Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራላዊ ሥርዓቱን መንካት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ያለማወቅ ነው!  

0 376

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ፌዴራላዊ ሥርዓቱን መንካት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ያለማወቅ ነው!  

አባ መለኩ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ላስመዘገብናቸው ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶች  ሁሉ የፌዴራል ስርዓቱ መሰረት ነው። አንዳንድ ጽንፈኛ አካላት የፌዴራል ስርዓቱን ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ምንም እንዳልፈየደ አድርገው፣ ሁሉንም ነገር አሳንሰው በማቅረብ ለማጣጣል ሲሯሯጡ ተመልክተናቸዋል። ጠባቦችና ትምክህተኞች አዲሲቷን ኢትዮጵያ አያውቋትም፤ በቅጡ ስለማያውቋት አገርም ገብተው ባንፈተፍቱ መልካም ነው።  የፌዴራል ስርዓቱ  የሰኬቶቻችን ሁሉ ማጠንጠኛ ነው። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዕድል በማመቻቸት  ዘላቂ ሰላም በአገሪቱ እንዲሰፍን ያደረገግው የፌዴራል ስርዓቱ ነው። ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአገራችን  እንዲረጋገጡም  የፌዴራል ስርዓቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

የፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩና አካባቢያቸውን ማልማት እንዲችሉ በማድረጉ  ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ  ዕድገት ማረጋገጥ ተችሏል። በመላ አገሪቱ ተጨባጭና ሁሉን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ልማት  ማስመዝገብ ተችሏል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ባለፉት ስርዓቶች ምንም ልማት አይተው የማየውቁ   አርብቶ አደሮች  የሚበዙባቸው አካባቢዎች ዛሬ ላይ ሁኔታዎች ተቀይረዋል።  የኢፌዴሪ መንግስት የተለያዩ መሰረተ ልማቶች  በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ማስፋፋት በመቻሉ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ኢንቨስትመንት በመስፋፋት ላይ ነው።  

ይህን የፌዴራል ስርዓት ዕውን ያደረገውን ህገመንግስት  ለማምጣት መራራ መሰዋትዕነት ተከፍሏል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለማረጋገጥ  ረጅም፣ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ  ትግል አካሂደዋል። በ17ቱ ከባድ የትጥቅ ትግል ሂደት የርካታ የህዝብ ልጆች ክቡር ህይወት አና አካል መስዋዕትነት ከፍለዋል።  በርካታ ንብረትም ወድሟል። ከዚያም ባለፈ   ህጻናት ያላሳዳጊ፣ አረጋዊያን ያለጧሪ ቀባሪ ቀርተዋል።  አዎ ያ ወቅት ዛሬ  አልፎ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ዕውን ሆናለች። ህገመንግስታዊ ስርዓት ተቋቁሟል። ይህን ያህል መሰዋዕትነት የተከፈለበትንና  በተጨባጭም  የደሃውንና ጭቁኑን ህይወት የቀየረውን   ስርዓት ጽንፈኛው ሃይል   ለማፍረስ ያላደረገው ጥረት  የለም።

ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን  ማስመዝገብ የቻለችው  በኢፌዴሪ ህገመንግስት ነው። የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ነው። የመንግስትን የስልጣን ወሰን የአስተዳደር ስርዓት  የሚመነጨው ከዚህ ሰነድ በመሆኑ  የስርዓቱ አጠቃላይ  ባህሪያትም  የሚወሰነው በዚህ ሰነድ ነው። አጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ  የሚካሄዱት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  ሁኔታዎች በዚህ ሰነድ ላይ ተመስርቶ በመሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮች በአገሪቱ ውስጥ   ወጥነት እንዲኖር አስችሏል። በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ተማሳሳይ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲኖር ህገመንግስቱ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።   

ህገ-መንግስታዊነት ዋንኛው መገለጫ ህገመንግስቱን ማክበርና በማስከበር የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው።  አንዳንድ  ምሁራን ህገ-መንግስታዊነትን   ከአስተሳሰብ፣ እምነቶች፣ እሴቶችና መርሆች ጋር የተያያዘ ትርጉም ይሰጡታል። ህገ-መንግስታዊነት ለማጎልበት የመጀመሪየ ያባለድርሻ የሆነው  መንግስት  ሁሌም  የህግ የበላይነትን እኩል የማረጋገጥ  ሃላፊነት ይወድቅበታል። በተመሳሳይ  ህገ-መንግስታዊነት እንዲጎለብት   እያንዳንዱ ዜጋም  በህገ-መንግስት የተደነገጉትን ዓላማዎች፣ እሴቶች፣ መርሆዎች፣ መብቶች፣ ግዴታዎች እና ሌሎቹም ድንጋጌዎች  ማክበር  ብቻ ሳይሆን  ሌሎች እንዲያውቋቸውና  እንዲያከብሯቸው  ማድረግ ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተከባብረው ተቻችለው ተማምነው መኖር ከጀመሩ 26 ዓመታትን አስቆጥረዋል። የኢትዮጵያ አንድነት  በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲመሰረት ሆኗል።  ኢትዮጵያዊነት ተወዶና ተፈቅዶ የሚገኝ ዜግነት እንጂ እንደቀድሞ ስርዓቶች በግድ ኢትዮጵያዊ ነህ የሚባልበት ጉዳይ አይደለም። በአዲቲቷ ኢትዮጵያ ማንኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ የፌዴራል መንግስቱ  አባል የሆነው መርጦና ፈቅዶ እንጂ በሃይል አይደለም። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ክልሎች መርጠውና ፈቅደው የፌዴራል መንግስቱ አባል እንደሆኑ ሁሉ ለመገንጠልም  ነጻነት የሚያሰጥ  አንቀጽ በህገመንግስቱ እንዲካተት ተደርጓል። ይህ አንቀጽ የመተማመኛ አንቀጽ ነው።

ባለፉት 26 ህገመንግስታዊ ዓመታት በአገራችን  ዘላቂ ሰላም በመስፈኑና  ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መተግበር በመቻሉ የህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በተጨባጭ ተረጋግጠዋል። በመሆኑም ህዝብና መንግስት ትኩረታቸውን ወደ ልማትና ዕድገት ማድረግ በመቻላቸው  አገሪቱ ለ14 ተከታታይ ዓመታት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት  በማስመዝገብ ላይ  ነች።  ዛሬ አገራችን  ከቀጠናው አልፋ በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  የፈጣን ልማት እና የሰላም ተምሳሌት ለመሆን በቅታለች።   ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ   በጎረቤት አገራት (በሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን) ሰላም  ለማስከበር  በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና በማበርከት ላይ ነች።  ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ስኬታማ ለመሆን የባችው  በአገር ውስጥ ማስመዝገብ በቻለቻቸው ስኬቶች ሳቢያ ነው። ግመሉ ይጓዛል ውሻውም ይጮኃል እንደሚባለው በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ጽንፈኛው ሃይል መርዘኛ  ፖለቲካውን ከመርጨት ታቅቦ አያውቅም፤ አገራችንም በስኬት ላይ ስኬት እየተረማመደች ነች።

ኢትዮጵያ የተከተለችው የፌደራል ስርዓት በህዝቦች መካከል መተማመንና መከባበርን እንዲጎለብት በማድረጉ የአገሪቱ አንድነት በጠንካራ አለት ላይ እንዲመሰረት አድረጎታል።  በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሁሉም በነጻነትን እኩልነት  ይተዳደራሉ።  ለልማታቸውም ሆነ ለውድቀታቸው  የመጀመሪያው ተጠያቂ ሊያደርጉት የሚገባው የቅርብ ተወካዮቻቸው ናቸው። በፌዴራል ደረጃ ሁሉም ክልሎች ፍተሃዊ በሆነ መንገድ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር  ተደርጓል።  የኢፌዴሪ ህገመንግስት  የህዝቦችን ማንነት ከማረጋገጡና ዕኩልነትን ከማስፈኑ  ባሻገር   ፍትሐዊ የኢኮኖሚ  ተጠቃሚነትን እንዲኖር   አድርጓል።

የህዝቦች አብሮነትና ተጠቃሚነት የማይዋጥላቸው ትምክህተኞችና ጠባቦች  አንዱን ህዝበ የበላይና ልዩ ተጠቃሚ፣ ሌላውን ደግሞ የበታችና የተጋፋ በማስመሰል መርዘኛ ፖለቲካቸውን በተለያዩ ሚያዎቻቸውና ማህበራዊ ድረገፆች በማሰራጨት አገሪቱን ወደ ሁከት ለማምራት ያላሰለሰ ጥረት በማደረግ ላይ ናቸው ። እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ፣ መነሻና መድረሻ የሌላቸው የተፈበረኩ መረጃዎች ህዝቦችን ለማጋጨት የአገሪቱንም ዘላቂ ሰላም በማደፍረስሰ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ፈጣን ልማት ላይ እንቅፋት የሚፈጥር እኩይ ተግባር ነው።

ፅረ- ሰላም ኃይሎች የህዝቦች አብሮነትና የአገር አንድነት አይዋጥላቸውም፤ ሰላምና ልማት ለእነሱ ምናቸው አይደለል። የእነዚህ ኃይሎች ፍላጎት ቢችሉ አገር ወደ  ለየለት ቀውስ እንድታመራ በማድረግ  ስልጣን  መቆናጠጥ፤ ካልሆነ ደግሞ  “ባልበላውም ልጫረው” እንደሚባለው  ሁከት መፍጠርና ህዝብን ማጋጨት ነው። ህብረተሰቡ  ከዚህ ቀደም ሲያደረግ እንደነበረው የእነዚህን ነውጥ ናፋቂ ኃይሎች የተሳሳተ መረጃ ጆሮ ሊሰጠው አይገባም።

ነውጥ ናፋቂ የሆኑት ጠባቦችና ትምክህተኞች  በህብረተሰቡ ውስጥ ሽብር ለማስንሳት የገበያ ያለመረጋጋት ለመፍጠር፣ ነጋዴው ሸቀጦችን እንዲያዘዋውር፣ አርሶና አርብቶ አደሩ ምርቱን በገበያ እንዳያቀርብ፣ ለማድረግ  የተለያዩ የጥፋት ጥሪዎችን በማድረግ ላይ ነው። ጠባቡና የትምክህት ሃይሉ  ሰሚ ጆሮ አላገኘም እንጂ ሁሌም የጦርነት ነጋሪቱን እንደጎሰመ ነው።  

ጠባቡና የትምክህት ሃይሉ ሰሞኑን እንኳን በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች  አመጽና ሁከት ለመቀስቀስ ሲሯሯጥ ነበር። ግብር አትክፈሉ፣ ገበያ አትሂዱ፣ ሱቃችሁን ዝጉ፣ ታክሲና ባጃጀጅ ወደስራ እንዳትወጡ በማለት የጥፋት ጥሪውን ቢያሰማም ሰሚ ጆሮ የሰጠው የለም።  ህብረተሰቡ እንደነዚህ ያሉ የጥፋት ኃይሎች ድረጊት ለፅጥታ ኃይሉ በማጋለጥ የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል። የአገር ሰላም በየትኛውም መስፈርት ከድርድር አይቀርብም።  ባለፈቅ ጊዜ በአገራችን በተለይ በኦሮሚያና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች ጽንፈኛው ሃይል ወጣቱን ለዓላማው ማሳኪያ ተጠቅሞበታል።  ይሁንና ወጣቱ ከሁከትና ነውጥ የሚያገኘው አንዳችም ነገር እንደሌለ ካለፈው ጊዜ  መገንዘብ ይቻላል። ጠባቦችና ትምክህተኞች ወጣቱን ለጥፋት ተልኳቸው ለመጠቀም ካልሆነ በስተቀር  ለወጣቱ  የሚፈዱት አንድም ነገር አይኖራቸውም።  የወጣቱ ችግሮች  ሊፈቱ የሚችሉት  መንግስት በቀየሰው  ወጣቱን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ በሚችሉ ፖሊሲዎችና  ስትራቴጂዎች ብቻ ነው።  የወጣቱ ችግር በዘላቂነት  የሚፈታው በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ ነውጥና ሁከት በሚፈልጉ በጠባቦችና ትምክህተኞች አስተሳሰብ አይደለም።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚያምንበትን አስተሳሰብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የማራመድ ህገመንግስታዊ መብት ተጎናጽፏል። ይህ በሆነበት ሁኔታ  ልዩነትን  በኃይልና በነውጥ ለማራመድ መሞከር ኢ-ህገመንግስታዊ ነው። የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የመንግስት ኃላፊነትና ግዴታ  ብቻ ሳይሆን የሁሉም የህብረተሰብ  ክፍል  መሆኑ  መቻል አለበት። አገራችን የጀመረችውን የዴሞከራሲ ሥርዓት ግንባታና ፈጣን ልማት በማስቀጠል የአገራችንን ህዳሴ  እውን ለማድረግ ህዝብና መንግስት በቅርበት መስራት  ይኖርባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy