Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግብርን መክፈል የዜጎች የውዴታ ግዴታ ነው!

0 611

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግብርን መክፈል የዜጎች የውዴታ ግዴታ ነው!

                                                            ታዬ ከበደ

ግብር የአንድ አገር ኢኮኖሚ የደም ስር ነው። ግብር መከፈል አገራዊ ግዴታ ብቻ አይደለም። ዜጎች ለአገራቸው ሲሉ ከሚያገኙት ላይ የሚከፍሉት የውዴታ ተግባርም ነው። እናም ግብርን በወቅቱ መክፈል የዜጎች የውዴታ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

እርግጥ ቀደም ሲል በቀን ገቢ ግብር ትመናው ወቅት ተፈጥሮ የነበረው ብዥታ በሂደት እየጠራ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ህዝብ ግብሩን በመከፈል ላይ ይገኛል። ለዚህም በአዲስ አበባ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ግብራቸውን መክፈል የሚጠበቅባቸው የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዩች 80 በመቶ ያህል ግብራቸውን መክፈላቸውንና ቀሪዎቹም 20 በመቶ እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ተራዝሞ በተሰጣቸው ጊዜ እንደሚከፍሉ ይጠበቃል። ለደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዩች የ10 ቀናት ጊዜ መራዘሙ በነበረው አለመግባባትና ቅሬታ በማስገባት ችግራቸውን ለመፈታት የተወሰደው ጊዜ ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው።

ግብር መክፈል አገራዊ ኩራትና የውዴታ ግዴታ ቢሆንም፤ ፅንፈኛው ሃይል ግብርን አስመልክቶ የሚያሰራጨው አሉባልታ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ነገር የሌለው መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

ይህ ሃይል የራሱን የብጥብጥ አጀንዳ ለማስፋፋት የሚያደርገው ተግባር ነው። ህዝቡም ይህን ተገንዝቦ ግብር መክፈል ጠንካራ አገርን መፍጠር እንዲሁም ግብርን መክፈል አገራዊ ኩራት መሆኑን አውቆ የእነዚህን ሃይሎች ተግባር ሊያመክነው ይገባል።  

ግብር ከፋዩ የህብረተሰብ ክፍል የሚከፍለው ግብር የውዴታው ግዴታ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። ግብር ሳይከፍል የሚኖር ህዝብ የትም አገር የለም። ግብር መክፈል አገርን ለማጠንከርና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ የሚያግዝ ነው።

በተለይም አገራችን ለሁለተኛ ጊዜ በነደፈችው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተወጠኑና ስራቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማስከናወን ግብር ከዜጎቿ መሰብሰብ ግዴታዋ ነው። ይህ ካልሆነ ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እውን ማድረግ አይቻልም። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን ማምጣትም የሚታሰብ አይሆንም። በእነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚዎቹ ዜጎች ናቸው። እናም ግብር መክፈላቸው ከአንደኛው ኪስ ወደ ሌላኛው ማዘዋወር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

ለአብነት ያህል በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የተያዘውን የኢንቨስትምንት ስራ እንመልከት። ይህን ዕቅድ ለመፈፀም የሚጠይቀው የኢንቨስትመንት መጠን ከፍተኛ ነው። አንዱና ዋነኛው ፈታኝ ጉዳይ ለኢንቨስትመንቱ መሸፈኛ የሚያስፈልገው የአገር ውስጥ ፋይናንስ ግኝት እንደሆነ ይታወቃል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የቁጠባ መጠን መሻሻል የሚታይበት ቢሆንም ያን ያህል አጥጋቢ ባለመሆኑ፤ ልማቱን ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በከፊል ለማቅረብ እንዲቻል የአገር ውስጥ የቁጠባ ምጣኔው በከፍተኛ ደረጃ ማደግ እንደሚኖርበት ይታመናል። ግብር ካልተከፈለ እነዚህን የእቅዱን ክፍል ማሳካት አይቻልም።

ሆኖም ይህን የሀገር ውስጥ ቁጠባን የማሳደግ ግብ ለማሳካት በመጀመሪያው ዕቅድ ዘመን በርካታ የማሻሻያ ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ከእነዚህም ውስጥም የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ የማስተማርና የማነሳሳት እንቅስቃሴዎች፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸውን ተቋማት የማስፋፋት፣ የወለድ ምጣኔን የማሻሻል፣ የግል ማህበራዊ ዋስትና አገልግሎትን የመዘርጋት፣ የመንግስት የማህበራዊ ዋስትና ሽፋንን ይበልጥ እንዲጠናከር የማድረግ፣ የቤት የቁጠባ ፕሮግራም የማከናወን እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቁጠባ ቦንድና ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ የቁጠባ ዘዴዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህን የማሻሻያ እርምጃዎች ይበልጥ ለማጎልበት የፋይናንስ ግኝት ያስፈልጋል። ይህ ግኝት ደግሞ የሚገኘው ከግብር ነው። እናም ግብር መክፈል የዜጎች የውዴታ ግዴታ የሆናል ማለት ነው።

ሌላ አብነት ማንሳት ይቻላል፤ በአሁኑ ወቅት እየተሳለጠ ያሉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ። እንደሚታወቀው በሁለተኛው የዕድገት ዕቅድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ እስከ 18 በመቶ የማድረስ ግብን ይጥላል። ሀገራችን ለያዘችው የመካከለኛ ገቢ ራዕይን ለማሳካትም መደላድል ይፈጥራል።

መዋቅራዊ ለውጡን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። ዛሬን ከነገ ጋር ብናስተያየው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም። ይህን አሃዝ ከፍ ለማድረግ ገንዘብ ያስፈልጋል።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል።

ይህን ዕውን ለማድረግም በአሁኑ ወቅት ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል። እነዚህን ድጋፎች ለማድረግ አሁንም ገንዘብ በበቂ ሁኔታ መገኘት ይኖርበታል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራቸው ከሚጠይቀው በጀት አኳያ ዘርፉ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ይታወቃል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከዘርፉ ተግዳሮቶች ውስጥ፤ ልማቱን ለማረጋገጥ ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግርና ግንባር ቀደም ባለሃብቶች በስፋት መሳብ የሚያስችል አቅም አለመኖሩ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ይሁንና እነዚህን ችግሮች መፍታት ይቻላል። የተሻለ አቅም በመፍጠር፣ የገንዘብ ምንጮችን በማዳበር ችግሮቹን እልባት መስጠት ይገባል። እልባቱን ለመስጠትም ገንዘብ የግድ ያስፈልጋል። መንግስት በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ በመሆኑ ፓርኮቹን ለመገንባት ገንዘብ ወሳኝ ነው። ይህ ገንዘብ ደግሚ ዜጎች ከሚከፍሉት ግብር የሚገኝ ነው።

የፓርኮቹ ልማት የሀገራችን ህዝቦች የስራ ዕድል አግኝተው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እንዲሁም ሀገራችን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የልማት ስትራቴጂ እንድታድግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው። እናም መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ፓርኮቹን ለማልማት እያደረገ ያለው ጥረት ለመደገፍ ዜጎች ተገቢውን ግብር መክፈል ይኖርባቸዋል። ከላይ ያነሳኋው አብነቶች የሚፈልጉት ገንዘብ  እርግጥም ግብር መክፈል የዜጎች የውዴታ ግዴታ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy