Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኋሊት ላለመመለስ

0 362

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኋሊት ላለመመለስ

                                                         ደስታ ኃይሉ

በማደግ ላይ ባለ አገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነትንና የሙስናን አስተሳሰብና ተግባር በሂደት መቅበር ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግም መንግስት ከሚያደርገው የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነትና የፀረ-ሙስና ህጋዊና አስተዳደራዊ ዘመቻዎች ባሻገር፤ አስተሳሰቦቹንና ተግባሮቹን የሚጠየፍ ማህበረሰብ መኖር አለበት። አስተሳሰቦቹና ተግባሮቹ በግለሰብና በህዝብ እንዲሁም በአገር ላይ የሚያስከትሉን አደጋ ከፍተኛ ነው። ስለሆነም በህብረተሰቡ ውስጥ መፈጠር ስለሚገባው የአስተሳሰብ ለውጥ ማተኮር ተገቢ ነው።

ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና የአገር ልማትና እድገት ማነቆ ናቸው። በድህነት ውስጥ የሚማግዱን ቋያ እሳቶች ናቸው። ቋያ እሳቶቹ የኋሊት የሚመልሱን ናቸው። ወደ ድህነት መልሰው የሚከቱን ናቸው። እንደሚታወቀው ሁሉ እዚህ ሀገር ውስጥ የተመሰረተው ስርዓት ድህነትን እየቀረፈ ነው።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች፡፡ በዚህም ከሰሃራ በታች ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ስፍራ ትገኛለች፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢፌዴሪ መንግስት በሀገራችን የተፋጠነ ልማት ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመንደፉም ባሻገር፤ በተግባር መተርጎም መቻሉ እንደሆነ ከማንም ከማንም የሚሰወር ጉዳይ አይደለም፡፡

በርግጥ በሀገራችን እየተመዘገበ ለሚገኘው ለውጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ጉዳይ የጠራ መስመር የያዘ፣ ሀገራዊውን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ በተግባር ላይ የሚያውል አመራርና በህዝባዊ ተሳትፎ የተደገፈ አቅጣጫን የሚከተል የልማታዊ መንግስት አካሄድ የመኖሩ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ታዲያ የኢፌዴሪ መንግስት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ባለፉት 26 ዓመታት በፌዴራላዊ ስርዓቱ ድህነትን መቅረፍ ችሏል።  

የኢፌዴሪ መንግስት የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመቅረፅ የፀረ ድህነት ትግሉን ያቀጣጠለው መንግስታችን ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ፈጣንና ተከታታይ ልማት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን መንግስት የበለጸጉት  ሀገሮች  ለመልማት  ባደረጉት  እንቅስቃሴ  በዓለማችን  ሥነ ምህዳር  ላይ በፈጠሩት  ቀውስ  ሳቢያ  በሚፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት የተለያዩ አህጉሮች  በድርቅ  አደጋ ይጠቃሉ፡፡  ከእነዚህም ውስጥ  እንደ አፍሪካ  ያሉ ያላደጉ አህጉሮች ባልፈጠሩት ችግር ግንባር ቀደም ሰለባ ይሆናሉ፡፡  በተለይም  የምስራቅ አፍሪካ  ሀገሮች  የችግሩ  ተጠቂዎች  ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በዚህ የበለጸጉት ሀገሮች  በፈጠሩት የአየር መዛባት  ምክንያት  በድርቅ  የምትጠቃው  ሀገራችን፤ ከድህነት ገና ሙሉ ለሙሉ ያልተላቀቀች  በመሆና የአየር ንብረቱ  የተለየ ክስተት  ሲያሳይ  በአንዳንዱ ዝናብ  አጠር  አካባቢዎች የምግብ  እጥረት  መከሰቱ የግድ ነው፡፡

ምንም  እንኳን  ድርቅና  ረሃብ  በአመዛኙ  በተፈጥሮ  የአየር  መዛባት  ምክንያት  የሚፈጠሩ  ቢሆኑም፤ ድርቅ በዝናብ  እጥረት   ሳቢያ  የሚፈጠርና  ጊዜያዊ  የምርትና  ምርታማነት  መስተጓጎልን  ሊያስከትል  የሚችል  ችግር ነው፡፡  

ረሃብ ግን በተከታታይ  በሚፈጠር ድርቅ ሳቢያ በሚከሰት  የምግብ  እጥረት  ህብረተሰቡ  የሚላስና  የሚቀመስ  ሳይኖረው  በመቅረቱ  ለሞት  የሚያበቃ  ችግር  መሆኑ  ይታወቃል፡፡ እርግጥ ከሀገራችን ተጨባጭ  ሁኔታ  አኳያ  ድርቅ  እንጂ  ረሃብ  አልተከሰተም፡፡ ይህም መንግስት ድህነትን ለመቀነስ ያደረገው ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ያሳየናል፡፡

ይህ የተፈጠረው ድህነትን የመቅረፍ አቅም በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና ተግባሮች ሊስተጓጎል አይገባም፡፡ ዛሬ በአገራችን በእንቅፋትነት የሚታወቀው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ከድህነት ጋር የጀመርነውን ትግል ያስተጓጉላል። እናም ትናንት ያልተሰበሰቡት ኪራይ ሰብሳቢ እጆች ዛሬ ላይ ሊሰበሰቡ የግድ ይላል። አሊያ ግን አገር ‘እንደ ግመል…’ የኋሊት ልትንሸራተት ትችላለች።

ይህን ለመከወን ደግሞ መንግስት ላይ ብቻ ሁሉንም ነገር መጣል አይገባም—በፖለቲካው መስተጋብር ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ በእሳት ውስጥ እየተፈተነም ቢሆን የበኩሉን ጠጠር መወርወር ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን እንዲያው ለታይታ ብቻ የሚከናወን ድርጊት በአንድ እጅ ማጨብጨብ አሊያም አንዲት ልጃገረድን በጨለማ ውስጥ እንደ መጥቀስ የሚቆጠር ይመስለኛል።

በአጭሩ የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ተግባርን ለማድረቅ የላቀ ቁርጠኝነት በሁሉም ዘንድ መኖር አለበት ለማለት ፈልጌ ነው። ይህም ያልተሰበሱትን ኪራይ ሰብሳቢ እጆችን ለመሰብሰብ የሚያስችል ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና አስተሳሰቦች የአገራችንን ነፃ ገበያ ሥርዓት እየተፈታተነው ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡን ለማራመድ የተዘረጉት እጆች ሊሰበሰቡ ባለመቻላቸው፤ አደጋው ምጣኔ ሐብታችን አሁን ካለው ፍጥነት በተሻለ ሁኔታ እንዳያድግ ብሎም ለፀረ- ዴሞክራሲያዊነት በር የሚከፍት ሁኔታን ሲፈጥር መቆየቱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ‘የእንዝረፍ’ ቁርኝትን ይፈጥራሉ። ታዲያ በእንዲህ ዓይነቱ ‘ዝረፍና ልዝረፍ’ የሚል ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ሲሰፍንም በፖለቲካው ላይ የራሱን ጫና ማሳረፉ አይቀርም። ይኸውም ማንም ተጠቃሚ የማይሆንበትን “የእከክልኝ ልከክልህ”ን ድምር በፖለቲካው ውስጥ ፀረ- ዴሞክራሲያዊነት እንዲያብብ ያደርጋል።

በመሆኑም ከዚህ ጎታች ባቡር ላይ ተጎታች የሆኑትን የትምክህት፣ የጠባብና የአደርባይነት ኃይሎችን ማንጠባጠብ ይገባል። በአስተሳሰቡ ውስጥ ያሉ እጆችም ቢሆኑ መሰብሰብ ይችሉ ዘንድ አስተማሪ የሆነ ርምጃ በመውሰዱ ረገድ ሊዘገይ አይገባም ባይ ነኝ። እርግጥ ዛሬ ሀገራችን ውሰጥ እያንዳንዱ ሰው በልማት ውጤቱ መጠን ሀብት የሚያፈራበት ሁኔታ አለ፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ሀብት፣ ጉልበትና ዕውቀት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በልማቱ ላይ እነዚህን አቅሞቻቸውን በላቀ ሁኔታ በተጠቀሙበት መጠን ተጠቃሚነታቸው ይረጋገጣል። ማንኛውም ሰው በልማቱ ላይ ባዋለው ዕውቀት፣ ጉልበትና ሀብት መጠን እኩል ሀብት የማፍራት ዕድል ያለው በመሆኑ፣ ይህን ዕድሉን ለኪራይ ሰብሳቢዎች አሳልፎ መስጠት አይኖርበትም።

በአገራችን ውስጥ የተፈጠረውን የተጠቃሚነት ዕድል ለማስፋት ያልተሰበሰቡ ኪራይ ሰብሳቢ እጆችን መሰብሰብ ተገቢና ትክክለኛ አገራዊ መፍትሔ መሆኑን ማመን ይገባል። ለዚህ ደግሞ መንግስት በሚያደርጋቸው ማናቸውም የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በላቀ ሁኔታ መሳተፍ ያስፈልጋል። በመሆኑም ኪራይ ሰብሳቢነት የኋሊት የሚጎትተን የዘቀጠ አስተሳሰብ ስለሆነ ህብረተሰቡ ከዚህ አኳያ ተግባሩን በመመልከት የአስተሳሰብ ለውጥን መጎናፀፍ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy