Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጣምራ ህመም፤ መንስዔውና መዘዙ

0 503

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጣምራ ህመም፤ መንስዔውና መዘዙ

ኢብሳ ነመራ

ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ጉድለት የኢፌዴሪ መንግስት መሰረታዊ ፈተናዎች ከሆኑ ከራርሟል። ይህን እውነት ከውጭ ወይም ገለልተኛ ሊባል ከሚችል አካል ይልቅ በመንግስት በራሱ ሲነገር ሰምተናል። የኢፌዴሪ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በተለይ ባለፉ ስድስትና ሰባት ዓመታት፣ የከፋ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለበት ያለማሰለስ ሲገልጽ ቆይቷል።

መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል የስርአቱ አደጋዎች ወደመሆን እየተሸጋገሩ መሆኑንም ገልጸዋል። ኢህአዴግ 2007 ዓ/ም ማገባደጃ ላይ ያካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤ ዋነኛ የውይይት አጀንዳና ውሳኔ ያሳለፈበት ጉዳይ የመልካም አስተዳደር መጓደልና ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚመለከቱ ነበሩ።

የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሩ በመንግስትና በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያለ በመሆኑ የሚታገለው ወገን ከጎኑ ባለው የችግሩ ተሸካሚ አንድ እጁ ተይዞ ነው ትግሉን የሚያካሂደው። ይህ ትግሉን ከባድና ውስብስብ አድርጎት ቆይቷል። በመሆኑም መንግስት በጸረኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ፣ ህዝብ መሳተፍ እናደለበት፣ ካለህዝብ ተሳትፎ መንግስት ብቻውን በሚያካሂደው የአንድ እጅ ትግል የትም እንደማይደረስ በይፋ ተናግሯል። በይፋ መናገር ብቻ አይደለም፣ ህዝባዊ ንቅናቄም አውጇል።  

በመሰረቱ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል የተነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም። ኪራይ ሰብሳቢነት ካለ የመልካም አስተዳደር ጉድለት መኖሩ አይቀሬ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት የመልካም አስተዳደር መጓደል ሳያስከትል ብቻውን እንደችግር ሊኖር አይችልም።

ኪራይ ሰብሳቢነት ሲኖር ፍትሃዊ መንግስታዊ አገልግሎት መስጠት አይቻልም። ኪራይ ሰብሳቢነት ሲኖር የተሟላ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን ለህዝብ ማቅረብ አይቻልም። ኪራይ ሰብሳቢነት ሲኖር ህግ በኪራይ ሰብሳቢዎች ይጠለፍና ፍትህ ይዛባል።  ኪራይ ሰብሳቢነት ሲኖር የፖለቲካ ስልጣን ህዝብን ከማገልገል ይልቅ ለግልና ቡድናዊ ብልጽግና ማስጠበቂያ ዓላማ ስለሚውል የህዝብ የስልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት ይሸራረፋል፣ የዴሞክራሲ መርሆች በወረቀት ላይ ይቀራሉ። ግልፅነት፣ አሳታፊነት፣ ተጠያቂነት . . . የሚሉት የመልካም አስተዳደር መርሆች ዋጋ ያጣሉ። ምናልባት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ግድግዳ ላይ የተለጠፉ ማንም የማይመለከታቸው አሰልቺ ዝርዝር ከመሆን ያለፈ ከቁብ የሚቆጥራቸው አይኖርም።

መንግስት የኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር መጓደል ጣምራ ህመም ህዝብ ላይ የተጫነበትን ሁኔታ ይዞ ሊዘልቅ አይችልም። ህዝብ አንድ ወቅት ላይ ህመሙ ሊታገሰው ከሚችለው በላይ ይሆንበታል። ይሄኔ በድንገት ገንፍሎ መንግስት ላይ መነሳቱ አይቀሬ ነው። ልጓም ያጣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል የስርአት አደጋ የሚሆነው በዚህ አኳኋን ነው። የኢፌዴሪ መንግስትና ገዢው ፓርቲ በሃገሪቱ ያለው የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር የስርአቱ አደጋ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ ይህን እየተናገሩ ነው። ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር ያስፈለጋቸውም ለዚህ ነው።

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አምስተኛውን ዙር የመንግስት ስልጣን ሲረከብ፣ የስርአቱ አደጋ ለመሆን በቅቷል ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ጉድለት በህዝባዊ ንቅናቄ ለመታገል ቃል ገብቶ ነበር። ይህ ቃል፣ በህዝቡና ከችግሩ በጸዱ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም በድርጅቱ አመራሮችና አባላት ዘንድ መነሳሳት ፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ የታወጀው ጸረ ኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ህዝባዊ ንቅናቄ መቀጣጠል ከመጀመሩ በፊት፣ ህዝብ ላይ የተፈጠረው ህመም ልኩን እያለፈ ኖሮ ቅሬታው በተቃውሞ መልክ ፈነዳ።

ባለፈው ዓመት መንግስት አምስተኛ ዙር የመንግስት ስልጣን ዘመን ሃላፊነቱን በይፋ ተረክቦ አንድ ወር እንኳን ሳይሞላው በኦሮሚያ የፈነዳውና ወደሌሎች ክልሎችም የተዛመተው በአመዛኙ ወጣቶች የተሳተፉበት ተቃውሞ የዚህ ውጤት ነበር። እርግጥ ይህ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል የፈጠረው ተቃውሞ ሃገሪቱን ዳግም ሃግር ልትሆን በማትችልበት ሁኔታ የማፈራረስ ስትራቴጂ ነድፈው በሚንቀሳቀሱ የውጭ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው ተጠልፎ ወደአውዳሚ ሁከትነት መቀየሩ አይካድም።

ያም ሆነ ይህ፣ ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰውና የተዛመተው፣ በረደ ሲባል እያገረሸ ለዜጎች ህይወት መጥፋት፣ ለህዝብ ሃብት ውድመት ምክንያት የሆነ ተቃውሞና ሁከት መሰረታዊ መነሻ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል ነበር። በመሆኑም ለዚህ ችግር መፍትሄ ከመስጠት ውጭ ሌላ የሚያበረደውና ዳግም እንደማይከሰት ዋስትና የሚሰጥ አማራጭ አልነበረም። ገዢው ፓርቲና የኢፌዴሪ መንግስት በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ የጀመሩት ይህን ለማደረግ ነበር።

በዚህ መሰረት ከብቃት ማነስና የመንግስትን ስልጣን ለህዝብ ጥቅም ከማዋል ይልቅ ለራስ የሞቀ ኑሮ ማደላደያነት በመጠቀም፣ እንዲሁም በዳተኝነት የመልካም አስተዳደር መጓደል መንስኤ ሆነዋል የተባሉ በፌደራልና በክልል መንግስታት ከላይ እስከታች ያሉ የስራ ሃላፊዎች ተነስተው በአዲስ እንዲተኩ ተደርጓል። በየክልሉ የዞንና የከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች ህዝብ ፊት ቀርበው እየተገመገሙ የህዝብ ይሁንታ ያገኙት ብቻ እንዲሾሙ ተደርጓል።

የከፋ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል እንዳለባቸው በተለዩ የክልልና የከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ በየደረጃው ያሉ የስራ ሃላፊዎችንና ባለሙያዎችን ከስራ ተሰናብተዋል፣ ከደረጃ ዝቅ የተደረጉም አሉ። ለመከሰስ የሚያበቃ ማስረጃ የተገኘባቸው ደግሞ በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል። በአጠቃላይ በጥልቀት የመታደሱ እርምጃ በተወሰ ደረጃ ጥሩ ተጉዟል ማለት የሚቻልበት ሁኔታ ታይቷል። በዙ የሚቀሩ እርምጃዎች መኖራቸው ግን አይካድም፤ በተለይ አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ከማድረግ አኳያ።

ታዲያ በጥልቀት የመታደስ አዋጅ ሲለፈፍ መንግስት በቅድሚያ ያደሰው ቃል በኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ የተዘፈቁ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ነጋዴዎችና አቀባባይ ደላሎች ላይ ምርመራ በማደረግ ማስረጃ በማሰባሰብ ለህግ ማቅረብን ነበር። ይህ አዲስ የተገባ ቃል አይደለም። መንግስት ቀደም ሲልም በዚህ ጉዳይ ላይ ጽኑ አቋም ነበረው። በ2009 መግቢያ ላይ ይህን ቃል አድሷል።

ይህን ተከትሎ ህዝብ በኪራይ ሰብሳቢነት የህዝብን ሃብት ለግል ጥቅም ያዋሉና ተጠቃሚነቱን ያጓደሉ፣ መንግስታዊ አገልግሎቶችን የነፈጉ፣ ፍትህ ያዛቡ . . . የስራ ሃላፊዎች ህግ ፊት ሊቀርቡ ነው በሚል በጉጉት ሲጠብቅ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ መሰረት በክልል መንግስታትና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በርካታ በኪራይ ሰብሳቢነት የተጠረጠሩ የስራ ሃላፊዎችና ባለሞያዎች የተከሰሱ መሆኑ ባይካድም በህዝቡ ዘንድ እርካታ የፈጠረ እርምጃ ተወስዷል ማለት ግን አይቻልም። ሰሞኑን ግን እመርታዊ ሊባል የሚችል እርምጃ ተወስዷል።  

በዚህ በሰሞኑ እርምጃ፣ በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 42 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል። የከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎቹ በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን፣ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ በስኳር ኮርፖሬሽን፣ በገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር እንዲሁም በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የስራ ሃላፊዎች፣ ነጋዴዎችና ደላሎች ናቸው። ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ለተጨማሪ ምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።

እነዚህ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች በተጠረጡበት የሙስና ወንጀል አድርሰዋል የተባለው ጉዳት፤ በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን 1 ቢሊየን 358 ሚሊየን ብር፣ በስኳር ኮርፖሬሽን (ከመተሃራ፣ ተንዳሆና ኦሞ ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች) 1 ቢሊየን 21 ሚሊየን ብር፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር፣ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን 198 ሚሊየን ብር እንዲሁም በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት 41 ሚሊየን ብር መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ የባከነው ወይም ለብክነት የተጋለጠው ሃብት 4 ቢሊየን ብር ገደማ ነው። ይህ ሃብት ትልቁ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅሰቃሴ የሚካሄድበት የአዲሰ አበባ ከተማ በዓመት የሚሰበስቡትን አጠቃላይ ገቢ ግማሽ ሊሆን ጥቂት ነው የሚቀረው። ይህ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያበቃው የሙስና ወንጀል ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል።

ዋና አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ መንግስት በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ የወሰደውና በቀጣይነትም የሚወስደው እርምጃ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ሪፖርትን፣ በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችንና የህብረተሰቡን ጥቆማ እንዲሁም መንግስት ባካሄደው ጥናት  በተገኘ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስታውቀዋል። ዋና አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው ሙስናው የተፈጸመበት አኳሃን ላይም ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይህ በመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ስለጠሰጠው በዝርዝር አላነሳውም። ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባሩ ቀጣይነት እንዳለውም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በሃገሪቱ ስር እየሰደደ የመጣውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የመዋጋት ጉዳይ የህዝቡን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ፣ ህግን ከኪራይ ሰብሳቢዎች እጅ መንጭቆ ፍትህን የማስፈን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሃገሪቱን ዘላቂ ህልውና የማረጋገጥም ጉዳይ ነው። ህዝብ የኪራይ ሰብሳቢነትንና የመልካም አስተዳደር መጓደል ጣምራ በሽታን ተሸክሞ ዘላለም መኖር አይችልም። አንድ ቀን ስቃዩ ሲበዛበት በድንገት ተቆጥቶ መነሳቱ አይቀሬ ነው።

ህመሙ ከሚታገሰው በላይ ሲደርስ የሚፈጥረው የህዝብ ቁጣ ግብታዊ ስለሚሆን አደገኛ ነው። ለሃገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላቶችም መንገድ ይከፍታል። ስለዚህ ሰሞኑን የተጀመረውን ኪራይ ሰብሳቢነትን የመታገል እመርታዊ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ህዝብም በዚህ ላይ በንቃት መሳተፍ አለበት። የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል ጣምራ ህመምን ሳይብስ ማስወገድ የህልውና ጉዳይ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy