Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወጪ ንግዱ ፈተናዎችና ተስፋዎች

0 338

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወጪ ንግዱ ፈተናዎችና ተስፋዎች

ብ. ነጋሽ

የወጪ ንግድ በአንድ ሃገር ኢኪኖሚያዊ እድገት ውስጥ ወሳኝ ድርሻ አለው። በተለይ ሁሉንም ፍላጎታቸውን – ምርትና አገልግሎት በራሳቸው አቅም መሸፈን ለማይችሉት በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት የወጪ ንግድ የማደግ ያለማደግ፤ የመልማት ያልመልማት ጥያቄ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የሃገር የህልውና ጉዳይም ነው። ሁሉንም ፍላጎታቸውን በራሳቸው አቅም ማሟላት የማይችሉ ታዳጊ ሃገራት በሃገራቸው ውስጥ የማያመርቱትን የሚያሟሉት በገቢ ነግድ ነው። የገቢ ንግድ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃል። የውጭ ምንዛሪው ቱሪዝምን ከመሳሰሉ የአገልግሎት ዘርፎችና ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ሊገኝ ቢችልም አስተማማኝና ዘላቂ የምንዛሪ ምንጭ ግን የወጪ ንግድ ነው።

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። ይሁን እንጂ የወጪ ንግዷ እሴት በማይጨምሩ የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ ነው። ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ቆዳና ሌጦ፣ ጫት፣ የቁም ከብት፣ እጣንና ሙጫ፣ ወርቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አበባ . . . የመሳሰሉት ዋነኞቹ የወጪ ንግድ ምርቶች ሆነው ቆይተዋል።

የሃገሪቱ የወጪ ንግድ ሚዛን ማለትም ወደውጭ የሚላከውና የሚገባው የምጣኔ ጉድለት ያሳያል። የሃገሪቱ የውጪ ንግድ በተወሰኑ የግብርና ምርቶች ላይ የተመሰረቱ ሆኖ ሳለ፣ የምታስገባቸው ምርቶች በአይነትም በመጠንም ከፍተኛ ናቸው። በተለይ ነዳጅ ከገቢ ምርት ከፍተውን ድርሻ ይይዛል።

ከዚህ በተጨማሪ መድሃኒት፣ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችና መለዋወጫዎች፣ ማሽነሪዎችና መለዋወጫዎች፣ የቤትና የቢሮ ፋሲሊቲዎች፣ አልባሳትና ጨርቆች፣ ብረታ ብረት፣ ወዘተ ከገቢ ንግዶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የሃገሪቱን የወጪ ንግድ በአይነትም በመጠንም በመጨመር የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አቅም ለማሳደግ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በተለይ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የታሰበውን የኢኮኖሚ እድገት ለማሳካት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ወሳኝነቱ ታምኖበት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ማብቂያ ላይ ማለትም በ2007 በጀት ዓመት የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ ከ5 በሊየን ዶላር በላይ ለማድረስ ታቅዶ ነበር። በ2002 ዓ/ም የእቅዱ ትግበራ መጀመሪያ ላይ የወጪ ንግድ ገቢ 2 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነበር።

በእቅድ ዘመኑ ማብቂያ የወጪ ንግድ ገቢውን ወደ 3 ቢሊየን ዶላር ገደማ ማሳደግ ቢቻልም፣ ታቅዶ ከነበረው ጋር ሲታይ አፈጻጸሙ እጅግ ዝቅተኛ ነው። በእቅድ ዘመኑ ማብቂያ ላይ የወቅቱ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሶፊያን አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ሀገሪቱ ለገቢ ምርቶች የሚያስፈልጋትን ወጪ በውጭ ምንዛሬ የመሸፈን አቅምን ለማሳደግ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። የወጪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ ድጋፎች መደረጋቸውን ያስታወሱት ሚኒስቴሩ፣

በዚህም ምክንያት የኤክስፖርት ገቢ በዕቅዱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ትግበራ ዓመታት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየት መቻሉን አመልክተዋል። ሆኖም ከ2005 በጀት ዓመት ጀምሮ የዕቃዎች የወጪ ንግድ ዘርፍ አፈፃፀም በጀመረበት መቀጠል ባለመቻሉ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ዕድገት ሳያሳይ እስከ 2007 በጀት ዓመት ድረስ በመዝለቁ፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጠው ከፍተኛ የኤክስፖርት ግብ ላይ መድረስ አለመቻሉን አስታወቀዋል።

በዚህ ዘርፍ ለታየው ደካማ አፈፃፀም አንዱ ምክንያት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ዋጋ በዓለም ገበያ መቀነስ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀው ነበር። ዋነኛው ምክንያት ግን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የወጪ ንግድ ምርቶች በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት የማቅረብ አቅም በሚፈለገው ደረጃ አለመዳበሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሠማራት ያለው ፍላጎት አድጎ እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ሆኖም የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በማጠናከር የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶችን ወይም አዳዲስ ምርቶችን በዓይነትና በብዛት በማምረት በስፋት ለውጪ ገበያ ለማቅረብ አለመቻሉን ገልጸዋል። በመሆኑም በቀጣይ ዓመታት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በማኑፋክቸሪንግ መስክ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የኤክስፖርት ሸቀጦችን አቅርቦት በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት ማሻሻልና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ትርጉም ባለው ሁኔታ ማሳደግ የላቀ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ወደ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የተገባው የወጪ ንግዱ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ነበር። ይሁን እንጂ በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን የመጀመሪያ ሁለት ዓመታትም የወጪ ንግዱን በሚፈለገው ልክ ማሳደግ አልተቻለም። እንዲያውም እድገቱ ማሽቆልቆል ያሳየበት ሁኔታ ነው የነበረው።

ኢትዮጵያ በ2008 በጀት አመት ለውጭ ገበያ ካቀረበቻቸው ምርቶች 2 ነጥብ 86 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላርን ብቻ ነበር ያገኘችው። ይህም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ ላይ ከተገኘው ከ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጻር ዝቅተኛ ነው። በ2008 በጀት ዓመት የተላከው ምርት በመጠን ከ2007 በጀት ዓመት የጨመረ ቢሆንም በገቢ ግን አነስተኛ ነበር። የገቢው መቀነስ ምክንያት የአቅርቦት ችግር ሳይሆን የአለም ገበያ ዋጋ መቀነስ እንደሆነ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የቅባት እህል ንግድ፣ የዓለም ገበያን አዲስ የተቀላቀሉት ታንዛንያና ማሊን የመሳሰሉት ምርቱን በስፋት ማቅረባቸው የገበያ ዋጋው እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል። በወርቅ፣ በቁም እንስሳትና በመሳሰሉት የኮንትሮባንድ ንግዱ መስፋፋት ገቢው ለመቀነሱ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

በ2009 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል። በበጀት ዓመቱ ለማግኘት የታቀደው 4 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ከእቅዱ ማሳካት የተቻለው 61 በመቶ ብቻ ነው። እርግጥ ከ2008 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻፀር የ1 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይህም ቢሆን ግን በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ ላይ ከተገኘው ያንሳል። ከተገኘው ገቢ ትልቁን ድርሻ የያዘው አሁንም የግብርና ምርት ሲሆን፣ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት፣ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል። በማኑፋክቸሪንግና ማዕድን ዘርፎች ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ኬሚካልና የግንባታ ግብዓቶች፣ ሞላሰስ፣ ታንታለም፣ ብረታ ብረትና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችም ወደ ውጭ መላካቸውን ነው የንግድ ሚኒስቴር መረጃ የሚያሳየው።

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እቅድ አለመሳካት፣ የግብዓት ኦቅርቦት እጥረት እንዲሁም የማኔጅመንትና የቴክኒክ አቅም ውስንነት በወጪ ንግዱ አፈፃፀም ላይ ተፅእኖ ማሳደራቸውን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል። በአንዳንድ ዘርፎች የኤክስፖርት ምርት አቅርቦት እጥረትና የጥራት መጓደል፣ የአብዛኛዎቹ የወጪ ንግድ ምርቶች የዓለም ገበያ ፍላጎት መቀዛቀዝና የህገወጥ ንግድ አለመገታት ለአፈፃፀሙ ዝቅተኝነት ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በአጠቃላይ የሃገሪቱ የወጪ ንግድ አፈፃፀም ከእቅድ በታች ብቻ ሳይሆን እያሽቆለቆለም መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። ይህ ዘርፉ የገጠመውን ፈተና ያሳያል። የቱሪዝም ዘርፉና በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደቤተሰቦቻቸው የሚልኩት ሬሚታንስ ባይኖር ኖሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሊፈጠር ይችል ነበር። የሃገሪቱን የቱሪዝም ገቢ ስንመለከት በ2008  በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ይህ ገቢ በ2009 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 32 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ነበር። የ2009 ገቢ መጠነኛ ቅናሽ ያሳየው በዓመቱ መግቢያ ላይ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት ምክንያት ነው። ባለፈው ዓመት ውጭ ሃገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተገኘው የሬሚታንስ ገቢ ወደ 4 ቢሊየን ዶላር ነበር። ዘንድሮም ቢያንስ ተመሳሳይ ገቢ ተገኝቷል ተብሎ ይገመታል።

ከቱሪዝምና ከሬሚታንስ የተገኘው ገቢ ከወጪ ንግድ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ አለው። ሁኔታው የወጪ ንግዱን የማሳደግ ጉዳይ አሁንም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለክታል። እርግጥ በቀጣይ አመታት ወደስራ ከገቡት የኢንደስትሪ ፓርኮች ተመርተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ መጠን ያሳድጉታል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ባለው ሁኔታ ከሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ብቻ በወር 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር እየተገኘ ነው። የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተያዘው በጀት ዓመት በሙሉ አቅሙ ወደስራ ገብቶ 100 ሚሊየን ዶላር ያህል ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ዘንድሮ በአጠቃላይ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የወጪ ንግድ ብቻ 400 ሚሊየን ዶላር ገቢ ይጠበቃል። በተጨማሪም 3 ሺህ ሄክታር ተጨማሪ መሬት ለአበባ እርሻ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ ነው። ይህ ተጨማሪ የአበባ ልማት ለዘንድሮ ባይደርስም ለመጪ አመታት ግን ከዘርፉ የሚገኘውን የወጪ ንግድ ገቢ ማሳደጉ እርግጥ ነው። እነዚህ ደግሞ በወጪ ንገዱ ላይ የሚታዩ ተስፋዎች ናቸው። አሁን ያለው የወጪ ንግድ ሁኔታ ግን አሳሰቢ መሆኑ ግን ግልጽ ነው።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy