Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌዴራል ስርዓቱ ለችግሮቻችን ሁሉ ፈውስ ሠጥቷል

0 346

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌዴራል ስርዓቱ ለችግሮቻችን ሁሉ ፈውስ ሠጥቷል

አባ መላኩ

አገራችን ለዘመናት ስትማስንባቸው ለነበሩ ችግሮች ሁሉ ምላሽ ያገኙት በኢፌዴሪ ህገመንግስት ነው።  የፌዴራል ስርዓታችን የህገመንግስታችን አንዱና ትልቁ   ቱሩፋት ነው።  የፌዴራል ስርዓታችን ለአገራችን  ዘላቂ ሰላም መስፈን  ዋንኛ መሰረት ነው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ማንም ብሄር ወይም ብሄረሰብ የበላይ ወይም የበታች የለም።  ሐኪም ከፈጣሪ ቀጥሎ የሰዎችን ጤና የሚንከባከብና ስቃይን የሚያስታግስ እንደሆነ  ሁሉ  የፌዴራል ስርዓታችንም በአገራችን ይስተዋሉ ለነበሩ ውለው ላደሩ ችግሮች ሁሉ እልባት የሰጠና ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ   መሰረት የጣለ  ነው።  

 

አገራችን የጀመረችው  የጸረ ድህነት ትግሉን  በያዝነው  ፍጥነት የምናስኬደው ከሆነ ባስቀመጥነው የጊዜ ገደብ  ውስጥ  አገራችን  መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ልናሰልፋት እንደምንችል  በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  የዛሬው  ነጻነትንና እኩልነት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  መራራ  የህይወትና የአካል መሰዋዕትነትን ከፍለውበታል። በርካታ ወጣቶች ውድ ህይወታቸውንና አካላቸውን ገብረውበታለ። ለዘመናት በአገራችን በተካሄዱት የእርስ በርስ  ጦርነቶች ሳቢያ   እንደኢትዮጵያ  ህዝቦች  የተንገላታ ህዝብ  ያለ አይመስለኝም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  የአገርና  የህዝብ  ቀንደኛ  ጠላት   ድህነት እንጂ የነጻነት እጦት አይደለም።  የድህነት ትግል  የህይወት መሰዋትነትም ሆነ የአካል መጉደልን አይጠይቅም።  የድህነት የትግል መንገድ መራብ መጠማትን፣ ተራራ መውጣትና ቁልቁለት  መውረድን፣ ስቃይና መከራን የሚጠይቅ አይደለም። ይልቁንም  አገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው  አገራት ተርታ ለመሰለፍ ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቀው   በተሰማራንበት መስክ  አገርንና ህዝብን በትጋትና ታማኝነት ማገልገል  ብቻ ነው። ይህን ማድረግ የሚከብድ አይደለም።  

 

ታላቁ መሪ   በአንድ ወቅት  ሲናገሩ  የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ድህነት እንደሆነ አስምረው፣ ይህን  ጠላታችንን  ማሸነፍ  ከቻልን  ችግሮቻችን ሁሉ  መፍትሄ ያገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል። የአገር ጡንቻ ፈርጣማ የሚባለው ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ስትችል ብቻ ነው።  ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላትን አገር ማንም ሊደፍራት አይቻለውም።  ጠንካራ ኢኮኖሚ  ያላትን አገር  ማንም በፈለገው ጊዜ እየተነሳ ይህን አድርጊ ወይም ይሄን አታድርጊ ሊላት አይችልም።   ለድህነታችን መንስኤዎቹም ሆነ መፍትሄ አምጪዎቹ እኛው ራሳችን እንጂ ማንም ሊሆን አይችልም። አሁን ላይ  አገራችን የድህነት መውጫ መንገዱን ተያይዛዋለች። የነብርን ጭራ አይዙም ከያዙም … እንደሚባለው ነው።      

    

የኢፌዴሪ ህገመንግስት  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና  ህዝቦች ነጻነትና እኩልነትን በተጨባጭ ማረጋገጥ አስችሏል። ዛሬ  ማንም የፈለገውን  ሃሳብ  በነጻነት ማራመድ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።  ያልተማከለ አስተዳደር  ስርዓቱ  ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደረ እንዲችሉ  ሁኔታዎችን ፈጥሯል።  ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን መፍታት የቻለችው ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት መከተል በመቻሏ እንደሆነ በተጨባጭ ታይቷል።  የፌዴራል ስርዓታችን ለአዲሲቷ  ኢትዮጵያ ዕውቅ ሃኪም ሆኗታል።   ህገመንግስታዊ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት በመቻሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ዕርስ በርስ በመተማመን ላይ የተመሰረተ አንድነት  መገንባት ተችሏል።  

 

አገራችን ትላንት ትታወቅበት የነበረው ድርቅ፣ ረሃብና ጦርነት ዛሬ የለም።  የአገራችን ገጽታ እጅጉን ተሻሽሏል። በረሃብ የሚሞት ወይም ቀየውን ለቆ የሚሰደድ ህዝብ የለም። መስራት የሚችልና የሚፈልግ  ማንኛውም  ዜጋ ይነስም ይብዛም  ጦሙን የማያድርባት አገር መፍጠር እየተቻለ ነው።  ለዚህ ጥሩ ማረጋገጫ የሚሆነው  አገራችን ከራሷ ህዝቦች ባሻገር  ወደአንድ ሚሊዮን ለሚጠጋ  የጎረቤት አገራት ህዝቦች መጠጊያ እስከመሆን ደርሳለች። ይህ በአትኩሮት ለተመለከተው ትልቅ ጥንካሬ ነው። ይህ የሆነው የፌዴራል ስርዓቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ ራሳቸውን በራሳቸው  ማስተዳደሩ እንዲችሉ፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያዳብሩ   ሁኔታዎችን  በማመቻቸቱ ሳቢያ ነው። ይህ በመሆኑም አሁን ላይ አገራችን ዘላቂ ሰላም ማስፈን ችላለች። ዘላቂ ሰላም  ማስፈን በመቻሉም አገራችን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን በቅታለች። ትላንት በጦርነትና ረሃብ ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ የኢነቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን በቅታለች።

 

አገራችን በአፍሪካም ሆነ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ የመጣው የውስጥ ጥንካሬዋ  ውጤት ነው። በአገር ውስጥ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ መቻሉና ዋስትና ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት በመጀመሩ መንግስትና ህዝብ ትኩረታቸውን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና  ልማትን ወደማፋጠን ሆኗል።  ኢትዮጵያ የምትከተለው  የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ  በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ  ያለመግባትና  የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት  ያደረገ  በመሆኑ  ከማንኛውም አገር ጋር  ተቀራርቦ መስራት የሚያስችል ሁኔታን ፈጥሮላታል። በቅርቡ እንኳን  በባህረሰላጤው አገራት መካከል ማለትም በሳዑዲ  በሚመራውና በኳታር መካከል በተነሳው ያለመግባባት ኢትዮጵያ አስቀድማ የኩዌትን አቋም በመደገፍ አገራቱ ችግሮቻቸውን በመነጋገር እንዲፈቱ ጠይቃለች።  

 

ኤኮኖሚክ ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገው የአገራችን  የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ  የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ  ከማረጋገጡም ባሻገር በቀጠናው አገሮች መካከል ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር እንዲፈጠር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን  በመገንባት ላይ ነች።  አገራችን  የተከተለችው  ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ በመሆኑ ዓለምን ያስደመመ ፈጣን እድገት  በማስመዝገብ ላይ ነች።   

 

የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ፤ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጎልበት እንዲሁም  ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ  ምቹ ሁኔታን  የፈጠረ  ነው። ልማትና ዴሞክራሲ ለአገሪቱ ዘላቂ ህይወት ወሳኝ ናቸው። በኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ነገሮች ናቸው። ምክንያቱም መንግስትን የሚመራው ድርጅት ለ17 ዓመታት የታገለው የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማረጋገጥ ነው። በኢትዮጵያ  የብሄሮችና ብሄረሰቦች   የእኩልነት ጥያቄ የዘመናት  በአገሪቱ ይስተዋሉ ለነበሩ  ግጭቶች  መንስዔ  በመሆኑ  እነዘህን  የህዝብ ጥያቄዎች መፍታት የሚቻለው  ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመተግበር ብቻ ነው።  በመሆኑም የኢፌዴሪ  መንግስት የዴሞክራሲ ስርዓትን ማጎልበትና  ልማትን ማፋጠን  የአገሪቱ ህልውና መሰረቶች አድርጎ በመውሰድ ለስርዓቱ ህልውና  እነዚህ ጉዳዮችን  ማሳካት የሞት ሽረት ጉዳይ  ነው።  

 

ከእንግዲህ በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት የማይቀበል  አገዛዝ  ተቀባይነት እንደማይኖረው በህገ-መንግስቱ ተረጋግጧል።  በመሆኑም  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ህልውና የሆነውን የፌዴራል ስርዓት  ለማፍረስ መሞከር አደጋው የከፋ ነው። የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት ልማትን በማፋጠንና የዴሞክራሲ ስርዓቱን  በማጎልበት ብቻ ነው። ልማትን ለማፋጠን ተብሎ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በኢትዮጵያ ሊተገበር አይቻልም። ለመተግበር መሞከርም ትርፉ ጦርነትና እልቂት እንደሚሆን ካለፈው ስርዓቶች ጥሩ ትምህርት ተቀስሟል። የኢፌዴሪ መንግስት የህብረተሰቡን ፍላጎት ያገናዘበ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትንና ልማትን ማጣጣም የሚያስችል አካሄድን መከተል በማስቻሉ  ባለፉት አስራ አራት   ዓመታት ዓለምን ያስደመመ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። የአገራችን ፈጣን ዕድገት  በአይናችን  ያየነው፣ በጃችን የዳሰስነው እንዲሁም  በእያንዳንዳችን ህይወት ላይ ተጨባጭ  ለውጥ ያመጣ   ነው።        

 

ከቅርብ ጊዜ በፊት በምግብ ሰብል ራሷን መቻል የተሳናት አገር በተከታታይ አመታት እንዲህ ያለ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ መቿሏ ጠንካራ አመራርና ትክክለኛ ፖሊሲ  እንዳላት የሚያሳይ ጉዳይ ነው። በአካባቢው ካሉ አገሮች ኢትዮጵያ በርካታ ህዝብ ያላት አገር ከመሆኗ ባሻገር ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት  በማስመዝገብ  ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ አገር እንድትሆን አስችሏታል። ዛሬ አገራችን በአገር ደረጃ  በምግብ ሰብል ራሷን ችላለች። ባለፈው የመኸር ወቅት ብቻ በዋና ዋና ሰብሎች  ከ320 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል መሰብሰብ ተችሏል። ይህን ምርት ዘንድሮ ወደ 345 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ በመሰራት ላይ ነው። አገራችን  በአጭር ጊዜ እንዲህ ያለ ተጨባጭ ለውጦችን ማሳየት መቻሏ ለአፍሪካ አገራት  ጥሩ ማሳያ ተደርጋ ልትወሰድ ትችላለች።  

ኢትዮጵያ  ለአፍሪካ  ሞዴል ልትሆን የምትችለው  በኢኮኖሚያዊ  ዕድገት ብቻ ሳይሆን በአካባቢው በዘለቄታ ይታይ የነበረውን ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ በምታደርገው ጥረትም  ጭምር ነው።  ኢትዮጵያ በፀረ ሽብር ትግሉ  የታላላቅ መንግስታት ጭምር ጠንካራ አጋር ለመሆን በቅታለች። በሶማሊያ ያለው የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው ጽንፈኛ አልሸባብን በሶማሊያና በአካባቢው አገሮች እያደረሰ ያለውን ጥፋት መመከት የተቻለው በአገራችን ግንባር ቀደም ተዋናይነት ነው።   በመሆኑም  የዛሬው የአገራችን  ሰላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ መሰረቱ  የፌዴራል ስርዓታችን ውጤት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። የፌዴራል ስርዓታችን ለአገራችን ችግሮች እልባት ሰጥቷል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy