Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ ግንባታ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም

0 591

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ ግንባታ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም

                                                                                        ፈቃዱ ውበቴ

አለሚቱ አየለ የባሕር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኛና የሶስት ልጆች እናት ናት፡፡ፋብሪካው በአንድ ቀን  ውስጥ ሶስት የምርት ፈረቃ ያለው ሲሆን እሷ የማታ ፈረቃ ሰራተኛ ናት:: እንደአለሚቱ ገለጻ በአሁኑ ወቅት የፋብሪካው የምርት ሂደት አብዛኛው በዘመናዊ ማሽኖች የሚከናወን በመሆኑ በፊት የነበረውን የሰራተኛ ልፋትና እንግልት በእጅጉ ለማስቀረት አስችሏል፡፡

ይሁንና እሷ ከመቀጠሯ በፊት ሰራተኛ የነበሩ ጡረተኛ  ጎረቤቷ እንደተረኩላት የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የምርት ሂደት ስራ ሲጀምር የነበረው ሁኔታ እንደአሁኑ ቀላል አልነበረም፡፡ፋብሪካው በተተከለበት ዘመን የማምረቻ ክፍሎች በእጅ የሚዘወሩና ኋላቀር በመሆናቸው ምክንያት የፈትል፣የሽመናና የመደወሪያ ወዘተ ክፍል ውስጥ የነበሩት ማሽኖች ቦታቸውን ጥለው የሚወረወሩና የታለመላቸውን ቦታ በመሳት የሰራተኞችን እጅ የሚቆርጡና አካለጎደሎ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የፋብሪካው አመራረት ስልት ከግብዓት ማቅረብ እስከ ማሸግ ድረስ ያለው አሰራር እጅግ ዘመናዊ ነው፡፡ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና እያንዳንዱ ማሽን  በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ አለሚቱም ሆነ ጓደኞቿ በተሰማሩበት ክፍል ውስጥ ያላቸው የስራ ድርሻ ቁልፎችን በመጫን የሚጠናቀቅና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የማሽኑን የስራ ሂደት በመቆጣጠር የሚከናወን ነው፡፡

እንደ አለሚቱ ገለጻ የአመራረት ስልት በእጅጉ ይለያል፡፡እሷ ስትቀጠር የነበሩት የተወሰኑ ማሽኖች የተወሰነ የሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው፣ሰው ጉልበቱን አፍስሶና ተረባርቦ የሚያስነሳቸው፣የምርት ግብዓት የሚያቀርብላቸው እንዲሁም ያመረቱትን ምርት ተከታትሎ የሚያሽግላቸው ነበሩ፡፡

አሁን ግን ይሄ ሁሉ እንግልት የለም፡፡በእያንዳንዱ የስራ ክፍል የተተከሉት ማሽኖች ዘመናዊ በመሆናቸው የሚያጋጥማቸውን ብልሽትና ችግር ራሳቸው ለሰራተኞችና ለጠጋኝ ባለሞያዎች የሚጠቁሙ ናቸው፡፡አሁን ማሽኖቹ የሚያበሩትን መብራት በማየት ብቻ ያሉበትን ሁኔታ መረዳትና ያጋጠማቸውን ችግር ማወቅ ይቻላል፡፡ሌላው ቀርቶ ክር ሲበጠስ ራሳቸው የሚጠቁሙና ማስተካካያ እንዲደረግ ምልክት የሚሰጡ ናቸው፡፡

ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር በተያያዘ አገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጉዞ  ለማስቀጠልና ለማፋጠን ብሎም ወደሚፈለገው ኢንዱስትሪ-መር የኢኮኖሚ ስልት እንድትሸጋገር ለማድረግ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ያስተዋወቁትን አስተሳሰብና አሰራር እንዲሁም ልማታዊ ተግባራት ወጣቱ ትውልድ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ብዙ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ የልማትን ታላቅ ዓላማ ከዳር ለማድረስ ከተፈለገ ዜጎች የታላቁን  መሪ መለስ ዜናዊ የፅናት ፈለግ መከተልና የቀየሷቸውን የኢንዱስትሪ-መር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ነሀሴ 14/2009 በተከበረው የመለስ ዜናዊ መታሰቢያ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገልጸዋል፡፡

 ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት ታላቁ መሪ መለስ ለአገሪቷ ዲሞክራሲን፣ልማትንና ብልፅግናን ለማምጣት ያስቻሉ አስተሳሰቦችን ያፈለቁ ናቸው።ስለሆነም ወጣቱ ትውልድ ይህንን አስተሳሰብ በመላበስ የመለስን ስኬቶች ማስቀጠል ይጠበቅበታል።የታላቁ መሪ አስተሳሰብ የኢንዱስትሪ ልማትን በፍጥነት በማቀጣጠል አገሪቱን ከድህነት አረንቋ ማውጣት በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ይህንን ወሳኝ መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ለአገር ልማት ያልተገደበ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ስለኢንዱስትሪ ልማት ሲነሳ ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ በአውሮፓ የተከሰተው ዘመነ አብርሆት ወይም ዘመነ ሕዳሴ ለአውሮፓ ቀዳሚ የዕድገት ግስጋሴ በር ከፋች ሆኗል፡፡ይህ ክስተት ሰዎች የጭንቅላትና የመንፈስ ተሃድሶ በማድረግ፣በአዲስ ዕውቀት በመመራት እንዲሁም የማሰብ ኃይላቸውን በመጠቀም የልማት ታሪክ ባላቤት እንዲሆኑ ፈር ቀዳጅ ሆኗል። ይህም የአውሮፓው የማኑፋክቸሪንግና ካፒታሊዝም ዕድገት ካለዘመነ አብርሆት ወይም ዘመነ ተሃድሶ መሰረትነት በፍጹም ሊታስብ የሚችል አለመሆኑን ያሳያል፡፡ይህ አዲስ  ሁኔታ ለከተማዎች ዕድገት፣ ለዕደ-ጥበብ ማበብና ለንግድ መስፋፋት እንዲሁም ለካፒታልና ለቁሳዊ ሃብት ክምችት መንገድ ጠራጊ ሆኗል።

የጨርቃጨርቅ አመራረትን ጨምሮ ዓለማችን ከ18ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ሶስት ዓይነት አብዮቶችን አካሂዳለች-የብሪታኒካ አውደ ጥበብ እንደሚያስረዳው፡፡የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ አብዮት በብሪታንያ በ1700ዎቹ መጨረሻ ዓመታት ጀምሮ የተቀጣጠለ ሲሆን ይህ አብዮት  በዕድገት ላይ ዕድገት፣በምርት ላይ ምርት እየጨመረና የሰዎችን ኑሮና ገቢ እያሻሻለ በመምጣት ወጋገኑን እስከ 18ኛውና 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመናት ድረስ ሊያዘልቅ ችሏል፡፡

የኢንዱስትሪ  አብዮት በዋናነት በግብርናና በኋላ ቀር አመራረት ስልት ሲንገዳገዱ የነበሩትን ማህበረሰቦችና አገራት ወደ ፍጹም ትርፍና የተትረፈረፈ  ምርት አምራችነት ለውጧቸዋል፡፡ይህም በየቤቱ በቀላል መንገድ በእጅና ቀላል የዕደ-ጥበብ መሳሪያዎች እንዲሁም የሽመና፣መደወሪያ፣ማጠንጠኛ፣መፍተያ፣ማንቀሳቀሻ ሽብልቅ ወዘተ ይሰሩ የነበሩትንና ከእጅ አይሻል ዶማ-ያረጁና ያፈጁ፣ጉልበት ፈጅና አሰልች አሰራሮችን በእጅጉ በመቀየር በውሃ፣ በንፋስና በእንፋሎት ጉልበት በሚገፋ ሞተሮች አማካኝነት በጥቂት የጊዜና የጉልበት ግብዓት አማካኝነት ብዙ ምርት ለማምረት ያስቻለ ነው፡፡

ሁለተኛው አብዮት የግብርና አብዮት የተካሄደበት ዘመን ነው፡፡ይህ ዘመን ኋላቀር የነበረውን የግብርና ስራና አመራረት ፍጹም ዘመናዊ ወደሆነ አሰራር የቀየረ ነው:: በዚህ ዘመን ለምግብ ፍጆታ የሚሆኑ አትክልት፣ፍራፍሬና ሰብሎችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ከማስቻሉም በላይ የኢንዱስትሪ ግብዓት የሆኑ ሰብሎችን ማለትም ጥጥ፣ የቅባት እህሎች፣በቆሎና ስንዴ ወዘተ በብዛት በማምረት ለፋብሪካዎች ለማቅረብ አስችሏል፡፡በተለይም የግብርና አብዮት ምርትን በብዛት በማምረት ለማትረፍረፍ እንዲሁም ሰዎችና እንስሳት ከዚያ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ይደርስባቸው የነበረውን የርሃብ አደጋ ለማስቀረት የቻለ ትልቅ አብዮት ነው፡፡

የመጨረሻው አብዮት የመረጃ ቴክኖሎጂና የኢንተርኔት አብዮት ነው፡፡ይህ አብዮት ኣለምን ወደ አንድ መንደርነት ለመቀየር ያስቻለና ከአንዱ የአለም ጥግ የተደረጉ ድርጊቶችና የታዩ ክስተቶች እንዲሁም እነዚህን የተመለከቱ መረጃዎች በፍጥነት ወደ ሌላኛው የዓለም ክፍል እንዲዳረሱ ያስቻለ ነው፡፡ይህ ስልክን፣ቴሌቪዥን፣ኢንተርኔትና ቪዲዮ ወዘተ የመሳሰሉ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች በመጠቀም ብዛት ያለው መረጃን ሩቅ ላሉ ሚሊዮን ተጠቃሚዎችና ተመልካቾች በቅፅበት ለማዳረስ ያስቻለ አብዮት ነው፡፡ይህ አብዮት መረጃን ብቻ ሳይሆን በርቀት ህክምና (ቴሌ  ሚዲሲን) አማካኝነት የህክምና አገልግሎትን ጭምር በርቀት ላሉ ታካሚዎች ለማዳረስ ያስቻለ አብዮትነው፡፡

በዚህ አብዮት ብዙ የአውሮፓና አሜሪካ አገራት ወደፊት ልቀው ለመጓዝ ችለዋል፡፡ይሁንና በዚህ  በሶስተኛው አብዮት እንኳን አፍሪካ ተሳታፊ አይደለችም፡አፍሪካ ከለውጡ ጋር ለመጓዝ ስላልቻለች የባህል ወረራና የግሎባላይዜሽን ተጠቂ እንዲሁም የርካሽ ሸቀጥ ማራገፊያ ሆናለች፡፡እናም አንዳንድ የቴክኖሎጂ ተንታኞች  አፍሪካ በፍጥነት ራሷን ካለው ለውጥ ጋር ማዛመድ ካልቻለች ከዚህ በፊት ከነበሩት አብዮቶች በባሰ ሁኔታ እንደምትወርድ  እየገለፁ ይገኛሉ፡፡  

የኢንዱስትሪ  አብዮት ከተጀመረ ሁለት ክፍለ ዘመናት ያለፉ ቢሆንም አፍሪካ ለራሷ የሚሆኑ ምርቶችን ከማምረት ይልቅ   አሁንም የአውሮፓና የአሜሪካ የኢንዱስሪ ምርቶችን በማስገባት ስራ ላይ ተወጥራ ትገኛለች፡፡ አሁንም ድረስ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ለራሷ እንዳትገነባ እግር ከወርች ተተብትባና ተደንግራ ለሌላው ዓለም ፍንትው ያለ ብርሃን በበራበት በአሁኑ ዘመን እንኳን አፍሪካ በጨለማ ዘመን ውስጥ እየዳከረች ትገኛለች፡፡ የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ለዘመናት ባለመሻሻሉ ምክንያት የአፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ አቅም እና የህዝባቸው አጠቃላይ የኑሮ ደረጃ ምንም መሻሻል አላሳየም።

የኢንዱስትሪ አብዮት በአፍሪካ ያደረገው ጉዞ እጅግ ቀርፋፋ ከመሆኑም በላይ ምንም ከሚባል ደረጃ ላይ የደረሰ ነው፡፡ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት የኢንዱስትሪ አብዮት ዜና ከተሰማበት ከ1860ዎቹ ዓመታት መባቻ ጀምሮ ያደረጉት ልማትና መሻሻል የለም ከሚባልበት ደረጃ ላይ የደረሰ ነው፡፡አለ ከተባለም የአውሮፓ አገሮች የሰሯቸውን ሞተሮችና ማሽኖች አስገብቶ መጠቀም ነው፡፡ማሽኖችና ፋብሪካዎች ስራ ላይ የዋሉት ያለምንም ለውጥና ማሻሻል ነው፡፡ለዚህም አስረጂ የሚሆነው የገቡትን ማሽኖችና ፋብሪካዎች ሞዴል በማድረግ ሌላ ማምረቻዎችና ፋብሪካዎች በአፍሪካውያን ሳይመረቱ ብዙ መቶ ዓመታት ነጉደዋል፡፡አሁንም እየነጎዱ ነው፡፡ሌላው ቀርቶ ፋብሪካዎችና ማሽኖች  ሲቆሙ ችግራቸውን ለይቶ መፍታና መቀያየሪያ የሚሆኑ አካላቶቻቸውን ማምረት አልተቻለም፡፡ይህም ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸው ፋብሪካዎችና ማሽኖች ቆሞ ቀር ሆነው  እንዲዘጉ አድርጓል፡፡

ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ከዘመነ አክሱም እሰከ ዘመነ ላሊበላ ድረስ በኪነ ሕንጻና ቅርጻቅርጽ ትልቅ ዕድገት ማሳየት ቢቻልም ይህ ዕድገት ሰፍቶና ጎልብቶ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ዕድገቱ ከራሱ አልፎ ወደ ኢንዱስትሪና ሌሎች ልማቶች መቀጠል ሲገባው ወደማያቋርጥ ዝምታ ተሸጋገረ፡፡የልማትና የዕድገት ፈር ቀዳጅ የሆኑትን ዕደጥበባት ማለትም የሸክላ፣ብረታ ብረትና የቆዳ ስራዎች እንዲሁም ሽመናና እነዚህን ስራዎች የሚሰሩ ባለሙያዎችን ማበረታታትና የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ አመራረት ስልት ማጎልበት አልተቻለም፡፡ይህ ሳይቻል ሲቀር እነሱን ማንኳሰስና መሳዳብ እንደትልቅ ነገር የአፍ ብልጠትና የአደባባይ መኮፈስ እንደትልቅ ነገር ተቆጠረ፡፡ይሕ ከንቱ ባሕል አገርን እንደተጠናወታትና እንዳታድግ ተብትቦ እንደያዛት ብዙ መቶ አመታት ነጎዱ፡፡

 

ከዘመነ ላሊበላ በኋላ ከእንቅልፋችን ሳንነቃና ምንም ልማት ሳናካሂድ ብዙ መቶ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ሌላው ቢቀር ከጣሊያን ጋር በተለያየ ጊዜ ያደረግነውን ጦርነት ማየት ለኋላቀርነታችን አብይ ማሳያ ይሆናል፡፡በ1896 ዓ.ም. ጣሊያኖችን በአድዋ ላይ ድል ስናደርግ በአብዛኛው የተጠቀምነው ከቆዳ የተሰራ ጋሻ እንዲሁም በቀላል እደጥበብ የተመረቱ ጦርና ጎራዴዎችን ነው፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ ጣሊያኖች በ1930ዎቹ አገራችንን ሊወሩ ሲመጡ በፊት ከነበረው ቴክኖሎጂያቸው እጅግ ተለውጠውና ተሻሽለው በታላቅ ወታደራዊ ሃይልና ኩራት ነበር፡፡እነሱ በሄሊኮፕተሮቻቸው ከምድር ለቀውና መጥቀው ቦንብና ክሎሪንን የመሰለ የመርዝ ጋዝ ከሰማይ ሲያዘንቡ ኢትዮጵያውያን ከመገረምና ከመሸሽ ውጪ ምንም ማድረግ የቻልነው ነገር አልነበረም ፡፡   

ከዚህ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት የእስካሁን አካሄዷን ፍፁም ሊቀይር የሚችል ኢኮኖሚያዊ አብዮት አካሂዳለች፤በማካሄድም ላይ ትገኛለች፡፡የአሁኑ ፈጣን ለውጥና ጉዞ ብዙዎች እንደሚስማሙበት ከአክሱምና ላሊበላ ጀምሮ የነበረውን የኋሊት ጉዞ ሊያካክስ የሚችል ነው፡፡በተለይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብና ኢንቨስትመንትና ፋብሪካዎችን በማስፋፋት በኩል እየታየ ያለው እመርታዊ ለውጥ ብዙዎችን ከማስገረሙም በላይ ለአፍሪካ አገራ ተምሳሌት እንደትሆን ያስቻላት ነው፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን አገራዊ ኢኮኖሚያችን በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተመዘገበው 20 በመቶ ዕድገት እመርታዊ  ከመሆኑም በላይ አገሪቱ ወደፊት ኢኮኖሚዋን በኢንዱስትሪ ምርቶችና በፋብሪካ ውጤቶች ኤክስፖርት ላይ መሰረት ለማድረግ የተለመችው የዕድገት ግብ  በቅርብ ጊዜ ዕውን ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ፈንጥቋል፤የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገታችን በተጨባጭ ሁኔታ ሊሳካ እንደሚችል ጠቋሚ ሆኗል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታለመውን ለውጥ እንዲቀዳጅና አገራዊ ዕድገታችን በሚጠበቀው ሁኔታ ከፍ እንዲል ለማድረግ ለማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዕድገት ልዩ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ይታመናል፡፡ይህንንም የመጀመሪያውን ልምድ በመቀመር፣በፊት የተገኙ ውጤቶችንና ድክመቶችን እንዲሁም መፍትሄዎቻቸውን በማጤን ተከልሶ የተዘጋጀው የ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  ያሳያል።

የሁለተኛው የዕደገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ዘመን ሁለት ዓመታት የተቀነሰለት ቢሆንም በእነዚህ ሁለት ዓመታት የታዪት ለውጦች በተለይም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባትና አልሚ ባለሃብቶች በመሳብ በኩል ዕቅዱ ውጤታማ ሆኗል፡፡ይህም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ወደር ያልተገኘላት የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን  አስችሏታል፡፡አሁን ላይ የዕቅዱን ሙሉ ስኬት ለመተንበይ ባይቻልም ባለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱ  በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ካስመዘገበችው ዕድገት በመነሳት በቀሪዎቹ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዓመታት ጥሩ ውጤት እንደምታስመዘግብ መናገር ግን ከባድ አይደለም፡፡

በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ውስጥ የሐዋሳ ፓርክ በቀዳሚነትና በሞዴልነት የሚጠቀስ ነው፡፡ከዚያ በኋላ  በቂሊንጦ፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ጅማ፣ ባህርዳርና አረርቲ ምንጃር፣ኮምቦልቻና መቀሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ፓርኮቹ በተለያዩ ምርቶች የኤክስፖርት ሞዴል ሆነው እንዲወጡ የተቀረፁ ሲሆን በተሰማሩበት ዘርፍ አመርቂ ለውጥ እንደሚያመጡ ይጠበቃል፡፡ለምሳሌ የመቀሌና ኮምቦልቻ ፓርኮች በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቂሊንጦ ፓርክ የህክምና መሳሪያዎች በማምረት ላይ ትኩረት አድርገው ለውጥ እንዲያመጡ የተገነቡ ናቸው።

በተለይም የኢንዱሰትሪ ፓርኮች ግንባታ በሰፊው እየተከናወነ መሆኑ እና እነሱን ተከትሎ ብዙ የውጭ አልሚዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው አገሪቱ በኢንዱስትሪ ላይ አብዮት እያካሄደች መሆኑን ያሳያል፡፡ለምሳሌ በቅርቡ የተከፈቱትን እንኳን ብንመለከተ የመቀሌና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ የግንባታ ሥራቸው ተጠናቅቆ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በይፋ መመረቃቸው ይታወሳል። እነዚህ ሁለት ፓርኮች በጨርቃጨርቅና አልባሳት አመራት ስልት ልቀውና የልህቀት ማዕከል ሆነው እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡

በቅርብ ከተመረቁት ለምሳሌ የመቀሌው ፓርክ በ75 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር 10 ሺህ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ፓርኩ በሙሉ ወደ ማምረት ሥራ ሲገባ 20 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች  የሥራ ዕድል እንደሚከፍት ይጠበቃል፡፡በአገሪቱ ከተገነቡትና ይገነባሉ ተብለው ከሚጠበቁት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሁሉ በትልቅነትና በስፋት የሃዋሳን የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚስተካከል የለም፡፡ ፓርኩ በአጠቃላይ 35 የማምረቻ ሼዶች አሉት፡፡ከእነዚህ ሼዶች ውስጥ 18ቱ በታዋቂ አምራች ኩባንያዎች የተያዙ ሲሆን በሁሉም ሼዶች የማምረት ሂደት ሲጀመር 60 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች የሰራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ከዚህም በላይ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአካባቢ ብክለትን በመከላከል በኩል ሞዴል እንዲሆን ታስቦ የተገነባ ፓርክ ነው፡፡ከማምረቻ ሼዶች የሚወጣውን ፍሳሽ ለማጣራት ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ አስተማማኝ የሆነ የፍሳሽ ማጣሪያ ተገጥሞለታል፡፡ማጣሪያው እጅግ ዘመናዊ ከመሆኑም በላይ በየቀኑ ከፋብሪካዎቹ ሊመነጭ የሚችለውን 11 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ የማጣራት አቅም አለው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችም የአካባቢ ብክለትን እንዳያስከትሉ ሆነው የተገነቡ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብዙ መቶ ሺህ ዜጎችን በመቅጠር፣ዘመናዊ የአመራረት ቴክኖሎጂ ከትልልቅ የውጭ አገር ኩባንያዎች ወደ አገራችን በማሸጋገርና አገራችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንድታመርት በማስቻል ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ሩጫ እንደሚያፋጥኑ ይጠበቃል፡፡ኢትዮጵያ በኢኮኖሚዋ ላይ ስር-ነቀል ለውጥ ለማምጣትና ግለ-ስልት የሆነ የኢንዱስትሪ አብዮት ለማካሄድ እየጣረች ትገኛለች። በተለይም ከሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ እየተተገበረ ያለው አገራዊ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢንዱስትሪው በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በማስቻል በኩል የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

አገራዊ ራዕያችን ኢኮኖሚያችንን በፊት ከነበረበትና በግብርና ውጤቶች ላይ ብቻ ከተንጠለጠለ የኢኮኖሚ አሰራር ወደ ኢንዱስትሪና ኤክስፖርት-መር ልማት መሸጋጋር ብሎም ከስድስት ዓመታት በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በመሆኑ አገራችን ይህንን የኢንዱስትሪ-ተኮር መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፡፡ የኢንዱስትሪ ልማትና ምርታማነት በሩብ ቢሊዩን ዶላር ተገንብቶ  ስራ በቀጠለው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተጀምሯል፡፡ይህ የልማት ተግባር በመቀሌ፣በኮምቦልቻ፣ባህርዳርና ቡሬና ሌሎች ከተሞችም ቀጥሏል፡፡የፓርኮች ግንባታ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በስፋት እንደሚተገበር ይጠበቃል፡፡

ልክ እንደ አለሚቱ ሁሉ ብዙ ወጣቶች በተለይም ሴቶች በተለያዩ  የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ለምሳሌ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሚገኘው አንድ የህንድ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥራ እየሠራች የምትገኘው ጋዲሴ ጉዲና የፓርኮች መጀመር ስራ አጥ ሆነው ረጅም ጊዜ ለተቀመጡ ብዙ ወጣቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው ትላለች፡፡

እንደ ጋዲሴ ገለጻ የስራ ዕድል ያላገኙ ብዙ ጓደኞች አሏት፡፡በፓርኩ ውስጥ ያሉትና ስትወጣ ስትገባ የምታያቸው ሁሉም  የማምረቻ ሼዶች ስራ ሲጀምሩ ስራ ፈላጊ ጓደኞቿ ስራ ሊያገኙ እንደሚችሉ ያላትን እምነት ገልፃለች፡፡አሁን እየሰራች ካለው ስራ አንጻር  የሚከፈላት ደመወዝ ዝቅተኛ ቢሆንም በፓርኮች ግንባታ ምክንያት ስራ በማግኘቷና የህሊና እረፍት በማግኘቷ ደስተኛ ናት፡፡ገቢዋም ወደፊት እንደሚስተካከልና ጥሩ ገቢ እንደምታገኝ ታምናለች፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy