Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጽንፈኞች  የፌዴራል ስርዓታችንን አያውቁትም አሊያም

1 570

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጽንፈኞች  የፌዴራል ስርዓታችንን አያውቁትም አሊያም …

ወንድይራድ ሀብተየስ

እንደእኔ ፌዴራልዝም ለአገራችን  የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የመጨረሻና ብቸኛ አማራጭ ይመስለኛል። ይህ የፌዴራል ስርዓት ለኢትዮጵያ እስትንፋስ ነው ብዬ አምናለሁ። አንዳንድ ጽንፈኛ  (የትምክህትና ጥበት) አካላት የፌዴራል ስርዓታችንን በተመለከተ የሚሰጡትን አስተያየት ሳደምጥ  ይገርመኛል። እነዚህ አካሎች አንድም የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ አያውቃትም፤ ወይም የዚህች አገር ቀጣይ እጣ ፈንታ አይገዳቸውም ስል አስባለሁ።  ምክንያቱም የፌዴራል ስርዓት ለማፍረስ መሞከር የኢትዮጵያን ስትንፋስ መዝጋት፣ አገርን እንደመበተን፣  ህዝብን ወደግጭት ማምራት  እንደሆነ ለእኔ ይሰማኛል።    

ለዘመናት በአገራችን ይስተዋል  የነበረውን የዕርስ በርስ ጦርነት እልባት ያስገኘው ይህ የፌዴራል ስርዓት ነው። ዛሬ  ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ጀምረዋል፤ ቋንቋቸውንና  ባህላቸውን መጠቀም በመቻላቸው በማንነታቸው  ኮርተዋል፤ አካባቢያቸውን ማልማት በመቻላቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ሆነዋል፤  ወዘተ  እንግዲህ  ይህን የህዝቦችን መብት ያስጠበቀ ስርዓት ንካት መዘዙ የከፋ እንደሚሆን መገመቱ የሚከብድ አይመስለኝም።  አገራችን ባለፉት 26 ዓመታት ፌዴራላዊ  ስርዓት መከተል በመቻሏ  ህብረተሰቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች በተጨባጭ ተጠቃሚ ሆኗል።  በአንድ የውይይት መድረክ ላይ አንድ የህግ ምሁር ስለፌዴራል ስርዓትን ያቀረቡት ቁም ነገር ሁሉም ቢያውቀው ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ ስላመንኩ ቀነጫጭቤ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።    

ፌደራላዊ ስርዓት ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ መንግስታት (ፌዴራልና ክልል መንግስታት) የሚፈጥሩት የራስ-አስተዳደርና የጋራ-አስተዳደርን ያጣመረ፣ በቃል-ኪዳን የሚመሰረትና የሚመራ አጋርነት ነው፡፡ አጋርነቱ በመካከላቸው ሊኖር የሚገባውን የስልጣን ክፍፍልና ዝምድና ይወስናል፡፡ አንዱ የሌላውን ቅንነትና አብሮ የመኖር እሳቤን በማመን ላይ የተመሰረተ፤ አንዱ የሌላውን ልዩ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት በማክበርና በእኩልነት በመጠበቅ ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን 28 የሚደርሱ ሃገራት በፌዴራላዊ ስርዓተ-መንግስት ይተዳደራሉ፡፡ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በእነዚህ ሃገራት ስር የሚተዳደር መሆኑም የፌዴራሊዝም ፀሃፊዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ዴሞክራሲን ለማስፈን ፌዴራል ስርዓት ከሌሎች የመንግስት አወቃቀር መልኮች የበለጠ በመሆኑ 21ኛው ክፍለ-ዘመን አገራት ወደ ፌዴራሊዝም አስተዳደር የሚሸጋገሩበት እንደሚሆን ይታመናል፡፡

አገራት ፌዴራላዊ ስርዓተ-መንግስትን የሚመርጡበት የተለያዩ ምክንያቶች ያሏቸው ቢሆኑም ብዙውን ጊዜ አራት ዋና ዋና ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ አንዱ ብዝሃነትን ማስተናገድ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ሰፊ ገበያና ትልቅ ኢኮኖሚ የመገንባት ፍላጎት ሲሆን ሶስተኛው ምክንያት ጠንካራ የመከላከያ ሃይልና የደህንነት ስርዓት ባለቤት ለመሆን ነው፡፡ አራተኛው ምክንያት አስተዳደራዊ አመችነትን መፍጠር ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት  ነጥቦች መካከል ኢትዮጵያን የፌዴራል ስርዓትን እንድትከተል ያስገደዳት በአገሪቱ ያለው ብዝሃነት ነው።  

የኢፌዴሪን ህገመንግስት መሰረታዊ ዓላማዎች  በህገ-መንግስቱ መግቢያ ላይ አጠር ባለ መልኩ እንዲህ ሰፍሯል። በአገራችን ባለፉት ስርዓቶች ይስተዋሉ የነበሩት የተዛባ ግንኙነቶችን ለማስተካከል፣ ቀድሞ ያላቸውን የጋራ አብቶችና እሴቶች  ትስስር ለማጠናከር፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ለማስፈን፣  የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቃል የገቡ መሆናቸውን፣ ይህን ለማሳካት የግለሰብም ሆነ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች መብቶችና የፆታ እኩልነት ማረጋገጥ፣ ባህሎችና አይማኖቶች ያለ አድሎና ልዩነት እንዲራመዱ ማድረግ ፅኑ እምነታቸው እንደሆነ መወሰናቸውን የሚል ነው፡፡ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ሁሉን ያሟላ ዘመናዊ የሚባል ህገመንግስት ነው። የኢፌደሪ ህገመንግስት በየዘርፉ ማለትም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ  የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያደርግ አንቀጾችን አካቷል።

 

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የአስተዳደረ ስርዓትን ትከተላለች። አገሪቱ በዚህ ስርዓት መተዳደር ከጀመረች ባለፉት 26 ዓመታት በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች።  ፌዴራል ስርዓት ከሌሎች ስርዓቶች የሚለይባቸው አምስት  መሰረታዊ የተባሉ ባህሪያት አሉት፡፡ የእኛንም  የፌዴራል ስርዓት እነዚህን ባህሪያት አኳያ ለማንሳት እሞክራለሁ።  የመጀመሪያው የመንግስት አወቃቀርና ተጠያቂነት ማስፈን ነው። ሁሉም ፌደራል አገሮች ቢያንስ ሁለት መንግስታት (ፌደራልና ክልሎች) አሏቸው፡፡ እነዚህ መንግስታት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ቀጥተኛ  ግንኙነት  አላቸው፣ ተጠያቂነታቸውም ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ እነዚህ መንግስታት ህልውናቸው የሚረጋገጠው በሕገ-መንግስት ነው፡፡

የፌደራል ስርዓቱ አወቃቀር እንደየ አገራቱ ሁኔታ ጂኦግራፊያዊ ወይም በማንነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና የክልል መንግስታት ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ ፌዴራል መንግስት የሚመረጠው በአጠቃላይ የአገሪቱ ህዝብ ሲሆን የክልል መንግስታት ደግሞ በየክልሉ ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች ነው፡፡ የእኛ ፌዴራል ስርዓት በዋናነት የተዋቀረው በህዝቦች ማንነት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ይህ የመንግስት አደረጃጀት የተመረጠበት ምክንያት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች ባለፈው ታሪክ የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን በሕገ-መንግስት ዋስትና እንዲያገኙና በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚያስችል አወቃቀር ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህ ህዝቦች የተዛባውን ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሳሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋራ ህልውና እንዲመሰረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው፡፡ የአገራችን የአከላለል መስፈርት ማንነትን፣ ቋንቋን፣ አሰፋፈርንና ፈቃደኝነትን ታሳቢ ያደረገው በአገራችን ህዝቦች የትግል ታሪክ የእኩልነት ጥያቄ መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ሲሆን የማንነት መገለጫ የሆኑትን ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋንቋን፣ ባህልንና ታሪክን ለማጥናት ለመንከባከብና ለማሳደግ ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ ነው፡፡

ሁለተኛው  የፌዴራላዊ ስርዓት ባህሪ የሆነው የስልጣን ክፍፍል  ማለትም የራስ አስተዳደር እና የጋራ አስተዳደር መመስረት መቻል ነው።  የስልጣን ክፍፍል የፌደራል ስርዓት ዋንኛ መገለጫ ነው፡፡ እያንዳንዱ መንግስት በተሰጠው አስተዳደራዊ ወሰን ውስጥ ሕግ የማውጣት፣ ሕግ የመፈፀም፣ ሕግ የመተርጎምና ገቢን የመሰብሰብ ስልጣን አለው፡፡ የስልጣን ክፍፍሉ እንደየአገራቱ ሁኔታ ቢለያይም አገራዊ ጉዳዮችንና አንድነትን ለማስጠበቅ ጠቀሜታ ያላቸው ስልጣኖች ለፌደራሉ መንግስት የሚሰጡ ሲሆኑ ከክልሎችና ብሄር ብሄረ-ሰቦች ልዩ ሁኔታና ባህል ጋር የተያያዙ ስልጣኖች ለክልሎች ይሰጣሉ፡፡ በኢትዮጵያም ፌደራል መንግስትና ክልሎች ሕግን የማውጣት፣ ሕግን የመፈፀምና ሕግን የመተርጎም ስልጣን አላቸው፡፡ የፌደራል መንግስት ስልጣን በአንቀፅ 51 የክልሎች ደግሞ በአንቀጽ 52 ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡ ተለይተው ያልተዘረዘሩ ቀሪ ስልጣኖች ለክልሎች ተሰጥተዋል፡፡

ሶስተኛው የፌዴራል መንግስታት ባህሪ የሆነው ሁሉም ፌደራል አገሮች የተፃፈ ሕገ-መንግስት ያላቸው መሆኑ ነው።  ሕገ-መንግስት የስምምነታቸው ወይም ቃል-ኪዳናቸው ማሰሪያ ሰነድ ነው፡፡ በአንድ በኩል አንዱ እርከን ስልጣኑን ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅት የሌላውን እርከን ስልጣን እንዳይነካ የሚገታው፣ ወይም ስልጣኔ ተነካ የሚል ካለ ተጠቃሽ ሆኖ የሚያገለግል የተፃፈ ሕገ-መንግስት መኖር የግድ ይሆናል፡፡ እንደየአገራቱ ሕገ-መንግስቱን የማሻሻል ስርዓት ቢለያይም ሁሉም ፌዴራል አገሮች የሕገ-መንግስታቸውን የተወሰኑ አንቀፆች ያለፌዴራል መንግስትና ክልሎች ስምምነት ሊያሻሽሉ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስትም የተለያዩ የፖለቲካ አይሎችና የህብረተሰብ ተወካዮች የድርድር ውጤት ነው፡፡

አራተኛው የፌዴራል ስርዓቶች ባህሪ የሆነው ሁሉም ፌደሬሽኖች ሁለት ምክር ቤቶች አሏቸው፡፡ አንዱ ‘‘የተወካዮች ምክር ቤት’’ ወይም ‘‘የታችኛው ም/ቤት’’ የሚባል ሲሆን ሌላው ደግሞ ‘‘የላይኛው ም/ቤት’’ ወይም ‘‘ሁለተኛ ም/ቤት’’ በሚል ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው ምክር ቤት በተለያዩ ፌዴራል አገራት የተለያየ መጠሪያ አለው፤ በኢትዮጵያ የፌደሬሽን ም/ቤት ተብሎ ይጠራል፡፡ አወቃቀርና ስልጣኑም እንደየ አገራቱ ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን የኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ አንድ ውክልና ለተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ተጨማሪ አንድ ወኪል እንዲኖር ያደርጋል፡፡ የምክር ቤቱ ተወካዮች አመራረጥን በተመለከተ በአንዳንድ ፈደሬሽኖች በቀጥታ በህዝብ ሲመረጡ በሌሎች ደግሞ ከግማሽ በላይ ወይም ከግማሽ በታች ተወካዮች በክልሎች ስራ አስፈፃሚዎች ይመረጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ አባላቱ በክልል ም/ቤቶች ይመረጣሉ ወይም ምክር ቤቶቹ በክልሎቹ ህዝቦች በቀጥታ እንዲመረጡ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፌደሬሽን ም/ቤት የፌደራልና የክልል መንግስታት የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበት መንገድ ይወስናል፣ የፌደራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ ቀመር በማውጣት ያከፋፍላል፣ ሕገ-መንግስትን ይተረጉማል፣ በክልሎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር መፍትሄ ይሰጣል፡፡

አምስተኛው የፌዴራል ስርዓት ባህሪያት የሆነው የሕገ-መንግስት ጉዳዮች ገላጋይ ተቋም  መኖር ነው። የፌደሬሽኖች ሕገ-መንግስታዊ የስልጣን ክፍፍል ጥቅል፣ መደራረብና መጋራት የሚታይበት ነው፡፡ በመሆኑም በአፈፃፀም ሂደት አንዱ የሌላውን ስልጣን ሊነካ ስለሚችል በዚህ ጊዜ የሚነሳን አለመግባበት በውይይት መፍታት ካልተቻለ የዳኝነት ፍርድ የሚሰጥ ገላጋይ ተቋም አላቸው፡፡ በዚህ ዙሪያም እንደየሀገሩ ልዩነቶች አሉ፡፡ በኢትየጵያ ሕገ-መንግስታዊ አለመግባባቶችን ግልግል የሚሰጠው ተቋም የፌደሬሽን ም/ቤት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት መከተል ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ በርካት ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነታቸውንና ነጻነታቸውን ማረጋገጥ በመቸላቸው ዘላቂ ሰላም ማስፈን በመቻላቸው  ፈጣን ልማት አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን ጥቅም ያስገኘላቸውን ስርዓት መነካካት ወይም ለማፍረስ መሞከር መዘዙ ብዙ ነው። በመሆኑም በሁለቱም በኩል ማለትም በትምክህትም ሆነ በጥበት  የምናስተውላቸውን   ጽንፈኛ ሃይሎች መዋጋት የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው። ትምክህትና ጥበት የፌዴራል ስርዓታችን ጠንቆች መሆናቸውን ተገንዝበን የሃሳብ ትግል ልናደርግባቸው ይገባል።

 

  1. Mulugeta Andargie says

    Guys!!! Whenever you are writing, we listen to you and understand. Well, you call yourselves as activists. We start writing just like you opposing the reality. You call us extremists. Please, let us share both names as points reflect or as the fingers pointing out the critics what we write.

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy