Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ታጋይ መለስ ከመድረክ መናገሩን ቀጥሏል፡፡

0 719

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

˝ይሄ ድርጅት አይፈርስም˝

በሀብቶም ገብረእግዚያብሄር (nahat143love@gmail.com) 13/08/17

ጊዜው እንዴት ይሮጣል? ታጋይ መለስ ዜናዊ ከሚወደው እና ከኖረለት ህዝብ የተለየው በዚሁ የነሐሴ ወር የዛሬ አምስት አመት ነበረ፡፡ የታጋይ መለስ ዜናዊ በአጭሩ መቀጨት የማይቆጨው እና የማያንገበግበው ኢትዮጲያዊ የለም፡፡ የዚህም ምንጭ ከነበረው ከፍተኛ ስብዕናና የኢትዮጲያን ህዝብ አንድ አድርጎ የመምራት ክህሎቱ ነበረ፡፡

ይህ ድንቅ ታጋይ ከ19 አመት እድሜው ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ ህይወቱን ለህዝቦች ልዕልና የሰጠ ድንቅ ሰው ነበረ፡፡ ለዚህም ሌላ መስካሪ ሳንሻ ህይወቱ እና በተግባር ያሳየው ስራ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ለሰፊው ህዝብ ልዩ ፍቅር የነበረው ታጋይ መለስ የአርሶ አደሩን ሂወት ለመለወጥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሲተጋ ኖሮ አልፏል፡፡ ማንኛውም ለህብረተሰብ ለውጥ እተጋለሁ የሚል ፖለቲከኛ ሊኖረው የሚገባውን ስብዕና በተሟላ መልኩ አሳይቶ ሄዷል፡፡ አስተምሮዎቹ እና እሳቤዎቹ ገና ብዙ ለውጥ የሚያመጡ እና ለአለምም ጭቁን ህዝቦች ባግባቡ ከተሰራባቸው ብዙ ትሩፋት የሚያስገኙ ናቸው፡፡

የሀገራችን ህዝቦችም ሆነ አለም ታጋይ መለስን በብዙ መልኩ ያስታውሱታል፡፡ ለዛሬ ግን ሁሌም የሚደንቀኝ እና ደጋግሜ ስመለከተው የማይታክተኝን  አንድ የታሪክ ሰበዝ እመዛለሁ፡፡

ጊዜው 1993 ዓ፡ም ነበረ፡፡ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሀከል አንዱ የሆነውና ራሱ ታጋይ መለስ በሊቀ መንበርነት የሚመራው ህውሃት/ኢህአዴግ የመሰንጠቅ አደጋ ውስጥ መግባቱ በስፋት የሚወራበት ወቅት ነበረ፡፡ ህዝቡም ሙሉ ትኩረቱን ወደ ሁኔታው አድርጎ ጉዳዩን በጥሞና ይጠባበቅ ነበር፡፡ ታጋይ መለስን ጨምሮ የህውሃት/ኢህአዴግ መስራቾች እና ከፍተኛ አመራሮች በመቐለ ከትመዋል፡፡ ስብሰባዎች ይካሄዱ የነበረው በከፍተኛ ውጥረት ነበረ፡፡

ታዲያ ሌት ተቀን ከሚካሄዱት ስብሰባዎች መሀከል በአንደኛው እንደሚከተለው ተከስቶ አልፏል፡፡ አዳራሹ ከአፍ እስከገደፉ ሞልቷል፡፡ የውጥረት ድባቡም የዛኑ ያህል ከፍተኛ ነበረ፡፡  በወቅቱ በሀሳብ ልዩነት አንጃ ፈጥረው የነበሩት ቡድን መሪዎች የአዳራሹ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ መድረኩን በብቸኝነት ይመራ የነበረው የወቅቱ ሊቀ መንበር መለስ ዜናዊ ነበር፡፡

በሀሳብ ልዩነት ስብሰባውን ረግጠው ወጥተው የነበሩ ነባር ታጋዮች በሽማግሌና በልመና ወደስብሰባው እንዲመለሱ የተደረገበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም ክስተት ለህውሃት አዲስ ነገር እና ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር፡፡ ለምን ቢባል በድርጅቱ ባህል ሃሳብህን በአመክንዮ ተከራክረህ ለማሳመን አልያም በክርክሩ ከተሸነፍክ ታምናለህ እንጂ ስብሰባን ረግጦ መውጣት ያልተለመደ ክስተት ነበረ፡፡ የሆኖ ሆኖ ስብሰባውን ትቶ የወጣው አንጃ ወደስብሰባው እንዲመለስ ሆኗል፡፡

አዳራሹ ዝብርቅርቅ ባለ ስሜት ተውጧል፡፡ ድርጅቱ መፍረሱ ነው ብለው የደነገጡ እና ድምፃቸውን አጥፍተው የሚያለቅሱ ተሰብሳቢዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ የሁሉም ተሰብሳቢ ገፅ ላይ የመቆጨት እና የመንገብገብ ስሜት በግልፅ ይታይ ነበር፡፡

ይህንን ድባብ የተላበሰን ጉባኤ መምራት ከፍተኛ ልምድ ላለው ሰው ካልሆነ በስተቀር በጣም ከባድ የሚሆን ነገር ነው፡፡ ልክ እንደ ሰባኪ ሁኔታዎች ከቁጥጥር እንዳይወጡ ታጋይ መለስ ማህል መድረኩ ላይ ቆሞ ያረጋጋ ጀመር፡፡ በወቅቱ የአንጃው መሪዎች መሀከል ከነበሩትና የቀድሞው የትግራይ ፕሬዝዳንት ታጋይ ገብሩ አስራት ከመድረኩ እድል ተሰጥቶት መናገር ጀመረ፡፡

ንግራቸውን እና ሀሳባቸውን በግርድፉ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ

˝የመጣነው ስብሰባውን እንድንካፈል ስለጠራችሁን ነው፡፡ ይህንን ስብሰባ ከመጀመራችን በፊት ለዚህ ቤት የምንሰጠው መረጃ አለን፡፡ የመጣነውም ይህንን ለማድረግ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ መረጃችንና ስለስብሰባው ያለንን አስተያየት እንድትሰሙን እጠይቃለሁ፡፡˝ ብለው ታጋይ ገብሩ ንግግራቸውን አጠናቀቁ

ወዲያው አዳራሹ በጫጫታ ተሞላ፡፡ አስተያየት መስጠት የፈለጉ ተሰብሳቢዎችም ቁጭ ብድግ እያሉ እድል እንዲሰጣቸው እጃቸውን ያወጡ ጀመር፡፡

ታጋይ መለስም ከታጋይ ገብሩ በስተግራ ተቀምጦ ለነበረው ታጋይ የማነ ጀማይካ የመናገር እድሉን ሰጠ፡፡ እሱም ከታጋይ ገብሩ በተለየ ከመቀመጫው ብድግ ብሎ መናገር ጀመረ፡፡

˝ እኛ እዚህ የመጣነው ኢንፎርሜሽን ለመስጠት ነው፡፡ እኛ ይህ ስብሰባ ይጠቅማል የሚል እምነት የለንም፡፡ እናንተ መምጣት አለባችሁ ስላላችሁን……….”  አዳራሹ በተቃውሞ ድምፅ ተናወጠ፡፡ ጀማይካም በጫጫታው ውስጥ

˝እናንተ መምጣት አለባችሁ ስላላችሁን ነው የመጣነው፡፡ ህግና ስርዐት ስለተጣሰ እና ህጋዊ ያልሆኑ ሰዎች ስላሉ፣ ይህንን ሳናስተካክል ይህ ስብሰባ ተገቢ ነው ብለን አናምንም፡፡˝ ብሎ ተቀመጠ

ቤቱ እንደገና ወደ ጫጫታው ተመለሰ፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ሀሳብ ለመስጠት እጃቸውን እያወጡ ነበር፡፡ ቁጭ ብድጓ አሁንም ነበረች፡፡

ታጋይ መለስም ለተሰብሳቢው እድል መስጠቱን ትቶ እንዲህ ሲል የውሳኔ ሀሳብ አቀረበ፡፡

˝አጠቃላይ ሪፖርት አድምጠን ቀጥሎ የምሰጠው መረጃ አለኝ ያለው አካል መረጃውን ተቀብለን ወደጥያቄ እና ማጣራት ብንሄድ፡፡ ስብሰባው በዚህ መልኩ ይቀጥል?˝ አለ

ይህን እንዳለ የአዳራሹን የመጀመሪያውን ረድፍ ይዘው የነበሩት ታጋይ አባይ ፀሀዬ(ሂስ አድርጎ ወደድርጅቱ ተመልሷል)፣ ታጋይ ገብሩ፣ ታጋይ የማነ እና ታጋይ ስዬ አብረሃ እንዲሁም ሌሎች የአንጃው አባላት ስብሰባውን ረግጠው መውጣት ጀመሩ፡፡ ከሪፖርቱ በፊት እኛ ልንሰማ ይገባል የሚለው አመለካከት እንደምክንያት ሆና ነበር፡፡

አዳራሹ በጨሀት ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ ግማሹ እየወጡ ያሉትን ነባር ታጋዮች የሚማፀን እና የሚገስፅ ነበረ፡፡ ልምናው በዛ ብሎ ጥርግ ይበሉ የሚል እሳቤ ያራመደ አይጠፋም ነበር፡፡

አብዛኛው ተሰብሳቢ ግን ጭንቅ ውስጥ ነበረ፡፡ ያ ሁሉ መስዋዕትነት ከንቱ ሲሆንና ድርጅቱ ሊፈርስ ነው ብለው የሰጉ ተሰብሳቢዎች ከኡኡታ የማይተናነስ ለቅሶ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ኡወጡ የነበሩትን ጃኬት ተፍንጎ እንዳይሄዱ የያዘ ነበረ፡፡ ተሰብሳቢው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከመቀመጫው ተነስቶ ቆሙዋል፡፡ ለነገሩ ታጋይ መለስም ቁጭ አላለም ነበር፡፡ እንደቆመ ተሰብሳቢው ሊያረጋጋ እየሞከረ ነበረ፡፡

˝እስቲ ሁላችሁም አንድ ጊዜ፣ አንድ ጊዜ፣ እስቲ በያላችሁበት ቁጭ በሉ፡፡˝ እስኪረጋጉና እስኪቀመጡ ታጋይ መለስ ይህንን እየደጋገመ ተናገረ

በተሰብሳቢው ልመና እና ተማፅኖ በድጋሚ እየወጡ የነበሩት ነባር ታጋዮች በድጋሚ እንዲመለሱ ሆነ፡፡

ታጋይ መለስ ከመድረክ መናገሩን ቀጥሏል፡፡

˝ሁላችሁም በያላችሁበት ቁጭ በሉ፡፡ አንድ ግዜ በያላችሁበት ተቀመጡ፡፡ ስነ ስርዐት ይከበር፡፡ ስነ ስርዐት አድርጉ፡፡˝

ሁሉም እንደተባለው አደረገ፡፡ ታጋይ መለስም መናገር ጀመረ፡፡

˝በዚህ ስብሰባ መሳተፍ የማይፈልግ ሰው፣ ተገዶ መሳተፍ የሚፈልግ ሰው ሽፍታ ነው፡፡˝ ይህንን ንግግር ተከትሎ በአዳራሹ ውስጥ የተወሰነ ጭብጨባ ተሰማ፡፡

መለስ ቀጠለ ˝ ይሄ ድርጅት ደግሞ የሽፍታ ድርጅት አይደለም፡፡˝

ድሮ ትምህርት ቤት ሳለን ጥያቄ ስንጠየቅ ለመመለስ እኔ፣ እኔ እንደምንለው ሁሉ ተሰብሳቢው ቁጭ ብድግ እያለ እድል እንዲሰጠው በየፊናው የመድረኩን መሪ ይወተውት ጀመር፡፡

ታጋይ መለስም እድል መስጠቱን ትቶ መጀመሪያ እንዲረጋጉ እና ቦታቸውን ይዘው ቁጭ እንዲሉ ይናገር ጀመር፡፡

˝ተረጋጉ አትቸኩሉ፡፡˝ አለ

˝አሁን እዚህ ውስጥ ያላችሁ ይሄ ድርጅት እየፈረሰ ነው ብላችሁ እያሰባችሁ ስለሆነ እያለቀሳችሁ ነው፣ እየተጨነቃችሁ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ስህተት ነው፡፡ ይሄ ድርጅት ሊፈርስ አይችልም፡፡ ማንም ሰው ሊያፈርሰው አይችልም! እደግመዋለሁ ማንም ሰው ሊያፈርሰው አይችልም! ˝

ከአፍታ ዝምታ በሗላ ቀጠለ

˝አሁን እኔ ተሰብሳቢ ነኝ፡፡ እኔ እዚህ ቦታ ባልኖር ይህ ድርጅት ይፈርሳል ማለት ነው?˝ ወደ ተሰብሳቢው እቺን ጥያቄ እንደዋዛ ሰነዘራት፣ ራሱም መለሳት ˝የማይሆን ነገር ነው! የማይሆን እና የማይሆን ነገር ነው!˝

ለአፍታ አዳራሹን ቃኝቶ ንግግሩን ቀጠለ

˝ ይሄ ድርጅት አይፈርስም፡፡ ይሄ ድርጅት እየፈረሰ ነው ብላችሁ አትናገሩ፣ አታልቅሱ፡፡ ሌላ የሚያስለቅስ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ድርጅት ፈረሰ ተብሎ ግን የሚያስለቅስ ነገር የለም፡፡ ጉድ እኮ ነው! ያልሞተን ሰው ኡኡ እያልክ ልትቀብረው ትሄዳለህ? ያልሞተ ሰው ይቀበራል?

ይህ ድርጅት እኮ አልሞተም፡፡ በርግጥ ታሟል፡፡ ነገር ግን አልሞተም፡፡ ለሞተ ሰው ይለቀስ ይሆናል እንጂ ለታመመ ሰው አይለቀስም፡፡

አሁን ድርጅቱ ታሟል፡፡ ታዲያ ምንድነው የሚደረገው? ታክመዋለህ! ድርጅቱ ከሞተስ? ታለቅሳለህ ከዚያም ትቀብረዋለህ፡፡ ለታመመ ግን ታክመዋለህ እንጂ አታለቅስም፡፡˝

ታጋይ መለስ መናገሩን ቀጠለ፡፡ እጁን ወደተሰብሳቢዎቹ እየጠቆመ

˝እዚህ ውስጥ ብዙ ሃኪሞች አሉ፡፡ ሃኪም ህክምና በሚሰጥበት ወቅት መጀመሪያ እጁን ይታጠባል፡፡ ከዛ ቁስሏ የቱ ጋር እንደሆነች ይለይና ያክማል፡፡ ይህንን ትቶ ያልተገባ ነገር ካደረግ ህክምና የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ እዚህ ውስጥ ብዙ ታጋዮች፣ ነባር ታጋዮች አላችሁ፡፡

እንደምታውቁት ከዚህ የከፉ መድረኮችን ከዚህ በፊት አሳልፈናል፡፡ ምናልባትም ከዚህ የከፋ መድረክም ለወደፊቱ ሊመጣ ይችላል፡፡ ችግር አያጋጥምም የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ትተን የህክምና ስራ እንስራ፡፡ የቀብር ስራ ላይ አይደለም አሁን ያለነው፡፡ የህክምና ስራችንን እንስራ፡፡ እዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ ሀኪሞች አሉ፡፡ ሀኪም ደግሞ በሽታው የቱ ጋር ነው ያለው ብሎ ይለያል እንጂ ወደመብረክረክ አይገባም፡፡ ስለዚህ አሁን በደንብ ተረጋጉ፡፡˝ ብሎ ከቆመበት መድረክ ላይ ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ

ታጋይ መለስ ቀጠለ ˝አባይ፣ ስዬ …… ከኛ ጋር እንድትቆዩ በቤቱ ስም እለምናቸዋለሁ፡፡˝ አሁንም ከቤቱ ጉርምርምታ ተሰማ

˝አንዴ ቆዩ፣ አንዴ ተረጋጉ……˝ አለ መለስ በእጁም ጭምር ምልክት እያሳየ

˝አንዴ ተረጋጉ፣ ይሄ እኮ የመጨረሻ ቀን አይደለም፡፡ ይህንን አንፈልግም ብለው ጥለው ቢሄዱ እንኳ በዚሁ ተቆራርጠን አንቀርም፡፡ እያልን ያለነው አቅጣጫ አስቀምጠን እንሂድ ነው፡፡ በአቅጣጫችን ላይ ተመልሰን ከነሱ ጋር ተመልሰን ልንገናኝ እንችላለን፡፡ ስለዚህ በህክምና አይን አይተን፣ ተረጋግተን ወደአጀንዳችን ገብተን እንወያይ፡፡ በዚህ መልኩ እንቀጥል?˝ ብሎ ለቤቱ ጥያቄ አቀረበ

ቤቱ እንደገና ወደጫጫታው ተመለሰ፡፡ ተቀምጠው የነበሩት የአንጃው አባላት እንደገና መውጣት ጀመሩ፡፡ እየወጡ ከነበሩት ነባር ታካዮች መኸከል ታጋይ ስዬ እኔ እናንተን አክብሬ እናንተ ስለጠራችሁኝ ነው የመጣሁት እያለ ነበር የወጣው፡፡ አዳራሹ እንደመጀመሪያውም ባይሆን እንደገና ወደ ጫጫታው ተመለሰ፡፡

ታጋይ መለስ እንደገና በቆመበት ያረጋጋ ጀመር፡፡

˝አንድ ጊዜ እንደማመጥ፣ ተረጋጉ፣ እንደማመጥ፡፡˝

ቤቱን ወደማረጋጋት ካስገባ በሗላ መቀመጫው ላይ አረፍ ብሎ ይናገር ጀመር፡፡

˝አታልቅሱ! እዚህ ቀብር የለም፡፡ ታመናል፡፡ ያለው ችግር ይሄ ብቻ ነው፡፡ ህመም ካልሆነ በስተቀር ሌላ ችግር የለም፡፡˝ አጠንክሮ እና በአፅንኦት ነበር የሚናገረው

˝ድንብርብር ካልን፣ የችኩል ችኩል፣ ችኩል ያለ ንግግር ካመጣን በሽታችን ይባባሳል፡፡

ልንተማመነው የሚገባ አንድ ነግር ግን አለ፡፡ በመቶ በመቶ እርግጠኛ ልትሆኑበት የሚገባ  ጉዳይ ቢኖር ይሄ ድርጅት አይፈርስም፣ ማንም ሰው ሊያፈርሰው አይችልም፡፡ ስለዚህ ወደ አጀንዳዎቻችን እንግባ፡፡ ተረጋጉ˝

እስገራሚ ስብሰባ ነበር፡፡

መከረና ችግር ካለፈ አይቆጭ ምነው?

ባሮጌው ጊዜያችን ስንቱን አሳለፍነው ነው ያለው መልካሙ ተበጀ˝

ስብሰባው ይህንን ስንኝ ያስታውሰኛል፡፡

ታጋይ መለስን ግን ምንግዜም ሳስበው ጭንቅላቴ ውስጥ የሚያቃጭለው በዚህ ስብሰባ ያደረገው የመጨረሻ ንግግር ነው፡፡

ይሄ ድርጅት እይፈርስም፡፡

ድርጅቱ በመርህ እና በመስመር ላይ እንጂ በግለሰብ ላይ እንዳልተንጠለጠለ መጀመሪያም ያስተማረው ታጋይ መለስ ነበር፡፡  ከነበረው ታላቅ ስብዕና ያለመመፃደቁ እና ትህትናው ሁልግዜም ያስደንቀኛል፡፡

አይ መለስ ˝አሁን እኔ ባልኖር ይፈርሳል?˝ ብሎ እንደዋዛ ጠይቆ አልፏል፡፡ እኔ አይፈርስም እላለሁ፡፡ እሱ ግን ቀድሞ መልሱን ያውቀው ነበር፡፡

˝እዚ ውድብ አይፈርስን!!

ማስታወሻ፡ ትግልንና ታጋይነትን ካንተና ከተሰዉ ታላላቅ ታጋዮች ተምረናልና ሀገራችንን ያስጀመራችሁትን ጉዞ አጠናክረን እናስቀጥላለን፡፡ አንተንም ሁልጊዜ እናስብሀለን፡፡

 

ቸር እንሰንብት˝

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy