CURRENT

መለስን ለማድነቅ…ከበቂ በላይ ምክንያት አለኝ

By Admin

August 24, 2017

ሰሞኑን ነው፤  ባሳለፈነው ሳምንት፡፡ ወደ ፌስ ቡክ መንደር ጎራ በማለት በራሴው ገፅ ላይ እንዲህ የሚል ሃሳብ አኖርኩ፤ “ከሳምንት በኋላ ወደ ፌስቡክ ስመለስ ምን ታዘብኩ? ድህነትን እና ጠበቃውን ካሸነፈ ከዚህ ዘመን ታላቅ መሪ ይልቅ፤ ነጭን ስላሸነፈ የዚያ ዘመን መሪ ወሬ መበርከቱን፡፡ ምን አልባት አባቷን ሳታውቅ አያቷን ናፈቀች ሆኖብን ይሆን?”፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ የፌስቡክ ተጓዳኞቼ ማለቴ ጓደኞቼ የቻሉትንና ማለት የፈለጉትን ያህል ሁሉ በውስጥ መስመር ሳይቀር አሉኝ፤ ወረዱብኝ፡፡ በተቃራኒውም ልክ ስለመሆኔ በላይክና በውስጥ መስመር የነገሩኝን አላጣሁም፡፡ እኔም የሰዎቹን ማንነት ሳይሆን የሀሳባቸውን ምንነት ሰከን ብዬ መዘንኩ፡፡ በተለይም በውስጥ መስመር የደረሱኝ ወቀሳና ስድቦችን ከስሜት ወጥቼ ለመመልከት ወሰንኩ፤ አደረኩትም፡፡ በመጨረሻም እንዲህ ስል ልጽፍ ተገደድኩ፡፡ “መለስን ለማድነቅ 100 አመት አል ጠብቅም፣ ከበቂ በላይ ምክንያት አለኝ” አዎን ታላቁን መሪ ለማድነቅ 100 አመት አልጠብቅም፡፡ ከበቂ በላይ ምክንያት አለኝ። እኔ ያመንኩበትን እናገራለሁ፤ እጽፋለሁም፡፡ በፌስቡክ ገጼም ብቻ ሳይሆን በዚህ አይነቱ ነጻ የጋዜጣ አምድ ላይ ጭምር፡፡ ይህንን የእኔን ሀሳብ ተቃውሞ መጻፍ ደግሞ ስልጣኔ ስለሆነ ሃሳቡን አከብራለሁ፤ ካመንኩበት እቀበለዋለሁ፤ ካልሆነ ደግሞ እሞግታለሁ፡፡ ይሄ ማንም ሳይሆን ታላቁ መሪ ታግለው የፈጠሩት ስርዓት የሰጠኝ መብት ነው፡፡ ይሄንን ለማድነቅ ደግሞ ዛሬ እንጂ 100 አመት አልጠብቅም፡፡ በመግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ያሳለፍነው ሳምንት የሚኒሊክ የልደት ቀን በመሆኑም ጭምር ይመስለኛል ከተቀሩት ቀናት በተለየ መልኩ የፌስቡክ መንደር ምኒሊክ ምኒሊክ ሲል ከርሟል፡፡ እውነት ነው ለአገር ባለውለታ ይሄን ያህል ክብር መስጠት ትክክልና ተገቢም ነው፡፡ እንዲያውም ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይሆንም፡፡ ከልብ ከሆነ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ አንዱ ሰው ስላደረገው ብቻ የሚያደርገው ነገር ይበዛልና ነው፡፡ ለማንኛውም ወደ ሃሳቤ ልመለስ፡፡ በግሌ ማንኛውም መሪ በዘመኑ ለሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ መመስገን አለበት የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ምኒሊክም ቢሆኑ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የትናንቱን መሪ መልካም ነገር የሚያመሰግን አንደበትና ብዕር የዛሬውን አይቶ እንዳላየ የሚሆን ከሆነ ሚዛናዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ አመስጋኝነቱም ወገናዊ ይሆናል፡፡ ስለሆነም የምኒሊክ ልደት ነው ተብሎ ብዙ የተወራበት ሳምንት የታላቁ መሪ አምስተኛ ሙት አመትም የሚከበርበት ነበርና ስለ ታላቁ መሪ ምንም አለማለት መብት ቢሆንም ሚዛናዊ ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡ የእኔም ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ሚዛናዊነት ላይ፡፡ አንድ ራሱን ሚዛናዊ ነኝ ብሎ የሚያምን ሰው በሚጽፈውና በሚናገረው ነገር ላይ እንዴት ግልጽ ስህተት ሊፈጽም ይችላል? እንዴትም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ትልቅ ስህተት በማይጠበቁ ሰዎች አማካኝነት ሳይቀር ሲፈጸም አይቻለሁ፤ አንብቤያለሁ፡፡ መለስን በዘመኑ በሰሯቸው ስራዎች የሚወቅስ ሰው፤ ምኒሊክ ምንም የሚያስወቅስ ስራ አልሰሩም ካለ የዚህ ሰው ሚዛናዊነት የት ላይ ነው? በተመሳሳይ መለስ በዘመናቸው ምንም የሚያስወቅስ ስራ አልሰሩም ካልንም ምኒሊክ የሰሯቸውን ስህተቶች ለመናገር ሞራል አይኖረንም፡፡ ይሄ ምንም የማያከራክር ሀቅ ነው፡፡ ፌስቡኩን የሞላው የሀሳብ ጎርፍ ግን ከዚህ የተዛነፈ ነው፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ምኒሊክ የስልክ፣ የመኪና፣ የባቡር፣ የዘመናዊ ትምህርት፣ ነጭን የማንበርከክ ወዘተረፈ ፋና ወጊነታቸው ሲሰበክ ባጅቷል፡፡ እስማማለሁ፡፡ እውነትም ነው፤ ምኒሊክ ስልክን ወደ ኢትዮጵያ ያመጡ፣ መብራትንም ያስተዋወቁ፣ ምንም እንኳን አልቆ ባያዩትም የባቡርን ትራንስፖርትን ያስጀመሩ፣ ወራሪ ፋሽስትን ድል የነሱ ወዘተረፈ የሆኑ ታላቅ መሪ ናቸው፡፡ ነገር ግን እርሳቸው ምንም ስህተት አልሰሩም፤ የዘመናቸው መልአክ ነበሩ ብዬ አላምንም፡፡ ስለሆነም ከግዛት ከማስፋፋትና ማስገበር ጋር በተያያዘ በሰዎች ላይ (በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ) ያደረሱት ግፍና ጭፍጨፋ፣ ወንጀለኛን የሚቀጡበት መንገድ፣ ለዛሬዋ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል የፈጸሙት ስህተትና (አንድን ህዝብን ከሁለት እንዲከፈል የሰሩት ስህተት)…ሌላም ሌላም አብሮ መነሳት የነበረበት የእርሳቸው ስህተት ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ይሄንን ይሄንን አይነቱን ጉዳይ ማንም አያነሳውም፤ ገብስ ገብሱን እንጂ፡፡ ቢያነሳውም የሃሳብ ውርጅብኙ አይጣል ነው፡፡ ለምን? አንድ ሚዛናዊ ነኝ የሚል ሰው እኮ ሚዛኑን እኩል ይሰፍራል እንጂ “ሁሉም ሰው እኩል ነው፤ እንትና ግን በጣም እኩል ነው” ሲል አይሞግትም፤ ስለሚዛኑም ትክክለኛነት አይከራከርም፡፡ ስለዚያ ዘመኑ ሚኒሊክ ፋና ወጊነት አውርተን ስናበቃ፤ ስለዚህ ዘመኑ ፋና ወጊ ታላቅ መሪ መለስ ዜናዊ አለማውራት ከሚዛናዊነት መስመር መውጣት ነው፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ከነችግሩም ቢሆን ዴሞክራሲን ያስተዋወቀ መሪ ማነው? ከምኒሊክ ዘመን ጀምሮ የተቆለለውን ድህነት መናድ የጀመረና ያስጀመረ መሪስ የቱ ይሆን? የአንችልምን መንፈስ የሰበረ፣ በራስ አቅም መስራትና መለወጥ እንደሚቻል ለአፍሪካ የሰበከና ያስሰበከ መሪ ማን ይሆን? የምዕራባዊያንን መስመር ትቶ፤ በራሱ መንገድ ተጉዞ ለውጥ አምጥቶ ራሳቸው ምዕራባዊያኑን ሳይቀር ሳይወዱ በግዳቸው ያስጨበጨበ የኢትዮጵያ መሪ የቱ ነው? ተቃዋሚ ፓርቲ ብሎ ነገር በዚህች አገር ያስጀመረ መሪና የፕሬስ ነጻነትን አጎናጽፎ ሲያበቃ ራሱን ሳይቀር በፕሬሱ(በጋዜጣም በመፅሃፍም) በውሸትም ጭምር እንዲዘለፍ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ኢትዮጵያዊ መሪ ከመለስ ውጭ ይሄ ነው በሉኝና እንከራከር እስኪ? ጎበዝ እየተስተዋለ እንጂ! ይሄንን ይሄንን አለመየት «አይነስውርነት» አይደለም፤ የአስተሳሰብ  ድህነት እንጂ፡፡ እንዴት የእነዚህን ሁሉ ተግባራት ፋና ወጊ መሪ አለማድነቅ ይቻላል? እንዴትስ ይሄንን ለማድነቅ ሌላ ጸረ ዴሞክራት መሪ ልንጠብቅና አወዳድረን “መለስ ይሻላል ልንል እንችላለን?” (ዛሬ ምኒሊክ የተሻሉ ናቸው እየተባለ ያለው ከእርሳቸው በኋላ ከመጡ መሪዎች ጋር ተነጻጽረው መሆኑን ልብ ይሏል) በምን ሂሳብስ መለስን ለማድነቅ 100 አመት እንጠብቃለን! እደግመዋለሁ እየተስተዋለ! ምኒሊክ በዘመናቸው የጀመሩት ግዛትን የማስፋፋት ተግባር ለኢትዮጵያ አንድነት ነው የሚል ስያሜ ሰጥተን ስናበቃ አሁን ያለውን የፌዴራሊዝም ስርዓት ከፋፋይ ነው የምንልበት ሞራልም ስሌትም አይኖረንም፡፡ የሚኒሊክ ግዛትን የማስፋፋት ያንን ለመተግበር የተከተሉት መንገድ ብዙ እልቂት ያስከተለ ቢሆንም በዘመኑ ልክ ነው ከማለት ውጭ  ልወቅሳቸው አልችልም፡፡ አሁን ያለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ለማንነት እውቅና የሰጠ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያጎናጸፈ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተከወነ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፤ ስርዓቱም የተከበረው እንደዚያ ዘመኑ ሁሉ በጉልበት ሆኖም ቢሆን ኖሮ ድርጊቱን ስህተት ነው ለማለት አላፍርም፤ አልፈራምም፡፡ ምክንያቱም ጉልበት ለዚህ ዘመን የማይመጥንና የማይገባም አማራጭ ነውና፡፡ እንደመታደል ሆኖ ግን የታላቁ መሪ ፌዴራሊዝም በህዝቦች ይሁንታ የተካሄደ ዴሞክራሲያዊም የነበረ ስለሆነ ከማመስገንና ከማድነቅ ውጭ አማራጭ የለኝም፡፡ ይሄንንም ለማድነቅ ደግሞ የግድ 100 አመት መጠበቅ የለብኝም፡፡ከበቂ በላይ ምክንያት አለኝና። በግሌ ታላቁ መሪ የሰሯቸው ስራዎች በአብነት መልክ ከላይ ከጠቃቀስኳቸውና  ከምናውቀውም በላይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን እርሳቸው በህይወት ዘመናቸው እያሉ ስለ እርሳቸው እንዲወራ አለመፈለጋቸው፤ ካለፉም በኋላ በሚዲያውና የመለስ ፋውንዴሽን በተባለው ተቋም ድክመት የተነሳ ገና አቶ መለስን ማወቅ ባለብን ልክ አውቀናቸዋል አልልም፡፡ አምስት አመት እየተጠበቀ የሚለቀቀው መረጃ ብቻም የእኝህን መሪ የአገር ባለውለታነት የሚመጥን አይደለም፤ አይሆንምም፡፡ ስለሆነም አካሄዱ ቢቀየር የተሻለ ነው እላለሁ፡፡ በአጭሩ ግን ማለት የምችለው የዚያን ዘመን መሪ ስናደንቅ የዚህን መዘን መሪም ዘንግተን መሆን የለበትም፡፡ ይሄንን ማድረግ መብት ቢሆንም ሚዛናዊ ግን አይሆንም፡፡ ሚዛናዊ አለመሆን አሁንም መብት ቢሆንም ሚዛናዊ ነኝ ብሎ መከራከር ግን ስህተት ነው፡፡ ስለሆነም የታላቁ መሪ ዘመን ጥቃቅን ህጸጾችን እየመዘዘ ትልቁን ስዕል ላለማየት የሚደረገው ሽቅድድም መቶ ሜትር እንጂ ማራቶን አይሆንም፡፡ ማራቶኑ እውነታው፤ ማራቶኑ ሚዛናዊነት፣ ማራቶኑ መለስን ለማድነቅ 100 አመት አለመጠበቁ ነው፡፡ አበቃሁ!

አርአያ ጌታቸው