Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌዴራል ስርዓቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሰረት ነው

0 345

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌዴራል ስርዓቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሰረት ነው

ዮናስ

 

በሃገራችን የፌዴራል ስርዓት እውን ከሆነ ጀምሮ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን  በራሳቸው ማስተዳደር ችለዋል፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብሯል፤ አካባቢያቸውን ማልማት ችለዋል፤ በሁሉም አካባቢዎች ልማትና ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል፤ በዚህም ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆን ችሏል። ይህ ብቻም አይደለም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ፍቃደኛ የሆነ ህዝባዊ መንግስት የተመሰረተ በመሆኑ ማንም ቅሬታ ያለው አካል ህጋዊ በሆነ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብ የሚችልበት ስርአት ተፈጥሯል። ያም ሆኖ ግን አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ የሆኑት ትምክህትና ጥበት ስርአቱን በመፈታተን ላይ ናቸውና  ጉዳዩን ማብላላት እውነታውን ለመገንዘብ ጠቃሚ ስለሚሆን ብናነሳው፤ አንስተንም ብንወያይበት ተገቢ ይሆናል።

 

የትምክህት ሃይሉ በብሄሩ ጥላ ስር ተከልሎ የተጠቃንና ተጎዳን አስተሳሰቡን በአግባቡ አሰናድቶ በማሰራጨት አማላይ ቃላትና ስስ የማህበረሰቡ ፍላጎቶችን በመነካካት የአገራችን ህዝቦች እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ ብሎም ወደመተላለቅ እንድሄዱ ያለማቋረጥ በመስራት ላይ ይገኛል። የትምክህት አስተሳሰቡን ለማራመድ የሚያስችለውን ህበረተሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ ቅሬታዎችን፣ አመራሩ አካባቢ የሚፈጠሩ የአመራር ጉድለቶችንና የመንግስት መዋቅር ውጤታማ ባልሆነባቸው አካባቢ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለቅሞ በመቀመር ለሁከትና ለአመፃ እየተጠቀመባቸው ነው።

 

በዚህ ስርአት ተወልደው ያደጉና ተምረው ስራ ያላገኙ የአርሶ አደሩን ልጆች በመያዝ ገና በማለዳው በህገ-መንግስቱ ላይ የተመለሰውን የማንነት ጥያቄ አወገርግሮ በማቅረብና በማዛባት፣ በተለያየ ምክንያት ከአመራር የተወገዱ ሰዎችን በአስረጅነት በማቅረብ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን የአፈፃፀም ክፍተቶች ከኒዮ ሊብራሊዝም አስተምህሮ በመነሳት በወጣቶቹ ላይ ሰፋ ያለ የማነሳሳትና የመቀስቀስ ስራ በመስራት ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የወጣት ሃይልን ለአመፃና ለሁከት ሲጠቀም ተስተውሏል። በዚህም ምክንያት በማህረሰቡ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲነግስ፣ ጥላቻ እንዲዘራ፣ በፀጥታ ሃይሎችና በህግ አስከባሪ አካላት ላይ እምነት እንዳያድር ከማድረግ አንስቶ የትምክህት ሃይሉ አንዳንድ ቦታ እንደተስተዋለው በመሳሪያ እስከመፋለም ደርሷል።

 

ሃገር ውስጥ የሚገኘው የትምክህት ሃይል በውጪ ከሚገኘው የዚህ ሃሳብ አቀንቃኝ ጋር በመዛመድ ገንዘብና ክሂሎቱን በማጣመር ሁሉንም የግኑኝነት አማራጮች በተሰላ መንገድ በመጠቀም የሞት ሽረት ትግል እያካሄደ ነው። ሲመቸው ከጥበት ሃይሉ ጋር ጋብቻ እየፈፀመ፣ ሳይመቸው ደግሞ ከዚህ ሃይልም ጋር እየተናቆረ እየቀጠለ ያለው ይህ የትምክህት ሃይል ሁሉም የልማታዊ መንግስታችን ክፍተቶች ሁሉ የኔ ምቹ ሜዳ ናቸው ብሎ በመውሰዱ ክፍተቶቹን በማባዛት፣ በማድመቅና በማጉላት እድሎቹን ሁሉ እየተጠቀመ ነው።

 

ሌላው የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ጥበት ነው። የጥበት ሃይሉ በአገራችን ፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም የረባ ለውጥ ሳያመጣ አሳቻ ጊዜና አመቺ ሁኔታ ሲፈጠር ብቅ እያለ መኖሩን የሚያሳውቅ፣ ሁከትን፣ ብጥብጥንና ትርምስን በመፍጠር የፈረሰች አገር ለመፍጠር እየሰራ ያለ ሃይል ነው። ይህ ሃይል በዋናነት መነጠልን የሚያቀነቅን ሲሆን፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የጋራ አገር ስለመፍጠር ፍላጎቱም ሆነ አስተሳሰቡ የለውም። በጋራ በመስራትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እምነት የለውም። እሱም እንደ ትምክህት ሃይሉ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ያጥወለውለዋል። የአገራችን የፌዴራሊዝም ስርአት በፍፁም አይዋጥለትም።

 

የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለጋራ ልማትና አገር ግንባታ የሚያደርጉት ርብርብ ስለማይመቸው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህን ለማደናቀፍ ይጥራል። ጠባብነት ሌላውን በጠላትነት የሚመለከት፣ ያለፈ በደልን ጭቶ እያከከ ቁስሉን በማመርቀዝ/በታሪክ  ሂደት ውስጥ ገዥ መደቦች የፈጠሩትን  ስህተት የአንድ ብሄር አባላት እንደፈፀሙት አድርጎ የማቅረብ ዘዴ ሰዎችን ለብጥብና ለጥላቻ እያነሳሳ የሚጓዝ ሃይል ነው። እየሆነው ስላለው እድገትና ህዝቦች በትግላቸው ስለተቀዳጇቸው መብቶችና ከመብቶቹም ስለተገኙ ጥቅሞች አብዝቶ ከመናገርና እነዚህን እድሎችና መብቶች አስፍቶ ከመጠቀም ይልቅ የፌዴራሊዝም ስርአቱ የአፈፃፀም ክፍተቶችን ለቅሞ በመቀመር፣ በአመራር፣ በመዋቅርና በፈፃሚው ሃይል የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችንና  ከኢኮኖሚ እድገቱ ጋር ተያይዘው የመጡ የእድገት ፍላጎቶችንና ጥያቄዎችን አውገርግሮ የፖለቲካ ጥያቄ በማደረግ ሁሌም የመነጠል ጥማቱን ለማርካት ሲሰራ ይሰተዋላል።

 

በዚህም ምክንያት በአስተሳሰቡ ዙሪያ ሰዎችን በማሰባሰብ፣ በማሰልጠንና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በመደለል ሁከትና ብጥብጥ ለመፈጠር ሰርቷል። እየሰራም ይገኛል። የአገራችንን ሰላም ለማደፍረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፤ በልማታዊ መንገድ ሠርተው ለመበልፀግ የሚጥሩ ዜጎችን ሃብት ንብረት አውድሟል። ብሄር ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ዘር በመዝራት ሰዎች እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ እንዳይተማመኑና ከልማት ግስጋሴያቸው እንዲገቱ ባለ በሌለ ሃይሉ ተሯርጧል፤ እየተሯሯጠም ነው።

 

የጥበት ሃይሉ በሚኖርበት አካባቢና አስተሳሰቡን በተሳሳተ መንገድ በሚሸምቱ  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የዘራው ጥላቻና የጥፋት አመለካከት ውድምትን ከማስከተል አልፎ ማህበረሰባዊ ቅራኔዎችንና ጥርጣሬዎችን እስከመፍጠር ደርሷል። ጥበትና ትምክህት በተለያየ ጫፍ የተሰለፉ እርስ በርስ የሚበላሉ ሃይሎች ቢሆኑም፣ የአንዱ ህልውና የተመሠረተው ሌላውን በጠላትነት በመፈረጅ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ነገር ግን ተቃቃቅፈው ሁከትና ብጥብጥ ለማንገስ ሲሰሩ የቆዩና እየሰሩ የሚገኙ ናቸው።

 

የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ እድል እያገኘ ሲመጣ፣ ከመደፈቅ ይልቅ ቀና የማለትና የመለምለም አጋጣሚ ሲበረክትለት መቀልበስ አስቸጋሪ ይሆናል። በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የተሃድሶ መስመሩ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ጥበትና ትምክህት ስርአቱን ለማፍረስ ብሎም እርስ በርስ ለመጠፋፋትና በመጨረሻም የማንም ያልሆነች አገር ለመፍጠር ለሰከንድም ቢሆን የማይተኙ ዋንኛ  አደጋዎች ናቸው። አመቺ እድልና አጋጣሚ ባገኙባቸው ጉዞ ውስጥ የተስተዋለው ሃቅም ይኸው ነው። ስለሆነም እነዚህን ሃይሎች አጥብቆ አለመታገል የሚያስከፍለው ዋጋ ውድ ነው።

 

የፌዴራል ስርዓቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የአንድነት መሰረት መሆኑን ተገንዝቦ እና ይህንኑ ሰንቆ እነዚህን ሃይሎች ሊፋለም ይገባል። የጥበትና ትምክህት ሃይሎች እርስ በርስ የሚያደርጉት ሽኩቻ  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽር፤ አንድነትን  የሚያላላ  መሆኑን  ተገንዝቦ በማስገንዘብ ይህን ሃይል ሊፋለመው ይገባል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሰረት የሆነው የፌዴራል ስርዓት በህዝቦች መካከል መቻቻልና መከባበር እንዲሁም መተማመንን ያጎለበተልን እንጂ ከላይ በተመለከተው አግባብ የሚያለያየን ስርአት አይደለም። የጥበትና የትምክህት አስተሳሰብ የአገሪቱን ህዝቦች እኩልነት የሚያደናቅፍ እኩይ አጀንዳ ነው። በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን አንድነትን የሚያናጋ፣ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለአደጋ የሚዳርግ አካሄድ በመሆኑ ሁሉም አካል ይህን ማውገዝና ብቻ ሳይሆን በተግባር ሊፋለመው ይገባል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy