Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

0 328

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላማችን ሁለንተናችን ነው!

                                          ደስታ ኃይሉ

ያለ ሰላም ልማትን ማሰብ ማሰብ አይቻልም። ልማት የአገራችን የህልውና ጉዳይ ነው። የተጀመረውን አገራዊ ልማት ለማስቀጠል አስተማማኝ ሰላም ስለሚያስፈልገን ለእኛ ሰላማችን ሁለንተናችን መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። እናም ሰላምን እውን ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ ሰላም የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይኖርበታል።

እርግጥ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ ማንኛውም ዜጋ ጥያቄዎችን በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚያቀርብበትን አሰራርና መብት እንዳስቀመጠ በሚገባ ያውቃሉ። በተለያዩ ጊዜያትም ይህን መብታቸውን እየተጠቀሙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

ዳሩ ግን ይህን መብታቸውን በሰላማዊ ትግል የሚያጠናክሩነትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዚህም የህዝቡን ፍላጎት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ጋር ነጥሎ በመመልከት ሰላማዊ ትግሉን ማጎልበት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆን የለበትም።

ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብና ህገ መንግስታዊ መፍትሔ መሻት የዜጎች ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ይህ ዴሞክራሲያዊ መብት በፅንፈኞች እንዲሁም በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች ተጠልፎ ህገ ወጥ በሆነ መስመር እንዳይጓዝ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።

ለነገሩ ፅንፈኞቹና ፀረ ሰላም ሃይሎቹ ለህዝቡ ያስገኙለት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለም። እነዚህ ሃይሎች ሰላሙን አጥቶ የየዕለት ተግባሩን እንዳያከናውን እንዲሁም በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት የተገኙትን ስኬቶች ከማስተጓጎል ውጪ የሚያመጡለት ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖርም ያውቃል።

የሀገራችን ህዝብ ዛሬ 15 ዓመት በፊት የተቀጣጠለው የተሃድሶ ንቅናቄ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ፈጣን በሆነ ሁኔታ የተቀየሰና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደነበር የሚያውቅና ለዚህ ዕውን መሆንም የተንቀሳቀሰ ነው። ለውጥ ማምጣትም ችሏል። የለውጡን ትክክለኛነትና ጥንካሬን ለማረጋገጥም በ50 ዓመት ታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ አጋጥሞን፤ ይህ ነው የሚባል የውጭ ድጋፍ ሳይገኝ በራስ አቅም መቋቋም ችለናል። በአሁኑ ወቅትም በሀገራችን የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም መንግስት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው።

ከመጀመሪያው ተሃድሶው ወዲህ ባሉት ዓመታት በከተሞች ውስጥ የኢንዱስትሪ ልማት መሰረቶችን ማስፋፋት መቻሉ ከህዝቡ የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። በተለይም በከተሞች ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የአነስተኛና ጥቃቅን ፕሮግራሞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው።

በከተሞች ያለው የተጠቃሚነት ሁኔታ በተለያዩ ስንክሳሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያህል መጓዝ ባይቻልም፣ ከፕሮግራሞቹ በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደተቻለ ህዝቡ በሚገባ ይገነዘባል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በእነዚህ ዓመታት በከተሞች ውስጥ ሲከናወን የነበረው የአገልግሎት ዘርፍ ተደራሽነትም ዕድገት ማሳየቱ የሚታበይ አይደለም። የእነዚህ ሁሉ ዕድገቶች ድምር መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ ነው። ይህም ወደፊት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ዜጎች ከልማቱ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባለፉት 26 ዓመታት በማህበራዊ መስክ ውጤት የተገኘባቸው ስራዎች መከናወናቸውን የሀገራችን ህዝብ የሚዘነጋቸው አይመስለኝም።

በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረተ-ልማት አቅርቦት ዘርፍ የተከናወኑት ወሳኝ ስራዎች ለዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው። ከእነዚህ ማህበራዊ መስኮች ህዝቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ በአኗኗር ዘይቤው ላይም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ተደርጓል።

እነዚህ ለውጦች የተገኙት ገዥው ፓርቲና እርሱ የሚመራው መንግስት የህዝብን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ በማድረጋቸው ነው። እርግጥ እዚህ ላይ አንድ የማይካድ እውነታ ያለ ይመስለኛል።

ይኸውም ባለፉት 26 ዓመታት የሀገራችን ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ማደጉና በዚያውም ልክ የወጣቱ ሃይል ቁጥር በመጨመሩ የለውጡ ግዝፈት የተጠበቀውን ያህል ሊሆን አለመቻሉ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዜጎችን ላያረካቸውና ስሜት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል። ዜጎች መንግስት እያመጣ ያለውን ለውጥ እያወቁት ቢሆን በመታተል ተገፋፍተው በፀረ ሰላም ሃይሎች አጀንዳ እንዲዋጡ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ቀደም ሲል የነበሩት የተዛቡ አስተሳሰቦች ከሞላ ጎደል በመታረማቸውና መንግስትም ድህነትን ለመቀነስ በወሰዳቸው ሰፋፊ ርምጃዎች ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ የሰላም መኖር ምን ያህል ፋይዳ እንደነበረው ያውቃል።

የሀገራችን ህዝብ በአምባገነኑ የኤርትራ መንግስት የተቃጣበትን ወረራ ፈጥኖ በመመከት፣ ውሰጠ-ድርጅት ህፀፆችን በአስቸኳይ ፈትቶ ፊቱን ወደ ልማት ባይመልስ ኖሮ፤ ያለ ሰላም በጦርነትና በንትርክ ጊዜውን ያጠፋ እንደነበር ግልፅ ይመስለኛል። ይህን ደግሞ ከዚህ ህዝብ በላይ ሊገነዘብ የሚችል አይመስለኝም።

እንዲህ ዓይነቱ ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን እውን ማድረግና ህዝቡም የተጀመረውን የፀረ-ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር። ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር።

አሁን እየከናወነ ያለውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንም ባላለመ ነበር። በዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ ዴሞክራሲው ሀገር በቀል ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት ወሳኝ ነው።

ህዝብ በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳድር ጋር እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዕዋትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ይህ የህዝቡ ስሜት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም። ሰላሙ የሁለንተናው መሰረት መሆኑን ህዝቡ በሚገባ ያውቃል። ከተግባር የበለጠ ትምህርት ቤት ባለመኖሩም፤ ይህ ህዝብ የሰላሙ ዘብ ሆኖ ቆሟል። ሁከቱን ለመቀልበስ በሀገራችን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስፈጻሚው አካል ታውጆ ተግባራዊ ሲሆንም ይህ ህዝብ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል። ለኢትዮጵያዊያን ሰላም ሁለንተናቸው ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy