Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያለ ግብር ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም!

0 269

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ያለ ግብር ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም!

ዳዊት ምትኩ

የቀን ገቢ ግብር አወሳሰንን ተመርኩዞ ሰሞኑን እሰጥ አገባዎች ተበራክተዋል። በእኔ እምነት እሰጥ አገባው የግብር አወሳሰኑ የግምት ሁኔታና ለነጋዴው ህብረተሰብ ተገቢው የግንዛቤ ማስጨበጫ አለመሰጠቱ ነው። ችግሩም የንግዱ ማህበረሰብ ስለ ግብር ካለው የተዛባ ግምትም የሚመነጭ ይመስለኛል።  

አገራችን ውስጥ የሚከናወኑት ማናቸውም የልማት ስራዎች በወሳኝነት ከህዝቡ በሚሰበስበው ግብር መሆኑ ግልፅ ነው። መንግስት ለህዝቡ የሚገነባቸው የልማት አውታሮች፣ መንገዶች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም የትምህርትና የጤና አቅርቦቶች ብሎም ማናቸውም ልማታዊ ተግባሮችና ድጋፎች ከህዝቡ በሚያገኘው ግብር የሚፈፅማቸው ናቸው። እናም ዜጎች ግብር ካልከፈሉ ልማትንና እድገትን እውን ማድረግ አይቻልም።

የአንድ አገር መንግስት የሚተማመነው በአገሩ ህዝብ ሃብት እንጂ ከውጭ በሚያገኘው ብድርና እርዳታ አይደለም። ምንም እንኳን ብድርና እርዳታ እንደ እኛ ላለው በማደግ ላይ የሚገኝ አገር ጠቀሜታ ቢኖራቸውም ዋነኛው የልማታችን ምሰሶ ሊሆን የሚገባው ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበው ግብር ነው።

መንግስት በአገር ውስጥ ግብር መንቀሳቀስ ካልቻለ የውጭ ሃይሎች ጥገኛ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ በራሱ የማይተማመን፣ ለህዝቡ ሳይሆን ለውጭ ሃይሎች ጥቅም የሚሰራ ያደርገዋል። በአገሩ ውስጥም ለህዝብ የሚጠቅም ይህ ነው የሚባል ልማት ሊያመጣ አይችልም። እንዲያውም ህዝቡ የውጭ ሃይሎች በገዛ አገሩ እንዳሻቸው ሲሆኑና እርሱም ‘የበይ ተመልካች’ ይሆናል።

ይህ ደግሞ በራስ አገር ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሱ የውጭ ሃይሎች የፈለጉትን ሲያደርጉ ህዝቡ ከተጠቃሚነት ጎዳና ወጥቶ የእነርሱ ፍላጎት አስፈፃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በመሆኑም ህዝቡ በአገሩ ውስጥ በሚከናወን እድገት ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን በቅድሚያ ጠንካራ መንግስት ሊኖረው የግድ ይላል። ጠንካራና ለሀዝቡ የሚሰራ መንግስት እንዲኖር ደግሞ ዜጎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ግብራቸውን መክፈል ይኖርባቸዋል። ጉዳዩ የራስ ተጠቃሚነት በመሆኑም ግብርን በአገራዊ ፍቅር መክፈል የማንኛውም ዜጋ በውዴታ ላይ የተመሰረተ ግዴታ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት አቅዳለች። አገራችን በምታራምደው የፊሲካል ፖሊሲ መሰረት በ2012 ዓ.ም ፍፃሜውን የሚያገኘው የሁለተኛው የዕድገት እቅድ የወጪ በጀትን በሂደት በዋናነት በሀገር ውስጥ ገቢ በመሸፈንና የበጀት ጉድለት ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለማስፈን ያለመ ነው።

በመሆኑም ባለፉት ዓመታት የታክስ ፖሊሲዎቹን በተሻለ ሁኔታ በማስተዳደር የመንግስት ገቢ ከፍተኛ ዕድገት እንዲያሳይ ተደርጓል። ሆኖም የታክስ ገቢው እያደገ ከመጣው የመንግስት የወጪ ፍላጎት አንፃር ብዙ የሚቀረው ሆኖ ተገኝቷል። እንዲሁም የታክስ ገቢው ዕድገት እየሳየ ቢመጣም፣ ምጣኔ ሃብቱ ሊያመነጭ ከሚችለው ጋር ሲነፃፃር የሚጠበቀውን ያህል መሻሻል አሳይቷል ተብሎ የሚገመት አይደለም።

ስለሆነም ባለፉት ዓመታት የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ብዙም ለውጥ ማሳየት አልቻለም። እናም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 17 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ውስጥ በምንም ዓይነት የተክስ ስሌት ውስጥ ያልነበሩ ነጋዴዎችን ወደ ታክስ ስርዓቱ ማስገባት ይገባል።

የታክስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓቱን ይበልጥ ማጠናከርና አሟጦ ጥቅም ላይ ማዋል፣ የታክስ ከፋዮችና የህብረተሰቡ በአጠቃላይ የታክስ ትምህርትና ግንኙነትን ማሳደግ፣ የታክስ ህግን ማስከበር እና የታክስና ገቢዎች መዋቅር ተቋማዊ አቅም ማሳደግ አሁንም ተገቢ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ነው።

በያዝነው የዕቅድ ዘመን የታክስ ስርዓቱን በጥብቅ ዲስፕሊን ተፈፃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በተጨማሪም የመንግስት ፋይናንስ አጠቃቀሙ ውጤታማነትን ለማሳደግ፣ የተሟላ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን፣ ብክነትን ለማስወገድና በጀቱን በቁጠባ ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ስራው እየተከናወነ ነው። ይህም ከህዝቡ በታክስ መልክ የሚሰበሰበው ግብር እንዳይባክንና ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል በጥብቅ የሚሰራበት ይሆናል።

እርግጥ የህዝቡ ግብር በጥሩ ሁኔታ ለታለመለት ግብ ከዋለ የመንግሥት ጠቅላላ ገቢ በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 199 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጨረሻ ዓመት (ማለትም በ2012 ዓ.ም) ወደ 627 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ከፍ ይላል።

ታዲያ እዚህ ላይ በ2012 ከሚጠበቀው ገቢ ውስጥ 605 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሀገር ውስጥ ገቢ (ታክስና ታክስ ያልሆኑ ማለቴ ነው) የሚሰበሰብ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ይህም አገራችን በዕቅድ ዘመኑ አሳካዋለሁ ብላ ላቀደቻቸው የልማት ስራዎች የሚውል ይሆናል።

ከዚህ ውስጥ መንግስት ዕድገትን በማፋጠን ድህነትን ለማስወገድ የሚረዱ የድህነት ተኮር ዘርፎች አወጣዋለሁ ብሎ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ ለያዛቸው የልማት ፕሮጀክቶች 469 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ያደርገዋል። ይህም ከጠቅላላ የመንግስት ወጪ 64 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ እቅዱ ያመላክታል።

እንግዲህ እነዚህ እውነታዎች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር በመንግስት የሚከናወኑት ማናቸውም ስራዎች በዋነኛነት ህዝቡ በሚከፍለው ግብር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ነው። እርግጥ ዜጎች ግብር ካልከፈሉ ምንም ዓይነት የልማት ስራዎችን ማከናወን አይቻልም። ከላይ እንደጠቀስኩት ግብር ካልተከፈለ መንግስት በእርዳታና ብድር ብቻ ለመኖር ይገደዳል።

ይህ ደግሞ መላው ስራው ብድርና እርዳታ ለሰጡት አካላት አስፈፃሚ እንዲሆን ያደርገዋል። ዜጎችም በአገራቸው መጠቀም አይችሉም። እናም ግብር መክፈል መልሶ ራስን መጥቀም መሆኑን ሁሉም ዜጋ ሊያውቀው ይገባል።

የመንግስት አገልግሎቶችን በጥራት ለማግኘትም ግብር ወሳኝ ሚና አለው። መንግስት ከዜጎቹ ተገቢውን ግብር ካገኘ ለህዝቡ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዚያው ልክ ጥራታቸው፣ ፍትሐዊነታቸው፣ ዴሞክራሲያዊነታቸውና ሁሉን አቀፍነታቸው ከፍ ይላል።

በመሆኑም ሰሞኑን በቀን ገቢ ግብር ትመና ላይ የተነሱት አንዳንድ አላስፈላጊ ሃሳቦችና ተግባሮች ይህን የግብር መክፈልን ጠቀሜታ ያገናዘቡ አይደሉም። እርግጥ በቀን ገቢ ግብር አወሳሰኑ ላይ ችግር ሊኖር ይችላል። ሆኖም ችግሩን ሌላ ችግር በመፍጠር መፍታት አይቻልም። አሁንም ቅሬታን ለማቅረብ የሚቻልበት አሰራር በመኖሩ ይህንኑ ከመንግስት ጋር በመመካከር ገቢራዊ ማድረግ ይገባል። ግብር መክፈል የዜግነት ኩራት ከመሆኑም በላይ ያለ ግብር ምንም ዓይነት ልማትን ማረጋገጥ አይቻልምና።

 

    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy