Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድርድሩ ዓላማውን እንዳይስት…

0 352

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድርድሩ ዓላማውን እንዳይስት…

                                                        ዘአማን በላይ

ኢህአዴግና 16 ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ድርድር እያካሄዱ ነው። በሚወያዩባቸው አጀንዳዎችም ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል። ታዲያ ፓርቲዎቹ በቀጣይ የሚያደርጓቸው ድርድሮች የተነሱበትን ዓላማ መሳት ያለባቸው አይመስለኝም።

እንደሚታወቀው ለድርድሩ አነሳሽ የሆነው ምክንያት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዮችንና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰባ ሲከፍቱ ግልፅ አድርገውታል። ይኸውም “…የተጀመረው ፈጣን ልማትና የሀገራችን አንድነት ቀጣይነት በብዝሃነታችን ላይ ከተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ግንባታ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲያችንን ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል። በዚህ ረገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ተቀራርቦ ለመስራት የተጀመሩት አሰራሮች የነበሩባቸው እጥረቶች እየተሻሻሉ እንዲጎለብቱ ይደረጋል።  መንግስት በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች የምርጫ ጊዜ ሳይጠበቅ የሚመካከርበት አሰራር እንዲዘረጋና በሂደት እየጎለበተ እንዲሄድ የተለምናቸው እቅዶችን የመተግበሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲከናወን ይደረጋል።…” የሚል ነው።

ይህ የፕሬዚዳንቱ አባባል ገዥው ፓርቲና መንግስት እዚህ ሀገር ውስጥ የዴሞክራሲውን ምህዳር ይበልጥ በማስፋት የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ አሁን ካለው በላይ እንዲጎለብት ያላቸውን ፍላጎት የሚያረጋግጥ ነው። በእኔ እምነት ይህ የፕሬዚዳንቱ አገላለፅ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ላለው የፓርቲዎቹ ድርድር ዓላማ ነው። እናም ገዥው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚዎች ይህ ሀገራዊ ዓላማ እንዳይሰናከል ጥረት ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል።

ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር መድረክ የሀገራችንን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያጎለብትና የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የሚያሰፋ ነው። ድርድሩ ገና በአጀንዳ ስምምነት ደረጃ ያለ ቢሆንም፤ እዚህ ሀገር ውስጥ በመገንባት ላይ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲሁም የሁሉንም ህዝቦች ውክልና የሚያጠናክር ነው። ስለሆነም ከጅምሩ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን የማጥበብና በሚያግባቡ ጉዳዩች ላይ ለሀገር ጥቅም ሲባል አንድ ላይ መስራት የግድ ይላል። ምክንያቱም ማናቸውም ዴሞክራሲያዊ ድርድር በመቻቻል መርህ መከናወን ስለሚኖርበት ነው።

የዚህ ሀገር ፖለቲካዊ አጀንዳ ህዝቡን የሚወክሉትና በሀገራችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ነው። ሌላ የማንም አይደለም። ስለሆነም በአንዳንድ ፅንፈኛ ወገኖችና የውጭ ተላላኪ ሃይሎች አማካኝነት አንዳንዴ ‘ህገ መንግስቱ ይቀየር’ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‘የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ’…ወዘተ. የሚል አተካራ እንዲነሱ ይሻሉ። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት አጀንዳዎች ከድርድሩ ፍላጎት ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅ የሌላቸው በመሆናቸው ነው። አስተሳሰቦቹ እንደ አስተሳሰብ የሚከበሩ ቢሆኑም፤ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን መጎልበት ረብ ያለው ፋይዳ የላቸውም።

በአሁኑ ወቅት በመደራደር ላይ የሚገኙት 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ዓላማዎቻቸው ዴሞክራሲን በማስፋት ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መጎልበት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው።   በመሆኑም በቀጣይ ድርድሮች ወቅት በድርድሩ ወቅት ሁሉም ወገኖች ማሰብ ያለባቸው የሀገራችን ዴሞክራሲ እንዴት መስፋት እንዳለበት ነው።

ታዲያ እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተገነባ ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጮርቃ መሆኑን መዘንጋት የሚገባ አይመስለኝም። የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ገና 26 ዓመታትን ብቻ ነው የተሻረገው። በዚህም ሳቢያ ዴሞክራሲን በተመለከተ የሚነሱ ፅንሰ ሃሳቦች በሁሉም ወኖች በኩል ምሉዕ የሆነ አረዳድ እንዳይኖር መሰናክል መፍጠራቸው የሚቀር አይመስለኝም።

ይህም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሁም መቻቻልን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ እሴቶችን በተገቢውና በፈጠነ ሁኔታ ገቢራዊ ለማድረግ ሳንካ ይሆናል። ፅንሰ ሃሳቦቹ አዲስ በመሆናቸውም በአስተማማኝ ሁኔታ ይተገበሩ ዘንድ የጊዜ ርዝማኔን መጠየቃቸው ርግጥ ነው። ያም ሆኖ ግን ባለው ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲን በሂደት ማሳለጥ ያስፈልጋል።

ከዚህ በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያ ያሉና ባለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች በህዝቦች መካከል ፈጥረውት ያለፉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በቀላሉ የሚሽሩ አይደሉም። ፀረ ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በዴሞክራሲያዊነት ለመቀየርም አስተሳሰብንና ተግባርን ማዋሃድ ይጠይቃል። ታዲያ እዚህ ላይ በህዝቦች ውስጥ ለዘመናት ሲፈጠሩ የነበሩትን የተዛቡ ግንኙነቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ ማስተካከል እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል።

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ዴሞክራሲ የማስረፅ ትግል ጊዜንና የአስተሳሰብ ልህቀትን ይጠይቃል። ይህ ሁኔታም ምናምባትም ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያሰናክል ይችላል። እናም ዴሞክራሲው እንዲሰፋ እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች መፍታት የግድ ይላል።

ይህን ዕውን ለማድረግም የህዝቡ ወኪሎች የሆኑት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል። በመሆኑም ፓርቲዎቹ በክርክሩና በድርድሩ ሂደት ውስጥ ‘እነዚህን የዴሞክራሲ ተግዳሮቶች ለመፍታት ከእኔ ምን ይጠበቃል?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል። ይህን ሲያደርጉም ለሀገራቸው ዴሞክራሲ መስፋት የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ ይመስለኛል።

ፓርቲዎቹ ሌላው ሊያነሱት የሚገባው ጉዳይ ክርክሩና ድርድሩ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ሊኖረው የሚገባውን ፋይዳ ነው። እንደሚታወቀው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት ተፈጥሮ ነበር። የሁከቱ አነሳሽ ምክንያት ምንም ይሁን ምን፤ ፓርቲዎች እንዲያ ያለው ሁከት ዳግም እንዳይፈጠር መስራት ይኖርባቸዋል።

ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ድርድር መቋጫው ጥርጣሬንና ግጭትን በማስወገድ ሰላምን ማምጣት ነው። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ። ያለ ሰላም ልማትን ማሰብ አይቻልም። ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱንም ስር እንዲሰድ ማሰብ ትርጉም አይኖረውም። ዴሞክራሲ ስር ባልሰደደበት ሀገር ውስጥ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልባቸው ሃሳባቸውን ለህዝባቸው ሊያስተዋውቁና በህዝቡ ይሁንታ በሚካሄድ ምርጫ ሀገር ሊመሩ አይችሉም።

በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከድርድሩ ዴሞክራሲንና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የራሳቸውን ህልውና ጭምር የሚያረጋግጡ መሆናቸውን መገንዘብ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። አሊያ ግን ክርክርንና ድርድርን ላለመግባባትና ለህገ ወጥነት የሚያልም የፖለቲካ ፓርቲ ካለ፤ ርግጥም ያኔ ህዝቡ የራሱን መፍትሔ መውሰዱ የሚቀር አይመስለኝም። እናም ዋናው ቁም ነገር በገዥው ፓርቲና በመንግስት በኩል የተቀመጡት የድርድሩ ዓላማዎች እንዳይይናቀፉ ማድረግ ይመስለኛል።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy