Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

0 431

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ድንበር ተሻጋራው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፋይዳ

 

ስሜነህ

 

አንድ የልማት ስራ ሲታቀድ፣ በልማድ ወይም እንደ ሀገሩ ህግ በግዳጅ፣ በፍጥረትና በተፈጥሮ ላይ በቀጥታ ወይም በተዘዋሪ መንገድ ስለሚያመጣው ተጽዕኖ “ስለአካባቢው ፍጥረት ተጽዕኖ ምርምር” (ኢንቫይሮንሜታል ኢምፓክት ስቴትሜንት (EIS)” የተባለ ጥናት አስቀድሞ ይካሄዳል። በዚሁ መሰረት የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ ግዙፍ ስራ ስለሆነ፣ ጉዳቱም ሆነ ጥቅሙ ለሀገርና ለሕዝብ እንዲሁ ከፍ ያለ ስለሚሆን፣ ባለሙያዎች የግድቡን ስራ በሚገባ መርምረው እና አጥንተው ስራው የተጀመረ መሆኑ ይታወቃል። በጥቅሉ ግድቡ የልማት እርምጃ ነው።

 

በአካባቢው መሬት አቀማመጥ መሰረት ለግድቡ ስራ ምቹ በሆነው ጉባ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  ላይ በአባይ ወንዝ ግራና ቀኝ ኮረብታዎች አሉ። ይህ ቦታ በለስ ወንዝ ከአባይ ወንዝ ጋር ከሚገናኝበት ስፍራ ወደ ሰሜን ራቅ ብሎ ነው። ኮረብታዎቹ ለግድቡ የተመቹ መሆናቸው ተረጋግጦ ነው ወደስራ የተገባው።  

 

አባይ ትንሿ ከጣና ሀይቅ ደቡብ-ምዕራብ ላይ ከሚገኘው ተራራ ስር ከዳንግላ ከተማ አጠገብ ተነስታ ጣና ሐይቅ ትገባለች ። በዛ ያሉ መጋቢ ወንዞች በሁሉም አቅጣጫ ወደ ሐይቁ ትንሽ ወይም በዛ ያለ ውሃ ይዘው ጣናን ይሞላሉ። ከዚያም ትልቁ አባይ ወንዝ ከጣና ሐይቅ ከደቡብ ጫፉ ከባህር ዳር ከተማ ማዶ በምስራቅ ተንስቶ፣ በግምት 800 ኪ/ሜ ተጉዞ ሱዳን ይገባል። አባይ ወንዝ የኢትዮጵያን ደጋ ምድር ሰንጥቆ በታላቅ ሸለቆ ውስጥ 400 ኪ/ሜ ከተጓዘ በኋላ ቆላው መሬት ይደርሳል። ከዚህ በኋላ ጎኑ ሰፋና ጠበብ እያለ ሌላ 400 ኪ/ሜ ተጉዞ ሱዳን ምድር ይገባል። አባይ ወንዝ ከጣና ኃይቅ ሲወጣ ከውቅያኖስ በላይ በግምት 1ሺ 800 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ ወደ ስምንት መቶ ሜትር ከፍታ የሚወርደው 400 ኪ/ሜ ተጓዞ ቆላው ምድር ሲደርስ ነው። በዚህ አካባቢ ተምዘግዝጎ የሚወርድበት ብዙ ቁልቁለት ወይም ሸለቆ ቦታ የለም። ስለዚህ፣ ብዙ ሳይንቦራጨቅና ሳይጮህ ሰጥ ለጥ ብሎ ይፈሳል። ዳሩ ግን፣ የክረምቱ ዝናብ 200,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆነውን ሰፊ ምድር በመጋቢ ወንዞቹ አማካይነት ጠርጎና አጥቦ በታላቅ ጎርፍ ኃይል ስለሚፈስ ባህሪው ይለወጣል። ያከማቸውን ደለል ጭኖ ትቂቱን አፈር በአንዳንድ ስፍራ ወደ ጎኑ እየቆለለ ሌላውን ተሸክሞ ሱዳን ይገባል።

 

ከድንበሩ ብዙ የማይርቀው የሱዳን ሮሳሪየስ የተባለው ታላቅ ግድብና የግድቡ ሀይቅ በዚህ የክረምት ጎርፍና ደለል ምክንያት ሲታወክ የነበረበት ዘመን በተከዜ ግድብ ብቻ ያበቃለት ቢመስልም በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመታወክ ይድናል። በተጨማሪም፣ የበለስ ወንዝ የፈጠረው ጎርፍና ደለል ችግሩን አባብሶት የነበረ መሆኑ ይታወቃል። በለስ ወንዝ ከአባይ ሀይቅ ዝናብ ማከማቻ ተራራ ጠርዝ ጀርባ ተነስቶ ወደ ምዕራብ በመፍሰስ 400 ኪ/ሜ ተጉዞ ከአባይ ወንዝ ጋር ይገናኛል ። በለስ ወንዝ ሰፊ የልማት ግስጋሴ የገለጠውን ደን፣ ቅጠል፣ ሳርና ችፍግ-ለበስ ምድር ለጥ ያለ መሬት ስላደረገው የላዩን አፈርና ሙሾ መሬት ጠርጎና ጭኖ አባይ ወንዝ ይገባል። አባይ ወንዝ ከጣና ሐይቅ ተነስቶ ሱዳን ምድር ለመድረስ 800 ኪ/ሜ የወሰደበትን በለስ ወንዝ ከጣና ሐይቅ በምዕራብ በኩል ተነስቶ በፍጥነት 400 ኪ/ሜ እየተምዘገዘገ ወርዶ ከአባይ ተቀላቅሎ ሱዳን ይገባል።

 

በለስ ለኢትዮጵያ ተፈጥሮ ሊያስክትል የሚችለው ጉዳት በቀላሉ የሚተመን አይሆንም። ጥሩ አፈሩን ብቻ ሳይሆን ውሃውም የተፈጥሮ ስራ ሳይቆጣጠረው የሰው ልጅ በአመጣው ለውጥ ምክንያት አምልጦ ወደ ሱዳን ይገባል። እንስሳው፣ አፈሩና ምድሩ፣ ዛፍና ቅጠሉ፣ አየሩ ሳይመጠውና ሳያግደው ቶሎ ፈሶ ጥሩ አፈር ጭኖ ሱዳን ምድር መግባቱ ታላቅ ጉዳት ሲያስከትል ኖሯል። አባይና በለስ ወንዝ የተሸከሙትን አብዛኛውን ደለል የሚያራግፉት ከመገናኛቸው ቦታ አካባቢ ጀምሮ እስከ ሱዳን የሮሳሪስ ግድብ ውሃ ድረስ ስለመሆኑ የምድሩን አቀማመጥ አይቶ መገመት አይከብድም። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ  ግድብ ሲጠናቀቅ ሱዳን በዚህ ምክንያት የገጠማት ችግር ይቃለልላታል።

 

ግድቡ የሚገኘው ከትልቅ ሸለቆ ይልቅ ትንሽ ከፈት ባለ ምድር ስለሆነ፣ ለግድብ አመች ካደረጉት ምክንያቶች  አንዱ ነው። የዚህ አይነት ገለጥ ያለ ምድር አንዱና ዋናው ጥቅም ደለሉን በየጊዜው ከሀይቁ ቧጦ ለማውጣት የሚያመች መሆኑ ነው። ይህም እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ግድቡ የፈጠረውን ሀይቅና የውሃ መቋጠሪያ ቦታ ደለል እንዳይሞላው ለመከባከብ ምቹ ስለ ሚያደርግ ነው። የግድቡ ተጠራቃሚ ውሃ ብዙ እንደሚሆን የምድሩ ተፈጥሮ ያመለክታል። ይህ የሚያስከትለው ችግር ቢኖር፣ የግድብ ስራ ከሚያስከትለው እንከኖች አንዱ እንጂ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ስራ በተለይ የሚፈጥረው ልዩ ችግር አይደለም።

 

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ጥልቅ ሸለቆ ለውሃ ማጠራቀሚያ ጥሩ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሸለቆ የደለል ጠንቅ ስለሚሆን ደለሉን በየጊዜው ቧጦ ለማውጣት የሚያስፈልገው ጥረት በገንዘብ ሲተመን የግድቡን ትርፍ ጥቅም እጅግ ዝቅ ሊያደርገው ይችላል። ጥልቅ ሸለቆ ለግድብ ጠንቅ የሚያደርገው ሌላው ችግር መሬት ከተደመረሰ ሀይቁን በአፈር በመሙላት ግድቡም እንዲናድ ስለሚያደርግ ነው። ይህ ደግሞ ግድቦችን ከሚያስጨንቁት አደጋዎች አንዱ ነው። የኢንጂነሪግ ጥበብ ይህን ችግርና ጥፋት እንዳይደርስ ቢከላከልም፣ ግድቦች በመሬት መናድ ብዙ ጊዜ ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑ የአለማችን ታላላቅ ግድቦች ያለፉበት ሂደት ያሳየን እውነታ ነው።  

 

የአባይ ወንዝ ብዙ የምርምር ጥናቶች ከተካሄዱበት አያሌ የኢትዮጵያ ወንዞች አንዱና ዋናው ነው። በእርግጥ ግብጽና ሱዳን ባያውቁ ኢትዮጵያንኖች የሚጨነቁበት ጉዳይ አይሆንም። ግን ጥናቱን ማካፈሉ በሰጥቶ መቀበል መርሆ ተገቢ ስለሆነና ከልማት ውጪ ሌላ አጀንዳ የሌለን መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።

 

ኢትዮጵያ ስለልማቷ ስራ ከማንም የምትሸሽግበት ጉዳይ አይኖርም። የኢትዮጵያን ስራ ግብፅ ለማጥፋት አትሞክርም።  ኢትዮጵያ ሊያስቸግሩ ይችላላሉ በማለት ታስብ የነበረው ግብፅን ሳይሆነ የአረቦችን መተባበርና አድማ ነበር። ያም ሁናቴ በነ ናስር ጊዜና በነሳዳት ዘመን ነበር። ከዚያ በኋላ፣ እያንዳንዱ የአረብ ሀገር ጉዳያችን ምን እንደሆን በሰራነው ዲፕሎማሲያዊ ስራ እየገባው ስለሄደ፣ ኢትዮጵያን መተናኮልና በኢትዮጵያ ላይ ማደሙን ትቶታል።

 

በግድቡ አካባቢ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ የሚካሄዱ ከሱዳን ዕድገት ጋር የሚነጻጸሩ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች አሁን እየተደረጉ መሆኑ የሚያመለክተውም ይህንኑ ነው። በአባይ ወንዝ ግራና ቀኝ ጠለቅ ብሎ ባለውም የሱዳን ምድር የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ጨምሮ  የእርሻ ልማቶች እየተፋፋመ የመሆኑ ሚስጥር የታላቁ ግድብ ትሩፋቶችን ታሳቢ ያደረገ ነው።

 

አባይ ወንዝ ሱዳን ምድር ሲገባ ብዙ ሳይጓዝ ሮሳሪየስ ከተባለው ታላቅ ግድብ ይገባል። የተጠራቀመው የዚህ ግድብ ውሃ፣ ባካባቢው ላሉት ታላላቅ የመስኖ እርሻ ልማቶች ያገለግላል። በተጨማሪም ደቡብ ሱዳን ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ እንደሚጋብዝ ይጠበቃል። የኤሌትሪክ ኃይል ተጨማሪ ሰፊ ልማት እንዲካሄድ ስለሚያበረታታ።  

 

የአባይ ወንዝ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ደጋ መሬት የዝናብ ውሃና አፈር ለሱዳንና ግብጽ ምድር አበርክቶ ሜድትራንያን ባህር ይገባል። አባይ ወንዝ ሰውና እንስሳ፣ ሳርና የዛፍ ስር ከሚመጠው፣ በጸሐይ ሙቀት ተኖ ከሚጠፋው፣ አፈርና መሬት ካገደው የተረፈውን ይዞ ሱዳን ምድር ይዘልቃል። ይህ ረጅም ጉዞ ለፍጥረትና ተፈጥሮ ሰፊ ጥቅም አለው። የአባይ ወንዝ ኢትዮጵያ አሁን ከምናያት ፍጥረትና ተፈጥሮ ሁኔታ ጋር የተጣመረ ነው። አባይ አሁን በሚሄድበት ምድር ባይፈስ ኖሮ በኢትዮጵያ የምናየውና የምናውቀው የአየር፣ የመሬት፣ የእንስሳ የሕዝብ ሁኔታ እጅግ ሊታሰብና ሊገመት በማይቻል በሌላ ዓይነት ተፈጥሮ ሁኔታ ይገኝ እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ ።  

 

ጥናቱ በጣና ሀይቅ አካባቢ የወደፊቱን ዕድገት አስመልክቶ በተለያዩ መስኮች ሊሰሩ የሚችሉትን ዕድገቶችና አስፈላጊ ስራዎች ይጠቁማል። ከነዚህ ውስጥ ውሃ፣ መሬት፣ ከብት፣ እርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ የኤሌትሪክ ኃይል፣ የደን፡ አሳ ልማት፣ የከተማ ዕድገት፣ የሕዝብ ባህል፣ ቅርስና ታሪክ ለኗሪውና ለጎብኝ ማራኪ ቦታ እንዲሆን፤ የጥናቱ ስራም ለዚህ ዕድገት እንደሚጠቅም ይዘረዝራል። ይህ እጅግ አስፈላጊ ስራ ነው።  

 

አንድ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም የሚሰራውን በጎ ስራ በጎ እስከሆነ ድረስ እንከን ቢኖርበትም እንኳን ጉድለቱ እንዲስተካከል እንጂ ጥረቱ በጠቅላላ እንዲከሽፍ የሚሻ ወገን ሊኖር አይችልም። በአባይ ወንዝ ላይ የግድብ ሀሳብ ሲነሳ የኢትዮጵያ ወገን የሆነ ሁሉ ልዩ ስሜት ይሰማዋል።  

 

ስለ ግድቡ ጠቃሚነትና ወይም ጉዳት እጅግ በጣም ሰፊ የሆኑ ምርምሮች በብዙ ወገኖች ተገልጸዋል። አሁንም ከብዙ አቅጣጫ ያለማቋረጥ እየጎረፉ ነው። ግድቡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ለጎረቤት ሀገሮች ብልጽግናና ዕድገትም ጠቃሚ መሆኑ በብዙ አግባቦች ተረጋግጧል። የሱዳንና የግብፅ ከተሞችና ኢንዱስትሪዎቹ የሚፈልጉት የኤሌትሪክ ኃይል እንዲሁም በሱዳን ምድር በአባይ ወንዝ ዳርና አካባቢ የሰፈረው ሕዝብ ከበለስና አባይ ወንዝ ደለልና ጎርፍ መጠበቃቸውም እንዲሁ ወሳኝ ከሚባሉት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ትሩፋቶች አንዱ ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy