Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህልም ተስፋችንም መልካም አስተዳደር ሰፍኖ ማየት ነው!

0 300

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህልም ተስፋችንም መልካም አስተዳደር ሰፍኖ ማየት ነው!

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከተዘረጋ ሁለት አሥርት ዓመታት አልፈዋል። በአገሪቱ የተፈጠረው ምቹና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀምም ቁጥራችው ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመሥርተው የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ባለፉት ሃያ ዓመታት በየአምስት ዓመቱ በተካሄዱ አራት ምርጫዎች ላይ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች የነበራቸው ተሳትፎ የጎላ እንደነበር እሙን ነው።

 

ይሁንና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገሪቱ ህገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት የህዝቡን ይሁንታና ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ እንዳሉ ቢታወቅም በተቃራኒው አንዳንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በህጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ስም ህገ መንግሥቱን ሲተላለፉ ይስተዋላሉ። የዜጎችን መብትና እኩልነት ያረጋገጠውና ዜጎች በፈለጉት የፖለቲካ ድርጅት ያለምንም ተጽዕኖ ተደራጅተው እንዲሳተፉ ሙሉ ነጻነታቸውን ያጎናፀፈን የአገሪቱ የበላይ ህግ የሆነው ህገ መንግሥት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመናድ ያለመ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታዝበናል።

 

ህልውናው የፈጠረላቸውንና በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ያስቻላቸውን የአገሪቱን ህገ መንግሥት አክብረው መንቀሳቀስና የፖለቲካ አጀንዳቸውን ወደ ሕዝብ በማስረፅ በምርጫ አሸንፈው ወደ ኃላፊነት መምጣት የሚያስችላቸውን ቀና  መንገድ ከመከተል ይልቅ ይህ ነው የሚባል አጀንዳ ሳይዙና በሕዝቡ መካከል ሁከትና ትርምስን በመፍጠር በግርግር ለመጠቀም አልመው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ህገ መንግሥቱን ሲተላለፉ ይስተዋላሉ

 

በቀደሙት ዓመታት በአገራችን የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያራምዷቸው ሕጋዊነት የጎደላቸው ተግባራት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ጥያቄ ያስነሱ እንደነበሩ ይታወቃል። በተለይም አገራችን የሚታካሂዳቸውን ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጣጣልና ተገቢ ያልሆነና የተዛቡ አስተያየቶችን በመስጠት የአገሪቱን ብሄራዊ  ድህንነት ሊፈታተኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ ውሣኔዎችን በመቃወምና ከአገሪቱ የውጭ ጠላቶች ጋር በማበርና በመተጋገዝ የተሳሳተ መንገድ ሲሄዱ መስተዋላቸው ይታወቃል። የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረት በመናድ የልማታዊ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

 

በገጠር የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረት ለመናድ የተለያዩ ርምጃዎች መወሰዳቸው ይታወቃል። የኢሕአዴግ መንግሥት ሰው በላውን የደርግ መንግሥት ገርስሶ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት በከተማም ሆነ በገጠር ኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የተንሰራፋበትና ልማታዊ አስተሳሰብ የሚባል ነገር ያልነበረበት ሁኔታ ነበር።

 

አርሶ አደሩ በላቡ ሰርቶ ጥሮና ግሮ አኗኗሩን መቀየር የሚችልበትን ሁኔታ በማመቻቸትና የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተከናወነው ተግባር በገጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ዋስትና ለማረጋገጥ የጎላ ድርሻ ተወጥቷል። ይህም ሁኔታ መፈጠሩ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ለመዝጋት ለተደረገው ጥረት አጋዥ ሚና እንደነበረው ለማየት ይቻላል። አርሶ አደሩ በተሰጠው የእርሻ ቦታ ላይ የራሱንና የቤተሰቡን ላብ አፍስሶና በመንግሥት ከሚመደቡ ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት እያገኘ ሰርቶ ከድህነት መላቀቅ የሚቻል መሆኑን በተግባር መገንዘብ በመቻሉ ልማታዊነቱ እያደገ በመጣ ቁጥር በገጠር የኪራይ ሰብሳቢነት መሠረት እየተናደ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

በአሁኑ ወቅት ከእርሶ አደርነት ወደ ኢንቨስትርነት የተቀየሩ አርሶ አደሮች ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በገጠር ሞዴል አርሶ አደሮች ሌላውን እየመሩና በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመሰባሰብ ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተው ልማታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ።  

 

ይህ ደግሞ ለኪራይ ሰብሳቢነት መሠረት መናድ ሌላው ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በዚህ መልክ ልማታዊነት እየተረጋገጠና ኪራይ ሰብሳቢነትን ነቅሎ ለመጣል እየተናነቀ ይገኛል። በከተማም በተመሳሳይ መልኩ የኪራይ ሰብሳቢነትን የበላይነት ለመድፈቅና ልማታዊነትን ለማንገስ ቀላል የማይባል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

 

እንደ መሬት፣ የመንግሥት ግዥ፣ ግብርና ንግድ የመሳሰሉ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋና ምንጭ ተደርገው የሚወሰዱ ዘርፎች ተለይተው በሰፊው እየተሰራበት ይገኛል። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ጥረት እየተደረገ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና ልማታዊነትን ለማጠናከር መልካም አስተዳደር ማስፈን ግድ ነው።

 

መልካም አስተዳደርን ማስፈን የኪራይ ሰብሳቢነትን አንድ መንገድ መዝጋትና የአገሪቱን ልማት ማፋጠን መሆኑን የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግሥት ለመልካም  አስተዳደር መስፈን የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ሆኖም ግን መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር የአንድ ጀምበር ተግባር አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል።  

 

ጊዜን የሚጠይቅና በሂደቶች የሚከወን እንደሆነ ይታወቃል። በአገሪቱ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ዕድገት የሚወሰነውንና በየጊዜው መሻሻል እያሳየ የሚገኘውን የመልካም አስተዳደር ክንዋኔን በአንድ ጀምበር እንዲጠናቀቅ የሚፈልጉ አንዳንድ ወገኖች በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር የለም እያሉ በተደጋጋሚ ከማስተጋባትም ባሻገር  በየጊዜው የተለያዩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በማምጣትና በአገሪቱ የተረጋገጠውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማያግዝና ለማጠናከር በማይጠቅም መልክ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።

 

የመልካም  አስተዳደር ጉዳይ እነሱ ስለዘመሩ ሳይሆን መንግሥት በአገሪቱ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር ልማታዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሚኖረው ሚናና የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ አንጻር ቀዳሚ አጀንዳውን አድርጎ የያዘው ጉዳይ በመሆኑ ነው። መልካም አስተዳደር የህልውና ጉዳይ ነው። ምክንያቱም መልካም አስተዳደርን  ማስፈን ካልተቻላ ኪራይ ሰብሳቢነትን ደፍቆ ልማታዊነትን ማረጋገጥ የራሱ አሉታዊ  ተጽዕኖ ስላለው ነው።

መልካም አስተዳደር በማስፈን ከፊት ለፊታችን የተጋረጠውን ኪራይ ሰብሳቢነት ለበርካታ አገራት የልማት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ሥርዓት የደረጀ ማህበራዊፍራ እንዳይዝና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዳይረጋገጥ አፍራሽ ሚና የሚጫወት ክስተት መሆኑን የተገነዘቡ የለውጥ ኃይሎች ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ትግል የገጠሙበትም ጊዜ ሩቅ መሆኑን የሚያመለክቱ ዓለም አቀፍ መረጃዎች ብዙ ናቸው፡፡

እንደ አገራቱ ደረጃና ባህሪይ የመጠን ልዩነት ቢያሳይም በአሁኑ ወቅት በተለያየ የዓለማችን ማዕዘን የድህነት ሥር እንዳይነቀልና ማህበራዊ ዕድገት የሚፈለገውን ያህል እንዳይፋጠን እንቅፋት ሆኖ መገኘቱ ግልጽ ነው፡፡ ከዚሁ የተነሳ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ህግጋትን እየደነገገና የመዋጊያ ሥልቶችን እየቀየሰ በጋራና በተናጥል የመንቀሳቀስ ብርታት የጨመረበት ጊዜ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ የሰመረ ጉዞ ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያም ኪራይ ሰብሳቢነት ሥጋት አይደለም ብሎ መከራከርና ማድበሰበስ የሚቻል አይሆንም፡፡ አገሪቱ ያላትን ውስን ጥሪት፣ ሰፊ ተፈጥሮ ሀብትና ማሣ የህዝቦቷን የመሥራት አቅም ተጠቅማ ከዘመናት ድህነት ለመውጣት የጀመረችውን ፈጣን የልማት ሩጫ በሥውር ገመድ ጠልፎ በግልጽ የሚጥል የዕድገት ጋሬጣ ስለሆነ አምርራ እየታገለችው ትገኛለች፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት በዘላቂ ዴሞክራሲና በልማት አስተሳሰብ ንቅናቄ ውስጥ ገብተው በህዳሴ ጉዞ ላይ የሚገኙ ህዝቦችን ጥረት ለማምከን የሚፈታተን ጥርኝ የማይሞሉ ጮሌዎች ተሠሰርቶ ባልተገኘ ሀብት እንዲሞላቀቁና ብዙሃን በድህነት ታጅለው እንዲቆዩ የሚደረግ አስተሳሰብና ድርጊት ስለሆነ የማስወገዱ ጉዳይ ይዋል ይደር የሚባል አይሆንም፡፡

ዛሬ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥታችን በላቀ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መላው ህዝባችንን ለልማት እያነቃነቀ ሙሉ ተሳታፊነቱንና ጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እየሰራ የሚገኝበት አፍላ ለውጥ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አገራዊ የህዳሴ ጉዟችን ለሰመረ ህዝባዊ ስኬት እየበቃ የሚዘልቀው፣ የልማትና የለውጥ ግለት ፍጥነቱን እየጨመረ ድህነትን የተሻገረ አገርና ትውልድ መኖሩን ለማረጋገጥ የሚቻለው ሲቪል ሰርቨሱ በሚወጣው ኃላፊነት ልክ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡

ሲቪል ሰርቪሱ የኪራይ ሰብሳቢነትና ድርጊት በመፀየፍና በመዋጋት መልካም አስተዳደርን በማስፈን የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ በአገርና በህዝብ ላይ ፈጣን ለውጥ እያመጣና ድህነትን ወደ ኋላ እየተወ መራመድ ያስችላል የሚል የፀና እምነት በመያዝና በዕለት ከዕለት ተግባር በመግለጽ የልማት ሠራዊት ቁመና ፈጥኖ በመያዝ የለውጥን መንገድ የሚመራ ኮምፓስ ሆኖ መገኘት ግድ ይለዋል፡፡

ይህ ደግሞ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የልማት ጊዜው ያቀረበው የለውጥ ጥሪ ነው፡፡ ወደ ድህነትና ኋላ ቀርነት አረንቋ ዞሮ መመለስ ምርጫ ይሆናል ተብሎ ስለማይታሰብ የልማትርምጃን ማፋጠን ይጠበቃል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ደግሞ የልማት እርምጃን የሚያደናቅፍ እንቅፋት ስለሆነ እየተፈናቀለ በየመንገዱ ዳርቻ ሊጣል ይገባል፡፡የኪራይ ሰብሳቢነት አረም እየተነቀለ በምትኩ መልካም አስተዳደርን በማስፈን አገርን ለማልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ማብቃት ነው፡፡

መልካም አስተዳደር ሰፍኖ ኪራይ ሰብሳቢነት እስካልተወገደ ድረስ የቱንም ያህል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አገራዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት አጢነው የህዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት አልመው የተዘጋጁ ወርቃማ ህግጋት፣ የልማት ፖሊሲዎችና የዕድገት ስትራቴጂዎች ቢወጡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ እናም ኪራይ ሰብሳቢነትን የማስወገድና መልካም አስተዳደርን መገንባት ይዋል ይደር ሊባል የሚችል ተግባር አይደለም፡፡

በዚህ ረገድ እንደ ተቋም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው የሚባሉትን የአመለካከትም ሆነ የተግባር ደረጃ በደረጃ በመለየት ለመፍታት ከምንጊዜውም የተሻለ የሥራ ግምገማ በማካሄድ ራሳችንን በጥልቀት በማየት፣ የለውጥ አመለካከት በማስረጽ፣ መልካም አስተዳደርን በማረጋገጥ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን በመድፈን የተጀመረውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማሳካት የአገሪቱ ህዳሴ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ከወዲሁ በእልህና በቁጭት የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተሰነዘረ ያለውን ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ታርሞ በቀጣይ በአገሪቱ ሠላም ሰፍኖና መልካም አስተዳደር ተረጋግጦ ማየት ነው፡፡ ህልም ተስፋችንም ይኸው ነውና!  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy