Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ አንድና ብቸኛው አማራጭ ነው!

0 381

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ አንድና ብቸኛው አማራጭ ነው!

ወንድይራድ ኃብተየስ

በአገራችን ድጋፍንም ሆነ ተቃውሞን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መግለጽ  ህገመንግስታዊ መብት ነው። በሰላማዊ መንገድ የሚካሄዱ ድጋፎችም  ይሁኑ ተቋውሞዎች  ክፋት የላቸውም። ህገመንግስታዊ መሰረትም ዋስትናም አላቸው።  ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ በማራመድ የሃሳብ ብዘሃነትን ማሳየት የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ  ነው። በኢትዮጵያ በርካታ ልዩነቶች ይስተዋላሉ። ለአብናት የሃሳብ፣ የሃይማኖት፣ የብሄር፣ የባህል፣ ወዘተ። ኢትዮጵያን እንደአገር እናስቀጥላት የምንል ከሆነ ልዩነታችንን የሚያስተናግድ  ስርዓት  መከተል የግድ ይላል። ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መተግበር  ለኢትዮጵያ አንድና  ብቸኛ  አማራጭ ነው።  በርካታ ፖለቲከኞች በተለይ ከፍተኛ አመራሮች ሲገዕጹ እንደምንሰማው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የምትተገብረው ማንንም ለማስደሰት ሳይሆን ዴሞክራሲ  የአገሪቱ ህልውና መሰረት በመሆኑ ብቻ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።  

 

የጥበትና ትምክህት ሃይሉ ይህን በአግባብ የተረዳው አይመስልም። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች እርስ በርስ በሚያደርገው መጓተት አገራችንን እንዳያውኳት  መከላከል የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል። ጽንፈኞች  ህዝቡ  ደም ቢፋሰስ አይገዳቸውም፣ ለንብረት ውድመት አይጨነቁም፣ ለአገር ገጽታ መበላሸት አያስቡም፣  የእነሱ ብቸኛ ህልም ወደ ስልጣን ማማው መሰቀል ብቻ ነው።  ለዚህም ይመስለኛል ጽንፈኛ ሃይሎች  በአገሪቱ  ሰላም እንዲሰፍን የተጀመሩ  ዴሞክራሲያዊ  ስርዓቶች  እንዲጎለብቱ ከማድረግ ይልቅ  ሁከትና ረብሽን  የሚናፍቁት።  

 

ከዚህ በፊት በአገራችን የተካሄዱ ተቃውሞዎች ሁሉ በጥፋትና በውድመት የታጀቡ ነበሩ። ለአብነት በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ሶስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ  በተከሰተው ተቋውሞ የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል። በወቅቱ ጽንፈኛ ሃይሎች ያሰቡት አልሳካ አላቸው እንጂ በርካታ ጥፋቶችን ለማድረስ አስበው ነበር። ሰላም ወዳዱ ህዝብ በቃችሁ፣ አብሮነታችንን አታበላሹት በማለት የጥፋት ሃይሎችን እያጋለጠ ለህግ እንደሰጣቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።  በቅርቡም የአማራና ኦሮሚያ  ክልሎች በአንዳንድ  አካባቢዎች የተካሄዱ ተቃውሞዎች ፈር የለቀቁ አብሮነትን የሚያበላሹ እንደነበሩ ተመልክተናል። ይህንንም የነውጥ አካሄድ የገታው የጸጥታ አስከባሪ ሃይሉ  ከየአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር እንደነበር ይታወቃል። አዎ ህዝብ ሁሉን ማድረግ እንደሚችል ያ ሂደት ጥሩ ማሳያ ነበር።

ጽንፈኛ ሃይሎች የህብረተሰብን ጥያቄ ከለላ በማድረግ  ለነውጥ ያነሳሳል  ያሉትን ስሜት ኮርኳሪ ነገሮችን በመጨማመር  ወጣቱን ወዳልተፈለገ መንገድ እንዲያመራ አድርገውታል። በዚህም ንጹሃንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ህይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረት ወድሟል ስነልቦናዊ ውድቀት ደርሷል። የአገራችን መልካም ስም አጉደፏል። ጽንፈኛው አካል ይህን የዜጋ ህይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት መውደም ከዝና ቆጥረውት  በየማህበራዊ ሚዲያው እኔ ነኝ እኔ ነኝ እንዲህ ያደረግሁት በማለት የጥፋትና የውድቀት ክሬዲት  ለማግኘት ሲፎክሩ ተመልክተን። የጥበትና የትምክህት ሃይሉ ከህዝብ የሚነጥለውን ነገር እንኳን በአግባብ አልተረዳውም።  ጽንፈኛው  አካል ጥሩ ፖለቲከኛ አይደለም። ከህዝብ የነጠለውን ነገር በዝና ሲያወራው ተመልክተናል።     

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መታወቅ ያለበት ነገር ማንም ይሁን ማንም  ከእንግዲህ  ወደ ስልጣን የሚመጣው  በህገመንግስታዊው መንገድን ማለትም ከምርጫ ኮሮጆ በሚገኝ ድምጽ እንጂ በአመጽና በሁከት ሊሆን እንደማይችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።   በዴሞክራሲያዊ መንገድ መንግስት ይመጣል መንግስት ይሄዳል። ኢህአዴግ በቀጣዩ ምርጫ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፤ ይህን የሚወስነው  ህዝብ ብቻ ነው።  ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ይህን ጉዳይ ያሰቡበት አይመስለኝም።

አንዳንዴ ሳስበው ጽንፈኛው አካል  በዚህ አቋሙ ስልጣን  ቢይዝ እንኳን  ማንን እንደሚያስተዳድር እንኳን በአግባብ ጠንቅቆ ያወቀው አይመስለኝም።  ከበሮ በሰው እጅ ያምር…  እንደሚባለው  እንደኢትዮጵያ ያለ በርካታ ልዩነቶች የሚንጸባረቁባት እና በርካታ ፍላጎቶች የሚስተዋሉበትን አገር በስኬት መምራት እንዴት ከባድ እንደሆነ መገመት የሚከብድ አይመስለኝም። እንደሰውኛ  ሆነን ብናስብ መልካም ነው። አገራችን ቤተሙከራ (ላቦራቶሪ) አይደለችም። ህዝብ የጠባቦችና የትምክህተኞች  አስተሳሰብ  መጓተቻ  ቦታ አይደለም።  

የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ጅምር ይሁን እንጂ  የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚችል ደረጃ  ላይ ደርሷል። አገራችን ህግመንግስታዊ መብቶች የተረጋገጡባት፣ ማንም የፈለገውን ሃሳብ  በሰላማዊ መንገድ  ማራመድ የሚችልባት  ሁኔታዎች ተመቻችቷል። የፌዴራል ስርዓቱ የህገመንግስቱ አንዱ ትሩፋት ነው። የፌዴራል ስርዓቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸውን እንዲያውቁ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ እድል አጎናጽፏል። ይህን ስርዓት በሃይል ለማፍረስ  ከሚንቀሳቀስ ሃይሎች ጋር ማበር የህግ  ተጠያቂነት ያስከትላል።  የኤርትራ መንግስት እና ግብራበሮቹ (ግንቦት ሰባት፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ወዘተ) የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት መልካምነት  እንደማይመኙ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በእርግጠኝነት እንድናገር ያደረገኝ  በአገራችንና በህዝባችን  ላይ ካካሄዱት ተደጋጋሚ የጥፋት ተልዕኮዎች በመነሳት ነው።  

የጥበትም ይሁን የትምክህት ድርጊት ብቻ ሳይሆን  አስተሳሰብ  ለፌዴራል ስርዓታችን ከፍተኛ ስጋት ናቸው። ይህ አስተሳሰብ በበርካታ ሰዎች ላይ እያስተዋልነው ነው። ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው ይህን አስተሳሰብ ወደ ተግባር ሳይሸጋገር ልንቀጨው ይገባል። የጥበትና ትምክህት አስተሳሰብን በመዋጋት መንግስት ብቻውን የሚያመጣው አንድም ነገር ሊኖር አይችልም። በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ይህን አስተሳሰብ መዋጋት ይኖርበታል።  

የሰላምን ዋጋ የሚያውቀው ጦርነትን ግጭትን  የሚያውቀው ነው። አዲሱ ትውልድ በደርግ ስርዓት የነበረውን የአፈናና የመከራ ወቅት  ስለማያውቀው ለጽንፈኞች  የተዛባ አስተሳሰብ ተጋልጦ ተመልክተናል።  የጥበትና የትምክህት ሃይሉ በማህበራዊ ሚዲያና በመርዘኛ ሚዲያዋቻቸው አገራችንን ወደ ሁኩት መክተት ለወጣቱን ለመጠቀም ዛሬም  በመሯሯጥ ላይ ናቸው።  ህዝብ የሚያነሷቸው ተገቢ ጥያቄዎችን ከለላ በማድረግ አገርን የሚያውኩ ዘረኛ ድርጊት የሚፈጽሙ ሃይሎችን ልንቃወማቸው ይገባል። የህዝብ ጥያቄዎች በነውጥ እንደማይመለስ ካለፈው ነገሮች ልንማር ይገባል። መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመመለስ ላይ ነው።  

በአገራችን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው  ብሎ መነሳት  ተዓማኒነትን ያሳጠል። እንኳን በእኛ ጀማሪ የዴሞክራሲ ስርዓት ይቅርና በምዕራባዊያን የጎለበት  ዴሞክራሲ ስርዓት  ውስጥ በርካታ ውጥንቅጦችን እየተመለከትን ነው። የትምክህትና ጥበት ሃይሉ ፍላጎት  ወደስልጣን ኮርቻው መሰቀል እንጂ  ለአገር ዕድገት እና  ለህዝብ  ጥቅም መቆም አይደለም። በአገራችን መልካም ጅምሮች  አሉ።  ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ከዜሮ በታች የነበረን ኤኮኖሚ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተደናቂ ማድረግ ተችሏል። በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ባለሁለት አሃዝ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነቱን ካረጋገጥን  በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ህዳሴያችንን ማረጋገጥ ይቻላል። ራዕያችን እውን የሚሆነውና  ፍላጎታችን የሚሳካው  ያለንን አስጠብቀን ተጨማሪ ልማቶችን ማስመዝገብ ስንችል ብቻ ነው።  

በኤርትራ መንግስት አስተሳሰብ  ጠንካራ  ኢትዮጵያ ለእርሱ ስጋት ነች። በእርግጥ የኤርትራ መንግስት አልተረዳውም እንጂ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለኤርትራ ህዝቦች  መጠጊያ መሸሻ ሆናለች።  ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በቀጥታ ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ዛሬ አገራችን  ከሁለት መቶ ሺህ በላይ የኤርትራ ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሳይሆን እስከሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የትምህርት ዕድል እንዲሁም የስራ ዕድል በመስጠት ላይ ነች።  እንዲህ ያለ ሁኔታዎች የተመቻቹት አዲሲቷ ኢትዮጵያ  ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት በመቻሏ እንጂ እንደቀድሞው ጊዜ ያለች ኢትዮጵያ ብትሆን ኖሮ  እንኳን ለጎረቤት አገራት ህዝቦች ይቅርና ለራሷም  አትሆንም ነበር። አሸባሪዎችና ሁከት ናፋቂዎች  ጠንካራዋን ኢትዮጵያ ቢጠሏት ወይም ቢፈሯት አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም  የጥፋት ሃይሎች (የኤርትራ መንግስትና አልሸባብ) ጠንካራዋ ኢትዮጵያ ለጥፋት ተልዕኮቸው አትመችም። የትምክህትና የጥበት ሃይሉ ከኤርትራ መንግስት ጋር በማበር በህዝባቸውና በአገራቸው ላይ የጥፋት ማሳኪያ መሳሪያ ሆነዋል።  

     

የጥበትና ትምክህት ሃይሎች  ትንሿን እንከን በማጉላትን  በህዝቦች መካከል ልዩነት በመፍጠር ተክነዋል። የእነዚህን የጥፋት ሃይሎች አካሄድ ልንቃወም የምንችለው ምክንያታዊ አስተሳሰብን  በማንገስ ብቻ ነው። ምክንያታዊነት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሊጎለብት ይገባል። እንደእኔ እንደኔ  ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምክንያታዊ ያለሆነ ትችት ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊ ያልሆነ ድጋፍም አይበጃትም።  የእነዚህ  ሁለት ሃይሎች  የጥፋት ዲግሪ ይለያይ እንደሆን እንጂ ውሎ አድሮ ምክንያታዊ ያለሆነ ድጋፍም ለመንግስት አይበጀውም።  በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ትችትም  ይሁን ድጋፍ  መንግስትን ያስተምራል፣ አገርን ያሳድጋል።   

የጥበትና ትምክህት አስተሳሰብ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ  የሚበጇት አስተሳሰቦች አይደሉም። ዘረኝነትና ጎጠኝነት  የጥፋት እና ግጭት ምክንያቶች ናቸው።  በመሆኑም  ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ  በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ የጥበትና ትምክህት አስተሳሰቦችን መዋጋት ይኖርበታል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ  የምንመለከታቸውን  ዘረኞች ከየትኛውም ብሄር፣ ከየትኛውም አካባቢ ወይም ከየትኛውም ኃይማኖት ይሁኑ ልናወግዛቸው ይገባል።   በስሜታዊነት  የሚቀሰቀስ አመጻና ነውጥ  መነሻውም መድረሻውም አይታወቅም። ባለፈው ጊዜ በአገራችን ለተከሰተው ሁከት ምክንያት የነበሩት የትምክህትና የጥበት ሃይሉ እንደነበሩ ማስታወስ ተገቢ ነው።  በመሆኑም የህግ የበላይነት የሚከበረው በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሰላም ወዳድ ህብረተሰብ በመሆኑ የጥበትና ትምክህት አስተሳሰቦችን መዋጋገት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy