Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዛለ ስትራቴጂ የተመረኮዘ ሰነድ – H. RES. 128

0 379

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዛለ ስትራቴጂ የተመረኮዘ ሰነድ – H. RES. 128

ክፍል አንድ

ኢብሳ ነመራ

ታላቋ አሜሪካ አሁን አሁን የዓለማችን አደገኛዋ ሃገር ለመባል በቅታለች። አደገኛዋ ሃገር ያሰኛት የሚያሳምንም ይሁን አይሁን፣ ተጨባጭ ማስረጃም ይኑር አይኑር ምንም ሳያሳስባት በማንአለብኝነት በሉዓላዊ ሃገራት ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና ጦርነት በማወጅ መንግስት አልባ ሃገራትን በመፍጠሯ ነው። አሜሪካ የሃገራት ሉዓላዊነት፣ የህዝብ መብትና ነጻነት የሚያሳስባት ሃገር እንዳልሆነች የባለፈ ግማሽ ምዕተ ዓመት ታሪኳ ያሳየናል። ለነገሩ ለሃገራት ሉዓላዊነት፣ ለህዝብ መብትና ነጻነት ደንታ ማጣት የአሜሪካ መንግስት ብቻ ባህሪ አይደለም። ቅኝ ገዢ የነበሩት የምዕራብ አውሮፓ ሃገራትም ይጋሩታል። ለአሜሪካና ለእነዚህ ምእራባውያን መንግስታት የእነርሱ ጥቅምና ፍላጎት የበላይነት አለው። ጥቅምና ፍላጎታቸው እንዲጠበቅ ሌሎች ሃገራትን እስከማፍረስ የዘለቀ ርምጃ ይወስዳሉ።  

ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ በቪየትናም ላይ የፈጸመችው ወረራ የዚህ ማሳያ ነው። በምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ላይ ያላትን የበላይነት ለማረጋገጥ በአፍጋኒስታን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አሁን ተመልሳ አሸባሪ ብላ የምትወጋውን አልቃይዳ እንዲፈጠር ምክንያት ሆናለች። እውነታውን ፈልፍለን ስንመለከት ለአልቃይዳ መፈጠር የአሜሪካ ድርሻ ጉልህ ሆኖ እናገኘዋለን። እርግጥ አልቃይዳ ተመልሶ የአሜሪካ ቀንደኛ ጠላት ለመሆነ በቅቷል። የሴፕተምበር 11 የሽብር ጥቃት የዚህ ውጤት ነው። አንዳንዶች አሜሪካ የእጇን ነው ያገኘችው ይላሉ።

የአሜሪካ መንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎች የዛሬ የርዕዮተ ዓለም የበላየነቱን ማሰጠበቁን እንጂ ከርመው ሊያስከትሉ የሚችሉ መዘዞች የሚያገናዝብ አይመስልም። እንደዛማ ባይሆን የቀድሞ ሶቭየት ህብረትን ያዳክምልኛል በሚል የተገደበ እይታ አልቃይዳ የሚፈጠርበትን ምቹ ሁኔታ ባላደላደለ ነበር። ራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት ISIS በሚል የሚጠራውና በኋላም ስያሜውን ወደ እስላማዊ መንግስት IS የቀየረው የዘመናችን አደገኛና አስፈሪ አሸባሪ የተፈጠረበትን ሁኔታም ያደላደሉት የአሜሪካ መንግስትና መዕራባውያን አጋሮቹ ናቸው። አሜሪካና እንግሊዝ የኢራቅ መንግስት ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ታጥቋል የሚል ያልተረጋገጠ ወሬን መነሻ በማድረግ፣ ዜጎቻቸው ላይ ስጋት የፈጠረ አስመስለው ኢራቅን የማውደም ጦርነት አወጁ። በዚህ ጦርነት ኢራቅ ወድማ መንግስት አልባ ሆነች።

አይ ኤስ እዚህ መንግስት አልባ የፈራረሰ ሃገር ላይ ነው የተፈጠረው። አይ ኤስ እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ያመቻቹለት አሜሪካና ምዕራባውያን በመጀመሪያ የዚህን አደገኛ አሸባሪ ቡድን ማንነት እንኳን መገንዘብ አልቻሉም ነበር። የኢራቅ የአልቃይዳ ክንፍ እያሉ ነበር የሚጠሩት። ይሁን እንጂ አይ ኤስ የዋሃቢ ሰለፊ አስተምህሮን እንደርዕዮተ ዓለም በመያዝ ካልሆነ ከአልቃይዳ ጋር አንድ የሚያደርገው አንዳችም ነገር አልነበረም።

አደገኛዋ አሜሪካና አጋሮቿ የርእዮተ ዓለም የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ የሶሪያን መንግስት የቀለም አብዮት በተሰኘ ስልት ለማስወገድ የወሰዱት እርምጃ እንዳሰቡት ሳይሳካ ይቀራል። በአል አሳድ የሚመራው የሶሪያ መንግስት የአሜሪካና የአጋሮቿን የመንግስት ለውጥ እንቅስቃሴ በሃይል ያከሽፋል። ይሄኔ በዜጎቹ ላይ ጭፍጨፋ ፈፀመ በሚል በርእዮተ ዓለም ከአልቃይዳና ከአይ ኤስ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ጥቃቅን የዋሃቢ ሰለፊ ቡድኖች አደራጀተው መሳሪያ በማስጣጠቅ በሶሪያ መንግስት ላይ የእጅ አዙር ጦርነት ከፈቱ። የምእራባውያን ሚዲያዎች ይህን እ ኤ አ በ2012 ዓ/ም የታወጀ የእጅ አዙር  ጦርነት የሶሪያ የውስጥ ግጭት እያሉ የጌቶቻቸው እጅ የሌለበት ለማስመሰል ይጥሩ ነበር።

ያም ሆነ ይህ፣ አሜሪካና አጋሮቿ የሶሪያን መንግስት ለማስወገድ ያወጁት የእጅ አዙር ጦርነት ሶሪያን አፈራረሳት፤ የሶሪያ መንግስት የማይቆጣጠረው ምድር ተፈጠረ። ይሄኔ ኢራቅ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውና ምእራባውያኑ የኢራቅ የአልቃይዳ ክንፍ ሲሉት የነበረው ቡድን ወደሶርያ ተስፋፋ። ስያሜውን የሶሪያና የኢራቅ እስላማዊ መንግስት (ISIS) ያደረገው በዚህ ወቅት ነበር። አሜሪካና አጋሮቿ በሊቢያ ላይ የከፈቱት ሃገር በማፍረስ መንግስት አልባ ሃገር የመፍጠር አካሄድ በቀላሉ መስፋፋት እንደሚያስችለው የገመተው ራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት ብሎ ይጠራ የነበረ ቡድን፣ ስያሜውን ወደእስላማዊ መንግስት IS ቀየረ። አሜሪካ በሊቢያም መንግስት አልባ ሃገር ፈጥራ ቦታ አመቻቸችለት፤ አይ ኤስም ተስፋፋ። አይ ኤስ የታጠቀው መሳሪያ በአብዛኛው አሜሪካና አጋሮቿ በተለይ የሶርያን መንግስት ለማስወገድ ላሰማሯቸው ትናንሽ እስላማዊ ቡድኖች ያስታጠቁት መሳሪያ ነው። አይ ኤስ የሚዋጋው በአሜሪካ መሳሪያ ነው። በአጠቃላይ አይ ኤስን የፈጠረችው አሜሪካ ነች ማለት ይቻላል።

ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይልና የኒዩክለር አረር ለመታጠቅ ያነሳሳት ሃገራት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የርዕዮተ ዓለም የበላይነት የማግኘት ፍላጎት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በተለይ አሜሪካ ለርዕዮተ ዓለም የበላይነት ልታካሂድባት ከምትችለው የመንግስት ለውጥና እንደነ ኢራቅ የማፈራረስ አደጋ ራሷን ለመከላከል ነው። የሰሜን ኮሪያ የኒዩክለር መታጠቅ ዓላማ ራስን መከላከል ነው። የምስራቅ አውሮፓ በተለይ የዩክሬይን ምስራቃዊ አካባቢ ግጭትና የክሪሚያ የሩሲያ አካል መሆን መነሻ ምክንያት የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ነው። አሜሪካና ምእራባውያን አጋሮቿ ርዕዮተ ዓለማቸውን ወደምስራቅ በማስፋፋት፣ የኔቶ ሃይልን በማሰማራት የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ በዩክሬይን በቀለም አብዮት የመንግስት ለውጥ ያደርጋሉ።

ይህ ሁኔታ ስጋት ላይ የጣላት ሩሲያ የትውልደ ሩሲያ መኖሪያ የሆነችውና ከዩክሬይን ይልቅ ለሩሲያ የምትቀርበውን ክሪሚያ በህዝበ ውሳኔ የሩሲያ አካል የሆነችበትን ሁኔታ አመቻችታለች። ክሪሚያ የሩሲያ አካል እንድትሆን በማድረግ ረገድ ዋነኛው ገፊ ሃይል ሩሲያ ሳትሆን አሜሪካ ነች። በምስራቅ ዩክሬይን የተፈጠረው ግጭት መንስኤም አሜሪካ የምትከተለው የቀለም አብዮት የመንግስት ለውጥ ስትራቴጂና የኔቶ ወደምስራቅ መስፋፋት ነው።

አሜሪካ የርዕዮተ ዓለም የበላይነቷንና የባለጸጎቿን ጥቅም ከማስጠበቅ ውጭ ለሃገራት ሉዓላዊነት፣ ለህዝብ ክብር፣ መብትና ነጻነት ቦታ አትሰጥም። ከሃገራት ጋር ወዳጅ በሆነችበት ወቅትም፣  ለመጠባባቂያነት የዛሬ ወዳጇን ጠላት በጉያዋ ሸሽጋ ትይዛለች። ይህ በጉያዋ የምትይዘው መርዝ አምልጦ ሊያስከትል የሚችለው የሰላምና መረጋጋት ስጋት አይታያትም። አሁን ሶሪያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት በአሜሪካ የሚደገፉ ዋሃቢ ሰለፊ እስላማዊ ቡድኖች፣ አልቃይዳ ወዘተ ለዚህ ማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ይህ የአሜሪካ አካሄድ በ1970ዎቹ የተነደፈ አዲስ የአለም አሰላላፍ/ New Worled Order የተሰኘ በመንግስት ለውጥ የርዕዮተ ዓለም የበላይነት የመቀዳጀት ስትራቴጂ ውጤት ነው። ይህ ስትራቴጂ ጊዜው ያለፈበት ቢሆንም የአሜሪካ መንግስት ራሱን ከጊዜው ጋር ማጣጣም አቻለም። አሁንም ለርዕዮተ ዓለም የበላይነት በሃገራት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የቀለም አብዮት በተሰኘ የከተማ ነውጥ መንግስት መለወጡን፣ በዚህ ያልተቻለውን ደግሞ በሚሳይልና ቦምብ በማፈራራስ ዓለምን ማተራመሱን እንደቀጠለበት ነው።

ወዳጆቼ፤ ዓላማዬ ስለ ታላቋ አሜሪካ ማንነት ማተት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአሜሪካ መንግስት በሃገራት ላይ የሚይዘው አቋምና የሚወስደው እርምጃ ያልተጤነና ራሱንም ጭምር የሚጎዳ አውዳሚ መሆኑን በማስታወስ፣ ሰሞኑን ክሪስ ስሚዝ የተባሉ አንድ የአሜሪካ ኮንግሬስ አባል ኢትዮጵያን በተመለከተ የቸከቸኩት H. RES. 128 የተሰኘ የውሳኔ ሃሳብ ሰነድን ምንነት መቃኘት ነው። ይህ የውሳኔ ሃሳብ ክሪስ ስሚዝ የተባሉት የኮንግሬስ አባሉ ፍላጎት ነው። ሰውየው ይህ ፍላጎት ያደረባቸው በተለያየ መክንያት ሊሆን ይችላል፤ በጥቅም በመደለል፣ በተሳሳተ መረጃ ወዘተ። ዋነኛው ምክንያት ግን የሃገራቸው መንግስት የሚከተለው በሉዓላዊ ሃገራት ጉዳይ ውስጥ  በዘፈቀደ ጣልቃ የመግባት ፖሊሲ ነው።

አሜሪካ ዓለም ላይ ለሚገኙ ሉዓላዊ ሃገራትን በሙሉ ሞግዚት መሆን ስለሚዳዳት የውስጥ ጉዳያቸው ያገባኛል ባይ ነች። ማንኛውም የኮንግሬስ አባል በሉዓላዊ ሃገራት ጉዳይ ላይ የተሰማውን የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብ መብት ያለው ለዚህ ነው። የተለያዩ ቡድኖች፣ የአሜሪካ መንግስት ውጤትን ሳያይ በዘፈቀደና በግብታዊነት በሃገራት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ያለውን ፍላጎት ተጠቅመው ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የኮንግሬስ አባላትን በገንዘብ ለመግዛት የሚሯሯጡት ለዚህ ነው።  

የኮንግሬስ አባላት የቡድን ፍላጎትን መነሻ አድርገው በሉዓላዊ ሃገራት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር የውሳኔ ሃሳብ እንዲቸከችኩ የሚከፈላቸው ገንዘብ እንደሙስና አይታይም። የኮንግሬስ አባሉ ሎቢ ለማድረግ እንደተሰጠው የአገልግሎት ክፍያ ነው የሚቆጠረው። ለመንግስት አሳውቆ ግብር ይከፍልበታል፤ ህጋዊ ጉቦ ነው።

እናም፣ እንደ እኔ እምነት ክሪስ ስሚዝ የሚባሉት የአሜሪካ ኮንግሬስ አባል ኢትዮጵያን በተመለከተ የቸከቸኩት H. RES.128 የተሰኘ የውሳኔ ሃሳብ የኢፌዴሪን ህገመንግስታዊ ስርአት በሃይል ለመናድ በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ህጋዊ ጉቦ ተሰጥቷቸው የቸከቸኩት ነው። ከእነዚህ ቡድኖች ጀርባ ደግሞ ምስራቅ አፍሪካን በማተራመስ ድርጊት በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ የተጣለበት በአንድ ግለሰብ የሚመራው የኤርትራ መንግስት አለ። እንደ እኔ አተያይ፣ ይህ ሰነድ በኤርትራ መንግስትና የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎቹ በአሜሪካ መንግስት አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ በማሳደር ቀጠናውን ለማተራመስ የሚያስችል እድል ለማግኘት በህጋዊ ጉቦ እንዲዘጋጅ ያደረጉት ነው። እንግዲህ፣ ይህን ለምን አልክ መባሌ አይቀርም። ጉዳዩ ወዲህ ነው። ክሪስ ስሚዝ የቸከቸኩትና ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ 56 የድጋፍ ድምጽ አገኘ የተባለው፣ በቀጣይ ለመጽደቅ የኮንግሬሱን፣ የሴኔቱንና የፕሬዝዳንቱን ይሁንታ ማግኘት የሚጠብቀው የውሳኔ ሃሳብ ላይ የተነሱ አንኳር አንኳር ጉዳዮችን እንመልከት።

H.RES.128 የተሰኘው የክሪስ ስሚዝ ሰነድ በመግቢያው ላይ፣ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልማት በተለይ በጤናው ዘርፍ ላሰመዘገበችው ስኬት እውቅና ይሰጣል። ሰነዱ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን፣ በአጠቃላይ ለሰላም ያበረከተችውንና የምታበረክተውን አስተዋጽኦ፣ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ትብብርና ይህ ትብብር ለአሜሪካና ለአካባቢው ሃገራት ብሄራዊ ጥቅም መጠበቅ ላበረከተው አሰተዋጽኦም እውቅና ይሰጣል። ይህ ሊካድ የማይችል መላው ዓለም የመሰከረለት እውነት ነው።

የክሪስ ስሚዝ ሰነድ በመቀጠል ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊ ሥረአት ወደአሳታፊ ዴሞክራሲ ለመሸጋጋር የምታደርገው ግስጋሴ በሌሎች መሰኮች የታየውን ያህል ስኬታማ አይደለም ይላል። ይህን የኢፌዴሪ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም የሚጋሩት እውነት ነው። ዴሞክራሲያዊ ሥርአት በፖለቲካ ፓርቲዎችና በመንግስት ፍላጎት፣ በአዋጅ . . . የሚሰፍን አይደለም። ከአምባገነናዊ ሥርአት ወጥቶ ዴሞክራሲን የማሰፈን ወይም የመገንባት ጉዳይ የአመለካካት ለውጥ የማምጣት ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲያዊ አመለካከትን የመንግስት ስልጣን ምንጭና ባለቤት በሆነው ህዝብና ከህዝብ በሚፈልቁ የፖለቲካ ቡድኖች አመራሮችና አባላት ውስጥ በማስረጽ ባህል ሆኖ የሚፈጠር ነው።

ኢትዮጵያ በዚህ ሽግግር ላይ ያለች ሃገር ነች። በመሆኑም ዴሞክራሲው ምሉዕ የሆነበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። የዴሞክራሲ አመለካካት ጉድለት የሚታየው በመንግስት ውስጥ ብቻ አይደለም። ዴሞክራሲን ካለመለማመድና ባህል ካለማደረግ የመነጨ ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ ከገዢው ፓርቲና ከመንግስት ይልቅ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ይስተዋላል። ተቃዋሚ ፓርቲዎቸ በውስጣቸው የሚፈጠረውን ችግር የሚፈቱበት አካሄድ ለዚህ አሰረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።

ችግሮች ሲያጋጥማቸው በሰላማዊ ውይይትና በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ ከመፍታት ይልቅ ፍልጥ እየመዘዙ ሲፈነካከቱና ፓርቲውን ሲያፈርሱ ወይም ሁለት ቦታ ሲሰነጠቁ ታይቷል። አንዳንድ ፓርቲዎች እስካሁንም የአምባገነኑ የወታደራዊ ደርግ አሃዳዊ ስርአት ተስፈኞች ናቸው። በአደባባይ አትመጣም ወይ መንጌ (መንግስቱ ሃይለማርያም) አትመጣም ወይ . . . የሚል መዝሙር ያሰማ ፓርቲ መኖሩን ልብ በሉ። እርግጥ ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ አምባገነን መናፈቅና ተስፋ ማድረግ በራሱ እንደጥፋት ላይወሰድ ይችላል።

በህዝቡም ዘንድ ተመሳሳይ አመለካካት ይታያል። በአብላጫ ድምጽ የሚደግፉት አመለካከት ስፍራ ያጣባቸው ዜጎች፣ የሚደግፉትን ቡድን በሃይል ወደስልጣን ለማውጣት በሰሜታዊነት የተነሱባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው እውነት ነው። የተተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባሉባት ኢትዮጵያ፣ እነዚህ ብሄራዊ ማንነቶች ተደፍቀው፣ አንድ ማንነት በሃይል የተጫነበት ስርአት እንዲመለስ የሚጸልዩ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

በዚህ ሁኔታ ምሉዕ ዴሞክራሲን ማሰፈን አዳጋች ነው። ራሱ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ጥበቃ የሚያደርግላቸው መብቶች፣ ዴሞክራሲውን ለማመንመን ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖችም እድል ስለሚሰጥ ጅምር ዴሞክራሲ፤ ዴሞክራሲያውያንና ኢዴሞክራሲያውያን የሚፋለሙበት መድረክ ነው። በኢትዮጵያም እየሆነ ያለው ይህ ነው። ይህን የአሜሪካ መንግስትና የኮንግሬስ አባላት እንዲገነዘቡት ይጠበቃል።

የዴሞክራሲን እድገት ሂደት ከአሜሪካ በላይ የሚያውቅ የለም። አሜሪካ የህገመንግስቷ መሰረት የሆነውን የነጻነት መግለጫ/ Declaration of Independece  የተሰኘው ድንቅ ሰነድ እ ኤ አ በ1776 ዓ/ም አዘጋጅታ፣ የሴቶችና የጥቁሮችን የመምረጥና የመመረጥ መብት ማስከበር የቻለችው ግን ከ200 ዓመታት በኋላ በ1950 ዎቹ ነበር። ክሪስ ስሚዝ ይህን ያውቃሉ። እናም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማቱን፣ የሰላምና መረጋገቱን ያህል ስኬታማ አለመሆኑ ሊደንቃቸው አይገባም ነበር። የማህበራዊና የኢኮኖሚ ልማቱና ኢትዮጵያ ሳምን በማስከበር ያላት ሚና የሃገሪቱ ዴሞክራሲ ውጤት መሆኑንም መዘንጋት የለባቸውም። የብሄር፣ የሃይማኖትና የአመለካካት ብዝሃነት ባለባት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት ባይዝ ኖሮ ሃገሪቱ ሰላም አይኖራትም ነበር። ከ1983 ዓ/ም በፊት የነበረውን ሁኔታ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

ክሪሰ ስሚዝ የዴሞክራሲውን እድገት ሂደት እንደትልቅ ችግር ከማየት ይልቅ መሰናክሎቹ ተለየተው እድገቱ ሊፋጠን የሚችልበትን መላ መጠቆም ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነበር። ያዘጋጁት ሰነድ ግን ከዚህ በተቃራኒ መሄዳቸውን ነው የሚያመለክተው። በሰነዱ ላይ ያሰፈሯቸው መረጃዎችና ሃሳቦች በሙሉ የሃገራቸውን ዜግነት (አሜሪካዊ ዜግነት) አግኝተው በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ተመዝግበው ዶላር እየሰበሰቡ፣ ቀጠናውን በማተራመስ ከሚታወቀው የኤርትራ መንግስት ጋር በማበር ሽብርተኝነትን ጨምሮ በማንኛውም የሃይል መንገድ የኢፌዴሪን ህገመንግስታዊ ስርአት ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የተገኙ መሆናቸውን በድፍረት መናገር ይቻላል።

እርግጥ ሰነዱ የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርትን በአስረጂነት ይጠቅሳል። የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱም ቢሆን መረጃዎቹን በራሱ መርምሮ ሳይሆን ያገኘው፣ የኤርትራ መንግስት ስር የተጠለሉትን ጨምሮ ስርአቱን በሃይል ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎችና ተቃዋሚዎቹን ዋቢ ካደረጉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን ባይ ድርጅቶች ነው።  

እነዚህ አሜሪካ በበጎ አድራጎት ድርጅትነት የተመዘገቡ የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ቡድኖች ኢትዮጵያ ላይ የሽብር ጥቃትን የሚጨምር ጦርነት ያወጁት በይፋ ነው። በኤርትራ በረሃ የሚንቀሳቀሱትም በይፋ ነው። የህን የአሜሪካ መንግስትም ያውቃል። ክሪስ ስሚዝም ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ። ከቀጥታ ጦርነትና ከሽብር ጥቃት በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚጠቀሙበት መንገድ ገጽታዋን በማበላሸት የበለጸጉ ሃገራትን የልማትና ሰብአዊ ድጋፍ እንዳታገኝ በማደረግ በሃገር ውስጥ ቀውስ መፍጠር ነው።

ይህን ቀውስ መልሰው በማራገብ በመንግስት ላይ ሰላማዊ ያልሆነ ተቃውሞ ይቀሰቀሳሉ። መንግስት ይህን የሃይል ተቃውሞ በማክሸፍ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወስደውን እርምጃ፣ መልሰው በመንግስት እንደተፈጸመ የሰብአዊ መብት ጥሰት የመብት ተሟጋች ነን ለሚሉ ርዕዮተ ዓለማዊ አጀንዳ ላላቸው ቡድኖችና እንደ ክሪስ ስሚዝ ላሉ ተጽእኖ የመፍጠር አቅም ላላቸው ግለሰቦች ያቀብላሉ። ይህን ሆን ብሎ ታቅዶ የሚከናወን ድርጊት በማራገብ በሃያላን ሃገራት ተጽእኖ መንግስት እንዲሽመደመድ ለማድረግ ይጠቀሙበታል። ክሪሰ ስሚዝ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ የቸከቸኩት የወሳኔ ሃሳብ ሰነድ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። ይቀጥላል

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy