Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳትና የህዝቡ ሚና

0 468

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳትና የህዝቡ ሚና

                                                        ዘአማን በላይ

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ላለፉት አስር ወራቶች በሀገራችን ገቢራዊ ሆኖ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቷል። ያለፉትን አስር ወራቶች ሪፖርት ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ፀሐፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለምክር ቤቱ እንዳስረዱት፤ የአዋጁ አፈፃፀሞች ደረጃ በደረጃ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ለማስቆም በየደረጃው ካሉ የመስተዳደር አካላትና ከህዝቡ ጋር በተቀናጀ ሁኔታ በተከናወነው ስራ የተፈጠረውን ሁኔታ መቀልበስ መቻሉን አቶ ሲራጅ ገልፀዋል። ይህም ማንም ሳይሆን የሀገራችን ህዝብ ለአዋጁ መነሳት እጅግ የገዘፈ ተግባር መከወኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ሰላምና መረጋጋትን በሀገራችን ለማረጋገጥ ህዝቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ባደረገው ጥረትም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልሎችና በአዲስ አበባ በብጥብጥ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 21 ሺህ 109 ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው በሁለት ዙር በማሰልጠኛ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉ ተወስቷል።  

በተለይም በወቅቱ በተፈጠረው ሁከት ወንጀል ስለመፈጸማቸው በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጦባቸው በኦሮሚያ ክልል አራት ሺህ 136፣ በአማራ ክልል አንድ ሺህ 888፣ በደቡብ ክልል አንድ ሺህ 166 እና በአዲስ አበባ 547 በድምሩ 7 ሺህ 737 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ህዝቡ ፀጥታ ሃይሎችን በመረጃና በማስረጃ የመደገፉ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአስር ወራት ቆይታ በህገ መንግስቱ መሰረት የተቋቋመው መርማሪ ቦርድ ከተጠርጣሪዎች አያያዝ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጉድለቶችን ነቅሶ እንዲያወጣ የህዝቡ ድጋፍ ከፍተኛ ነበር።

ርግጥ ማንኛውም አዋጅ ያለ ህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ የታለመለትን ግብ ሊመታ አይችልም። ይህ የህዝቡ ወሳኝ ድጋፍ በየአካባቢው የታጠቁ አሸባሪዎችን፣ ፀረ ሰላም ኃይሎችንና ነውጠኞችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረግ ችሏል። በዚህ መሰረትም በኦሮሚያ 325፣ በአማራ 275 እና በደቡብ ክልል 109 በአጠቃላይ 709 የታጠቁ አሸባሪዎች፣ ፀረ ሰላም ኃይሎችና ነውጠኞች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠርም በተመረጡ አካባቢዎች 97 አዳዲስ ኬላዎችን በማቋቋምና 196 ነባር ኬላዎችን በማጠናከር ሁለት ሺህ 732 የጦር መሳሪያዎች፣ 181 ቦምቦችና ሁለት የግንኙነት ሬዲዮኖች እንዲያዙ ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር የፈፀመው ተግባር ከፍተኛ ነው።

ርግጥ የየትኛውም ሀገር ህዝብ ሁሌም ከማናቸውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን የሚያጤን እንዲሁም የአካሄዶቹን አሉታዊና አዎንታዊ ጎን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሳኔ የሚሰጥ ነው። የሀገራችንም ህዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሆኑን ስለሚያውቅ፤ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆም ነው።

የሰላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንግዜውም በላይ በየአካባቢው ለሰላሙ ዘብ እንደቆመ ነው። ባለፉት አስር ወራቶች ከኮማንድ ፖስቱና ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ያከናወናቸው ሰላምን የማረጋገጥ ተግባሮች የዚህ እውነታ አረጋጋጭ ናቸው።

በእነዚያ ወራቶች ህዝቡ የየቀየውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ ዋነኛ መሰረት ሆኗል። የቀየው ለሚከሰት ማናቸው የፀረ ሰላም ሃይሎች ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን መሆኑን ስለሚያውቅ ለሰላሙ ተግቶ ሰርቷል።

የሀገራችን ህዝብ ከሰላም ምን ሊገኝ እንሚችል ባለፉት 26 ዓመታት፣ በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በሚገባ ተገንዝቧል። ሰላሙ የልማቱ፣ ሰላሙ ዕድገቱ፣ ሰላሙ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ ሀገር በቀል በሆነ መንገድ ስር እንዲሰድ መሰረት መሆኑን በሚገባ ያውቃል።  

ይህ ህዝብ ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ ነው። ወጣቶችን ከጥፋታቸው የመመለስ፣ የተሃድሶ ትምህርት ከወሰዱም በኋላ ወደየቀያቸው ሲመለሱ ምክርና ተግሳፅ በመስጠት እንዲሁም ወጣቶቹ የየአካባቢያቸውን ሰላም በኃላፊነት ስሜት እንዲጠብቁ አድርጓል። ታዲያ ይህ የህዝቡ ስሜት መነሻው ከምንም የተነሳ አይደለም— የሰላምን እሴት በምንም ሊለካው እንደማይችል ያለፉት ተጨባጭ የኑሮ ውጣ ውረዶቹን በሚገባ ስለሚገነዘብ እንጂ።

‘ከህይወት ተሞክሮ የተሻለ ትምህርት ቤት የለም’ እንደሚባለው፤ ህዝቡ ላለፉት አስር ወራቶች የሰላሙ ዘብ ሆኖ መቆሙ ትክክልም ተገቢም ነው። ሁከቱን ለመቀልበስ በሀገራችን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስፈጻሚው አካል ታውጆ ተግባራዊ በሆነበት በእነዚያ ወራቶች የህዝቡ ሚና የማይተካ ነበር። እናም በአስሩ ወራት ውስጥ በሀገራችን ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ በማድረግ ረገድ ህዝቡ የላቀ ተግባር አከናውኗል።

ህዝቡ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት የተራመዳቸው ተስፋ ሰጪ መንገዶች እንዲሁም አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ ዛሬ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ በማድረግ መግለፅ የሚችል ነው።

የሀገራችን ህዝብ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ በተከናወኑት ልማት ተግባራት ራሱ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ሀገሩም በልማቱ መስክ የአፍሪካ ተምሳሌት ሆናለች። የቀጣናውን ሀገራት በልማት ለማስተሳሰር በምታደርገው ጥረት ተጠቃሽ መሆኗንም ያውቃል። በአረንጓዴ የልማት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተችም እንደሆነ ይገነዘባል።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የቀጣናውን ሀገራት ሰላም እያስከበረችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት እንዳላትም ይረዳል። ይህ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቁመናችን እንዳይሸራረፍም ሰላምን በፅኑ እንደሚሻ እሙን ነው። ባለፉት አስር ወራቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ገቢራዊ ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት የዚህ እውነታ ማሳያ ነው።

ያም ሆነ ይህ ሀገራችን ሰላም መረጋገጥ መሰረቱ ህዝቡ መሆኑ አይካድም። በዚህም ሳቢያ ባለፉት አስር ወራቶች የሀገራችን ሰላም በመደበኛው ህግ ሊፈቱ ከሚችሉ ጥቃቅን ጉዳዩች ውጪ በአብዛኛው ወደ ነበረበት የተመለሰው ህዝቡ ለሰላም ካለው የማይናወጥ ፍላጎት የመነጨ ነው። ሰላምን በፅኑ የሚሸው የሀገራችን ህዝብ ደሙን ዋጅቶና አጥንቱን ከስክሶ ያመጣው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገድ እንዳይደናቀፍ እንዲሁም የኋሊት እንዳይቀለበስ አይፈቅድም።

ይህ የህዝቡ የማይተካ ሚና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በወራቶች ጊዜ ውስጥ እንዲነሳ አድርጓል። ታዲያ እዚህ ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራ ወቅት ‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምን አይነሳም?” በማለት ሲጮሁ የነበሩ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ የሁከትና የትርምስ ኃይሎች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳው በውጭ ሃይሎች ግፊት ነው” በማለት ያለ ሃፍረት እየደሰኮሩ ነው።

ሆኖም አዋጁ የተነሳው ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ባደረገው ቅንጅታዊ ስራ በሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ እንጂ የውጭ ሃይሎችን ለማስደሰት ሲባል አይደለም። እዚህ ሀገር ውስጥ በውጭ ሃይሎች ፍላጎት የሚከናወን ምንም ዓይነት ነገር የለም። እናም ማናቸውም የሀገራችን ተግባሮች የሚከናወኑት ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች በሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብቻ እንጂ በየትኛውም የውጭ ሃይል አለመሆኑን የሁከትና የትርምስ ሃይሎቹ ሊያውቁት ይገባል።

ዛሬ ሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ተገንብቷል። በዚህም ሳቢያ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሰላማዊ ትግልን ማካሄድ የሚችልበት አውድ ዕውን ሆኗል። ይህ ሰላማዊ አውድ ሊገኝ የቻለው ህዝቡ ስለ ሰላም ካለው ቀናዒ ምልከታ ነው። ባለፉት አስር ወራቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆንና አዋጁ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ህዝቡ የተጫወተው የማይተካ ሚና፤ ሰላም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው የተገነዘበ ሚዛናዊ ህዝብ መፈጠሩን የሚያሳይ ይመስለኛል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy