NEWS

972 የ60/40 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ቅዳሜ ይወጣል

By Admin

July 06, 2017

972 የ60/40 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ቅዳሜ ይወጣል

እጣው የሚወጣው ለ972 ቤቶች፣ 320 የንግድ ቤቶች  ሲሆን  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቤቶቹ ለባለ እድሎች ይተላለፋሉ ተብሏል፡፡

በ40/60 የቤቶች መርሀ ግብር 140 ሺህ ሰዎች እየቆጠቡ ሲሆን በእጣ ውስጥ እንዲካተቱ የተመረጡት ከ18 ወራት በፊት የቤቶቹ ዋጋ ሙሉ በሙሉ የቆጠቡ   መሆናቸው ተገልጿል።

ከሚወጣው እጣ ውስጥ 20 በመቶ ለመንግስት ሰራተኞች፣ 3 በመቶ ደግሞ ለዲያስፖራ ቅድሚያ እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡

ቤቶቹ  በካሬ 5ሺህ 680 ብር ወጪ የተደረገባቸው ቢሆንም መንግስት ባደረገው ድጎማ በካሬ 4918 ብር ዋጋ ተተምኖባቸዋል።

የከተማ አስተዳደሩም በአጠቃላይ 170 ቢሊዮን ብር ለቤቶቹ ግንባታ ድጎማ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በ40/60 የቤቶች መርሀ ግብር ሰው ሲቆጥብ የነበረው ለባለአንድ መኝታ፣ ባለሁለት መኝታ እና ባለሦስት መኝታ ቢሆንም አሁን ባለአራት መኝታ በእጣው እንዲካተት ተደርጓል ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው ባለአንድ መኝታ የሚል እጣ እንደማይኖር የተገለጸ ሲሆን ባለአንድ የቆጠቡ ሰዎች በዚህኛው ዙር ከእጣ አወጣጡ ውጭ ሆነው በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች እንዲካተቱ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በግንባታው የዋጋ ልዩነት የተፈጠረበት ምክንያት ከመዘግየቱ ባሻገር ውል ከተገባው ቤት በስፋትና በጥራት እንዲሁም በውበት መጠበቂያ ልዩነት ስላለው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባለሁለት መኝታ 75 ካሬ ውል ተገብቶ የተገነባው 124 ካሬ ነው የተገነባው፡፡ ባለ3 መኝታ 100 ካሬ ተብሎ የተገነባው 150 ካሬ ሆኖ ተገንብቷል፡፡ ባለአራት መኝታ ውል ውስጥ ባይኖርም 168 ካሬ ሆኖ ተገንብቷል ተብሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ተአምርአየሁ ወንድማገኝ