Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግ፡ የነጻነት አርማ

0 1,225

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግ፡ የነጻነት አርማ

አሜን ተፊሪ

የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ‹‹ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን›› የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ሁለት ድምጾችን እየሰማን ነው፡፡ አንደኛው ‹‹መጀመሪያም አስፈላጊ ያልነበረ አዋጅ ነው›› የሚል ደምጽ ነው፡፡ ሌላው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ይቀበል፡፡ ሆኖም፤ ‹‹ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁን አንዲነሳ መደረጉ ተገቢ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በደንብ የታሰበበበት አይደለም›› ይላል፡፡ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ኢህአዴግ ይህን አዋጅ ያነሳው በውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ የተነሳ ሊሆን እንደሚችልም ይጠቅሳል፡፡ ይህ እርምጃ በውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ የመንበርከክ ልማድ ያልነበረው ኢህአዴግ ዓመሉ እየተቀየረ መምጣቱን የሚያመለክት ‹‹የአደገኛ በሽታ›› ምልክት መሆኑን ይገልጻል፡፡

በበኩሌ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ አስፈላጊ መሆኑን አምናለሁ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ አዋጁ ከታወጀበት ከጥቅምት ወር ቀደም ብሎ ሊታወጅ ይገባው እንደ ነበር የምከራከር ነበርኩ፡፡ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀደም ብሎ ሊነሳ የሚገባው መሆኑን የምቀበል ነኝ፡፡ በመሆኑም ቀደም ብሎ ሊታወጅ የሚገባው መሆኑን እና ቀደም ብሎ ሊነሳ የሚገባው መሆኑን አምናለሁ፡፡

ነገር ግን በሁለቱም የታቃውሞ አቋሞቼ ውስጥ ጎልቶ የሚታየኝ ጉዳይ አለ፡፡ ከእኔ አቋም አንጻር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማወጅ ረገድ ኢህአዴግ መዘግይቱም ሆነ፤ ከአንዳንዶች አቋም አንጻር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀደም ብሎ መነሳቱ የሚያመለክተኝ መሪው ድርጅት ለነጻነት ያለውን ትልቅ ሥፍራ ነው፡፡ ኢህአዴግ አሁን አዋጁን በማንሳት ብቻ የተገለጸ አቋም አይደለም፡፡ የአዋጁ እንዲራዘም የሚያደርግ ውሳኔ ሲያሳልፍም፤ መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎችን ቀደም ሲል እንዲነሱ አድርጓል፡፡ በዚህም ለነጻነት ያለውን ክብር አረጋግጧል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የሐገራችን የነጻነት እና የመብት እሴቶች ጠባቂዎች ሊሆኑ የሚገባቸው ወገኖች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችል ቁመና አለመያዛቸውን የሚያሳዩ ጉዳዮች ብቅ ሲሉ እንመለከታለን፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና የህዝብ እንደ ራሴዎች ጭምር ናቸው የአዋጁን መነሳት ሲቃወሙ የተመለከትነው፡፡ የእነዚህ ወገኖች አስተያየት ከቀና ህሊና የመጣ ሐሳብ መሆኑን አልጠራጠርም፡፡ እነሱ የኢህአዴግን አቋም በደንብ የተጠና አለመሆኑን እንደ ጠረጠሩት እኔም የእነሱ አቋም በደንብ የተጤነ አቋም አለመሆን በእርግጠኝነት ለመናገር እችላለሁ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ሚና አላቸው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ የዕለት ተዕለት አሰራር እና አፈጻጸም እግር በእግር እየተከተሉ፤ ገዢው ፓርቲ እውቆ በድፍረት ወይም ሳያውቅ በስህተት የሚፈጽመውን የህግ ወይም የመብት ጥሰት በማጋለጥ አደብ እንዲገዛ የማድረግ፤ ህግን ተከትሎ እንዲራመድ የማድረግ በጎ ተጽዕኖ ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ዋስትና እንዲኖረው ለማድረግ ይችላሉ፡፡ ሆኖም፤ በሌሎች አቋሞቻቸው የምናውቃቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት አስመልክተው የሰጡት አስተያየት ከመነሻዬ እንደጠቀስኩት ‹‹ቀድሞም ሊታወጅ የማይገባው አዋጅ ነበር›› የሚል ነው፡፡ ይህ ለህዝብ ጥቅም የሚቆሙ ኃይሎች አለመሆናቸውን የሚያሳይ አቋም ነው፡፡ አቋማቸው አዲስ አይደለም፡፡ እዚህ የተወሳውም አዲስ አካሄድ በመሆኑ አይደለም፡፡ ይልቅስ ነባር መልካቸውን ጠብቀው እየተጓዙ መሆናቸውን ለማሳየት የሚያግዝ በመሆኑ የተወሳ ነጥብ ነው፡፡ ሆኖም አቋማቸው በሐገር ህልውና ጭምር ለመደራደር ወደ ኋላ የማይል መሆኑን የሚያሳይ አቋም ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው የህዝቡ አብሮ የመኖር እሴት እየተሸረሸረ፤ መደበኛ የህይወት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ፤ ከአንድ ክልል ወደ ሌላው ለመሄድ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ፤ በየክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ስጋት ላይ ወድቀው ከቤት በቀሩበት፤ በስንት ማባበል እና ሸንጎበት ማሸት የመጡ የውጭ ባለሃብቶች የማምረቻ ተቋማት በእሣት መጋየት በጀመረበት ወዘተ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ አደጋው እንኳን በሐገር ቤት ለምንገኘው ለዜጎች ቀርቶ ሩቅ ባሉ ወዳጆቻችን ዘንድ መመለሻ ከሌለው ነጥብ መድረሳችንን ይናገሩ በነበረበት ሁኔታ ውስጥ የታወጀ አዋጅ ነው፡፡ የአስቸኳ ጊዜ አዋጁ ከጥቀምት በፊት ሊታወጅ የሚገባው ነበር ያሰኘኝም ይኸው ነው፡፡ ሆኖም ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ስለአዋጁ መነሳት ከአሜሪካ ድምጽ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹መጀመሪያም መታወጅ ያልነበረበት አዋጅ ነው›› ነበር ያሉት፡፡

ያ ችግር እንኳን የሐገሪቱን ሁኔታ ሥራዬ ብሎ ለሚከታተል እና በሥልጣን ተስፈኝነት ለሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት አመራር ቀርቶ፤ ለወትሮው ፖለቲካ ሲጠበስ የማይሸታቸው ሰዎች እንኳን የሀገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖባቸው ነበር፡፡ እውነት ለመናገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል ከጭንቀት የገላገለ አዋጅ አልነበረም፡፡ በመሆኑም፤ ባለስልጣናቱ ይህን አዋጅ በማወጃቸው ሳይሆን ከቀደም ብለው ባለማወጃቸው ሊወቀሱ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡

እንዲህ እንደ ዶ/ር በየነ ያሉ ደንታ ቢስ ፖለቲከኞች፤ እንኳን ለነጻነታችን፤ በጭቆና የምንኖርባትን እና በስማችን የምትጠራ ሐገርን ለማቆየት የሚችሉ መሆናቸውን እንድናምን የሚያደርጉን አይደሉም፡፡

ከአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን እና የህዝብ እንደራሴዎች የሰማናቸው አስተያየቶችም ለተመሳሳይ ትዝብት የሚያጋብዙን ናቸው፡፡ የመገናኛ ብዙሃን እና የህዝብ እንደራሴዎችለመብቶች እና ነጻነቶች መከበር ዋስትና የሚሆን አቋም ሲያራምዱ፤ የገዢው ፓርቲ ከአስተዳደራዊ ፋይዳ አንጻር እየመዘነ መብቶችን የሚያጣብብበት ዕድል እንዳይኖር ዘብ ሆነው ሊሰሩ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ኢህአዴግ የመንግስት አመራር የያዘ በመሆኑ፤ በአስተዳደር ጣጣዎች ተሸንፎ፣ ነገር ለማሳለጥ ብሎ፣ ሰንፎ ወይም ከሽፎ ከመንገድ ሊወጣ ይችላል፡፡

የገዢው ፓርቲ፤ የገዢ ፓርቲነቱ በአንድ ጊዜ ተጫዋች እና ዳኛ የመሆን ዕዳ የሚያሸክመው በመሆኑ፤ የሁለቱ ሚናዎች ተጣራሽ ባህርያት አሳስተውት ወይም ከመንገድ አስወጥተውት ስህተት የሚሰራበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ይህ አደጋ ያልዳበረ የዴሞክራሲ ባህል እና ተቋማት በሚኖሩበት ሁኔታ ሁልጊዜም ድርስ ሆኖ የሚኖር አደጋ ነው፡፡ በዚህ መሰል ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ፓርቲ በመሆኑ ከዚህ አደጋ የሚጠብቁት ንቁ የመገናኛ ብዙሓን እና የህዝብ እንደራሴዎች ያስፈልጉታል፡፡ በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት ለፖለቲካ ገጽታው ብሎ የማይቀበልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ በመሆኑም፤ የሐገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን አዋጁ እንዲታወጅ በመገፋፋት፤ አዋጁ ከታወጀ በኋላም አፈጻጸሙ ህግን የተከተለ መሆኑን በመመርመር ቁጥጥር ማድረግ፤ አደጋው ሲወገድም አዋጁን እንዲያነሳ መጎትጎት የሚገባቸው ወገኖች አዋጁን ለምን አነሳህ ብለው ሲሞግቱት ማየት ግራ አጋቢ ነው፡፡

ይህን የምለው ‹‹የሐገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን አዋጁ እንዲታወጅ ወይም ጸንቶ (እንዲቆይ) መገፋፋት›› አለባቸው ማለቴን ዘንግቼው አይደለም፡፡ ምናልባት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ካላቸው ‹‹አንዳንዶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ እንዲህ እናደርጋለን እያሉ ባለበት ሁኔታ ይህን አዋጅ ማነሳት ለምን አስፈለገ?›› ከሚል ድፍን እና ደካማ አስተያየት ተሻግረው፤ የአዋጁን ጸንቶ መቆየት አስፈላጊነት ማስረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲሁም ‹‹ሰሞኑን የሚዩት ሁኔታዎች ደስ የማይሉ ናቸው›› በሚል አዋጁ ጸንቶ እንዲቆይ መጠየቅ ወንወጀል ባይሆንም በዚህ ሐገር ያለው ነጻነት እና መብት ከኢህአዴግ የተሻለ ዋስ የለውም ለማለት የሚገፋፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

በርግጥ ‹‹ሰሞኑን የሚዩት ሁኔታዎች ደስ የማይሉ ናቸው፡፡›› ሆኖም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ ወይም ጸንቶ ሊቆይ የሚገባው ‹‹ሰሞኑን የሚዩት ሁኔታዎች ደስ የማይሉ ናቸው›› በሚል ሳይሆን፤ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 እንደተገለጸው፤ ‹‹ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን›› ብቻ ነው፡፡ ‹‹ሰሞኑን የሚዩት ሁኔታዎች ደስ የማይሉ ሁኔታዎች ናቸው›› ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን፤ እንዲሁም በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻሉ ችግሮች መከሰታቸውን ማሳየት ይኖርብናል፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀንቶ እንዲቆይ የሚጠይቅ ሰው፡፡

አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ይኖርብናል፡፡ እንኳን ተቋማዊ ሁኔታው ደካማ በሆነበት የአምባገነን አገዛዝ ባህል ለረጅም ዘመናት ፀንቶ በኖረበት ሐገር፤ የዳበረ ዴሞክራሲ አላቸው በሚባሉት ሐገሮችም ነጻነት እና መብቶች የዜጎች ሐብት ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉት ዜጎች በማያንቀላፋ ትጋት ‹‹ነጻነት እና መብቶች››ን መጠበቅ ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ ነጻነት እና መብት ተከብረው እንዲኖሩ እንዲህ ያሉ ታጋይ ዜጎች ያስፈልጉናል፡፡ ስለሆነም መቼም መች ቢሆን በማናቸውም ህዝባዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚያደርግ ዜጋ ወይም ባለስልጣን ለነጻነት እና ለመብቶች የሚያደላ አዝማሚያ ይዞ መሥራት ይኖርበታል፡፡

ሐገራችን አሁንም በከፋ ድህነት ውስጥ የምትገኝ ሐገር ነች፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱ የደህነት ሸክማችንን ገና አላራገፈውም፡፡ አሁንም ድህነት ድርቅ እንዳጎበጠን የምንኖር ህዝቦች ነን፡፡ ከዚህ ድህነት በፍጥነት መውጣት ይኖርብናል፡፡ አሁን ያለው ድህነት እንደ ድሮው በዓለት ላይ የቆመ ድህነት አይደለም፡፡ በየጊዜው የሚናድ በድቡሽት ላይ በአሸዋ ላይ የቆመ ድህነት ነው፡፡ ይህ ድህነት በአስቸኳይ ካልተቀረፈ ጦሱ አደገኛ ነው፡፡ ከትንሿ ብሄራዊ ዳቦ ለመሻማት ስንሞክር እርስ በእርስ የምንበላላበት አስቀያሚ የዕልቂት ምዕራፍ ውስጥ የምንጋባት ዕድል አለ፡፡ የገዢው ፓርቲ የተጨባጭ ሁኔታ ንባብ እንዲህ ያለ ነው፡፡

በዚህ ግንዛቤ እና ስሜት ውስጥ ሆነን የመንገድ ሥራዎችን ወይም ሌሎች ከፍተኛ የስራ ዕድል የመፍጠር ሚና ያላቸውን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ስንገነባ ‹‹የወሰን ማስከበር›› ጥያቄ ይዞ ከፊታችን የሚቆም ሰውን ጉዳይ የምንመለከተው እንዴት ነው? ይህ ሰው የድህነት ዘበኛ ነው? ፀረ ልማት ነው? ወይስ ጉዳዩ በህግ አግባብ ሊታይ የሚገባው ተገቢ ጥያቄ ያለው ዜጋ ነው? እነዚህ ሁለት ወደረኛ የሆኑ ጥቅሞች በዕኩል ሚዛን ሊታዩ የሚገባቸው ናቸው፡፡ እዚህ ውስጥ አንተ ከሰፊው ህዝብ ትበልጣለህ?›› ተብሎ ሊገፋ የሚችል አይደለም፡፡  ተጨባጩ ሁኔታ እና ጥድፊያው ‹‹አንተ ከሰፊው ህዝብ ትበልጣለህ?›› ወይም ሌላ ነገር ብሎ ለመራመድ የሚገፋፋ መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ህገ መንግስታዊ ድንጋጌው በዚህ መንገድ ለመሄድ አይፈቅድልንም፡፡ ገዢው ፓርቲ በማናቸውም መሰል ጉዳዮች ጫና የዜጎችን ነጻነት እና መብት እንዳይጋፋ በንቁ አይን መከታተል ይኖርብናል፡፡ ሁልጊዜም ለመብት እና ለነጻነት በሚያደላ አስተያየት ጉዳዮቹን የመመዘን ዕድል የሚኖረው፤ ከአስተዳደራዊ ጣጣ እና ግፊት ወጣ ብሎ ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ያላቸው ዜጎች እና ተቋማት ናቸው፡፡ ሚዛን እና ቁጥጥር የሚሉት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መርሆ ትርጉሙ ፍንትው ብሎ የሚታየን በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ ሆኖም አሁን የምንመለከተው ሁኔታ ለነጻነት እና ለመብት የሚያደላ አቋም ይዞ የተመለከትነው መንግስት ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፀንቶ እንዲቆይ የሚጠይቅ ሰው፤ መብቶች እና ነጻነቶችን የሚገድብ አዋጅ ፀንቶ እንዲቆይ እየጠየቀ መሆኑን ማሰብ አለበት፡፡ ከነገረ ቀደም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታዋጀው መንግስት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ሳይኖሩ ሥራውን በተረጋጋ ሁኔታ የመሥራት ዕድል እንዲኖረው አይደለም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታዋጀው መብቶች እና ነጻነቶቻችን የሚከበሩበት ሥርዓት አደጋ ላይ በመውደቁ እና በመደበኛ አሰራር የተከሰተውን ችግር ለመቋቋም የምንችልብት ዕድል በመጥፋቱ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታዋጀው ለነጻነት እና ለመብት መከበር መደላልድል ለመፍጠር ነው፡፡

ሌላም እዚህ ላይ መታወስ ያለበት ነጥብ አለ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥራውን በአግባቡ ለማይሰራ ሥራ አስፈጻሚ የሥቃይ ማስታገሻ መድሃኒት ሆኖ የሚታይ አይደለም፡፡ ሥራ አስፈጻሚው የየአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብርድ ልብስ ተከናንቦ እንዲተኛ ለማድረግ አይደለም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚያስፈልገው ሁኔታዎችን ወደ መደበኛ መስመር ለማስገባት ፋታ ለማግኘት እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መደበኛ አሰራር ለማድረግ አይደለም፡፡ ስለሆነም ዋነኛ ትኩረታችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀንቶ መቆየት የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ላይ አይደለም፡፡ ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ችግሮችን በማስወገድ ሥራ ላይ ነው፡፡

ኢህአዴግ ከተከሰተው አመጽ ጋር ያለው ግንኙነት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነውን ሁኔታ ለመግለጽ ያህል፤ ‹‹ኢህአዴግ የአመጹ ደጋፊ እና ተቃዋሚ ነበር›› ማለት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል፤ የችግሩ ምንጭ የራሱ ችግሮች መሆናቸውን ተቀብሏል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ህዝቡ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ መሄዳቸውን አስቀድሞ የተረዳው እና የገለጸው ራሱ ኢህአዴግ ነበር፡፡ በምርጫ ባሸነፈ ማግስት ‹‹ህዝቡ እኛን የመረጠው የልቡን ስለሞላንለት አይደለም፡፡ ሕዝቡ ድምፁን የሰጠን የበሰለ ቅሬታውን በጉያው ይዞ፤ ከእናንተ የተሻለ ሌላ አማራጭ የለኝም ብሎ በሆደ ሰፊነት የሰጠን ድምጽ ነው›› ብሎ በይፋ አውጇል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሩ ዋነኛ መገለጫ የሆነው ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑን ተረድቶ፤ በዚህ ችግር ላይ በሙሉ ልብ ለመዝመት ቆርጦ ሲነሳ የህዝቡ ድጋፍ ወሳኝ ነበር፡፡ በመሆኑም፤ የህዝቡ ተቃውሞ ለዚህ ትግል አጋዢ እንጂ አደናቃፊ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በተወሰነ ደረጃ የህዝነቡን ተቃውሞ የትግሉ ማቀጣጠያ ነዳጅ ሊያደርገው ይፈልግ ነበር፡፡ ችግሩ የመጣው የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች በነገሩ ገብተው ተቃውሞውን ከሰላማዊ እና ህጋዊ ማዕቀፍ ሲያወጡት ነው፡፡ በመሆኑም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታዋጀው ይህን ትግል ለማጠናከር እንጂ የዜጎችን ትግል ለማፈን አይደለም፡፡ ስለሆነም ዋና ሥራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀንቶ እንዲቆይ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን እየፈለጉ የአዋጁን ዕድሜ ማራዘም አይደለም፡፡ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ እንጂ…..›› በሚል ወይም በሌላ ምክንያት ሁከት ለማስነሳት የሚዝቱ ሰዎች ወደፊትም ሊኖሩ እንደሚችሉ የታመነ ነው፡፡ የሻአቢያ ጎረቤት የሆነ ሐገር ከዚህ ዓይነት ችግር ሊወጣ የሚችልበትን ዕለት እየናፈቀ ለመኖር የሚገደድ ሐገር ይሆናል፡፡ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ እንጂ…..›› የሚሉ ወገኖች እንደ ክብሪት ሁከት ለመቀስቀስ የሚጠቀሙበትን እኛም ኣሳምረን የምናውቀውን፤ አመነን ለህዝብ ይፋ ያደረግነውን ችግር ማስወገድ መሥራች እንጂ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ እንጂ…..›› የሚሉ ወገኖችን ዛቻ በዚህ ስሌት ማግባት የለብንም፡፡ ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ችግሮች አስቀድመን በመለየት፤ ከመደበኛ አሰራር የሚወጡ ችግሮች እንዳይሆኑ ወይም ችግሮች እንዳይፈጠሩ መሥራት ይኖርብናል፡፡

የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መንግስት ሁሌም የሚናጥ ሁሌም ጥቅሞችን ለማቻቻል ቀን ከሌት የሚሰራ፤ ያለፋታ የሚሞገት እና የሚነቀፍ መንግስት መሆኑን ማመን ይኖርብናል፡፡ ለአስተዳደር ቀላል የሆነው፤ የመጨረሻው ቀን እስኪመጣ ሳይጠየቁ እና ሳይሞገቱ ለመኖር የሚቻለው በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶች ለማስተዳደር ቀላሉ መንግስት ጨቋኝ መንግስት ነው የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ አድርግ-አታድርግ ብሎ መተኛት የሚቻለው በአምባገነን መንግስት አስተዳደር ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ መንግስት ሁሌም እየባነነ የሚኖር መንግስት ነው፡፡ ይሞገታል ይፈተናል፣ ይገፋል፣ ይሰደባል በህዝብ ድምጽ ከስልጣን ይገዳል፡፡

ኢህአዴግ የታገለው እንዲህ ዓነት መንግስት በኢትዮጵያ ምድር እንዲቆም ነው፡፡ እልፍ ሰማዕታት በበየጥሻው የወደቁት የኢትዮጵያን ህዝብ ለ17 ዓመታት ከዘለቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህይወት ለማላቀቅ ነው፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዲነሳ የወሰነው በውጭ ኃይሎች ግፊት ሳይሆን ሺህ ሰማዕታት ህይወታቸውን የሰውለትን ዓላማ ለማስከበር ነው፡፡ የኢህአዴግ ውሳኔ ‹‹በኢትዮጵያ ምድር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊ የሚያደረግ ችግር አለመኖሩን የሚያሳይ በመሆኑ፤ በዲፕሎማሲው መድረክ ወቀሳን የሚያስከትል ችግር መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ የጠነሳ አይደለም፡፡ የተነሳው በሐገራችን ከመደበኛ አሰራር ሊሸፈን የማይችል ችግር አለመኖሩ በግልጽ የሚታይ በመሆኑ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊታወጅ ወይም ሊጸና የሚችለው ለምናልባት ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል ስሌት ሳይሆን፤ በተጨባጭ ባሉ ችግሮች መነሻ ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ የነጻነት አርማ ነው የሚያሰኘኝም ይኸው ነው፡፡ ኢህአዴግ ያን ያህል ግፊት ሳይኖርበት የታገለለት ዓላማ የኢትዮጵያ ህቦችን መብት ለማስከበር እንጂ መብታቸውን ለማፈን አለመሆኑን የተረዳ ፓርቲ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ጥቅም ለማስከበር የቆ ,መ ፓርቲ መሆኑን አስመስክሯል፡፡    

            

    

 

    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy