Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራሊዝምና የተጠያቂነት አሰራር

0 409

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራሊዝምና የተጠያቂነት አሰራር

ዳዊት ምትኩ

በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ የተጠያቂነት አሰራር የራሱ የሆነ መንገድ አለው። በፌዴራላዊ ስርዓት ውስጥ በየደረጃው የሚገኝ ህዝብና የህዝብ ወኪል የአስፈፃሚውን አሰራር ይገመግማሉ። በዚህም የተሰሩና ያልተሰሩ ስራዎችን ይለያሉ። የእርምት ርምጃም እንዲወሰድም ያደርጋሉ። ይህም ፌዴራሊዝምና የተጠያቀነት አሰራር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ያሳየናል።

በየትኛውም ዴሞክራሲን በሚከተል ፌዴራላዊ አገር ውስጥ ስራ አስፈፃሚውን የመቆጣጠር ስራ የስርዓቱ “የሞት ሽረት” ጉዳይ ነው። የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤትን ከዚህ አኳያ ማንሳት ይቻላል። የአገራችን ፓርላማ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባይኖሩም፤ አስፈፃሚውን አካል የመቆጣጠሩ ስራ ወሳኝ ብቻ ሳይሆን ለውይይት የሚቀርብ አጀንዳም አይደለም።

ምክንያቱም የመድረኮቹ ተዋንያን የሆኑት የህዝብ ወኪሎች እነዚህን ጉዳዮች በመከወን የሀገሪቱን የልማት ዕድገት የማስቀጠል አሊያም አሁን ካለበት ይበልጥ እንዲመነደግ የማድረግ ቁልፍ ህገ-መንግስታዊና ህዝባዊ ኃላፈነት ያለባቸው በመሆኑ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም በምክር ቤቱ ውስጥ የሚገኙት የገዥው ፓርቲ አባላት የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ- ኢኮኖሚ አካሄድ በልማታዊ ኢኮኖሚ እሳቤ መተካት እንዳለበት የሚያምኑ ናቸው። እርግጥ ኪራይ ሰብሳቢነት በሂደት ተንዶ በልማታዊነት ሊተካ የሚችለው አመለካከቱን ውጤታማ በሆነ አኳኋን ሊፋለም የሚችል ልማታዊ አስተሳሰብ እየጎለበተ ሲሄድ ነው። በመሆኑም አመለካከቱን በሂደት ለማክሰም በቂ የዴሞክራሲ መድረኮች ሊኖሩ ይገባል።

እናም ከእነዚህ መድረኮች ውስጥ አንዱ በሆነው ፓርላማ ውስጥ የሚገኙት የህዝብ ወኪሎች፤ ለዚህ ተግባር ቀን ተሌት ይተጋሉ እንጂ የተቃውሞው ጎራ አንዳንድ አመራር ነን ባዮች እንደሚሉት ፓርላማው ጥሩ ድባብ እንዲኖረው አያደርጉም። ለዚህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከዋናው ኦዲተር የኦዲት ግኝት በመነሳት የተከናወኑትን የተጠያቂነት አሰራሮችን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል።

እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችንን ጨምሮ በዓለም ላይ ያሉ ልማታዊ መንግስታት ኪራይ ሰብሳቢነትን በሂደት ለማስወገድና ልማታዊነትን ለማጎልበት ከሚጠቀሙባቸው ቁልፍ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ የገበያ ጉድለትን በተመረጠ፣ በተቀናጀና ሁሉን አቀፍ በሆነ ሁኔታ ጣልቃ በመግባት ክፍተቱን መሙላት ነው።

ሆኖም ይህ ተግባር መንግስታቱ ለስራው የሚሆን ገንዘብ እንዲያወጡ ስለሚያደርጋቸው ኪራይ ሰብሳቢነትን ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ታዲያ ስራው በጥንቃቄ ካልተከናወነና የተጠያቂነት ልጓም ካልተበጀለት፤ እንደ ቅርብ ጊዜው የሙስና ትዕይንት ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ፖለቲካዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው በኪራይ ሰብሳቢነት አረንቋ ውስጥ የመዘፈቅ ዕድላቸው የሰፋ ሊሆን ይችላል።

እናም በየትኛውም ልማታዊ መንግስት ውስጥ መከሰቱ የማይቀረውን ይህን አደጋ ለመቋቋም፤ አጠቃላይ ህዝቡን በትግሉ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ስለሆነም በፓርላማው ውስጥ የሚገኙት አባላት የህዝቡ ወኪል እንደመሆናቸው መጠን ይህን በማሳካት ረገድ ቁልፍ ሚና አላቸው። ምክንያቱም ከሀገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሂደታዊ እመርታ ጋር በተያያዘ ፓርላማው የዴሞክራሲ ትምህርት ቤት እየሆነ መምጣቱን የትኛውም ወገን ቢሆን የሚገነዘበው እውነት በመሆኑ ነው።  

እናም የህዝብ ተወካዩቹ ትናንት፣ ዛሬም ይሁን ነገ የፌደራላዊ ስርዓቱ ምሶሶ በሆነው ዴሞክራሲያዊ መርህ እየተመሩ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካካከት ተግባር በሂደት ለማከሰምና ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች በፓርላማው መድረኮች ላይ በማቅረብ ተጠያቂነት ባለው አኳኋን የአስፈፃሚው አካል ስራዎች እንዲፈተሹ ያደርጋሉ።

ከዚህ በተጨማሪ የምክር ቤቱ አባላት ፓርላማው ሰፊ የመከራከሪያ አጀንዳ ኖረውት ድባቡም አሁን ካየነው የበለጠ እንዲሆን ያደርጋሉ። በመሆኑም አባላቱ እንደ ህዝብ እንደራሴነታቸው የስራ አስፈፃሚውን ዕቅድ አፈፃፀም በጥብቅ የመፈተሽና የህዝብን ቅሬታዎች የማንሳት ኃላፊነት አላቸው።

የምክር ቤቱ አባላት ስራ አስፈፃሚውን የሚቆጣጠሩበትን ዋነኛ ምክንያቶችን መጥቀስ ያስፈልጋል። አባላቱ ስራ አስፈፃሚውን የሚቆጣጠሩት፤ ስህተቶች ካሉ በወቅቱ ታውቀው በፍጥነት እንዲስተካከሉ፣ በህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ካልሆኑ ለማብራራት እንዲቻል፣ ተገቢ ከሆኑ ደግሞ በወቅቱ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ ነው።

ምንም እንኳን ስራ አስፈፃሚው የራሱን ዕቅድ ለመገምገም የሚያስችለው አሰራርና ስርዓት ያለው ቢሆንም፤ በፌዴራላዊ ስርዓቱ ይህ ብቻ በቂ አይሆንም። ምክንያቱም ፈፃሚው አካል ምንም እንኳን ራሱን በራሱ ሲገመግም ትክክለኛ ግምገማ ሊያካሂድ ቢችልም፣ ሁኔታዎችን ከራሱ ምልከታ አንፃር ማየቱ ማየቱ የግድ መሆኑ ስለማይቀር ነው።

ስለሆነም በአፈፃፀሙ ላይ ያልነበሩ ወገኖች የራሳቸውን ነፃ ግምገማ እንዲያካሂዱ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም አብዛኛዎቹ የገዥው ፓርቲ አባላት ከአፈፃፀም ስራው ነፃ ስለሚሆኑ፤ ከአስፈፃሚው ዕይታ ነፃ በሆነ አኳኋን ሁኔታዎችን የማየት ዕድል አላቸው።

ታዲያ የምክር ቤቱ አባላት የስራ አስፈፃሚውን አካል ስራ ሲገመግሙ ሃቆችን በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርተው እንጂ በስሚ ስሚ አሉባልታዊ ዲስኩሮችን አይደለም። ይህን የሚከውኑትም አደራውን ለሰጣቸው ህዝብ ሲሉ ከማንም በተሻለ ፍላጎትና ቁርጠኝነት በመነሳት ነው።

ከዚህ ውጭ ስህተቶችን ወይም ድሎችን ማጋነን ወይም ፈጥሮ ማውራትን በዓላማነት የሚይዙ የህዝብ ወኪሎች አይደሉም። እናም ዓላማቸው ሃቁ በማውጣት ስራ አስፈፃሚው ማብራሪያ እንዲሰጥበት ወይም ፈጥኖ እንዲያስተካክለው ለማድረግ የሚያስችል መረጃና ግፊት እንዲያገኝ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።

ተጠያቂ የሆኑትም በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ አካሄድን ሊከተሉ ይችላሉ። ይህም የፌዴራለዊ ስርዓቱ ራሱን ለማረም የሚያደርገውን ተግባር ብቻ ሳይሆን ስርዓቱና የተጠያቂነት አሰራር መሳ ለመሳ የሚሄድ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

እርግጥ ፌዴራሊዝም ከተጠያቂነት በተጨማሪ ነፃነትንና ዴሞክራሲን በማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የመንግስትን ስልጣን እንደተለመደው ወደ ጎን በማለት በህግ አውጪው፣ በሕግ አስፈፃሚውና በዳኝነት አካላት መካከል ብቻ አያከፋፍልም።

ይልቁንም ፌዴራሊዝም የመንግስትን ስልጣን በአግድሞሽ በፌዴራል መስተዳድሩና በአባል ክልል መንግስታት መካከል በማከፋፈል በመንግስት ስልጣን ላይ ተጨማሪ ገደቦችን በመጣል ለግለሰቦችና ለማህበረሰቦች የተግባር ነፃነትንና የፖለቲካ ስልጣን ምህዳርን ያረጋግጣል። ይህ ሲሆንም አብሮ የተጠያቂነት አሰራር እንዲተገበር ያደርጋል። ፌዴራላዊ ስርዓቱ ዜጎችን ሁሉ በእኩል ዓይን የሚመለከት በመሆኑ ማንንም ከማንም ሳይለይ መጠየቅ ያለበትን የትኛውንም አካል ህጋዊ አሰራሮችን ተከትሎ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ግንዛቤ መያዝ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy