Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግድቡና ቁርጠኛው ህብረታችን

0 344

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግድቡና ቁርጠኛው ህብረታችን

                                                                 ዘአማን በላይ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በተለያዩ የሀገራችን ክፍል ውስጥ እየተዘዋወረ ነው። በዋንጫው ዝውውር በተለይም በአሁኑ ወቅት ተረኛ በሆነው የደቡብ ክልል የግድቡን ዋንጫ በማዘዋወር 500 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ እንደነበር ይታወቃል። ሆኖም በአንድ ሳምንት ውስጥ በክልሉ ስምንት ዞኖችና ሁለት ወረዳዎች ብቻ ከ968 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ እንደተቻለ መረጃዎች ያስረዳሉ። በቀሪ ጊዜያትም ከስድስት ዞኖችና ከሁለት ልዩ ወረዳዎች ተጨማሪ ገንዘብ ይሰበስባል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ዕውነታም የሀገራችን ህዝቦች ግንባታ ፍፃሜ በነቃ ተሳትፎና በባለቤትነት ስሜት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተግባር ነው።

ርግጥ የሀገራችን ህዝቦች በየትኛውም የልማት ስራ ላይ ፋና ወጊ ናቸው። በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የባንዴራቸው ፕሮጀክት መሆኑን በመገንዘባቸው ለግድቡ ከፍፃሜ መድረስ እየተረባረቡ ነው። እጅግ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀሩ ለግድቡ ግንባታ ከዕለት ቀለባቸው ጭምር እየቀነሱ በገዛ ፈቃዳቸው እያከናወኑ ያሉት የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የቀሳቁስና የሞራል ድጋፍ እጅግ የሚያኮራ ነው።

ነጋዴው የህብረተሰብ ክፍልም ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። ምንም እንኳን ይህ የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ሰራተኛው ጋር ሲነፃፀር የሚገባውን ያህል ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን እገዛ አድርጓል ብዬ ባላምንም፤ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ግን በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም።

ያም ሆኖ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ለግድቡ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ርግጥ ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን ነጋዴው ክፍል እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ግብር ከመስጠት በላይ ነው።

የግብር ጉዳይ ከባንዴራው ፕሮጀክት ጋር ሊነፃፀር አይችልም። ግብር መክፈል የውዴታ ግዴታ ነው። የሀገራዊ ክብርና ኩራት መገለጫም ነው። እናም የሀገራችን ልማት ዋነኛ ተጠቃሚ የሆነው ነጋዴው የህብረተሰብ ክፍል ግብሩን እየከፈለ ለግድቡ ግንባታ እንዳለፈው ጊዜ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንዳለበት ግንዛቤ መያዝ ያለበት ይመስለኛል። በጥቅሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን በገዛ ፈቃዱ የሚያደርገው የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የቀሳቁስና የሞራል ድጋፍ ርብርብ እስከ ግድቡ ፍፃሜ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ግድቡን ለመገንባት ለዘመናት ሳይደፈር የቆየውን የዓባይን ወንዝ የመድፈር ተግባር በዚህ ትውልድ እውን ሆኗል። በዚህም ይህ ትውልድ የትናንቱን ትውልድ የልማት ጥያቄ፣ የዛሬውን ትውልድ ተጠቃሚነትና የነገውን ትውልድ አደራ ተቀብሎ እየሰራ ነው። የታላቁ የአትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዚህ ረገድ ሁነኛ ማሳያ ነው። መቻላችንን የምናሳይበት የቁርጠኛ ህብረታችን አንድ መገለጫ ነው።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በዕውቀቱ ለመደገፍ የገባውን ቃል አሁንም ቀጥሏል። ምንም እንኳን ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ሃይሎች የፈለጉትንና ያሻቸውን ቢያወሩም፤ በኢትዮጵያ ህዝቦች ርብርብ ግንባታው ዛሬም ድረስ ለአንድ ሰከንድ እንኳን አልተቋረጠም። “የነብርን ጭራ አይዙም፣ ከያዙም አይለቁም” እንዲሉ አበው፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ይህን ፕሮጀክት አውን ለማድረግ ልማቱን በነብር ጭራ መስለው ይዘውታል። አይለቁትም።

በተምሳሌታዊ ዘይቤው የነብርን ጭራ ከለቀቁ በነብሩ መበላት ስለሚሆን፤ ተምሳሌታዊውን የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በመተው ወደ ድህነት አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ አይሹም። ማደግና መበልጸግ እንደሚችሉ አንድ ማሳያ የሆነውን የግድቡን ግንባታ በመተው የድህነት መገለጫ ሊሆኑ አይከጅሉም። ያ ታሪክ በሂደት እየተቀረፈ፣ ህዝቡም ከዕድገት የሚያገኘውን ጥቅም እያጣጣመ ነው።

እናም የህዳሴው ግድብ ለአንዲት ሰኮንድም ሊቆም የማይችለው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በጋራ ተጠቃሚነት ማናቸውንም ልማታዊ ተግባሮች ማከናወን እንደምንችል ማሳያ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው። በሌላ በኩልም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተፋጠነ ባለው የልማት ተግባር ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪዎች “እየበቀሉ” ነው። ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ታዲያ ይህን የዕድገት ፍላጎት በአግባቡ ለማስኬድ የኤሌክትሪክ ሃይልን ከከባቢ ብክለት በነፃ መንገድ መጠቀም የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ ታዳሽ የተፈጥሮ ሃይላችንን መጠቀም ይኖርብናል። ይህን ካላደረግን አሁንም ከነበርንበት የከፍታ ቦታ ተንሸራትተን የኋሊት በድህነት አረንቋ ውስጥ ልንዘፈቅ እንችላለን። ይህን ደግሞ የሚፈቅድ ትውልድ የለም። እናም የህዳሴው ግድም ለአፍታም ቢሆን የማይቆምበት ሁለተኛው ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።

እኛ ስናድግም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራትም የሁኑ ሌሎች የቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። እኛ ከቀጣናው ሀገራት ተነጥለን ልንለማ አንችልም። የእኛ እድገት የቀጣናው ሀገራት ጭምር ነው። የግድቡ ግንባታ የቀጣናውን ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ችግርም የሚቀርፍ ነው። እናም ሶስተኛው ግድቡ ለአንድ ሴኮንድም ቢሆን ሊቆም እንዳይችል የሚያደርገው ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።

መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እነዚህን እውነታዎች በሚገባ ያውቃሉ። ምንም ዓይነት ብዥታ የለባቸውም። ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዥ ዋንጫው በየክልሉ ሲዞር ከተጠበቀው በላይ ገንዘብ በማውጣት ቦንድ የሚገዙትም ለዚሁ ነው። ቀደም ሲል የጠቀስኩትና በደቡብ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ የተሰበሰበው ገንዘብ ይህን ሃቅ የሚያረጋግጥ ነው።

ይህ ዕውነታ በሀገር ቤት ውስጥ ብቻ የሚገለፅ አይደለም። በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዚሁ ግድብ ግንባታ እየፈፀሙት ካለው ቀላል የማይባል የቦንድ ግዥን ጨምሮ ካሉበት ቦታ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የግድቡን ግንባታ በመጎብኘትና ሌሎች ኢትዮጵያዊንም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማነሳሳት ረገድ እየተጫወቱ ያሉት ሚናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ይህ ቁርጠኛ የህብረት ስሜት ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ድረስ የሚታይ ነው። ማንም በገሃድ የሚያየውም ጭምር። እናም ይህ የህዝቦች አንድነት የራስን የተፈጥሮ ሃብት በራስ አቅም የማልማትና በእርሱም ራስንና ከባቢውን የመጥቀም ተምሳሌት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ይህን የማስተባበር ስራ የሚያከናውኑት አካላትም ስራቸውን ሳያቆራርጡና ያዝ ለቀቅ ሳያደርጉ በቋሚነት ማከናወን ያለባቸው ይመስለኛል።

ርግጥ አሁን ያለውንና ግድቡን ከፍፃሜ ለማድረስ ያለውን የህዝቡን ስሜት በተገቢው መንገድ መምራት ከተቻለ፤ ትናንት ‘ዓባይ የሌላው ሲሳይ’ የሚለውን አባባል፤ ‘ዓባይ የእኛና የጎረቤቶቻችን ሲሳይ’ ወደሚለው የተጠቃሚነት እሳቤ መለወጣችን አጠያያቂ አይሆንም። የየትኛውም ሀገር የልማት ምንጭ ህዝብ መሆኑ፣ ከዚህ አኳያ በተለይ ታታሪው የሀገራችን ህዝብ ለማደግ ያለውን ቀናዒ አስተሳሰብና ተግባር በሚፈለገው ፍጥነትና ደረጃ ማስኬድ ይገባል። ይህን ቁርጠኛ የህብረት መንፈስና ህዝባዊ ስሜት ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ አሁንም ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ያም ሆነ ይህ በኢትዮጵያዊያን ቁርጠኛ የህብረትና የአንድነት መንፈስ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ግድቡ እውን መሆኑን ሁሌም በርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy