Artcles

ለድርድር የማይቀርበው የህግ የበላይነት

By Admin

August 31, 2017

ለድርድር የማይቀርበው የህግ የበላይነት

                                                      ታዬ ከበደ

መንግስትም ሆነ ገዥው ፓርቲ በየትኛውም ጊዜ የህግ የበላይነትን ለድርድር አቅርበው አያውቁም። ዜጎች በህግ የበላይነት እስካልተመሩ ድረስ ማንኛውም ዓይነት አዋጅ፣ ህግና ደንብ እንዲሁም መመሪያ ሊተገበር እንደማይችል ይገነዘባሉ። መብትና ግዴታቸውንም ሊያስፈፅሙና ሊፈፅሙ እንደማይችሉም እንዲሁ።

ይህም በአገር ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ አሉታዊ ጫናን ይፈጥራል። እናም ሁሉም ዜጋ የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር አገራዊ ሃላፊነቱን መከወን የእለት ተእለት ተግባሩ ሊያደርገው የሚገባ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት ሊሸራረፍና ህገ-ወጦች እንዳሻቸው የሚሆኑበት አውድ የለም። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህ የህግን የበላይነት የማረጋገጥ ጉዳይ በመከባበበርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተውን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የመሰረቱት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔሰቦችና ህዝቦች ያስገኙት ነው። የአገራችን ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት የህግ የበላይነትን ፅንሰ-ሓሳብ የተገነዘበና የሚያጋጥሙትን ነባራዊ ችግሮችን በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ እየፈታ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው።

እንደሚታወቀው በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። የመኖር ዋስትና በሌለበት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የሚደረስ ይመስለኛል።

ታዲያ ያኔ መብት ሰጪና ነሺ በጉልበታቸው የሚተማመኑ ኃይሎች ይሆናሉ። ጉልበተኞቹም ልክ እንደ ጎንደሮቹ ህገ-ወጦች ሌሎች ዜጎችን እንዳሻቸው ለማድረግ መሻታቸው አይቀሬ ነው።

እንኳንስ ዜጎችን ቀርቶ፣ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ የሚተጉ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎችን ጭምር በአጉራ ዘለለልነት እስከመግደል ሊደርሱ ይችላሉ። ለዚህም የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ህገ ወጦች ፖሊስንና የፀጥታ ሃይሎችን መግደላቸውን የኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለፓርላማ ካቀረበው ሪፖርት መገንዘባችንን እናስታውሳለን።

እናም ይህን ሁኔታ ለመከላከልና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር የግድ ይላል። በጎንደር ውስጥ በሻዕቢያና በተላላኪዎቹ አማካኝነት ለተከናወነው የሁከት ተግባር ተጠያቂ የሚሆኑት ተጠርጣሪዎች ሁኔታም ከዚህ አንፃር መታየት ይኖርበታል።

እርግጥ መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየደረጋቸው ከመጣው መንገድ መውጣት የለበትም።

መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በህጉ አግባብ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የተጎጂዎችን እምባ ማበስ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ የተመሰረተውን ስርዓት በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም።

ይህ የመንግስት የህግን ልዕልና የማረጋገጥ እርምጃ በህዝቦች ደም ስልጣን ላይ ለመውጣት ለሚሹ አሸባሪዎች፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ፅንፈኞች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ እነርሱ የሚመኙት ዓይነት ምህዳርና ህዝብ አለመኖሩን እንዲገነዘቡ ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንጂ፤ በደማቸው ፍላፃነትና በአጥንታቸው ወጋግራነት የገነቧት ሀገራቸው እነርሱ እንደሚመኙት ዓይነት በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህገ-ወጦችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ከተያያዙት ድህነትን ድል የመንሳት ትግል አንድም ስንዝር ቢሆን ፈቀቅ ሊሉ የሚያደርጋቸው አይደለም።

እርግጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው።

ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚኖርባት ይመስለኛል።

የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሰላምን እንጎናፀፋለን። ሰላምን ስንጎናፀፍ ደግሞ የምናውዳቸውን የልማትና የዴሞፐክራሲ ስራዎችን ዕውን እናደርጋለን። ህጎች ለአንዱ የሚሰሩ ለሌላው ደግሞ የማይሰሩ ለሆኑ አይችሉም።

ህግ ለድርድር ሳይቀርብ ሲቀር ሁላችንም በህግ ፊት እኩል እንስተናገዳለን። የሚያንስም ይሁን የሚበልጥ አይኖርም። የህግ የበላይነት ሲኖር ሁላችንም ከሚገኘው ሀገራዊ ጥቅም ተካፋዩች እንሆናለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሀገራችንን ህገ መንግስት አክብረን እናስከብራለን።

እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑ፤ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደሆነ፤ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ህገ መንግስቱን የማክበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ይደነግጋል። ይህን የህግ የበላይነት አለመፈፀምና ለድርድር ለማቅረብ መሞከር መልሶ ከህገ መንግስቱ ጋር መጋጨት ይሆናል።

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችን የምታከብረው የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ስለሚያዛት ብቻ ነው። ስርዓቱ ደግሞ ህዝቦች በበርካታ መስዕዋትነት ያመጡት ነው። ራሳቸው ይሁንታ እነዚህ ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የፈቀዱት ነው። ሰብዓዊ መብቶችን በማይነካና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የህግ የበላይነትን የማስከር ስራ እንዲከናወን ይፈቅዳል።

በአጠቃላይ ሰላምን እውን ለማድረግ፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የህግ የበላይነት እውን እንዲሆን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

ስለሆነም የህግ የበላይነትን ማስከበር የፌዴራላዊ ስርዓቱ ምሰሶ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህም መቼምና በምንም ዓይነት ሁኔታ የህግ የበላይነት ለድርድር እንዳይቀርብ ያደርገዋል። ምክንያቱም በህግ የበላይነት ላይ መደራደር የስርዓቱን ምሶሶ እንደመናድ ስለሚቆጠር ነው።