Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉዞ ወደ ኢንዱሰትሪ አብዮት!

0 381

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉዞ ወደ ኢንዱሰትሪ አብዮት!

ሰለሞን ሽፈራው

ዛሬ “ለጋሽ “ በመባል የሚጠሩትን ባለጸጋ ምዕራባውያን ሀገራት ጨምሮ መላው የዘመናችን ዓለም አንድ ወቅት ላይ ልክ እንደኛው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኋላ ቀር የግብርና ስራ ዳዴ የሚል ኢኮኖሚ እንደነበረው ይታመናል፡፡ ይልቁንም ደግሞ እንደ ቻይና፤ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ዓይነቶቹ የምስራቁ ክፍለ ዓለም ሀገራት፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከኛ እንብዛም በማይሻል አጠቃላይ እውነታ ውስጥ ይዳክሩ እንደነበር ነው ታሪክ የሚነገረን፡፡ እናም ሌላው ዓለም ካረጀ ካፈጀው የግብርና ኢኮኖሚ ስልተ ምርት ተላቅቆ አሁን ላይ የደረሰበትን ስልጣኔ ለመቀዳጀት ይችል ዘንድ የየራሱን ሀገር የኢንዱስትሪ አብዮት ስለማካሄዱ ጭምር የታሪክ መዛግብቶቹ አክለው ያስረዳሉ፡፡

ይህን ስንልም ደግሞ፤ ማንኛውም የዘመናችን ዓለም አካል የሆነ ልዑዋላዊ ሀገር ከድህነትና ኋላ ቀርነት ወጥቶ የህዝቦቹን ወይም የዜጎቹን ቁሳዊ ፍላጎት በሚያወላዳ መልኩ ለማሟላት ወደሚያስችለው ምጣኔ ሀብታዊ የዕድገት ደረጃ ላይ መድረስ ካለበት፤ የግድ የኢንዱስትሪ አብዮት አካሂዶ ነባሩን የኢኮኖሚያዊ መዋቅር በአዲስ ዓይነት ስልተ ምርት መለወጥ /መተካት/ ይጠበቅበታል ማለታችን ይሆናል፡፡ በእርግጥ አንድ አገር የራሱን የኢንዱስትሪ አብዮት ለማካሄድ ይችል ዘንድ፤ መሟላት አለባቸው ተብሎ የሚታመንባቸውን ቁልፍ ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ መገኘት እንደሚጠበቅበት የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡

እናም ከዚህ መሰረተ ሃሳብ አኳያ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለውን የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አጠቃላይ እውነታ ስንመለከት ሀገራችን ወደማይቀረው የኢንዱስትሪ አብዮት ጉዞ ጀምራለች ብለን እንድናምን የሚያደርጉን ቅድመ ሁኔታዎች ስለመሟላታቸው ደፍሮ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እንዴት ማለት? ለምትሉኝ የመጣጥፌ አንባቢያን አስተያየቴን በምክንያት አስደግፌ ለማብራራት እሞክራለሁና እነሆ አብረን እንመልከት፡፡

ስለዚህ አሁን በቀጥታ የማልፈውም ወደ ዋናው የጽሑፌ ማጠንጠኛ ነጥብ ነው፡፡ ስለሆነም፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከልጅነት እስከ እውቀት በዘለቀ ህይወቱ ደጋግሞ ሲነገረው የሚሰማውን ጉዳይ አንስቼ ሃሳቤን ፈር ማስያዝ እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ እንግዲያውስ ከሀገራችን ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር ውስጥ 85 ከመቶ ያህሉ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የግብርና ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚኖር ስለመሆኑ ከትናንት እስከ ዛሬ በየአጋጣሚው ሲነገር የምንሰማውን መሰረተ ሃሳብ አንስተን ብንመረምረው ጠቃሚ ይመስለኛልና እርሱን ላስቀድም፡፡

መቸስ እንደ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የህዝቧ ቁጥር 85 በመቶው ለዘመናት የዘለቀ የገጠር ህይወትን እንደ ዋነኛ የኑሮ ዘይቤው ወስዶ እርሱኑ የሙጥኝ እንዳለ በቆየባት ሀገር ውስጥ ድህነትና ኋላ ቀርነት ምን ያህል ስር ሊሰድ እንደሚችል መገመት አንብዛም አይከብድም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱ ዘመናትን ባስቆጠረ የአኗኗር ዘይቤ ላይ የተመሰረተ የአርሶና አርብቶ አደር ህይወትን ሲገፋ የቆየ አብዝሃ ህብረተሰብ አለ ማለት፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አጠቃላይ ይዞታ፤ እንኳንስ ለኢንዱስትሪ አብዮት መቀጣጠል የሚያመች መደላድል ለመፍጠር የሚያስችል ሆኖ ሊገኝና በሬ እየጠመዱ ማረስ ጭምር ብርቅ ተደርጎ የሚወሰድበት የህብረተሰብ ክፍል ጥቂት አይደለምና ነው፡፡          

ከዚህ የተነሳም ነበር በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ገና ሀገር ወደ መምራቱ ስልጣን ሲመጣ ጀምሮ፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አጠቃላይ ቁመና በጥልቀት መገንዘብን የሚጠይቅ የጥናትና ምርምር ተግባር በማካሄድ ረገድ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደረግ የተስተዋለው፡፡ እናም ገዢው ፓርቲ አበክሮ ከመረመረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሀገራዊ ቁመና ያገኘውን ግብረ መልስ መሰረት አድርጎ የሚነድፋቸው የፈጣን ልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሁሉ፤ በተለይም ወደ ማይቀረው የኢንዱስትሪ አብዮት የሚያደርስ ቅኝት እንዲኖራቸው ታስቦ የተቀረፁ መሆናቸውን ማስታወስ ይቻላል ባይ ነኝ እኔ፡፡

ለዚህ አስተያየቴ የተሻለ ማረጋገጫ ሊሆነኝ ይችላል የምለውም ደግሞ፤ ኢህአዴግ እንደ አንድ ነገር ፓርቲ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፕሮግራሙን አጠቃላይ ቁመና በማያሻማ መልኩ ተንትኖ ለማቅረብ በሞከረባቸው የንድፈ ሃሳብ ጽሑፎች ላይ የሰፈረውን ማብራሪያ ነው፡፡ ይልቁንም ደግሞ ግንባሩ በ1993 ዓ.ም ላካሄደው ድርጅታዊ ተሃድሶ ውይይት “የዴሞክራሲ መሰረታዊ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የቀረበው የኢህአዴግየትንታኔ መጽሐፍ ላይ ጉዳዩን ለማብራራት የተሞከረበት ዝርዝር ሐተታ ጥሩ አብነት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል፡፡               

ምክንያቱም፤ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት የታተመው መጽሐፉ ከአራት መቶ በላይ ገፆች የያዘ ከመሆኑም ባሻገር፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፕሮግራም ከኛ አገር ተጨባጭ እውነታዎች አኳያ ተቃኝቶ ሲተገበር የሚኖረውን ፈርጀ ብዙ አንድምታም ከየትኛውም የጽሑፍ ሰነድ በተሻለ ስፋትና ጥልቀት የተነተነበት አግባብ እንዳለ አይቶ መፍረድ አይከብድምና ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም አሁን ላይ ሀገራችን ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት አብዮት ለማቀጣጠል ይቻል ዘንድ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ደረጃ በደረጃ የማዘመን ስራ የመስራትን አስፈላጊነት ጉዳይ “የዴሞክራሲ መሰረታዊ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ ያለው የኢህአዴግ ንድፈ ሃሳባዊ መጽሐፍ ላይ በስፋት መተንተኑን ነው እኔ የማስታውሰው፡፡ ይህ ማለትም ደግሞ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ እውነታ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ታዳጊ ሀገር ሊያደርገው ይገባል ሲል መጽሐፉ ያሰመረበት መሰረታዊ ነጥብ፤ ደረጃ በደረጃ እያደገ በሚቀጥል ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ለውጥ ሂደት ውስጥ ወደሚቀጣጠል የኢንዱስትሪ አብዮት መሸጋገር የሚቻለው፤ ነባሩን የግብርና ምጣኔ ሀብታዊ መሰረት ከአዲሱ የኢንዱስትሪ ስልተ ምርት ጋር ተመጋጋቢ እንዲሆን የማድረግ ስራ መስራት ሲቻል ብቻ እንደሆነ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አበክሮ ከማስገንዘብ ቦዝኖ እንደማያውቅ የሚያነመለክት ጉዳይ ነው፡፡

ጉዳዩን ከዚህ አኳያ አንስተን ስናየው የሚገለጽልን መሰረታዊ ጥሬ ሀቅም፤ የየትኛውም ሀገር ህብረተሰብ ከኋላ ቀር የአኗኗር ዘይቤ የሚመነጭ ድህነትን ታግሎ ለማሸነፍና በምትኩ የዘመናዊነት ትሩፋቶችን ለመቋደስ ወደሚያስችለው ምጣኔ ሀብታዊ የዕድገት ደረጃ ለመሸጋገር፤ ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ለውጡን ሂደት ቢያንስ ከግብርና ስልተምርት መጀመር ይጠበቅበታል ብለን እንድናምን የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከመቸውም ጊዜ በተዳለ ስፋትና ጥልቀት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችውን ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ለውጥ የማምጣት ጥረት ይበልጥ በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ሁለት ወሳኝ የሚባሉ ሀገር አቀፍ የቤት ስራዎችን የመስራት ጉዳይ እጅጉን አንገብጋቢና የጋራ መግባባትን የሚጠይቅ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

ከሁለቱ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱና ምናልባትም ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠውን ሀገር አቀፋዊ የቤት ስራ መስራት ይጠይቃል የሚባለው ወሳኝ ነጥብ፤ በተለይም አብዛኛው ህዝብ የቤት አንስሳትን ጭራ ተከትሎ ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ የተመሰረተ ህይወት ሲገፋ በኖረባቸው ክልሎች ውስጥ የሚስተዋለውን እውነታ ትርጉም ባለው ስፋትና ጥልቀት የመቀየር እንቅስቃሴ ላይ ማተኮር ይገባል የሚለው ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በግልጽ አነጋገር የሀገራችን አርብቶ አደር ህብረተሰብም ልክ እንደ አርሶ አደሩ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ሁሉ፤ በአንድ በተወሰነ አካባቢ ሰፍሮ የእርሻ ስራ ላይ እንዲሰማራና ገበያ ተኮር ሰብሎችን እያመረተ በማቅረብ ጭምር የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት ሂደት የሚያፋጥን አወንታዊ ሚና እንዲጫወት ከማድረግም አልፎ የኢንዱስትሪ አብዮቱ አካል እንዲሆን የማዘጋጀት ተግባር ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይታመናል፡፡

ይሄን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ የሚሆንበት ዋነኛው ምክንያትም ደግሞ፤ ከላይ እንደተጠቆመው፤ አንድን ሀዝብረተሰብ ከአርብቶ አደርነት ቀጥታ ወደ ኢንዱስትሪ መር ክፍለ ኢኮኖሚ ማሻጋገር ስለማይቻል፤ ቢያንስ አብዛኛው ህዝብ ከምጣኔ ሀብታዊ የመዋቅር ለውጡ ሂደት ጋር የሚመጋገብ የግብርና ምርትን እንደ ግብዓት የማቅረብ ስራ ላይ መሰማራት ይኖርበታል ተብሎ ይታመናልና ነው፡፡ ስለሆነም፤ የሀገራችንን አርብቶ አደር ህዝቦች የጋራ ግንዛቤ በሚጠይቅ ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ተግባራዊ መደረግ አለበት ሲባል፤ የድህነትና ኋላ ቀርነታችን መገለጫ ሆኖ ከቆየው ልማዳዊ የኑሮ ዘይቤ ቀስበቀስ እየወጣን ወደ ተሻለ ህይወት እንሸጋገር ዘንድ ታስቦ ለተጀመረው የኢንዱስትሪ አብዮት ይበልጥ መፋፋም መላው ኢትዮጵያዊ ህብረተሰብ የየራራሱን ታሪካዊ ሚና ይጫወት ዘንድ ይጠበቅበታል ከሚል እምነት ጭምር እንጂ በምግብ አህል ራሳችንን እንድንችል ብቻ አይደለም የሚለው ነጥብ ላይ ልናሰምርበት ይገባል፡፡

ይህ በተለይም የአርብቶ አደር ክልሎችን መንግስታት ግንባር ቀደም ጥረት የሚጠይቅ ሀገር አቀፋዊ የቤት ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሌላው አብሮ መነሳት ያለበት ሁለተኛ ቁልፍ ነጥብ ደግሞ የሀገራችን አርሶ አደር ህዝቦች በሚኖሩበት የገጠሪቷ ኢትዮጵያ ብዙ አካባቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ የእርሻ መሬት እጥረት የሚስተዋልበት አሳሳቢ ሁኔታ የመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ የአርሶ አደር ህብረተሰብ መኖሪያ በሆኑ ዞኖችና ወረዳዎች እየተስተዋለ ላለው የእርሻ መሬት ጥበት ወይም እጥረት እንደመሰረታዊ ምክንያት ሊወሰድ የሚችለውም፤ የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱና ከእያንዳንዱ አባወራ አብራክ ተከፍሎ ለአቅመ አዳም (ሔዋን) የሚደርሰውን ወጣት ዜጋ ራስ የሚያስችል ትርፍ መሬት ስለማይገኝ እንደሆነ ጥናታዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚያ ላይ ደግሞ አሁን አሁን ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ሲደጋገም የሚታየውና ከዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ቀውስ ጋር እንደሚያያዝ የሚነገርለት የድርቅ አደጋ ሲታከልበት፤ የብዙኃኑን ኢትዮጵያዊ ህብረተሰብ የገጠር ህይወት ይበልጥ በሚያጠጥር ፈረና የተሞላ እንዲሆን ሳያደርገው እንዳልቀረ መገመት ይቻላል፡፡ ስለዚህም፤ እኛ የዚች አገር ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደህብረተሰብ የምንታወቅበትን የጋራ ህልውናችንን፤ ስር ከሰደደው ድህነትነትና ኋላ ቀርነት አላቅቀን በተሻለ የዕድገት ጎዳና ማስቀጠል እንችል ዘንድ፤ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ጎላ ባለመልኩ እየተስተዋለ ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት አብዮት ይበልጥ እንዲቀጣጠል ከማድረግ ውጪ አማራጭ መፍትሄ እንደማይኖር ነው በርካታ የምጣኔ ሀብት ምሁራን የሚያስረዱት፡፡

በዚህ መሰረተ ሃሳብ ዙሪያ መሰል አስተያየት ሲሰጡ የሚደመጡት የኢኮኖሚስት ሙያ ዘርፍ ተንታኞች አክለው እንደሚሉትም፤ በሐዋሳ፤ በቐለና በኮምቦልቻ ግንባታቸው ተጠናቆ የተመረቁትን ዓይነት የኢንዱስትሪ ልማት መንደሮች (ፓርኮች) የመገንባት ጥረቱ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በዛሬዋ ኢረትዮጵያ የሚስተዋለው አጠቃላይ እውነታ ሀገሪቷ ለኢንዱስትሪ አብዮት መቀጣጠል የሚያመች የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ድባብ ውስጥ እንደምትገኝ የሚያመለክት መሆኑን ሲያስረዱም፤ የዘርፉ ተንታኞች “እንደ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ የሚወሰደው አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት አለ፡፡ እንዲሁም ደግሞ እንደመንገድና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዓይነቶቹን መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድም፤ ይሄ መንግስት እምብዛም ችግር እንደሌለበት ይታወቃል” ነው የሚሉት፡፡

እነዚህ እነዚህን እጅግ በጣም ጠቃሚ የመሰረተ ልማት ግብዓቶች በማሟላት ረገድ ቀላል ግምት የማይሰጠውን ርቀት የመጓዛችንን ያህል፤ አሁን የተጀመረውን ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በጥራትና በስፋት የመገንባት ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ፤ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ብቻም ሳይሆን፤ ከእርሻ መሬት እጥረት በሚመነጭ ችግር ምክንያት ወደየትም ለመሰደድ ሲገደዱ ለሚስተዋሉት የገጠሪቷ ኢትዮጵያ ወጣቶች ጭምር የስራ እድል የሚፈጥሩ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ማምረቻ ተቋማት በመላው የሀገራችን ከተሞች የምናይበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ነው የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ የሚያስረዱት፡፡ ስለዚህ እኔ ራሴን እንደ አንድ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከፈርጀ ብዙ ድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ የሚያደርጉትን ያላሰለሰ ጥረት ሁሉ ከመደገፍ ቦዝኖ የማያውቅ ዜጋ፤ ሀገራችን አሁን ላይ የጀመረችውን የኢንዱስትሪ ልማት አብዮት ብሩህ ጉዞ አጠናክራ ትቀጥል ዘንድ ተገቢነት ያለው ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ለማንኛውም ግን የዛሬውን ሐተታዬን በዚሁ አጠቃልያለሁ፡፡ መዓሰላማት!       

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy