Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ልማታዊ ዲፕሎማሲያችን

0 285

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ልማታዊ ዲፕሎማሲያችን

                                                         ዘአማን በላይ

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መንግስት ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን አድርጓል። ተጨባጭ ስኬቶችንም ማስመዝገብ ችሏል። በተለይም ሀገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንትን ከመሳብ፣ ወደ ውጭ ለሚካሉ ምርቶች ገበያ ከማፈላለግ እና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጠናቀቀውን የበጀት ዓመት አስመልክቶ ከመሰንበቻው በሰጠው መግለጫ፤ የሀገራችንን ልማታዊ ዲፕሎማሲ ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።  

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስኬት መለኪያ ‘ዲፕሎማሲው የሀገሪቱን የልማት ፍላጎት ምን ያህል አግዟል?’ የሚል መነሻ ያለው በመሆኑ፤ ከዚህ አኳያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 84 ትላልቅ የውጭ ኩባንያዎች በሀገሪቱ ስራ እንዲጀምሩ ማድረግ ተችሏል። እነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ የካፒታል አቅማቸው እስከ አንድ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስም ይገኙባቸዋል። ይህም በልማታዊ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ የተጓዘችበትን ርቀት የሚያስረዳ ይመስለኛል።

ርግጥ ልማታዊ ዲፕሎማሲውን እውን ለማድረግ ሀገራችን የምትመራበት ትክክለኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የላቀ ድርሻ አለው። ፖሊሲው በርካታ ባለሃብቶችን በመሳቡ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲስፋፋ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ይህን በመመርኮዝም የኢትዮጵያ መንግስት የግሉ ሴክተር በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ፋይዳ በመረዳት የኢንቨስትመንት አዋጁን በተለያዩ ጊዜያት በመከለስ ይበልጥ ምቹና ተወዳዳሪ፣ ሳቢና ግልፅ በማድረግ አሻሽሎታል። ይህም የውጭ ኢንቨስትመንቱ ሳቢና ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ለማድረግ ያለመ ተግባር ነው፡፡ ይህም መንግስት ያቀደውን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ አይታበይም፡፡    

የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሠላምና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን በመገንዘብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ተወላጆች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ማህብረሰብ ዘንድ የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት እየሰራ ይገኛል።

እርግጥ የኢትዮጵያን በጎ ጎን ማስተዋወቅ የጥቂት ሙያተኞች ወይም የፖለቲካ ሹመኞች ስራ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የተሳካ አፈጻጸም ሊኖር የሚችለው መላው ህዝብ እንደ ሁኔታው የሀገሩ አምባሳደር ሆኖ ሲሳተፍ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ በመንግስት በኩል ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው መንገዶች መንግስት እያከናወነ ያለው ጠንካራን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመደገፍና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

እርግጥ የኢፌዴሪ ህገ- መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሰላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ እውን ለማድረግ እየሰራች መሆኑን አመላካች ነው፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው አንድ ሀገር ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት ለማለት በርካታ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሠላምና የተረጋጋ ፖለቲካ፣ የተረጋጋና እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ፣ የዳበረ የመሰረተ – ልማት አውታር፣ ሰፊ የገበያ ዕድል፣ በቂ የሰለጠነና ውጤታማ የሆነ ሰው ኃይል እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያሳካ ፖሊሲና ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ ሀገራችን ውስጥ ሠላምና የፖለቲካ መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ መኖሩ፣ ኢኮኖሚው የተረጋጋና ፈጣን ዕድገት ማሳየቱ እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የመሠረተ ልማት አውታር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ያሳያል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች መኖራቸው ብቻ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ዋስትና አይደሉም፡፡ የቱንም ያህል ጥሩ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቢኖርም ሀገሪቷ ለኢንቨስትመንት ያሏትን ምቹ ሁኔታዎች በውጭው ዓለም የሚያስተዋውቃቸው አካል ከሌለ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

እናም በዚህም የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመመራት በዋነኛነት የስራው ባለቤት የሆነው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አመቺ የኢንቨስትመንት መስኮችን በውጭው ዓለም በማስተዋወቁ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰሳቸው በአሁኑ ጊዜ የውጭ ኢንቨስትመንት በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ረገድ በ2009 ዓ.ም የተከናወነው ስራ ውጤታማ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለፀው 984 አነስተኛና መካከለኛ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና የኢንቨስትመንት አዋጭ ጥናት እንዲያካሂዱ ማድረጋቸው ተጠቃሽ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በቱርክ፣ ጃፓን፣ ሞሮኮ፣ ብራዚል እና በሌሎች ሀገራት 31 የቢዝነስ ትስሰር መድረኮች የተካሄዱ ሲሆን፤ 672 የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የውጭ የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው ተድርጓል። ይህም የውጭ ምንዛሬን ከማጎልበት አኳያ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። ለዚህም በበጀት ዓመቱ የገበያ ዕድሎችን ለማመቻቸት በተከናወነው ስራ ከ494 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ብቻ መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

በአጠቃላይ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የሀገራችን ልማታዊ ዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤታማ ነበሩ ማለት ይቻላል። እነዚህ ስራዎች በተለይም የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ እየተመዘነ በተጀመረው የበጀት ዓመትም ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy