Artcles

ለአርሶ  እና አርብቶ አደር ህይወት መለወጥ

By Admin

August 22, 2017

ለአርሶ  እና አርብቶ አደር ህይወት መለወጥ

አባ መላኩ

 

ኢትዮጵያ ልማትን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው በሚል መረባረብ ከጀመረች ሀያ አምስት ዓመታት አልፈዋል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ዘርፈ ብዙ የልማት ግንባታ  እየተከናወነ ይገኛል። በአገሪቱ ፍትሃዊ ልማትን እውን ለማድረግና በተለይም ባለፉት ሥርዓታት ትኩረት ተነፍገው የነበሩ አርሶና አርብቶ አደሮች ከዚህ ልማት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የግብርና ልማትን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራበት ይገኛል። አርብቶና አርሶ አደሩ ተዘፍቀውበት ከነበረው የከፋ ድህነት ተላቀው የተሻሻለ ህይወት እንዲኖሩ ለማስቻል ቀላል የማይባል ለውጥ ተካሂዷል።

 

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ነች። በአገሪቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕጋዊ እውቅና አግኝተው የተወከሉ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቁጥርም 75 ደርሷል። የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ ቢሆንም አብዛኛው ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና ነው። ከ85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖርና በግብርና ሥራ የሚተዳደር በመሆኑ በግብርናው ዘርፍ እየተካሄደ ያለው ልማት የህዝቡን ጥያቄ የመለሰ ሆኗል።

በዚህ ማዕቀፍ ከሚገኙት ህዝቦች መካከል የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ህዝቦች ይገኙበታል። እነዚህ ህዝቦች በተለይም በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ አካባቢዎች የሰፈሩ ናቸው። እነዚህ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጠረፋማ አካባቢዎች ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች ከ15 ሚሊዮን በላይ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል።

የአርብቶና ከፊል አደር ህዝቦች ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በንጽጽር ሲታዩ በሁሉም መልክ ተጠቃሚነታቸው የቀነሰ ነው። በአሁኑ ወቅት በመላ ኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ በፈጣን የዕድገት ምህዋር ላይ ይገኛል። የመንገድ፣ የስልክ፣ የመብራትና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ተስፋፍተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የመሠረተ ልማት ዝርጋት ግን ከቀደሙት ሥርዓታት በተወሰነ ደረጃ መሻሻል ቢያሳይም ከተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ጋር ሲነጻፀር አሁንም ገና ብዙ ይቀረዋል። በነዚህ አካባቢዎች ያለውን እውነታ ማየት ይቻላል። የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንመልከት። አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ያለው የልማት ለውጥ ከሌላው የአገሪቱ ክፍል ካለው በእኩል ደረጃ መጓዝ አልቻለም። እነዚህ አካባቢዎች መሠረተ ልማት በተፈለገው መልኩ ካልተስፋፋባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው።  

 

በአካባቢዎቹ የመሠረተ ልማት አለመስፋፋት ደግሞ የአገልግሎት ተቋማት እንዳይስፋፋ ከፍተኛ መሰናክል ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል። የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎቶችን በሚፈለገው ደረጃ የሚገኝበት ሁኔታ አልነበረም። ለመሠረተ ልማትም ሆነ ለአገልግሎት ተቋማት በተፈለገው መልክ አለመስፋፋት ዋናው ምክንያት አካባቢዎቹ በቀደሙት ሥርዓታት ትኩረት ተነፍጓቸው የነበሩ ስለሆነ ነው።

በአገራችን በህዝብ ድምጽ ልማታዊ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ ለአካባቢዎቹ የተለየ ትኩረት በመስጠት የአገልግሎት ተቋማትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና  በሚፈለገው መልክ ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ጋር ተጣጥሞ መሄድ አልቻለም። ለዚህም መሰናክል ከሆኑት ዐበይት ምክንያቶች መካከል የሕዝቡ በተወሰነ ሥፍራ ተረጋግቶ አለመኖሩ ነው።

አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ ህዝብ አንድ የተወሰነ የሚኖርበት ሰፈርም ሆነ መኖሪያ የለውም። የሚተዳደረው በእንስሳት ዕርባታ በመሆኑ የእንስሳት ግጦሽና ውኃን ፍለጋ ወቅትን ተከትሎ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በመዘዋወር መኖር ግድ ሆኖበት ዓመታት ተቆጥረዋል።

 

በዚህ ሁኔታ የሚኖረው የአካባቢው ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በመሥራት ላይ ይገኛል። የዚህን ህዝብ ችግር በጊዚያዊነት ለመፍታት መንግሥት ከማኅበረሰቡ አኗኗር ጋር የሚጣጣም ማህበራዊ አገልግሎት ማቅረብን ነው። በዚህ መልክ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ተንቀሳቃሽ እንዲሆኑ ተደርጓል።

አርብቶ አደሩ አንድን ሰፈር ለቆ ወደ ሌላ ሰፈር በሚጓዝበት ወቅት የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም የሰው ኃይላቸውንና ቁሳቁሳቸውን ይዘው ከአርብቶ አደሩ ጋር አብረው እንዲሄዱና በሚያርፉበት አካባቢም ሆነው አገልግሎቱን ያለማቋረጥ እንዲሰጡ የማድረግ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራበት ነው።

 

በዚህ መልክ የተወሰነ ርቀት መሄድ ተችሏል። ይህ የመፍትሄ አካል ግን የአርብቶ አደሩን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚችልና የልማት ተጠቃሚነቱን ሙሉ በሙሉ ሊያረጋግጥ የሚችል አይደለም። መፍትሄው በጊዚያዊነት አርብቶ አደሩን ለማገዝ የተወሰደ ነው። ከዚህ አንድ ዕርምጃ ወደፊት በመሄድ ሌላ መፍትሄ ማፈላለግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።

እንደሚታወቀው ከ1983 ዓ.ም በኋላ በአገሪቱ በተፈጠረው የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት አቅጣጫ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ህዝብ ህይወት ለመቀየር የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተነድፈው በመተግበራቸው መሠረታዊ ለውጦች መታየት ጀምረዋል። መንግሥት አገሪቱን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በመተግበር ላይ በመሆኑ አገሪቱ በዚህ የዕድገት አስተሳሰብና የዕድገት ምህዋር ውስጥ ገብታለች።

 

በዚህ መልክ የተቀረፀው የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ የአርብቶ አደሩ ጉዳይ በሰፊው እንዲያካትት በመደረጉ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት በተወሰነ ደረጃ እየተረጋገጠ መጥቷል። የአርብቶና የከፊል አርብቶ አደሩን ህይወት መቀየር የሚያስችል የሥራ እንቅስቃሴ ለማድረግ በልማት ስትራቴጂው ከሰፈሩ ታላላቅ አጃንዳዎች አንዱ አካባቢውን ማልማት ነው። የአርብቶ አደሩ አኗኗር በእንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሁሉንም አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር በቀጥታ ወደ አርሶ አደርነት በአንድ ጊዜ መቀየር ስለማይቻል ኑሮውን ለመለወጥ እየተደረገ ያለው ጥረት በሁለት መንገድ የሚፈፀም ይሆናል።

 

አንደኛው አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ ባለበት ሁኔታ ኑሮውን ማሻሻል እንዲችል ማገዝ ነው፤ ሌላው ደግሞ በዘላቂነት ወደ አርሶ አደርነት እንዲለወጥ ማድረግ ነው። የመጀመሪያውን አቅጣጫ ለማስፈፀም ተንቀሳቃሽ የአገልግሎት ተቋማትን ማስፋፋት ነው። አርብቶ አደሩ ለእንስሳት ግጦሽና ውኃ ፍለጋ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ አብረው የሚንቀሳቀሱ ትምህርትና ጤና ተቋማትን ማስፋፋት ነው። የሰውና የእንስሳት የህክምና ባለሙያዎች በሰፊው በመመደብ አርብቶ አደሩ ጋር እንዲኖሩ እየተደረገ ነው። እነዚህ ባለሙያዎች ከአርብቶ አደሩ ጋር እየተዘዋወሩ እየኖሩ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር ይጥራሉ።

በተመሳሳይ መልኩ ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶች በማዘጋጀትና መምህራንን በመመደብ የአርብቶ አደሩ ልጆች የትምህርት ማዕድ ተቋዳሽ የሚሆኑበት መንገድ ተመቻችቶላቸዋል። መንግሥት የአርብቶ አደሩን ችግር ለመፍታት የወሰደው ርምጃ መጀመሪያ አርብቶ አደሩ ያሉበትን ችግሮች ለይቶ ማውጣት ነበር። በመሆኑም ሦስት ዐበይት ችግሮች ተለይተዋል።

 

የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች በልማት ወደ ኋላ የቀሩ በመሆኑ በህዝቡ የሥራ ባህል አለመዳበር፣ አማራጭ የገቢ ማስገኛ መስኮች አለመኖር፣ ሥር የሰደደ የሥራ አጥነት ችግር መኖሩ ዋናው ችግር ነበር። ሌላው ደግሞ ምንም እንኳን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ለውጦች ቢታዩም አሁንም በአንጻራዊነት ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት በሚፈለገው መጠን ባለመስፋፋታቸው ችግሩ አሁንም አለ። አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ ህዝብ ያልተደራጀና ተበታትኖ የሚኖር መሆኑ የህዝቡን የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በሚካሄደው ጥረት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

 

በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደተመለከተው የአርሶ አደሩን ችግር በጊዚያዊነት ለመፍታት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማጠናከር በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል። በዘላቂነት ኑሮውን መቀየር የሚቻለው ከአርብቶ አደርነት ተላቆ የተረጋጋ ህይወት መምራት ሲችል ነው። የተረጋጋ ህይወት ሊኖረው የሚችለው ደግሞ የራሴ የሚለው ቋሚ መንደርና መኖሪያ ሲኖረው ነው።

ይህ ማለት ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት መቀየር ሲችል መሆኑ እሙን ነው። አርብቶ አደሩ ህዝብ ወደ አርሶ አደርነት በመቀየር ከዚያም አርሶ አደሩን ከድህነት ለማላቀቅ እየወሰደ ያለውንና በርካታ የአርሶ አደሮችን ህይወት በመቀየር በርካቶች ወደ ኢንቨስተርነት መቀየር ያስቻለውን የግብርና ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመጠቀም ህይወታቸው ለመቀየር እየተሰራ ነው።

 

ከዚህ ባሻገር በአርብቶ አደርነት የሚኖር ህዝብ ኑሮው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ተረጋግቶ ስለ ህይወቱ መሻሻል የሚያስብበትና ትምህርትና ሥልጠና የሚወስድበት እዕድል ይኖረዋል። በመሆኑም የማስፈሩ ዓላማ አንድም ተበታትነው የሚኖሩትን በማቀራረብ ማህበራዊ ቁርኝታቸውን የበለጠ ለማሻሻል ነው። በሌላ መልክ ደግሞ የተረጋጋና የተሻሻለ ህይወት እንዲኖረው ለማድረግ ነው።

 

በመሆኑም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመንደር የማሰባሰብ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ትላልቅ ልማቶች በሚካሄድባቸው አካባባዎች ህዝቡን በመንደር የማሰባሰቡ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። በተለይም የስኳር ልማት እየተስፋፋባቸው ባሉ አካባቢዎች በኦሞ፣ በወልቃይትና በአፋር እየተገነቡ ባሉ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በልማቱ ምክንያት ለሚነሱ ነዋሪዎች መንደርን ገንብቶ የማስፈር ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። በቤንሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎችም አርሶ አደሩ የሚኖረው ተበታትኖ ስለነበር በመንደር የማሰባሰቡ ተግባር ቀጥሏል። በዚህ መሠረት ባለፈው ጊዚያት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በመንደር ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮቹ ተበታትነው የሚኖሩ በመሆኑ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በአርብቶ አደሩ አካባቢ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የአርብቶ አደሩን አኗኗር በመቀየርና በማሻሻል ረገድ የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው።