Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሙስናን መዋጋት የሃገርን ዘላቂ ሠላም የማስጠበቅ ጉዳይ ነው

0 518

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሙስናን መዋጋት የሃገርን ዘላቂ ሠላም የማስጠበቅ ጉዳይ ነው

ብ. ነጋሽ

ሰሞኑን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ነጋዴዎችና ደላሎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። እስከአሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ቁጥር 55 ደርሷል። ሙስና በአንድ ግለሰብ የሚፈጸም ሳይሆን ተገቢ ባልሆነ የጥቅም ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ሰንሰለት ሰላለው በቁጥጥር ስር ሊውሉ የሚችሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር መጨመሩ እንደማይቀር ይገመታል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ በሙስና የተገኘ ገንዘብ በአክስዮን ድርሻ፣ በሽርክና ወይም በሌላ መንገድ ኢንቨስት እንደተደረገባቸው የሚያመለክት መረጃ የተገኘባቸውና ከሙስና ተጠርጣሪዎቹ ጋር የገንዘብ ትስስር አላቸው ተብለው የተገመቱ 210 ተቋማትና ግለሰቦች ሃብታቸው እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል። ህዝብ ይህን የመንግስት እርምጃ በበጎነት ተመልክቶታል። ይሁን እንጂ አሁንም የመንግስትን ሙስናን የመከላከል ቁርጠኝነት የሚጠራጠሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን ቀላል አይደለም።

ሙስና ለመልካም አስተዳደር መጓደል ቀዳሚው ምክንያት ነው። ሙስና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶችን ያደናቅፋል። ይህም የህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። የሙስና መዘዝ በዚህ አያበቃም። ሙስና ከሰላም እጦት ጋር ተመጋጋቢ የሆነ ተግባር ነው። ሙስና መልካም አስተዳደርን በማጥፋት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልንና የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት በማዛነፍ ህዝብ መንግስቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ ያደርጋል።

በሙስና የተጨማለቁ ባለስልጣናት፣ ጥቅማቸውንና የሃብታቸው ምንጭ የሆነውን ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ አምባገነን ይሆናሉ። የልማት ተጠቃሚነት እጦት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛነፍና አምባገነንነት ህዝብ በመንግስቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ፣ እንዲቆጣና ለአመጽ እንዲነሳ ያደርጋል።  ይህ የህዝብ መንግስቱ ላይ አመኔታ ማጣት የአክራሪዎችና አሸባሪዎች፣ የጠባቦችና ትምክህተኞች እንቅስቃሴ ስር እንዲሰድ ማድረግ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። ሙስና የሰላም እጦት ዋነኛ መንስኤ ነው። ሙስና ገዢ በሆነበት ስርአት፣ የእርስ በርስ ግጭትና ሽብርተኝነትም ገዢ ይሆናሉ።

በሌላ በኩል በእርስ በርስ ግጭትና በሽብርተኝነት የሚታመስ ሃገር ለሙስና አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። ሙስና ለሰላም መደፍረስ መንስኤ የመሆኑን ያህል፣ የሰላም መደፍረስና የህግ የበላይነት መጥፋት ለሙስና አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ሙስናና የሰላም እጦት ተመጋጋቢ ሁኔታዎች ናቸው። ሙስና የሰላም መደፍረስ ምክንያት ይሆናል፤ የሰላም መደፍረስ ለሙስና አመቺ የሆነ ሁኔታን ያደላድላል። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው የዓለም ሃገራት የሙሰና ኢንዴክስ ይህን በግልጽ ያሳያል። በሙስና ደረጃ የዓለማችን የመጨረሻ ሀገራት ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ናቸው። እነዚህ ሃገራት በሰላም ደረጃም የዓለማችን የመጨረሻ ሃገራት ናቸው። ሙስናን በጣም አስፈሪ የሚያደርገው ይህ እውነታ ነው።

ሙሰኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አይፈልጉም። የሰላም መስፈንና የህግ የበላይነት መረጋገጥ ሙሰኞችን ስፍራ ያሳጣል። በሙስና ያገኙትን ጥቅምና፣ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚገለገሉበትን ስልጣን ያሳጣቸዋል። ሰላም የሰፈነበትና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ሁኔታ ለሙሰኞች መቀመቅ ነው። በመሆኑም ሙሰኞች የሰላምና የህግ የበላይነት ቀበኞች ናቸው። ሰላም የህግ የበላይነት ተረጋግጦ መቀመቅ ከሚወርዱ፣ ሃገር ብትጠፋ ይመርጣሉ። ከሃገር ሸሽተው መኖር የሚያስችላቸው ሃብት በውጭ  ሃገር ስለሚያከማቹ፣ የሃገር መፍረስ ብዙም አያሳስባቸውም። የሚያሳስባቸው የሰላም መስፈንና የህግ የበላይነት መረጋገጥ ነው።  

እንግዲህ፣ የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የሙስና አደጋ የተረዳው ይመስላል። ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት ሙሰኛ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የወሰዳቸው የህግ እርምጃዎች፣ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠርና ሙስናን የመቆጣጠር ዓላማ ያለው የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በአዋጅ እንዲቋቋም መደረጉ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ይሁን እንጂ ህዝብ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኘነት እንዲጠራጠር የሚያደርጉ ሁኔታዎች አሉ። ሙስና በስውር የሚሰራ ይሁን እንጂ ተጽእኖው ይፋ ነው። በኢትዮጵያ ይህ የሙስና ተፅእኖ በአዋጅ የተፈቀደ እስኪመስል በይፋ ይታያል።

በፌደራልም ይሁን በክልል ፍርድ ቤቶች ፍትህ ማግኘት፣ ጭው ባለ በረሃ ውሃ የማግኘት ያህል ተስፋ የሌለው ጉዳይ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ፍርድ የሚሰጠው እውነትና ማስረጃ ላለው ሳይሆን ገንዘብ ላለው ነው።  የፍትህ ሚዛን ተዛንፏል።

ይህ የፍትህ ሚዛን መዛባት ዜጎች ፍትህን በገንዘባቸው እንዲገዙ የሚያስገድድ ሁኔታን ፈጥሯል። የፍርድ ቤት ሙግት ያላቸው ሰዎች እውነት ቢኖራቸውም ባይኖራቸውን በብቁና ሃቀኛ ጠበቃ የመወከል ፍላጎት የላቸውም። ፍትህን በዘነጉት ፍርድ ቤቶች የህግ እውቀትና ሃቀኝነት ቦታ የላቸውም። ጠበቆች የሚመረጡት ከዳኞች ጋር ባላቸው ቅርበትና ፍርድን በጉቦ ለማግኘት ባላቸው ድፍረት ነው። ብቁና ሃቀኛ ጠበቆች ቤተሰባቸውን ማስተዳደር እንኳን የማይችሉ መናጢ ድሆች ሆነው ቀርተዋል። በሌላ በኩል የሙስና ተላላኪ ጠበቆች መኪና የሚቀያይሩ፣ ውድ የመኖሪያ ህንጻዎችን የገነቡ በእንድልቅ የሚኖሩ ባለጸጎች ናቸው። ይህ የሃገራችን የፍትህ ስርአት ውስጥ የሚታይ ተጨባጭ እውነት ነው።

በኢትዮጵያ ያለው ሙስና ተጨባጭ ማሰረጃ ለሚፈልጉት የጸረሙስና አቃቤ ህጎች እንጂ ለህዝቡ የተሰወረ አይደለም። ህዝቡ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ፕሮጀክቶች፤ የህክምና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች፣ መንገድ፣ ግድብ፣ ፋብሪካዎች ግንባታ ጋር በተያያዘ ያለውን ምዝበራ በሚገባ ያውቃል። ለምዝበራው ቅርብ የሆኑ ከምዝበራው የማይደርሳቸው የበታች ሰራተኞች – ጸሃፊዎች፣ የሂሳብ ሰራተኞች፣ ሹፌሮች . . . የሚሰራውን እያንዳንዱን የሙስና ድርጊት ጠንቅቀው ያውቃሉ። በህዝቡ ውስጥ ስለሚኖሩ ህዝቡም ይህ መረጃ ይደርሰዋል።

መንግስት ከሚከፍላቸው ደሞዝና ጥቅማጥቅም አንጻር ሲታይ በሺህ እጥፍ የሚበልጥ ሃብት ያላቸውን የመንግስት ባለስልጣናትን ህዝብ ያውቃል። ከአስር ሺህ ብር የማይበልጥ ደሞዝ እያገኙ በሚሊየን በሚቆጠር ብር የመኖሪያ ህንጻዎች ያስገነቡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ነብሰጡር ሚስቶቻቻው በታይላንድ ባንኮክ የህክምና ክትትል የሚያደረጉና በአሜሪካ የሚገላገሉ ባለስልጣናትም እንዲሁ በርካቶች ናቸው። ቤተሰቦቻቸው የእረፍት ጊዜያቸውን በኢሲያ፣ በአወሮፓ ሃገራት እንዲሁም በአሜሪካ የሚያሳልፉትም እንዲሁ በርካቶች ናቸው። እነዚህን የስራ ሃላፊዎች ህዝብ አንድ፣ ሁለት ብሎ ያውቃቸዋወል።

የስነምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን/መንግስት ግን ይህን ህዝብ በገሃድ የሚያወቀውን እውነት ማየት የቻለ አይመስልም። በዚህ ምክንያት ህዝብ መንግስት ሙስናን ለመከላከል ያለው ቁርጠኝነት ላይ እመነት አጥቷል።

መንግስት በሙሰኞች ላይ እርምጃ ሲወስድ የቆየ ቢሆንም፣  እርምጃው ወቅት ጠብቆ አንድ ወቅት ላይ ብልጭ ብሎ  በዘመቻ መልክ ህዝብ ከሚያውቃቸው ሙሰኞች ላይ ጨለፍ አድርጎ የሚጠፋ መሆኑም ህዝብ መንግስትን ማመን እንዳይችል አድርጎታል። ሙስናው ሁሌም ያለ ሆኖ ሳለ፣ ሙሰኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ በየአምስት ዓመቱ ዙር እየጠበቀ ብቅ የሚል መሆኑ፣ እርምጃው ሙስናን ከመከላከል ይልቅ የህዝብን የተቃውሞ ስሜት ማብርጃ ስልት ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጓል።

ይህ ብቻ አይደለም። በተለይ ከሰባት ዓመት በፊት የተጀመረው የከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሃብት ምዝገባ ጉዳይ ይፋ መሆን አለመቻሉ ህዝብ መንግስት ሙሰኞችን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኝነት በእጅጉ እንዲጠራጠር አድርጓል። መጠራጠር ብቻ ሳይሆን ሙስና በስርአቱ ውስጥ የበላይነት አግኝቷል የሚል ስጋት እንዲያድርበት አድርጓል። ሁላችንም እንደምናውቀው የሃብት ምዝገባው ይፋ ይደረጋል ከተባለ እንኳን አምስት ዓመት ሊሞላው ነው።

የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የሃብት ምዝገባ ሰነዱን በድረ ገጹ ላይ እንደሚያሰፍር በተደጋጋሚ ሲናገር መቆየቱ ይታወቃል። ይህ ግን ከወሬ አልፎ እውነት መሆን አልቻለም። ህዝብ፣ መንግስት ይህን ሰነድ ይፋ ማድረግ የፈራበት ምክንያት ስጋት አሳድሮበታል። ይህ ሁኔታ  ህዝብ ላይ ውዥንብር መፍጠር ለሚፈልጉ ቡድኖችም መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል። ንጸሃኑን ከሙሰኞቹ መለየት የሚያስችል ምንም መረጃ ባለመኖሩ ህዝብ ሃቀኞቹን በጥርጣሬ እንዲያይ ሃሰተኛ የሃብት መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ እየተለቀቀ ይገኛል።

በአጠቃላይ ሙስና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማደናቀፍ ከድህነት የመላቀቂያ ተስፋን የሚያጨልም ብቻ አይደለም፣ ሃገር ሊያፈርስ የሚያስችል የሰላም መጥፋት ስጋት ምንጭ ጭምር ነው። በመቶ ሚሊየን የሚቆጠር የህዝብ ሃብት የዘረፉ ሙሰኞች በኢትዮጵያ ሰላምና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የፈልጋሉ ብሎ ማሰብ፣ መጥፊያቸውን ይፈልጋሉ ብሎ ከማሰብ የተለየ አይደለም።

እናም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከሚፈጠሩት ሁከቶች ጀርባ፣ ሙሰኞች ከለየላቸው የትርምስ ቡድኖች ጋር አብረው ላለመኖራቸው ማረጋገጫው ምንድነው? ከነቤተሰቡ በውጭ ሃገር የተደላደለ ኑሮ መኖር ለሚችል ዘራፊ፣ እርሱን መቀመቅ የምትከት ሰላም የሰፈነባትና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ምኑ ናት? እናም ለሃገራችን ዘላቂ ሰላምና ለህግ የበላይነት መከበር ሙስናን እንዋጋ።           

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy