Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሙስና የልማታችን እንቅፋት እንዳይሆን…

0 572

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሙስና የልማታችን እንቅፋት እንዳይሆን…

                                                           ደስታ ኃይሉ

ሙስና በማደግ ላይ ላሉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት የልማት ማነቆ መሆኑ ይታወቃል። የአንድ አገር የልማት ግስጋሴን ሙስና አላላውስ ብሎ እንቅፋት ከሆነው የታለመውን ዕድገት ማምጣት አይችልም። ህልውናንም ያናጋል። በመሆኑም መንግስት በሙስና ላይ እየወሰደ ያለው ቁርጠኛ አቋም ይህን አገራዊ ህልውና የማረጋገጥ ሃላፊነት ስላለበት መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

ሙስና የአስተሳሰብ ጉዳይና በአቅራቢያችን የምናውቀው በመሆኑ ሁሉም አስተሳሰቡንና ተግባሩን መፀየፍ ብሎም መታገል ይኖርበታል። ተግባሩን መኮነንና መታገል የመንግስት ተግባር ብቻ መሆን የለበትም። ህዝቡም በነቂስ ችግሩን ፊት ለፊት በመጋፈጥ የመፍትሔው አካል መሆን ይኖርበታል።

እርግጥ በሙስና ተግባር ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን፣ ሰጪዎችንም፣ ተቀባዮችንም፣ አገናኞችንም በቁጥጥር ስር ማዋልና ለህግ ማቅረብ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባራት ወይም የአሰራር ችግሮችን ከመፍታት አንፃር እንደ አንድ የማስተካከያ እርምጃ ብቻ የሚታይ ነው።

ዋናው ጉዳይ ህብረተሰቡ በፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ላይ ለመሳተፍ ያለው ቁርጠኝነት ነው። ከዚህ አኳያ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ስንመለከት ቀደም ባሉት ጊዜያትም ይሁን በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ባለው የፀረ-ሙስና ትግል ህብረተሰቡ የላቀ አስተዋፅኦ እንደነበረው ለመገንዘብ አይከብድም።

መንግስት ለፀረ ሙስና ትግሉ አዲስ አይደለም። የኢፌዴሪ መንግስት ያለፉት ተግባሮች እንደሚያስረዱት ይዞት የመጣው የግምገማ ባህል ለፀረ-ሙስና ትግሉ የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል። እያበረከተም ነው። በአሁኑ ሰዓትም እየተላሄደ ባለው የፀረ ሙስና ትግል ይህንኑ የግምገማ ባህል በመጠቀም አጥፊዎችን ወደ ህግ ፊት እያቀረበ ነው። ታዲያ በዚህ አሰራሩ ውስጥ ህብረተሰቡ ግልፅ ጥቆማ በመስጠት ጉልህ ሚና ነበረው። አሁንም ይህ ሚናው እየጎለበተና እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ይገኛል።

ሆኖም የሙስና ተግባር በባህሪው ውስብስብ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት ተችሏል ሊባል አይችልም። ይሁንና ረጅም ጉዞ መጓዝ ተችሏል። ለዚህ መነሻው የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የተደረገው ግምገማ ነው። በወቅቱ በአንድ በኩል ስልጣንን የኢኮኖሚያዊ ሃብትና የብልፅግና መሳሪያ በማድረግ ፀረ-ዴክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በሚሹ ወገኖች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የሃብት ምንጭ እንዳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲያብብና እንዲዳብር ብሎም የጥገኝነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዳያገኝ በሚተጉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ግምገማና የመድረክ ትግል መካሄዱን እናስታውሳለን።

በእነዚህ ሁለት ፅንፍ አመለካከቶች ዙሪያ በተካሄዱ ግምገማዊ የሃሳብ ፍጭት፤ ስልጣን የጥቂቶች የሃብት ማካበቻ እንዳይሆን እንዲሁም ዴሞክራሲና ዴክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ብሎም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት እንዳያገኝ የታገለው ወገን ነጥሮ እንዲወጣ አስችሎታል።

ይህም በመንግሥት ከፍተኛ የአመራር እርከን ላይ የነበሩት ጥገኛ ኃይሎች በተግባር እንዲንገዋለሉ አድርጓቸዋል። ልማታዊ ዴሞክራሲውም በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም አስችሎታል።

እርግጥ የዛሬ 15 ዓመቱ የተሃድሶ ግምገማ ባይካሄድ ኖሮ ሀገራችን እንዲህ በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴ ውስጥ አትገባም ነበር። ህዝቡም በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ተተብትቦ ከኢኮኖሚው ዕድገት በየደረጃው የሚያገኘው ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ አይችልም ነበር። መንግስትም የሀገሪቱን ህዳሴ በፅኑ መሰረት ላይ ሊያቆምና ህዝቡን በላቀ ደረጃ ሊጠቀም የሚችለውን የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ከአንዴም ሁለቴ ባልነደፈና ውጤት ባላማጣም ነበር።

እነዚህ ሃቆች የገዥው ፓርቲ ዴክራሲያዊ አካሄድ የሆነው የግምገማ ባህል ዓላማና ብሎም የፀረ-ሙስና ትግሉ ግብ ምን እንደሆነ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩን እንጂ፤ አንዳንደድ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች እንደሚያስቡት አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን ጎድቶ ሌላውን ለመጥቀም አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

መንግስት የሚያካሂደው ማንኛውም ግምገማምና እርሱን ተከትሎ የሚካሄደው የፀረ-ሙስና የሂደት ትግል፤ በምርጫ ወቅትና ማግስት ለህዝቡ የገባውን የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም እመርታ ቃልን በላቀ ቁርጠኝነት ለመፈፀም ያለመ ከመሆን ውጪ ሌላ የተለየ አጀንዳ እንደሌለው መረዳት ያስፈልጋል።

ፅንፈኞች መንግስት የጀመረውን ሙስናን የመዋጋት ዘመቻ መቃወም የጀመሩት ዛሬ አይደለም። በአንድ ወቅትም “መንግስት በሙሰኞች ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት” ሲሉ እንዳልነበር፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ መንግስት ባለበት ህዝባዊ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በህዝብ ሃብት ዘረፋ አዘቅት ውስጥ በገቡ ግለሰቦች ላይ ወቅታዊና ተገቢ እርምጃ ሲወስድ “መዋቅሩ በሙስና የተተበተበ ነው” የሚል ፈፅሞ ከእውነታ የራቀን አሉባልታ ማራገባቸው ለሰሚው ቢሆን ግራ የሚያጋባ ነው። ዛሬም ከዚህ የተለየ አቋም እያራመዱ አይደለም።

በተለይም ጉዳዩ መንግስት በልማታዊ  እንቅስቃሴውና በህዝቡ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ እንቅፋት ሊፈጥር የሚችለውን የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ድርጊት ለማዳከም በሚያደርገው አዎንታዊ ተግባራት ውስጥ አፍራሽ ሚና መጫወቱ ይቀራል ብሎ ማሰብ አይቻልም።

እርግጥ በየትኛውም ዴክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነባራዊ ክስተት ነው። ምንም እንኳን በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ ቢሆንም፤ እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ከዚህ ነባራዊ ክስተት የፀዳንና ጉድለቶች የሉብንም ብሎ ለመናገር አይቻልም።

ለነገሩ የኢፌዴሪ መንግስትና እርሱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን በየጊዜው በሚወስዷቸው በርካታ ርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች በመጠኑም ቢሆን እየቀረፉ ቢሆኑም፤ የሚፈለገው የአስተሳሰብ ለውጥ ተገኝቷል ማለት አይቻልም።

እንዲያውም አስተሳሰቦቹ እየገነገኑ ጫፍ ላይ እየወጡ ይመስላሉ። በአመዛኙ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የሚፀየፍና እንደ ነውር የሚያይ የመንግስት ስራ አስፈፃሚን ብሎም ህዝብን በተሟላ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም።

ባለፉት የጥልቅ ጊዜያት ወቅቶች በተካሄዱት ጥልቅ የተሃድሶ መድረኮች አማካኝነት በተሰብሳቢዎቹ አማካኝነት በተገኙት ግብዓቶች ሳቢያ በየደረጃው የተወሰዱት እርምጃዎችም የመንግስትን ቁርጠኝነት አመላካቾች ናቸው። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ የመንግስት ስራ ፈፃሚዎች ላይ የተወሰዱት የአስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ይህም ሙስና አገራችን የጀመረችው ፈጣንና ተከታታይ ልማት እንቅፋት እንዳይሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy