Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አገራችንን ወደ ስኬት ማማው የሰቀላት ሕገ-መንግስታችን ነው!

0 296

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አገራችንን ወደ ስኬት ማማው የሰቀላት ሕገ-መንግስታችን ነው!

አባ መላኩ

የኢፌዴሪ ህገመንገስት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህልውና መሰረት ነው። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትና እኩልነት የተረጋገጠባት፣ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ ፈጣን ልማት ተረጋገገጠባት አገር እንድትሆን ያደረጋት የኢፌዴሪ ህገመንገስት ነው። በርካቶች በ1983 ዓ.ም ኢትዮጵያ ልተፈረስ ነው፤ ልትበታተን መስቀልያ መንገድ ላይ ቆማለች፤ ወዘተ ሲባልባት የነበረች አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ  ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና  ወደ ዕድገት ጎዳና እንድታመራ ያደረጋት  ይህ ህገመንግስት ነው።  

የኢፌዴሪ ህገመንግስት  በህዝበች መካከል መቻቻልን አስፍኗል፣ አንድነትን አጽንቷል፣  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዕኩልነትን አረጋግጧል፣ የሃይማኖትን ዕኩልነትን አምጥቷል እንዲሁም መንግስትና  ሃይማኖትን እንዲለያዩ አድርጓል፣ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉ እድል ፈጥሯል። በአጠቃላይ  የኢፌዴሪ ህገመንግስት  ብዝሃነት በአገሪቱ እንዲስተናገድ በማድረጉ  ኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እንድታገኝና ፈጣን ልማት እንዲረጋገጥባት እና በህዝቦች መካከል ፍተሃዊ  የኢኮኖሚ  ተጠቃሚነት እንዲሰፍን አድርጓል።

ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም  ልትበተን፣ ልትፈርስ፣ ደም መፋሰስ ሊነግስባት፣ ገደል አፋፍ የቆመች እየተባለ ሲሟረትባት የነበረች አገርን የኢፌዴሪ ህገመንገስት  አገሪቱን ቀኝ ኋላ   ወይም ፈረንጆች (U turn) እንደሚሉት እንድትዞር በማድረግ ከከፋ ጭቆናና ስር ከሰደደ  ድህነት  ወደ ነጻነትና ዕኩልነት፤ በኢኮኖሚውም ረገድ ወደ  ፈጣን ልማት አንባነት እንድትሸጋገር አስችሏታል። ዛሬ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት ይዟል፤ ፈጣን ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በመረጋገጥ ላይ ነው። ይህ ከየትም የመጣ ሳይሆን ህገመንግስታችን  ስጦታ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።

አንዳንድ ሰዎች  ህገመንግስትን ማክበርን ብቻ  እንደ ግዴታ አድርገው በመቁጠር ስለሌላው  እንደማያገባቸው አድርገው ይናገራሉ። ይሁንና ህገመንግስትን ማክበር ብቻ ምልዑ አያደርግም። ህገመንግስትን ማክበር አንድ ነገር ቢሆንም  ማስከበርም ሌላው  ትልቅ ጉዳይ ነው። ሕገ-መንግስት ማክበርና ማስከበር  የሁሉም አካላት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መሆን መቻል አለበት። እንደእኔ እንደኔ ህገመንግስትንና የአገር ህልውና አንድና አንድ በመሆናቸው አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ ህገመንግስት ማክበርና ማስከበር እኩል ሃላፊነት አለበት።  

በአገራችን ሕገ-መንግስት የህጎች ሁሉ የበላይ ነው።  ሕገ መንግስቱን የሚቃረን ማንኛውም ሕግ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው፣ ዜጎች የመንግስት አካላት፣ ማህበራትና ድርጅቶች ለዚህ ህግ  ተገዢ መሆን እንዳለባቸው በሕገ መንግስቱ በግልጽ ተደንግጓል። በሕገ-መንግስት ከተደነገገው ውጭ ማንኛውም አካል ሁሉ የመንግስትን ስልጣን መያዝ እንደማይቻል  በግልጽ ሰፍሯል። በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግስት አካላት ከሕግ በታች የሆኑበት፣ ግጭትና ጦርነት ማካሄድ ሳያስፈልግ በምርጫ ብቻ ወደ ስልጣን የሚመጣበት ስርዓት በአገራችን ዋስትና ያገኘው በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ነው። ይህም ባለፉት 22 ዓመታት በተካሄዱ  አምስት አገራዊ ምርጫ በተግባር ተረጋግጧል። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይሆነናል ያሉትን አካል ወደ ስልጣን ከማውጣት ባሻገር አመኔታ አጥተንበታል፣ የፈለግነውን አላሳካም ያሉትን ተወካይ ከስልጣን ማውረድ እንደሚችሉም በተግባር አሳይተዋል። ለእኔ ይህ ነው ተጨባጭ የፖለቲካ ስልጣን ማለት።   

የኢፌዴሪ ህገመንግስት በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ትግል እውን የሆነ ህገመንግስት እንደመሆኑ ሁሉ  ለእነዚህ አካላት የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች  መሆናቸውንም እውቅና ይሰጣል። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በማረጋገገጡ ባለፉት 22 ዓመታት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን አሳይተዋል። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መስራችና ባለቤቶች በመሆናቸው በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ  እኩል ተዋናዮች ብቻ ሳይሆኑ ፍትሃዊ ተጠቃሚዎች ጭምር ናቸው።  

የኢፌዴሪ ህገመንግስት  መግቢያው ላይ የህዝቦችን አንድነትና ፍትሃዊ  ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አንድ ትልቅ አስተሳሰብ ሰፍሯል። አንድ  የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ መገንባት የህገመንግስቱ ዋንኛ ዓላማ ነው። የመጀመሪያው አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በውስጡ በርካታ የስርዓት ግንባታ አጀንዳዎች የያዘ ቢሆንም ጥቂቶችን ወስደን ስንመለከት ዋንኛው ጉዳይ በሕገ-መንግስትና በሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ አገራዊ መግባባት እንዲሁም የጋራ አቋምና ተመሳሳይ አመለካከትን መያዝ ማለት ነው። ሌላው አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ግንባታ ሲባል የጋራ አገራዊ ራዕይ በመላበስና ተመሳሳይ አመለካከት በመያዝ አገራዊ ራዕይን ማሳካት ማለት ነው። አገራችን የቀረፀችው ራዕይ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ራዕዩን ለማሳካት ሁሉም በጋራ የሚረባረቡበት ሁኔታን መፍጠር ማለት ነው።

ከዚህም ባሻገር አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ መገንባት ማለት  በአገራዊ እሴቶች፣ በመሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና በወሳኝ አገራዊ ጥቅሞች ላይ ተመሳሳይ አመለካከትና የጋራ አቋም መያዝንም ያጠቃልላል።  የአገርንና የህዝብን  ጥቅም ማስቀደም፣ ብዝሃነትን መቀበል፣ እኩልነትን ማክበርና በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ሕበረ-ብሄራዊነትን ማጎልበት ላይ የጋራ አቋም መያዝ አንዱ ያጋረ  የፖለቲካ ማሕበረሰብ የመፍጠር ዓላማ ነው። ለአገራችን ፀጥታና ደህንነት ዋስትና በሚሰጡ አገራዊ ፖሊሲዎች ላይ የማይዛነፍ አቋም  የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ መያዝ ይገባል። ለሕገ-መንግስት ተገዢ መሆን ማለት  ህገ-መንግስቱን ማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር ሃላፊነትንም ያካትታል። በመንግስት ጥረት ብቻ   የሕግ የበላይነት የትኛውም አገር  ዋስትና ሊያገኝ አይችልም። በመሆኑም ዜጎች ህገመንግስትን ከማክበር ባሻገር ሌሎች እንዲያከብሩ የማድረግ  ሃላፊንት እንዳለባቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል።   

ሁለተኛው  ጉዳይ ማለትም  አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ግንባታ ዓላማ ከኢኮኖሚያዊ ፍተሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያዘ ነው። ልማታዊ አስተሳሰብን የበላይነት የሰፈነበትና ድህነትን ለማጥፋት በሚካሄዱ አገራዊ የልማት አጀንዳዎች ላይ ዜጎች የጋራ አመለካከት በመያዘ ለልማታዊነት የሚረባረብ ማህበረሰብን መፍጠር ማለት ነው።  በሁሉም አካባቢዎች  ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ላይ ህዝቦች  ተሳትፎ  የሚያደርጉበት  እንዲሁም  ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ነው።  ይህም ማለት  ህብረተሰቡ በልማቱ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ  ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዲሁም በሁሉም አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት ማረጋገጥ መቻል ማለት ነው።

በኢፌዴሪ ህገመንግስት አገራችን በተጨባጭ  ተለውጣለች። ልትበተንና ልትፈርስ የነበረች አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓት ልምድ መቅሰሚያ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ተምሳሌት ለመሆን በቅታለች። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያለሟት ኢትዮጵያን እውን አድርገዋል።  አዲሲቷ ኢትዮጵያም የህዝቦቿን  ፍላጎት ማሳካት ጀምራለች። አሁን ላይ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በህዝቦች መካከል ፍተሃዊ ተጠቃሚነት ማንገስ ስተችሏል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትና እኩልነት  ማረጋገጥ የቻለችው በዚህ ህገመንግስት ነው። በመሆኑም ማንም አገር ወዳድ ዜጋ የህግ ህገመንግስት ማከበር ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እንዲያከብሩ ማድረግ ይጠበቅበታል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy