Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተሰሚነታችንን እና ተጽዕኖ ፈጣሪነታችንን ያሳደገልን

0 359

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተሰሚነታችንን እና ተጽዕኖ ፈጣሪነታችንን ያሳደገልን

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ

 

ስሜነህ

 

ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር እና ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውን በሱዳን ተነባቢ የሆኑ ጋዜጦች እና ድረ ገጾች በተለይም የsudantribune.com ሰሞንኛ አጀንዳ ነው ። የሁለቱ መሪዎች ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ በደቡብ ሱዳን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት እና የኢትዮጵያ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መሆኑን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ማስታወቃቸውን ነው ዘገባዎቹ የሚያመለክቱት። በተለይም sudantribune.com ድረገጽ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር የኢትዮጵያ እና የሱዳን ግንኙነት ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ማስታወቃቸውን ዘግቧል። የታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚካሄድ ውይይት ግብጽን ባሳተፈ መልኩ የሚካሄድ ነው፤ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ከውኃ ጉዳዮች ያለፈ ነው፤ ውኃ የሱዳን፣ የኢትዮጵያ እና የሌሎች የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው ፤ሲሊ ሚኒስትሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸውን ድረገጹ አስነብቧል።

 

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርየያም ደሳለኝ በሱዳን ጉብኝታቸው ወቅት ኢትዮጵያ 50 በመቶ የሚሆነውን የወጪ ምርቷን በፖርት ሱዳን በኩል ለውጪ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላት ማስታወቃቸውን Xinhua ዘግቧል።ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሁለቱ አገራት ሁለንተናዊ ትብብር ዙሪያ  ከፕሬዝዳንት አልበሽር ጋር ከተወያዩ በኋላ እንዳሉት ፤አሁን ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የጅቡቲ ወደብ ለአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ሩቅ በመሆኑ  ለተጨማሪ የትራንስፖርትወጪ እየዳረጋት ነው። ችግሩን ለማቃለል የሱዳን ወደብን መጠቀም የተሻለ አማራጭ መሆኑን  ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከውጭ ከምታስገባቸው  እቃዎች ግማሽ ያህሉን በሱዳን ወደብ በኩል የማስገባት ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል፡፡

ፍላጎቱን እውን ለማድረግም በሁለቱ ሀገራት በኩል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት፡፡ሀገራቱ በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን ትብብር  አጠናክረው ለማስቀጠል  ለመሰረተ ልማት ስራዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አብራርተዋል።ይህን ተከትሎም በመተማ የደረቅ ወደብ ለመገንባት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም ተሰምቷል።

የሁለቱ አገሮች መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገርና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በጋራ እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውም ሌላኛው የጉብኝቱ ፍሬ ነገር ነው።ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽር በሀገራቸውና በኢትዮጵያ መካከል ምንም ዓይነት የድንበር ውዝግብ የለም ካሉ በኋላ የሁለቱም አገራት ግንኙነት ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የአከባቢ ውህደት ለማሳካት እየሰሩ መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት። የድንበር ማካለል ሥራዎችን በተመለከተ ሁለቱ አገሮች በመግባባት ደረጃ ላይ እንደደረሱና በቀጣይ የድንበር መለያ ምልክቶችን የማስቀመጥ ተግባር እንደሚሸጋገር  አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንት አልበሽር የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ ያደረገው ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ከፍታ የሚወስድና በቀጣናው ያለውን የሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ነው ያስረዱት ፡፡

ሁለቱ አገሮች በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በአገር መከላከያና ደህንነት እንዲሁም በባህልና መረጃ ልውውጥ የበለጠ ተቀራርቦ መስራት በሚቻልባቸው ምቹ ሁኔታዎች ላይም ምክክር ተደርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በመግለጫው ላይ እንዳገለጹት፤ አገራቱ በሚፈጥሩት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ዜጎቻቸው ተጠቃሚና የኢንቨትመንትና የንግድ ልውውጡም ቀልጣፋ እንዲሆን እየተሰራ ነው።

ሃገራቱ ከዚህ ቀደም በሰላም፣ ጸጥታ፣ በንግድ፣ ኢኮኖሚ ትብብር፣ በመንገድ ትስስር፣ የደን ልማትና እንክብካቤን  የሚመለከቱ ወደ ስምንት የሚጠጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን መፈራረማቸው በመግለጫቸው ተነስቷል፡፡በተጨማሪም የሁለቱ አገሮች የጸጥታ አካልም ከአገሮቹ አልፎ በቀጣናው ሰላም ለማስፈን በጋራ እየሰራ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ይህ ሁሉ የሆነው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገው የሃገራችን  የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው። ይህ ፖሊሲ የሃገራችንን ገጽታ መቀየር አስችሏል። ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በኢኮኖሚ እንዲተሳሰር አስችሏል። ከላይ የተመለከቱት የዘገባ ውጤቶችና የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ማረጋገጫዎች የሚያጠይቁትም ይህንኑ ነው።

አገራችን በተከተለችው ትክክለኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምክንያት ከጎረቤቶች ህዝቦችና መንግስታት ጋር ለዘመናት የነበረን ያለመተማመን ግንኙነት በመሰረቱ ተቀይሮ በወዳጅነትና በጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሰረተ መልካም ግንኙነት መመስረት ችለናል። ከታላላቅ የአለም መንግስታትና አገሮች ጋር ለረዢም ዘመን በሰጪና ተቀባይ፣ በእርዳታ ብድር ላይ የተመሰረተው ግንኙነት በህዳሴው ማግስት ግንኙነቱ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የንግድና ኢንቨስትመንት አጀንዳ ዙሪያ ያጠነጠነ እየሆነ መጥቷል። ሀገራችን ከአፍሪካ ታላላቅ የኢንቨስትመንት መዳረሻ፣ በምስራቅ አፍሪካ ደግሞ በዘርፉ ቀዳሚ መዳረሻ ለመሆን ችላለች።

ከሰጭና ተቀባይ ግንኙነት ተላቅቆ ከሀሉም አገራትና መንግስታት ጋር በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ስኬታማ የውጭ ግንኙነት ገንብተናል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን የአለምን ቀልብ በበጎ መሳብ በመቻሏ ያደጉትና በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉት ሀገራት መሪዎች ወደ ሀገራችን በመምጣት ግንኙነታቸው ለመጠናከር ፍላጎታቸው መግለፃቸውንና የተለያዩ ስምምነቶችን መፈራረማቸው ለዚህ በአብነት የሚነሳ ነው።  

የአለም ህብረተሰብ ካለፉት አመታት ወዲህ በአዲስ መልክ ለአገራችን የሰጠው በጎ ገጽታ አሁንም ቢሆን ሊለወጥ አልቻለም። በውስጧ በፈጠረችው የመቋቋም አቅም እና ከሁሉም አገሮች ጋር በገነባችው የወዳጅነት ግንኙነት ችግሩን ለመቋቋም ስሟ በድርቅና ረኃብ ብሎም በእርስ በርስና የጎረቤት ጦርነት የሚታወቀው ሀገራችን አሁን ስማችን በበጎ ከመነሳባቸው መስኮች ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገታችን፣ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ መሆናች፣ ግዙፍና ስኬታማ የአየር መንገድ ባለቤት መሆናችንን፣ በአለም ከትላልቆቹ ተርታ የሚሰለፍ የሃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባን መሆናችንን፣ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹና ተመራጭ መሆናችን፣ አለም አቀፍ የፖለቲካ ማዕከል የሆነች ርዕሰ ከተማ ያለን መሆናችን የአለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል። አለም አቀፍ ታዋቂ ሚዲያዎችና ታላላቅ የአለም አገራት መሪዎች አገራችን በህዳሴ ውስጥ ስለመሆኗ እየመሰከሩና ገፅታዋም በመልካም ሁኔታ እየተገነባ መጥቷል።   

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ከሩዋንዳ ጀምረን በላይቤሪያና በሴራሊዮን እንዲሁም አሁን በሱዳንና በሶማሊያ የተሳተፍንባቸው የሰላም ማስከበርና ማረጋጋት ስራዎች በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ረገድ ስኬታማ የሆንባቸው ናቸው። ለዘመናት በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ ተግባራዊ ሆኖ የቆየው ኢፍትሃዊ የውሃ ከፍፍል በምክንያታዊና ፍትሃዊ የአጠቃቀም መርህ እንዲተካና ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም በተፋሰሱ አገራት መካከል እንዲኖር ስኬታማ ስራ ሰርታለች። በዚህም ስምምነቱ በአዲስ መልክ እንዲቀረፅ አገራችን ግምባር ቀደም ሚና መጫወቷና የአብዛኞቹን ተፋሰስ አገሮች ይሁንታና ድጋፍ ማግኘቷም የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ስራችንን የመራንበትን አግባብ ውጤታማነት የሚያረጋግጥ ሌላው እና ከላይ ስለተመለከተው አጀንዳችን ማረጋገጫ ነው፡፡

ካስመዘገብነው ስኬታማ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ስራዎች መካከል በናይል ተፋሰስ አዲስ የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ሁሉንም የላይኞቹን ተፋሰስ አገራት በብሄራዊ ጥቅማችን ዙሪያ ማሰለፍ ችለናል፡፡ የዲፕሎማሲ ስኬታችን ይበልጥ ደምቆና ጎልቶ የሚታየው በናይል ተፋሰስ ዙሪያ ጊዜ ያለፈባቸውን ኢፍትሃዊ የሆኑና አሮጌ የቅኝ ግዛት የተናጠል ስምምነቶች ውድቅና ፈራሽ እንዲሆኑ ደግፈው የተፋሰሱ የራስጌ ሀገራትን ከጎናችን ማሰለፍ መቻላችን ነው፡፡ ይህ ውጤት የተገኘውም የተፋሰሱ የራስጌ አገራትን በአገራችን ትክክለኛና ፍትሃዊ አጀንዳና መርህ ዙሪያ በብቃት ማሰባሰብና አንድ አይነት አቋም እንዲይዙ ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ በመንቀሳቀሳችን ነው፡፡ በዚህም ዘመን ያለፈበት የግብፅ ኢፍትሐዊ አቋም ትክክል እንዳልሆነና አግባብነትም እንደሌለው የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲገነዘቡት በማድረጋችን የግብፅ ፖለቲከኞችን ኢፍትሃዊ አቋም ማጋለጥ ችለናል፡፡ በዚህ በናይል ተፋሰስ አጠቃቀም ላይ የሱዳንን መንግሥት የግድቡን ሥራ ከመቃወም ይልቅ እንዲደግፍ ማድረግ የቻልነው በግብፅም በኩል ከጭፍን ተቃውም ይልቅ ጉዳዩን በውይይትና ድርድር መፍታት ይቻላል የሚል መንፈስ እንዲያድርባቸው ማድረግ የቻልነው ለጋራና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ቁርጠኛ መሆናችንን ማሳየት በመቻላችን ነው፡፡ስለሆነም ከላይ የተመለከቱት የሁለቱ ሃገራት ስምምነት ተገቢና ምክንያታዊ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ  ከሁሉም የጎረቤት አገራት   ከጅቡቲ፣  ከሱዳን፣ ከኬንያ ደቡብ ሱዳን ሶማሊያ ጋር  በመሰረተ ልማት ማስፋፋት፣ በሃይል አቅርቦት፣ በንግድ፣ በትምህርት ዕድል  ወዘተ   የምታደርገውን ጥረት ሀነኛ ማረጋገጫ ነው ። ኢትዮጵያ  የህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ከሃገሯ ዜጎች አልፋ የጎረቤት ሃገራት አርአያ ሆናለች።  የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስኬት  አንዱ ማሳያ በአገሪቱ  እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ነው። የኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ የውጭ ግንኙነት መርሃችንም  የአገራችንን  ገጽታ ከመለወጡ ባሻገር  በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ መድረኮችም  ተሰሚነታችንን እና ተጽዕኖ ፈጣሪነታችንን አሳድጎልናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy