Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለተሳለጠ የወጪ-ገቢ ንግድ ሲባል፤ የሎጀስቲክስ እና የጉሙሩክ አሰራር ስርአታችንን ይፈተሽ

0 1,272

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለተሳለጠ የወጪ-ገቢ ንግድ ሲባል፤ የሎጀስቲክስ እና የጉሙሩክ

አሰራር ስርአታችንን ይፈተሽ

ስሜነህ

ለአገሪቱ የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዕድገት የትራንስፖርት አገልግሎት የበለጠ ተወዳዳሪ፤ ደህንነቱ የተጠበቀና ብቃት ያለው ሆኖ እንዲራመድ ክትትል ስለሚያስፈልገው፤ የትራንስፖርት ዘርፉ አደረጃጀት የመንግሥት ፖሊሲን በአግባቡ ለመተግበር አመቺ ሁኔታ በሚፈጥር መልኩ እንደገና መዋቀር ስለሚገባው፤ ትራንስፖርትን አስመልክቶ የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባር በማያሻማ ሁኔታ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ፶፭/፩/ መሠረት የትራንስፖርት ዘርፉን ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ (አዋጅ ቁጥር ፬፻፷፰/፲፱፻፺፯) መውጣቱ ይታወቃል፡፡

በዚሁ አዋጅ መሰረትም፤ በኣዋጁ ላይ የሰፈረውን እንዲያስፈጽም ባለስልጣን ተቋም ተቋቋመ። ተቋሙም የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ሲሆን በመንገድ ትራንስፖርቱ ዘርፍ የልማት አጋሮችን በማስተባበር እና በመደገፍ፤ የትራንስፖርት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በስራ ላይ በማዋል በመላ ሀገሪቱ ቀልጣፋ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ደህንነቱና ምቾቱ የተጠበቀን የትራንስፖርት አገልግሎት የማስፈንና የማስፋፋት ሃላፊነት ተሰጥቶታል፤ ተረክቧልም። ቀልጣፋ፣ ብቁ፣ ኢኮኖሚያዊና የተመጣጠነ የትራንስፖርት ሲስተም እንዲስፋፋ ማድረግ፣  የትራንስፖርት አገልግሎት ደህንነቱ የተጠበቀና ምቾት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ፣ ያገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የትራንስፖርት አገልግሎት መሥመሮች እንዲዘረጉና እንዲደራጁ ማድረግ፤ እንዲሁም ትራንስፖርት በማንኛውም ረገድ እንዲያድግ ማበረታት ለባለስልጣኑ ከተሰጡት ተልእኮዎች መካከል ስለአጀንዳችን ሊጠቀሱ ግድ የሚሉ ናቸው፡፡ 

 

አጀንዳችን ሰሞንኛ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የሱዳን ቆይታና የሃገረ ሱዳን ጥያቄ ነው። በዚህና ሶስት ቀናትን በወሰደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋዊ ጉብኝት በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተደርገዋል። በልኡካኑ ጉብኝት ወቅት የሱዳን ባለሃብቶች በሃገራችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለቀረበላቸው ጥያቄ በዋናነት ያነሱት ጥያቄ ነበር፤ እሱም የሎጀስቲክስና የጉሙሩክ ስርአታችሁን አስተካክሉ የሚል መሆኑን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶ/ ነገሪ ሌንጮን ጠቅሶ ኢቢሲ ዘግቧል።

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢም በአጠቃላይ የሃገሪቱን የወጪ እና ገቢ ንግድ በማሳለጥ በኩል ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ  ያብራሩ ዘንድ ባለድርሻ አካላትን ጋብዞ በዚሁ ሰሞኑን የቀጥታ ስልክ የኤፍኤም ሬዲዮ ውይይት አድርጎ ነበር። በዚህ ፅሁፍም የጉዳዩን ወሳኝነት መነሻ በማድረግ የሱዳን ባለሃብቶችን ጥያቄ በሚያጠይቅ መልኩ አንዳንድ ነጥቦችን ሊያነሳ ወዷል።

የሎጀስቲክስና የጉሙሩክ ስርአታችሁን . . . ሲባል እንግዲህ ከባህር ወደብ እስከ ደረቅ ወደብ አገልግሎት፤ ከመንገድ ምቹነት እስከ ፍተሻ ጣቢያና የትራንስፖርት ፍሰት፤ አሽከርካሪዎችን፣ ትራንስፖርተሮችን እና የጉሙሩክ አስተላላፊዎችን ወዘተ የተመለከቱትን ማለት እንደሆነ አያጠያይቅም። በዚህ ረገድ ከላይ የተመለከተውን እና በአዋጅ የተቋቋመውን ባለስልጣን ጨምሮ የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባለድርሻ ይሆናሉ ማለት ነው። በተለይም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሚናና ሃላፊነት የጎላ ይሆናል። ድርጅቱ የወጪና ገቢ ንግድን ለማፋጠንና ለማሳለጥ የተቋቋመ ከመሆኑ አንጻር የወደብ የጭነትና የጉሙሩክ ስነስርአቶችን ማስፈጸምን ጨምሮ ደረቅ ወደቦችን እንዲያስተዳድር ሃላፊነት ተሰጥቶታል። እነዚህን ሃላፊነቶቹን የሚወጣው ደግሞ አዲስ በተዘረጋው የመልቲ ሞዳል የጭነትና የወደብ አገልግሎት ስርአት መሆኑ አያጠያይቅም።

የአገሪቱን ገቢ ምርቶች ወደ መሃል አገር ለማስገባት እስካሁንም አገልግሎት ላይ ካለው የዩኒ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓት የበለጠ ጠቀሜታ ይሰጣል የተባለውን ይህንን የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓት ሁሉም ወገን እንዲጠቀምበት ለማድረግ ከመወሰኑ በፊት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እስከ 2004 ድረስ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።

መልቲ ሞዳል የትራንስፖርት ስርአት ዕቃዎችን ከተጫኑበት ወደብ እስከ ደረቅ ወደቦች ድረስ በአንድ ዶክመንት ማጓጓዝ የሚያስችል ነው። ደንበኞች ዕቃዎቻቸውን ከጅቡቲ ወደብ ለማንሳት ዋናውን የማስጫኛ ሰነድ ማቅረብና የባህር ትራንስፖርት ዋጋ መክፈል ሳይጠበቅባቸው ዕቃዎችን በአጓጓዡ በየኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት  ሙሉ ኃላፊነት ወደ አገር ውስጥ በአንድ ዶክመንት ብቻ ለማስገባት የሚያስችለው አሠራር፣ የደንበኞችን ወጪ ከመቀነሱም ባሻገር ለጊዜ ቁጠባም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የድርጅቱ የመልቲ ሞዳል መምሪያ ዳይሬክተር የተለያዩ አስረጂዎች በመጥቀስ አረጋግጠዋል።

ከነዚህም መካከል የመልቲ ሞዳል ሥርዓት በጅቡቲ ወደብ ለመጋዘን ኪራይ ይወጣ የነበረውን ወጪ ማስቀረቱ አንደኛው ሲሆን፤ የንግዱ ኅብረተሰብ በዚህ ሥርዓት መጠቀሙ ዕቃዎቻቸውን ለማስመጣት በተለያዩ ቦታዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች ይከፍል የነበረውን አሠራር በማስቀረት ዕቃው ደረቅ ወደብ ከደረሰ በኋላ በማስከፈል ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገው መሆኑም ሌላኛው ፋይዳ ነው። ስርአቱን ቀድሞ ከነበረውና አሁንም በአማራጭነት በስራ ላይ ካለው የዩኒ ሞዳል ስርአት ጋር በማነጻጸር የገለጹት ዳይሬክተሩ  ቀደም ባለው አሠራር ወይም በዩኒ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓት አስመጪው ከባህር ትራንስፖርት አጓጓዡ ጋር ውል ይፈጽማል፤ እንደገና ለየብስ ማጓጓዙ ሥራ ከየብስ አጓጓዡ ጋር ውል ይፈጽማል። ከዚያ ባህር ወደብ ዕቃውን ክሊር አድርጎ ለየብስ አጓጓዡ ከሚያስረክብለት ትራንዚተር ጋር ውል ይፈጽማል። በመልቲ ሞዳል ግን በአንድ የጉዞ ሰነድ በአንድ ውል ከአንድ አጓጓዥ ድርጅት ጋር ብቻ በመዋዋል ዕቃውን የሚፈልገው ቦታ ድረስ ማጓጓዝ መቻሉ አገራዊ ጥቅም አለው ብለዋል:: ዕቃውን በማጓጓዝ ሒደቶች ላይ ያሉትን ውጣ ውረዶችና ማንኛውንም ዓይነት ችግር ሁሉ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ኦፕሬተሩ ኃላፊነቶች ስለሚሆኑ፣ ተመራጭ የአገልግሎት ዓይነት ነው ብለዋል።

እሳቸው ይህን ቢሉም በተለይ በደረቅ ወደብ አካባቢ ያለው አገልግሎት ኋላቀር፤ በዘመናዊ መሳሪያና በሰለጠኑ ባለሙያዎች ያልተደራጀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁንም የወጪ/ገቢ ንግዱን ማቀላጠፍ ያልተቻለ መሆኑን ሌሎቹ ባለድርሻ አካላት የገለጹ ሲሆን የድርጅቱ ሃላፊም በዚህ ቅሬታ ላይ ተስማምተዋልና የሱዳን ባለሃብቶች መሰረታዊ ጥያቄ ተገቢ ይሆናል ማለት ነው።

በሌላ በኩል ትራንስፖርት ባለስልጣን ከጅቡቲ መንግስት ጋር ሆኖ ሊያከናውነው የሚገባው ከጅቡቲ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ጋላፊ ያለው የ162 ኪሎ ሜትር መንገድ ፍጹም መንገድ ሊባል አለመቻሉ፤ 162 ኪሎ ሜትርን በ8 ሰአት ጉዞ እንዲያጠናቅቁ ለተገደዱት አሽከርካሪዎች የወጪ/ገቢ ንግዱን ማሳለጡ ይቅርና ለተጨማሪ የትራፊክ አደጋና ስልቹነት፤ ይልቁንም የጫኑትን ጭነትና የሚያሽከረክሩትን ተሽከርካሪ ለአደጋ በማጋለጥ እየተጓዙ መሆኑን መስክረዋል፤ እናም የሱዳን ባለሃብቶች ጥያቄ ተገቢነት ይኖረዋል።

የጉሙሩክ መፈተሻ ኬላዎች ጠባብና ወረፋቸው ዘግናኝ መሆን፤ ለ(ከፋ)ሙስና ተጋላጭ መሆናቸውና በዘመናዊ መፈተሻ መሳሪያ እንኳን ያልተሟሉ መሆን፤ በተለይ ከአዋሽ- ጅቡቲ ድረስ ያለው በረሃ በሆቴል፣ የምግብና መጠጥ፣ የውሃ (መታጠቢያ እና መጸዳጃን ጨምሮ)፤ እንዲሁም በመኝታ አገልግሎት ያልተደራጀ መሆኑ፤ ይህ ቀርነት ደግሞ በአሽከርካሪው ላይም ሆነ በጭነቱ ላይ አደጋና ስጋትን ሁሌም ያዘለ የመሆኑ ጉዳይ በሚመለከታቸው ሁሉ በሚታወቅበት አግባብ እስከዛሬ ተመልካች ማጣቱ የሱዳን ባለሃብቶችን ጥያቄ “ተገቢ” እንድንለው ያስገድደናል።

ከሁሉም በላይ ጎልቶ የወጣው ግን የጋላፊ-ጅቡቲ መንገድ በሚገባ ቢሰራና 8 ሰአት የሚፈጀው ጊዜ ከ3 ባልበለጠ ሰአት ተጠናቆ (ምልልሱ ቢበዛም) የሞጆ ደረቅ ወደብ ከላይ በተመለከተው አግባብ በዘርፉ ሙያተኞች ያልታገዘ፤ በዘመናዊ የመጫኛ እና ማውረጃ እንዲሁም ሌሎች የአይሲቲ ቴክኖሎጂዎች ባልተደራጀበት አግባብ አሁንም ከዚህ የፈጠነ እና የተሳለጠ የወጪ ገቢ/ንግድ ማከናወን አዳጋች እንደሚሆን በተሳታፊዎቹ እና ባለድርሻ ከነበሩ አስተያየት ሰጪዎች ተረጋግጧል። እናም፣ የሱዳን ባለሃብቶችን ጥያቄ “ተገቢ ጥያቄ” ነው ብለን ማለፍ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይም ይህን ፈርተውና ሰግተው የሚቀሩ ሌሎች የውጭ ባለሃብቶችን ታሳቢ በማድረግ መንግስት ዘርፉን በሚገባ ሊፈትሸው፣ ሊመረምረውና ሊያርመው ይገባል፤ ባስቸኳይ!!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy