Artcles

ድርቅ እና ኪራይ ሰብሳቢነት

By Admin

July 11, 2017

 

ድርቅ እና ኪራይ ሰብሳቢነት

ኢዛና ዘመንፈስ

ኪራይ ሰብሳቢነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ቅኝት ጎልቶ በሚስተዋልበት ሀገር ውስጥ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለውም ደግሞ መንግስት ስለፈለገ አይደለም፡፡ ይልቅስ የኪራይ ሰብሳነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን የህልውናቸው መሰረት አድርገው የሚቆጥሩት ጥገኛ ኃይሎች፤ የየራሳቸውን ጠባብ ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ የሚፈጥሩት አሉታዊ ተጽዕኖ በመንግስት አሰራር ላይ የበላይነትን ስለሚይዝ እንጂ፡፡ እናም ያልዘሩትን ማጨድ፤ ያልደከሙበትን ምርት ማፈስ የለመዱት ወገኖች እዚሁ የመንግስት እቅፍ ውስጥ ተወሽቀው ከድሃው ህዝብ የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ላይ እየቀሙ በመውሰድ ያላግባብ ሲከብሩ እያየን የሚታደገን የሕግ አካል እስከማጣት ብንደርስ እምብዛም ላያስገርም ይችላል፡፡

   የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ “መንግስት አንድ እጁን በኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ስለተያዘ በቀረችው አንድ እጁ ብቻ ነው የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስና የልማት ፖለሲዎቹን ለማሳካት ያለመ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘው” ሲሉ እንቅጩን ከነገሩን ዓመታት ተቆጥረው የለ? ስለዚህም፤ እርሳቸውን ያህል በቀላሉ ተስፋ እንደማይቆርጡ የቅርብም የሩቅም ታዛቢ የመሰከረላቸው ታጋይ የሀገር መሪ፤ የአደጋውን አሳሳቢ ገጽታ በዚያን ዓይነት ስፋትና ጥልቀት ለምልዓተ ህዝቡ ሲገልጹ ከተደመጡበት ንግግር የተሻለ ማስጠንቀቂያ ሊኖር እንደማችል ነው ለኔ የሚገባኝ፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያን ጊዜው የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ የጸረ ሙስና ትግል ጥሪ በኋላ እንኳን እንደ ህብረተሰብ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን አደጋ የተገነዘብን አንመስልም፡፡

ከዚህ የተነሳም ነው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተግባርና አስተሳሰብ የሚገለጽባቸው ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች በጎላ መልኩ የሚስተዋሉበት አግባብ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ እንደመጣ የሚያመለክት ችግር ህዝቡን ቁም ስቅሉን እያሳይ ይገኛል፡፡ ይልቁንም ደግሞ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የሚከሰት የድርቅ አደጋ ተደጋግሞ በሚስተዋልባቸው የሀገራችን ክፍሎች የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ወገን የዕለት ጉርስ እያረረበት፤ እርሱን በረሃብ ከማለቅ ለመታደግ ሲባል በዕርዳታ መልክ የሚቀርበውን የምግብ እህል እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የህይወት አድን ፍጆታዎችን ሳይቀር ተረጅው ህዝብ ዘንድ ከመድረሳቸው በፊት መንገድ ላይ ተመሳጥረው እየሸጡ የየግል ኪሳቸውን በማደለብ የሚታወቁ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ጥቂት እንዳልሆኑ ሲታሰብ ጉዳዩን እጅግ በጣም አንገብጋቢ መፍትሔ የሚሻ ያደርገዋል፡፡

ስለሆነም፤ አሁን ላይ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ምክንያት ለምግብ እህል አጥረት ተዳርገው የእለት ደራሽ ዕርዳታ ለመጠበቅ የተገደዱ ሰባት ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን ህዝቦች እንዳይራቡ ለማድረግ ሲባል፤ እቺ ምስኪን ሀገር አቅሟ የፈቀደውን ያህል እየገዛች የምታቀርበውን እህልና ሌላም ተያያዥ የምግብ ፍጆታ ተረጅው ህዝብ ወደሚገኝበት አካባቢ ከመድረሱ በፊት በመሀል ተቀራምተው ሲያስቀሩት የሚስተዋሉ ምግባረ ቢስ የሥራ ኃላፊዎች መኖራቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች እንዳሉ የሚያከራክር አይደለም፡፡

ከዚህ ዓይነቱ አስነዋሪ የሙስና ተግባር በሚገኝ ገንዘብ አማካኝነት ያልተገባ ሀብት አጋብሰው በአቋራጭ የሚበለጽጉ የዕርዳታ እህል ስርጭት አስፈፃሚዎችና እንዲሁም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ተመሳጥረተው ለድርቅ አደጋ ተጠቂዎቹ ወገኖች መድረስ የሚገባውን የህይወት አድን እህል እየመዘበሩ በመቸብቸብ የሚታወቁት ሕገ ወጥ ነጋዴዎች፤ ድርቅን እንደዋነኛ የገቢ ምንጭ ማስገኛ ክስተት ሲቆጥሩት ይስተዋላሉ ተብሎ እንደሚታመንም ነው የተረዳሁት፡፡ ከዚህ አኳያ ለማነሳው አስተያየት የተሻለ ምሳሌ ሊሆን ይችላል የምለውም ደግሞ፤ የድረቅ አደጋ ለሚያስከትለው የምግብ እህል እጥረት ተጋላጭ ተደርገው በሚወስዱት አንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የሚኖረው አርብቶና አርሶ አደር ህብረተሰብ፤ የእርዳታ ስንዴ እየቀሸቡ በመሸጥ ብቻ ህይወታቸውን ስለሚለውጡ ኪራይ ሰብሳቢዎች የሚያውቀውን ጥሬ ሀቅ አስመልክቶ በየአጋጣሚው ሲናገር መስማት የተለመደ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡

እንደ አብነትም፤ የ2007 ዓ.ም ድርቅ ባስከተለው የምግብ እህል እጥረት ምክንያት የዕለት ጉርስ ተቸግረው ለነበሩት አንዳንድ የምስራቅ አማራና የደቡብ ትግራይ ወረዳዎች ነዋሪ ህዝብ የሚላከውን ስንዴና ዘይት ሸጠው ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ የአስተዳደር አካላት በህዝቡ ጥቆማ ተደርሶባቸው መያዛቸውን ያኔ መገናኛ ብዙኃን ከዘገቡበት ዜና መረዳቴን ማስታወስ ይቻላል፡፡  እንዲሁም ደግሞ አሁን ላይ በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ ጎላ ባለመልኩ የሚስተዋል የምግብ እህል እጥረትን ባስከተለባቸው፤ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ለሚኖረው ተረጂ ህዝብ መድረስ የነበረበትን የምግብ አቅርቦት በማጓደል   አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉት ምግባረ ቢሶቹ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ በግልጽ አነጋገር፤ አልፎ አልፎ ለተረጂዎቹ ወገኖች የሚከፋፈለውን የምግብ ፍጆታ አቅርቦት ከታቀደለት ጊዜ አስቀድሞ የማለቅ ችግር ሲያጋጥመው የሚስተዋልበት ምክንያት ቀሽበው እየሸጡ የግል ኑሯቸውን የሚያደላድሉት ሙሰኞች በመበራከታቸው እንጂ የአቅርቦት ስርጭቱ ላይ የጎላ ችግር ኖሮ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ስለዚህ፤ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተግባርና አስተሳሰብ እስከ ምን ድረስ በወረደ የሞራል ዝቅጠት ሊገለጽ እንደሚችል ለመረዳት የተሻለ ማሳያ ይሆናል የምለውም፤ በተለይ የድርቅ አደጋ ለሚያስከትለው ተረጅነት የሚጋለጡ ወገኖችን ከረሃብ ለመታደግ ያለመ ጥረት ሲደረግ ከሚስተዋልበት የምግብ ዕርዳታ ክፍፍል ጋር በተያያዘ መልኩ የሚፈፀምበትን አግባብ ስንገነዘብ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለምሳሌ ያህልም በቅርቡ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ምክንያት ለተረጂነት የተጋለጡ ወገኖችን ከረሃብ ለመታደግ ሲባል የሚደረገውን ጥረት የሚያስተጓጉል የዕርዳታ አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠመ አድርገው መዘገባቸውን ተከትሎ በተደመጠ የነዋሪው ህዝብ አስተያየት፤ ችግሩ ሊከሰት የቻለው አንዳንድ የምግብ እደላ ስርጭቱን የማስፈጸም ኃላፊነት ወስደው የሚንቀሳቀሱት የበታች አስተዳደር አካላት ድርቁን በአቋራጭ ለመበልጸግ ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ የሚስተዋሉበት አግባብ በመኖሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ በተረፈ ለዛሬው እዚህ ላይ ይብቃኝ፡፡