ህዝብ ያልተቀበለውን ጫካ አይሸሽገውም
ብ. ነጋሽ
ኢትዮጵያ ከ1980ዎቹ ማገባደጃ ጀምሮ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ሰለባ ሆና ቆይታለች። የሽብር ጥቃቶቹ ንጹሃን ዜጎችን ዒላማ ያደረጉ ነበሩ። ጥቃቶቹ የተሰነዘሩት ሰላማዊ ዜጎች የሚሰበሰቡባቸው ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ጎዳናዎች ወዘተ ነበሩ። እስከ 2000 ዓ/ም ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በመቶ የሚቆጠሩ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን በሽብር ድርጊት ህይወታቸውን አጥተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋሚ የአካል ጉዳት አደጋ ደርሶባቸዋል። በሽብር ጥቃቶቹ፣ ህጻናት ያለአሳዳጊና ተንከባካቢ ወላጅ ቀርተዋል። አዛውንት ጧሪ አጥተዋል። ሰርተው ማደርና ሌሎችን መደገፍ ይችሉ የነበሩ ዜጎች የአካል ጉዳተኞች ሆነው ቤት ውለዋል። እርግጥ የተፈጸሙትንና ጉዳት ያደረሱትን የሽብር ጥቃቶች ያህል ማክሸፍ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ላይ የሽብር ጥቃት የሚፈጽሙት፣ በይፋ የሽብር ጥቃት አውጀው የሚንቀሳቀሱ በውጭ ሃገራት ያሸመቁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያደራጇቸው ቡድኖች ናቸው። ኢትዮጵያን የሽብር ጥቃት ዒላማ ያደረጉ የውጭ አሸባሪዎችም አሉ። በኢትዮጵያውያንና በትውልደ ኢትዮጵያውያን የተደራጁት፣ አብዛኞቹ ኢትዮጵያን መቆጣጣር ይህ ካልሆነ ዳግም ሃገር ልትሆን በማትችልበት ሁኔታ የማፈራረስ ስትራቴጂ ነድፎ የሚንቀሳቀሰው የኤርትራ መንግስት ስር የተሸሸጉ ናቸው። ዋና ማዘዣቸው፣ ገንዘብ ማሰባሰቢያቸውና የመሪዎቹ መኖሪያ ግን አሜሪካና እንግሊዝ ነው። ግብጽ ውስጥ ያሸመቁም አሉ። ከውጭዎቹ አሸባሪዎች መሃከል አልሸባብ የተሰኘው ተጠቃሽ ነው። አልቃይዳ የተሰኘው ዓለም አቀፍ አሸባሪም የኢትዮጵያ ስጋት ነው።
በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከተደራጁት አሸባሪዎች መሃከል ቀደምቱ አሁን በተለያዩ ቡድኖች የተከፋፈለው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው። በኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ስለተተፋ አሁን አሁን ብዙም ድምጹ የማይሰማው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) የተሰኘው ቡድንም ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃት ካደረሱት አሸባሪዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
ከ2000 ዓ/ም በኋላ ደግሞ ራሱን ግንቦት 7 ብሎ የሚጠራው ቡድን በይፋ ኢትዮጵያ ላይ የሽብር ጥቃት አውጆ በአሜሪካ በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ተመዝግቦ መንቀሳቀስ ጀምሯል።
ይህ በአሜሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት ነኝ ብሎ የተደራጀ ቡድን ሽብርተኞችን የሚያሰለጥነውና የሚያሰማራው ልክ እንደቀደምቶቹ ኦነግና ኦብነግ ምስራቅ አፍሪካን ለማተራመስ በሚፈጽማቸው ድርጊቶች በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ከተጣለባት የኤትርትራ መንግስት ጋር በመተባባር ነው። መሪዎቹም ልክ እንደ ኦነግና ኦብነግ የምእራባውያን ሃገራት በተለይ የአሜሪካና እንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ናቸው። ዜግነት የሰጧቸው ሃገራት ህግ፣ ካለመንግስታቸው ውሳኔ በሌሎች ሃገራት ጉዳይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የማይፈቅድ ቢሆንም፣ በይፋ ብረት ታጥቀው፣ የወታደር መለዮ ለብሰው ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በኤርትራ ዱሮች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ዜግነት የሰጧቸው መንግስታት ይህን እያወቁ ዝምታን የመረጡበት ምክንያት ለብዙ ኢትዮጵያውያን እንቆቅልሽ ነው። ከሁሉም የሚያስገርመው፣ በይፋ ገንዘብ እያሰባሰቡ መሳሪያ ገዝተው ከኤርትራ መንግስት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ላይ የሽብርና የሽምቅ ጥቃት ለመሰንዘር ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች እንዲፈቱ የሚጠይቁበት ሁኔታ መኖሩ ነው።
ግንቦት 7 የተባለው አሸባሪ በአቅም እጅግ ደካማ ቢሆንም፣ ከኤርትራ መንግስት ማስታወቂያ ሚኒስቴር በሚሰጠው የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫና ሆርን ቲቪ በተሰኘ የኤርትራ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሚያሰራጨው የሽብር ፕሮፓጋንዳ ከሌሎቹ ለየት ብሎ ስሙ ጎልቷል። በዚህ ምክንያት ከኤርትራ መንግስት ጋር ተባብሮ በመንቀሳቀስ በእድሜ የሚቀድሙትንም በስሩ ማሰለፍ ችሏል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን። ከእነዚህ በተጨማሪ ስማቸው ያልገነነ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የተሰኘውን አይነት በኤርትራ መንግስት የተደራጁ በርካታ ደቃቅ ቡድኖች አሉ።
የኢፌዴሪ መንግስት አሸባሪዎቹ በይፋ የሽብር ጥቃት ማወጃቸውን፣ ይህን ለማስፈጸም የሚያደርጉትን ተጨባጭ እንቅስቃሴና አንዳንዶቹም በተጨባጭ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙትን የሽብር ጥቃት መነሻ በማድረግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ አድርጓል። በዚህም ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት 7፣ አልሸባብና አልቀይዳ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጀዋል።
እርግጥ የሽብር ጥቃት የመፈጸም ዓላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሆነው በሽብርተኝነት ያልተፈረጁ ጥቃቅን ቡድኖች አሉ። ብዙዎቹ በአሸባሪነት የተፈረጁት ላይ ተለጥፈው የሚንቀሳቀሱ ስማቸው የማይታወቅ ናቸው።
የሽብር ድርጊት ዒላማ የሚያደረገው የአንድን ሃገር የመከላከያ ወይም የጸጥታ ሃይል አይደለም። የሽብር ድርጊት ዒላማ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው፤ አዛውንት፣ እናቶችና አባቶች፣ ወጣቶች፣ ህጻናት ወዘተ፤ የውጭ ሃገር ቱሪስቶችም እንዲሁ ዒላማዎች ናቸው። የጥቃቱን ዜና ዓለም አቀፍ ሽፋን እንዲያገኝ ስለሚያግዙ ቱሪስቶች አሸባሪዎችን በተለየ ሁኔታ ያስጎመዣሉ። የአሸባሪዎች የጥቃት ስኬት የሚለካው፣ የመከላከያ ወይም የፖሊስ ሰራዊት ሃይል ላይ ባደረሱት ጉዳት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ባደረሱት ጉዳትና በደረሰው ጉዳት ዘግናኘነት መጠን ነው። ለአሸባሪዎችች አስር የመከላከያ ሃይል ወይም የፖሊስ ሰራዊት አባል ከመገድል አንድ ሰላማዊ ዜጋን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል የበለጠ ስኬታማ ተደርጎ ይወሰዳል።
ይህ የሆነው ህዝብ በማንኛውም ስፍራና ሰአት ሊፈጸምበት የሚችለውን ዘግናኝ የሽብር ጥቃት በመፍራት የአሸባሪዎችን ትእዛዝ እንዲፈጽም፣ በውክልና ስልጣን የሰጠው መንግስት የአሸባሪዎቹን ጥያቄ እንዲያከብር ጫና እንዲያሳድር ማድረግ ይችላል በሚል እሳቤ ነው። በሌላ በኩል የእያንዳንዱን ሰው ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት የተጣለበት መንግስት በንጹሃን ዜጎቹ ላይ የሚፈጸም ዘግናኝ የሽብር ጥቃትን ለማስቀረት የአሸባሪዎቹን ፍላጎቶች እንዲያሟላ የሚያስገድድ አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ነው።
ከላይ የተገለጸውን ዓላማና ስልት ይዞ የሚፈጸም የሽብር ጥቃት በመከላከል ረገድ በኢትዮጵያ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ማለት ይቻላል። ሽብርተኝነትን የመከላከል ተግባር ውጤታማ እንዲሆን ያስቻለው ዋነኛ ምክንያት ህዝቡ ውስጡ የሚደበቁትን አሸባሪዎች አጋልጦ በመስጠት በጸረሽብርተኝነት ትግሉ በመሳተፉ ነው። እርግጥ በ2001 ዓ/ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የፀረሽብርተኝነት ህግ የሽብር ጥቃትን አስቀድሞ በመከላከልና ከተፈጸመም በኋላ አጥፊዎቹ ሳያመልጡ በህግ ስር ውለው እንዲቀጡ የማድረጉን ተግባር ውጤታማ እንዲሆን አግዟል። ህጉ ከጸደቀ በኋላ የሽብርተኝነት ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።
ከኤርትራ መንግስት ጋር በመተባበር ንጹሃን ኢትዮጵያውያንን ዒላማ ያደረገ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ያለሙ ቡድኖች ከ2000 ዓ/ም በኋላ የሽብር ጥቃት መፈጸም አልተሳካላቸውም። ከዚያ ይልቅ የልማት ጥያቄያቸው ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ፣ በስራ እድል እጦት፣ በመልካም አስተዳደር መጓደል ወዘተ በመንግስት ላይ ቅሬታ ያደረባቸው ዜጎች በተለይ ወጣቶች ያነሱትን ተቃውሞ በመጥለፍ ሁከት የመቀስቀስ አካሄድ ላይ በርትተዋል። ለአሸባሪዎቹ ቡድኖች ይህን መልካም አጋጣሚ የፈጠረላቸው ግን የመንግስት ድክመት መሆኑ አይካድም። አሸባሪዎች ባለፈው ዓመት በማህበራዊ ሚዲያ በመታገዝ የቀሰቀሱት አውዳሚ ሁከት የዚህ ውጤት ነው።
አሸባሪዎቹ የቀሰቀሱት ሁከት በመደበኛ ህግን የማስከበር ስርአት መቆጣጣር የማይቻልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበረ ይታወሳል። እናም በመደበኛ ህግ የማስከበር ስርአት መቆጣጠር ያልተቻለውን ሁከት በመቀልበስ፣ በመደበኛ የህግ ስርአት መቆጣጣር የሚቻልበትን ሁኔታ ለማስፈን፣ ከመስከረም እስከ ሃምሌ 2009 ዓ/ም ለአስር ወራት ስራ ላይ የቆየ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አውጇል። ከዚህ ጎን ለጎን የመልካም አስተዳደር መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ ለመወሰድ ተሞክሯል። በማወቅም ይሁን በአቅም እጦት የመልካም አስተዳደር መንስኤ መሆናቸው በተጨባጭ የተረጋገጠ ከፌደራልና ከክልል መንግስታት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮች ከሃላፊነታቸው ተነስተው በሌሎች እንዲተኩ ተደርጓል። በዞን፣ በወረዳና በከተሞች አስተዳደሮች አዲስ የተመደቡ አመራሮች በህዝብ ተገምግመው ይሁንታ ያገኙ ብቻ እንዲሆኑ ተደርጓል። በተለያየ መክንያት የተጓተቱና የተቋረጡ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደአገልግሎት እንዲገቡ ለማስቻል ጥረት ተደርጓል። እርግጥ በዚሀ ረገድ አሁንም የሚፈለገውን ያህል የህዝብ እርካታ መፈጠር አልተቻለም።
መንግስት የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አዲስ የወጣቶች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፓኬጅ አዘጋጅቷል። በተለይ የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ለስራ ፈጣሪ ወጣቶች በብድር የሚሰጥ የ10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቧል። ተዘዋዋሪ ፈንዱን በመጠቀም ረገድ በአብዛኛው ውጤታማ ተግባር ባይከናወንም አጠቃላይ እቅዱ ግን በወጣቶች ዘንድ ተስፋ ፈጥሯል።
እነዚህ ሁኔታዎች ኤርትራ ያሸመቁ የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚ ቡድኖች ባለፈው ዓመት ቀስቅሰውት በነበረው አይነት ሁከት መቀስቀስ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። በዚህ ዓመት የተካሄደውን የነጋዴዎች የዕለት ገቢ ግምት መነሻ በማድረግ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ሁከት ለመቀስቀስ ያደረጉትም ሙከራ አልተሳካም። ተስፋ አድርገው የነበረው የጎንደር ነጋዴ በአዲሱ የገቢ ግምት መሰረት የተወሰነለትን ግብር እየከፈለ ነው። በጎንደር ከተማ በተካሄደ የቀን ገቢ ግምት ጥናት መሰረት የግብር ውሳኔ ከደረሳቸው 7 ሺህ 939 የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች መካከል ይህ ጽሁፍ እስከተዘጋጀበት ድረስ ከ7 ሺህ በላይ ወይም 90 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ግብራቸውን ከፍለዋል። እናም የኤርትራ ተላላኪዎቹ አሜሪካውያንና እንግሊዛውያን ሊቀሰቅሱት አስበውት የነበረው ሁከት አልተሳካም።
በተለይ በባህርዳር ከተማ ዝክረ ነሃሴ 2008 በሚል የተቀሰቀሰው አድማ እንደታሰበው የጎላ ተጽእኖ ሳያሳርፍ ከሽፏል። እርግጥ በተለይ ነጋዴዎች መደብሮቻቻውንና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶቻቸውን እንዲዘጉ በተካሄደ ማስፈራራት በተወሰነ ደረጃ የንግድ ተቋማት የተዘጉበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም። ይህ ግን አሸባሪዎቹ ያሰማሯቸው የሁከት አስፈጻሚ ቅጥረኞች ባካሄዱት ማስፈራራት እንጂ በህዝቡ ወይም በነጋዴው ፍቃደኝነት የተካሄደ አይደለም። ጥቂት በፍቃዳቸው ድርጅታቸውን የዘጉ፣ ተሳስተውም ይሁን አውቀው የአሸባሪ ቡድኖች ዓላማ የሚጋሩ መኖራቸው ግን አይካድም።
ህዝቡን በቀላሉ ለአድማና ሁከት ማነሳሳት ያቃታቸው የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች ወደለየለት የሽብር ጥቃት የመሸጋጋር አዝማሚያ እያሳዩ ነው። ነሃሴ 6፣ 2009 ዓ/ም ምሽት ሁለት ሰአት ገደማ በባህር ዳር ከተማ ተጥሎ ለሁለት ንጹሃን ዜጎች ጉዳት ምክንያት የሆነው ጥቃት የዚህ ማሳያ ነው።
በጽሁፉ መገቢያ ላይ እንደተመለከተው የጥቃቱ ዓላማ፣ ንጹሃን የከተማዋንና የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስፈራራት የአሸባሪዎቹን ትእዛዝ እንዲፈጽሙ ማድረግ ነው። የሚፈጸመው የሽብር ጥቃት በተደጋገመና ጉዳት እያደረሰ በሄደ ቁጥር፣ ህዝብ ፍርሃት ስለሚያድርበት ከቤት አትውጣ፣ ስራ አትሂድ፣ መደብርህን አትክፈት ወዘተ በሚል የሚያስተላልፉትን ትእዛዝ ለመቀበል የሚገደድበትን ሁኔታ ይፈጥራል። በጎንደር ከተማም ተመሳሳይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ የነበሩና አድማ ለመቀስቀስ ሲራወጡ የነበሩ የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከክልሉ መንግስት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ሐምሌ 23፣ 2009 እና ነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች የቦምብ ጥቃት ለመፈፀም በሂደት ላይ የነበሩ 4 ተጠርጣሪዎች በፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል። ሐምሌ 30፣ 2009 ዓ/ም በመንገድ ላይ ቦምብ ያፈነዱ ሦስት በዋና የድርጊቱ ተሳታፊነት ሁለት በተባባሪነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ወለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ይገኛል። በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ ብጥብጥና የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ሲቀሰቅሱ የነበሩ ሶስት ግለሰቦች እንዲሁም ለአድማ የሚያነሳሳ መልዕክት የያዘ ወረቀት ሲበትኑ የነበሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በተጨማሪም የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ከታጠቁት ቦብም ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል። ነሃሴ 6 ቀን 2009 ዓ/ም ምሽት በባህር ዳር ከተማ ቦምብ ወርውረው ለሁለት ሰዎች ጉዳት ምክንያት ሆነዋል የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
እነዚህ እውነታዎች የጸጥታ ሃይሉ በተለመደው ህግ የማስከበር ስርአት ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ መቻሉን ያመለክታሉ። ህዝቡ በአሸባሪዎቹ ተወናብዶና ፈርቶ የሁከት ፈጻሚያቸው ለመሆን ፍቃደኛ አለመሆኑንም ያመለክታሉ። የአሸባሪዎቹ ሁከት የመፍጠር ዓላማ እንዳይሳካ፣ ሁከት ለመፍጠር የተደረገ ሙከራም እንዲከሽፍና የሁከት መሪዎቹና ፈጻሚዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ህዝቡ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑ ግልጽ ነው። ያለህዝብ ትብብር ጸጥታ አስከባሪ ሃይሉ በራሱ አቅም ብዙም ስኬታማ ስራ ማከናወን አይችልም። የአሸባሪዎች መደበቂያ ህዝብ ነው፤ ህዝብ ካልሸሸጋቸው ህልውና አይኖራቸውም። ህዝብ ያልተቀበለውን አሸባሪ ጫካ ሊደብቀው አይችልም። በሰሜናዊ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሰሞኑን የምንመለከተው ይህን እውነት ነው።