደር አይነት ይመስለኛል። ቢያንስ ዛሬ ላይ ማንም በግዴታ ወደጦርንት እየታነቀ አይላክም። ማንም ለህይወቱ  አይሰጋም። ይሁንና ህብረተሰቡ አሁን ላይ  ችግር  የሆነበት  በኑሮው ውጣ ውረድ የገጥሙት የአገልግሎት መጓተት፣ በአገልግሎት ሰጪው በኩል የሚታዩ የማይገባን ጥቅም የመፈለግ  አካሄዶች ግን እንዲወገዱለት ይፈልጋል።

 

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የዓለም ህብረተሰብ ኢትዮጵያ የሚመለከታት በተደጋገጋሚ በድርቅ የምትጠቃና በጦርንት የደቀቀች አገር አድርጎ ነበር።  በእርግጥም  ስር የሰደደ ድህነት፣ የእርስ በርስ ጦርነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የአገሪቱ መገለጫ ተደርገው ቢወሰዱ ሃሰት ናቸው ብሎ መሞገት አይቻልም። በእኩልነት እጦት ሳቢያ  ለረጅም ዓመታት የተካሄደውን የእርስ በርስ ግጭት  የአገሪቱን ገጽታ ክፉኛ  ጎድቶታል።  ይሁንና ይህን አስከፊ ገጽታ ለመቀየር  የኢትዮጵያ   ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ባደረጉት መራራ ትግል ዛሬ ሁኔታዎች ተቀይረዋል።  የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ፈጠንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ናቸው።  

በእኛ አገር ግን አንድ የቀበሌ ወይም የወረዳ አስተዳዳሪ የሚፈጽመው በደል  በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በተለይ በዳያስፖራ ፖለቲከኞች  እንደስርዓቱ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድበት አሰራር ተገቢ አይመስለኝም። ለዴሞክራሲ ስርዓቱም መጎልበት ለአገራችንም ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚበጅ አይደለም። እውነታንና ስሜትን ለየቅሉ እንመልከት። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓቱ ጅምርና ያልጎለበተ ይሁን እንጂ ለአገራችን በርካታ ለውጦችን ማስገኘት ችሏል። ይህን የአገራችንን መለወጥ ያመላከተንን ስርዓት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መወረፉ የሚያመጣውን መዘዝ ካለማሰብ ይመስለኛል። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንሰሳ ማሰብ ተገቢ አይመስለኝም።    

 

የልማት ፍላጎት ጥያቄዎችን  ተንተርሰው መርዘኛ ፖለቲካ የሚረጩ  የዳያስፖራ ፖለቲካ አቀንቃኞችን መታገል የእያንዳንዳችን ተግባር መሆን የለበትም። የወንጭፍ ፖለቲካ ለአገራችን አይበጃትም። የወንጭፍ  ፖለቲካ  መበታተን፣ መለያየትንና ውድመትን እንጂ አንድነትንና ልማትን ይዞ አይመጣም።  መንግስትም ሆነ ህዝቡ እነዚህን አካሄዶች  በመረዳት ነቅቶ መታገል ይገባል። በመልካም አስተዳደር ረገድ ለሚታዩት ጉድለቶች፤ የመንግስት የማስፈጸም አቅም ደካማ መሆን አሌ የሚባል ባይሆንም ለመልካም አስተዳደር መጎልበት ህብረተሰቡስ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ጉቦ ሰጪ ከሌለ ጉቦ ተቀባይ አይኖርም እንደሚባለው ህብረተሰቡ ለጥፋት በር የሚከፍቱ አካሄዶችን ማስወገድ ይኖርበታል። ሁሉም መብቱንና ግዴታውን ካወቀው መጠየቅ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy