Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የስርዓቱ ስኬቶች ሲጨለፉ

0 373

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የስርዓቱ ስኬቶች ሲጨለፉ

                                                     ታዬ ከበደ

አገራችን እየተከተለች ያለችው ፌዴራላዊ ስርዓት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የአንድነት መሰረት ነው። ስርዓቱ ህዝቦች ከመለያየት ይልቅ የአንድነት መስመርን አጥብቀው የያዙበት፣ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ሆኖ ዛሬም ድረስ የዘለቁበት ነው። ሆኖም ፅንፈኞች እርስ በእርስ የሚያደርጉት ሽኩቻ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽርና አንድነትን የሚያላላ በመሆኑ፤ መፍትሔው ያለው የአገራችን ብቸኛ መድሃኒት የሆነውን ስርዓት በመገንዘብ ወደፊት ማስቀጠል ብቻ ነው።

እናም በዚህ ፅሁፍ የፌዴራላዊ ስርዓቱን ስኬቶች በመጠኑም ቢሆን ጨልፎ ማየት ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው በጋራ መኖር የሚችሉበትን ባህል እያዳበሩ መጥተዋል። በብዙ ቋንቋዎች መናገር ሳያስማማ እንደሚቀር ይመስላቸው ለነበሩ ሰዎች ከ80 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች እየተነጋገሩ መግባባት እንደሚቻል በኢትዮጵያ ታይቷል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ብዙ እምነቶችና የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት የሚከተሉ ሆነው ሲያበቁ በተግባር ግን ተከባብረው መኖር እንደሚቻል ያሳዩ የፌዴራል ስርዓቱ ልዩ መለያ ሆነዋል ማለት ይቻላል።

እርግጥም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መግቢያ ላይ የሰፈረው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ስምምነት በተጨባጭ እየተሳካ እንደሆነ ያለፉት 26 ዓመታት ጉዞ በተጨባጭ ያሳየ ይመስለኛል። ዛሬ ሀገራችን ውስጥ ብዝሃነት የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መገለጫ ሆኗል። ይህም ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዝሃነትን አስመልክተው ይራመዱ የነበሩ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ሙሉ ለሙሉ የቀየረ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውሰጥ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአጋርነት ታሪክ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና በማግኘታቸው የአብሮነቱ እሴቶች ሊሆኑ ችለዋል። አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ የተቻለበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ዛሬ በኢትዮጵያ የመገንጠል መብት ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ቢያገኝም፤ የማኅበረሰብ ጥያቄ መሆኑ እያበቃለት ይገኛል—በጊዜ ሂደት የነበሩት አስተሳሰቦች ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ እየተመዘኑ በመክሰም ላይ መሆናቸውን መናገር የሚቻል ይመስለኛል።  

እርግጥ የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ በወደቀበት ማግስት የነበሩት የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳንዶቹ ያነገቡት ዓላማ መገንጠልን እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም አብሮ በመኖር ሂደት የተገኘ ጥቅም እያደገና እየሰፋ ስለመጣ የመገንጠል አስተሳሰብ ማኅበረሰባዊ መሰረት አለው ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም። ለነገሩ አንድ ህዝብ መብቶቹ ተከበረው በጋራ ተጠቃሚነት ውስጥ እስካለ ድረስ ስለ መገንጠል ማሰቡ ሚዛናዊ ዕይታ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም።

ያም ሆኖ የደርግ መንግሥት በወደቀ ማግስት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው አፈ ታሪክ መሰረት የሌለው ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ህዝቦች ብዝሃነት ከግምት ውስጥ ያላስገባም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብዝኃነት የሀገራችን ጉልበትና አቅም ሆኗል። ሀገራችን ውስጥ ያሉት የተለያዩ ማንነቶች በተናጠል ከሚያስገኙት ጥቅም ይልቅ በጋራ የላቀ ጥቅም እንደሚያገኙ አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት ማረጋገጥ ችለዋል። ህብረታቸውን የሚፈታተንና ሰላማቸውን የሚያናጋ ኃይል በጋራ ታግለው ማሸነፋቸው የዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅ ነው። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የታየውን የብዝሃነት ህብረትን እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን ከፍተኛ መነቃቃትና ተነሳሽነት ብቻ መጥቀሱ ከበቂ በላይ ማሳያዎች ይመስሉኛል። ሃምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰው ሸክም አለመሆኑን ያረጋገጡ የብዝሃነት ሃይልና ጉልበት መገለጫዎች ናቸውና። የኢትዮጵያ ህዝብ በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ነገር ግን እንደ አንድ ማኅበረሰብ በአንድነት ለልማትና ዕድገት የሚነሳ ህዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። አዎ! ብዝሃነታችን ሀገራችን በዓለም ፊት ያላትን ገፅታ እየቀየረ ነው።

ምንም እንኳን አንዳንዶች በብሔርና በጎሣ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ቢገልፁም፤ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ የሚያሳየው ግን ከእነርሱ ምልከታ የተለየን ሁኔታ ነው። ብዝሃነት የመጪው ዘመን ዕድላችን በር መክፈቻ ሆኗል። ሆኖም በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ብዝሃነትን ዕድል ማድረግ የሚቻለው ማንነቶች የሀገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ ትምህርት ሰጥተው አልፈዋል።

በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ተከታታይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ የብዝሃነት አያያዝ ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ምርጥ ትምህርት የሚሰጥ ሆኗል። በዚህም ብዝሃነት በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ ሊሆን ችሏል።

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የብዝሃነት መሰረቶች የፌዴራላዊ ስርዓቱ ምሶሶና ማገር ናቸው። መሰረቶቹም በስርዓቱ የፖለቲካ ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ናቸው።  በኢፌዴሪ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው አካሄድም ይህንኑ ሃቅ የሚደግፍ ነው።

የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት በብዝሃነት ውስጥ ላሉ ማንነቶች የሰጠው መብት ከብዙ ፌዴሬሽኖች ጋር ሲነጻጸር የላቀና ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው። ይህም የፌዴራላዊ ስርዓቱ ዓይነተኛ ስኬት ነው ማለት ይቻላል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦላቸዋል። በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረትም ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት እንዳላቸውም በገሃድ እየታየ ይገኛል።

የልማት እንቅስቃሴው ዋና ዓላማም የዜጐችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት በመሆኑ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ስለመሆናቸው ከጋራ መግባባት ላይ  ተደርሷል። ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ባለፉት ሥርዓቶች ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፍትህ ሳያገኙ የቆዩና በዚህም ምክንያት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝ}ቦች በመንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ሰጥቷል።

በዚህ መሠረትም የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል። እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትንም ይጨምራል።

የግንቦት ትሩፋቶች የሆኑት የህገ መንግሥቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ድንጋጌዎች ተጠቃለው ሲታዩ በነጻ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ወሣኝነትን የሚያመለክቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሀዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን የሚያመለክቱ ናቸው። የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ መሆናቸውንም ያሳያሉ። የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የልማት እንቅስቃሴዎች ዋና ዓላማ መሆን እንዳለበት ከህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም።

የክልሎችን እኩል የመልማት እድል ማረጋገጥና ልዩ ድጋፍ መስጠት መገንባት ለሚፈለገው በነፃ ፍለጐት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው።

በራስ አቅምና በራስ ፍላጐት ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ለአገሪቱ ዘላቂ ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ወሳኝ መሆኑን የህገ መንግሥቱ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። ህገ መንግሥቱ ልማት የመብት ጉዳይ መሆኑን ይገልጻል። የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም የዜጐችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል መሆኑ ተደንግጓል። በድንጋጌው መሰረትም ሁሉም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኗል። ይህን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት ስርዓቱን መጠበቅና መንከባከብ የግድ ይላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy