Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፀረ ሙስና ትግሉ!

0 467

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፀረ ሙስና ትግሉ!

                                           ይነበብ ይግለጡ

በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ መቀጠል ያለበት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ብቻ ሳይሆን ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት መንግስታዊ ተቋማትን እያሽመደመደ ያለ የከፋ ችግር ከመሆኑም በላይ መልካም አስተዳደርና የፍትሕን መከበር የሚደፍቅ የዜጎችን መብት የሚጥስና የሚደፍር የመንግስትና የሕዝብን ሀብት በመዝረፍ ላይ ያነጣጠረ ለዚህም የሚሰራ በመሆኑ ነው፡፡

ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች በመንግስትና በሕዝብ የተሰጣቸውን አደራ በመተላለፍ ብልሹ አሰራር እንዲሰፍን ሕዝብ ምሬት ውስጥ እንዲገባ አይነተኛ ሚና በመጫወት በመንግስትና በሕዝብ መካከል ከፍተኛ አለመተማመን እንዲፈጠር ሆን ብለው ሲያደርጉ የነበሩና የሚያደርጉም ናቸው፡፡

ሳይሰሩ በመዝረፍ የመክበር ፍላጎቶችና አላማዎች ወደተግባር የሚለወጡት ከውጭ ያለው አቀባባይ ከበርቴ የጥቅም ፍላጎቱን ለማስከበር ሲል በተለያየ ደረጃ በመንግስታዊ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሰዎችን ለሚፈልገው ጉዳይ ማሳኪያነት በጥቅም እየደለለና በመረቡ ውስጥ በማስገባት የጥቅም ተጋሪ እያደረጋቸው በሚፈጽመው ወንጀል ነው፡፡

በሕገወጥ መንገድ ለሚያገኙት ጥቅም ሲሉ ሕግን መተላለፍ ብልሹ አሰራርን መከተልን ይመርጣሉ፡፡ በእከክልኝ ልከክልህ ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ከሹማምንቱ ጋር የጥቅም ተጋሪነት ጡት በመጣባት በመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመጠቀም ነው ወደ ሀብት ማግበስብ ስራ ውስጥ የገቡት፡፡

የግል ሕይወታቸውን በዙሪያቸው የተኮለኮሉትን ጭምር በሀብት ለማክበር የተቻላቸውን ያህል ቢያደርጉም ከሕግ ተጠያቂነት የሚያመልጡበት መንገድ የጠበበ ነው፡፡ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ አጋራቸው የጥበትና የትምክህት ኃይሉ ነው፡፡የሚሰሩትም በቁርኝት ተሳስረው ነው፡፡

በዚህ መልኩ ሰፊ የሀገርና የሕዝብ ሀብቶች ተዘርፈዋል፡፡ ከሰሞኑ መንግስት የጀመረው በሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢው ላይ ያነጣጠረው እርምጃ በዋነኛነት የሚያጠነጥነው በተጨባጭ በድርጊቱ የተሳተፉትን በማስረጃ ለይቶ በማውጣት ለሕግ የማቅረብ ስራ ነው እየተሰራ ያለው፡፡

በዚህም መሰረት ቁጥራቸው ከ55 በላይ የሆኑ ቀደም ሲል በተለያዩ ከፍተኛ መንግስታዊ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በፍርድቤት ትእዛዝ ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራና እየተመረመረ ይገኛል፡፡ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከእነሱ ጋር በተያያዘ የነበሩ ድርጅቶች ካምፓኒዎችና ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል፡፡

በሕግ ጥላ ስር የዋሉት ሰዎች ቁጥር ከሕዝቡ በሚቀርበው ጥቆማ መሰረት እየጨመረ እንደሚሄድ ይታመናል፡ መንግስት በጸረ ሙስና ትግሉ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ መስጠት የጀመረበትን ሁኔታ በገሀድ አሳይቶአል፡፡ ተጨባጭ ማስረጃዎች እስከተገኙ ድረስ በየትኛውም የኃላፊነት እርከን የሚገኝ ሰው ሚኒስቴር ይሁንም አይሁንም በሕግ ከመጠየቅ ሊድን አይችልም፡፡

የሙስናው መረብ ውስብስብነት ከታች ወደጎንና ጎን እንዲሁም ወደላይ ያለው የሚሳሳብበት ቁርኝትና ትስስር ረዥም ርቀት የሚሄድ የሚለጠጥ መሆኑ በሌሎችም ሀገራት የታየ የኪራይ ሰብሳቢው የዘረፋ ባሕርይ ስለሆነ ይሄንን ከስሩ ተከታትሎ በማስረጃ ለመድረስ መንግስት ረዥምና የተጣራ ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡የምርመራ ቢሮዎቹም እንደዚሁ፡፡

የምርመራና የማጣራቱ ሂደት አንድም ስህተት እንዳይፈጠር የሰዎች ሰብአዊ መብት ያለአግባብ እንዳይጣስ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ በእኛ ሀገር ተደጋግሞ በታየ ልምድና ተሞክሮ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ሲፈጠር በቂ ማስረጃ በሌለው ሁኔታ ጥቆማ በመስጠት ቀድሞ በሆነ አጋጣሚ የተቃቃሩትን ሰው የመበቀልና የማጥቃት መንፈስ አይሎ ስለሚገኝ ሕግና ፍትሕ አላማው ማስተማር እንጂ መበቀል አይደለምና ይህን የመሳሰሉት ጉዳዮች ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃሉ፡፡

ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የሀገር ልማትና እድገትን በእጅጉ የሚጎዳ የመንግስትና የሕዝብ ሀብትን በመዝረፍ ባልሰሩበት ባልደከሙበት በሕገወጥ መንገድ መክበርን ግብ ያደረገ ነው፡፡ ይህንን ስር የሰደደ ሀገራዊ ኢኮኖሚን የሚጎዳ የመንግስትን ካዝና የሚያራቁት ነውረኛ የወንጀል ድርጊት ማጋለጥና መዋጋት ያለብን ለማንም ተብሎ ሳይሆን ሀገርን ሕዝባችንን ልማትና እድገታችንን ለመታደግና ለማስቀጠል ሲባል ነው፡፡ የተሀድሶው መሰረታዊ አላማ ከዚሁ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ የተጀመረው ዘመቻ የጥልቅ ተሀድሶው ውጤት ነው፡፡ መንግስት ግለሰቦችን የማሰር ፍላጎትና አራራ የለውም፡፡ ሆኖም ግለሰቦቹ ሕግና ስርአትን ተላልፈው ሲገኙ በወንጀል ስራና ድርጊት ሲጠረጠሩ ማስረጃ ሲገኝ የግድ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡

ትልቁ ሀገራዊና ትውልዳዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው አዲስ አስተሳሰብና አተያይ እንዲፈጠር ጠንክሮ መትጋት፤ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚጸየፍ ትውልድ እንዲፈጠር ከመዋእለ ሕጻናትና ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ወደላይ እያደጉ በሚሄዱት በሁሉም የትምሕርት ተቋማት  ትውልድ የመቅረጽ ስራን አጠናክሮ መስራት ግድ ይላል፡፡-

ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት እጅግ በሰፉ ብዙ መልኮቹ ይገለጻል፡፡ በተቋማት ውስጥ ሲካሄዱ ከነበሩት የፕሮጀክቶች መመሳጠርና ያለጨረታ ብቃት ለሌላቸው ኩባንያዎች መሰጠት፤ ብቃትና ጥራት የሌላቸው ተወዳዳሪዎች በገንዘብ ኃይል ወይንም በዝምድና ትስስር እንዲያሸንፉ በማድረግ የኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታዎችን መስጠት የሙስናው አንድ አካል ሆኖ ተሰርቶበታል፡፡

የምሕንድስና እውቀትና ልምድ ለሌላቸው ሰዎች ብዙ ሰዎች በጋራ የሚኖሩበትን ቤት እንዲሰሩ መስጠት ምን ያህል በሕዝብ ሕይወትና በሀገር ገንዘብ የመጫወት ወንጀል መሆኑን ሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢው እያወቀው ሲሰራበት ኖሮአል፡፡የእነሱ ፍላጎት ከገንዘብ እና ገንዘብ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው፡፡ ስለሕዝብ ሕይወት መጠበቅ ስለሀገር ልማትና እድገት በቃላት ከማስመሰል ውጭ ደንታ የላቸውም፡፡

ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች እነሱና እነሱ ብቻ የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም መክበር ነው የሚፈልጉት፡፡ ሲሰሩ የኖሩትም ለዚህ ነው፡፡የሚሰሩት ኮንዶሚኒየም ቤቶች በአጭር ግዜ የመሰንጠቅ የመተርተር የመፍረስ አደጋ ላይ የሚወድቁበትም ምስጢር ይሄ ነው፡፡

በድሮ ግዜያት በጠንካራና ብቃት በነበራቸው መሐንዲሶች ተሰርተው ሀምሳና መቶ አመት የዘለቁትን ዛሬም ያሉትን ፎቆች ስናይ ምን ያህል ብቁ ሙያተኞች ትላንት ነበሩ ለማለት ያስችላል፡፡ ይኼ ሁሉ ብልሹ አሰራር የሚመነጨው መንግስታዊ ኃላፊነታቸውንና አደራቸውን ጠብቀው ለመወጣት ባልቻሉ በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ገንዘብ በተጠለፉ ሹማምንት መነሻነት ነው፡፡

ጥብቅና መንግስታዊ መመሪያውን የተከተለ ቁጥጥር አያደርጉም፡፡ሕጉና ስርአቱ ደንቡ ከሚፈቅደው ውጭ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር በመመሳጠር ሕዝብና ሀገርን አደጋ ላይ ጥለዋል፡፡

ብቁ ሙያተኞች ካልሰሩት በብዙ ሚሊዮኖች የሀገሪቱ ገንዘብ ወጥቶባቸው የተሰሩ መንገዶች ድልድዮች ኮንዶሚኒየም ቤቶች በአጭር ግዜ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ፡፡ ይበላሻሉ፡፡ በቂ አገልግሎት ሳይሰጡ ለእድሳት ተጨማሪ ወጪ መንግስትን ያስወጣሉ፡፡ በተፈፀመ ውል በተሰጠው የግዜ ገደብ መጠናቀቅ ያለበት ስራ የውሉን ግማሽ ክፍያ ስራውን ለመጀመር ወስደው ጭርሱንም የማይሰሩበት ስራውንም የማይጀምሩበት ተራ ምክንያት በማቅረብ እንደገናም ተጨማሪ ወጪ ተሰልቶ ለበላይ አቅርበው የሚፈቀድበት እጅግ በጣም አሳዛኝ ሀገርና ሕዝብን የጎዱ ተግባራት ሲፈጸሙ ኖረዋል፡፡

የበላይ ኃላፊዎች የሚያዙበት የሚፈርሙበት ገንዘብ ከድሀውና ከግብር ከፋዩ የተሰበሰበ የሕዝብ ገንዘብ መሆኑን ለማስተዋል አለመቻላቸውም አስገራሚ ነው፡፡ አብዛኛው ሙስና በብዙ ተቋማት ጭምር ሲካሄድ የኖረው ያልበላ ያልዘረፈ ይቀጣል የተባለ ይመስል የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ በሚል እሳቤ ከእለታት በአንዱ ቀን እንጠየቃለን ብለው ለማሰብ በተሳናቸው ሕሊናቸው በጥቅም በታወረ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ነው፡፡ በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ ፤እልም ካለው ገደል ገብተህ ቀረህ ወይ የሚባለው አይነት መሆኑ ነው፡፡

በየደረጃውና በተለያዩ ምድብ ስራዎች የነበረው ከፍተኛ አመራር እግር በእግር እየተከተለ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ባለማድረጉ ምክንያት የተፈጠረ ችግርም ነው፡፡ ሌላው የነገሰው አድርባይነት የምንአገባኝ ስሜት የመንግስት ሀብት ሲዘረፍ ከማጋለጥ ይልቅ በተባባሪነት መቆም የጥቅም ተጋሪ መሆን ለሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት መንሰራፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎአል፡፡በሕዝብ ንቅናቄ በመደገፍ ልንታገለው ልናስወግደው ግድ ይላል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy