Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

    “ሰላም ከፈለክ ትግልህን መድፉ ከመተኮሱ በፊት አድርገው”

0 2,765

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

    “ሰላም ከፈለክ ትግልህን መድፉ ከመተኮሱ በፊት አድርገው”

የጊዜ ልቃቂትን ወደኋላ አሽከርክረን ታሪክ ስንቆፍር የፈረንሳይ ጦረኛ መሪ የነበረውን ናፖሊዮን ቦናፓርቲን እናገኘዋለን፡፡የአሮፓውያኑ የዘመን ዕድሜ 1821 ዓመታት ሲሞላው ወታደራዊና አብዮታዊው ናፖሊዮን ጨጓራውን ታመመ ተብሎ ከአልጋ ቁራኛነቱ ሳይነሳ በተኛበት እስከወዲያኛው አሸለበ፡፡

በመፈንቅለ መንግሥትና አብዮት፣ በጦር ሜዳና ረጃጅም ዘመቻዎች አብዛኛው አውሮፓን በጉልበት ለመጠቅለል ሲኳትን ኑሮ በ51 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው ይህ መሪ ከህይወቱ ተሞክሮ የተናገራቸው አባባሎች አሉት፡፡

ያን ሁሉ የጦርነት እልቂትና ዘመቻ ከማካሄድ ይልቅ መነሻውን ማስቀረት ነበር ጀግንነትስ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ ህይወቱ ከማለፉ በፊት ባሉት የመጨረሻዎቹ ጥቂት ዓመታት የሰላም እንጂ የጦርነት አሸናፊ ወገን እንደሌለውም መስበክ ጀምሮ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ከእሱ አንደበት በወጡ ወርቃማ አባባሎች አስደግፈው አቅርበዋል፡፡

የመሪዎች ብቃት መለኪያው ጦር አዝምቶ ማታኮስና የተቃራኒ ወገን ሰዎችን መግደል አይደለም፤ ብቁ መሪ ይህ እንዳይሆን አበክሮ እርምጃ በመውሰድ የጦርነት መንገዶችን ቅርንጫፍ ሳያበጁ ዘግቶ የሚያስቀር መሪ ነው የሚል አቋም ላይ ደርሶ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከሚታወቁለት አባባሎቹ መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ “ሰላም ከፈለክ ትግልህን መድፉ ከመተኮሱ በፊት አድርገው” (If they want peace nations should avoid the pin-pricks that precede cannon shots)ጦርነት የተሻለ አማራጭ መስሎት በዘመቻ መሪነት ሲዳክር የኖረው የፈረንሳዩ የቀድሞ መሪ ቦና ፓርቲ የተናገረው የሩቅ ዘመን አባባልን ማንሳቴ የግጭት አማራጭ አዋጭነት እንደሌለው የሚያስረዱ የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ጠፍተው አይደለም፡፡

ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ አበው ከታሪኩ ባለቤቶች፤ የክስተቱ ፈጣሪና ዋና ተሳታፊዎች የተቀዳ የህይወት መመሪያ ቁም ነገር አይጠፋውም በሚል ነው በመልካ ምድር ከኛ ከራቀችው አውሮፓዊት ሀገር ፈረንሳይ የታሪክ መጽሐፋቸውን የተዋስኩት፡፡

“ጦርነት ወይም ግጭት አማራጭ አይሆንም” የሚለው የቀድሞው የፈረንሳይ መሪ ናፖሊዮን ቦና ፓርቲ (1769-1827 እ.ኤ.አ.) የቆየ አባባልን እውነተኛነት ግጭት መገለጫው የሆነው የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ሁኔታ አሳምሮ ያስረዳናል፡፡

በጥንታዊነቷ፣ በሥልጣኔዋና በሰማይ ጠቀስ ፎቆቿ የምትታወቀው ሶሪያ ጦርነት ክፉኛ ደቁሷት ትላንት ከነበረችበት የክብር ማማ ላይ ቁልቁል ተንሸራታለች፡፡ ታሪካዊቷ የደማስቆ ከተማ ወደ ቀድሞው ውበቷ ለመመለስ 50 እና 60 ዓመታት ይወስዱባታል እስክትባል ድረስ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይራለች፡፡ በንግድ ማዕከልነቷ ወደር ያልነበራት ሌላኛዋ የሶሪያ ሁለተኛ ግዙፍ ከተማ አሌፖም ከ6 ዓመታት በፊት የነበረውና የአሁኑ ቁመናዋ በፍፁም አይገናኝም፡፡ የእርስ በርስ ጦርነቱ ህይወታቸውን የነጠቀባቸው የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር ከሩብ ሚሊዮን (250 ሺ) በላይ ተሻግሯል፡፡

በአጭር አገላለፅ የአሁኗ የተጎሳቆለች ሶሪያ ከ6 ዓመታት በፊት ከነበረችው ሶሪያ ጋር ቆሞ ለመወዳደር የሚያስችላት አንድ እግር እንኳን የላትም፡፡ ጦርነት፣ ግጭት አማራጭ አይሆንም የሚለው ሀሳብ በተለይም ለሶሪያ የተነገረ ይመስላል፡፡

ከ45 ዓመታት በላይ የዘር ሀረግ እየተመዘዘለት የዘለቀው የፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ ሥልጣን ማብቃት አለበት ብለው ጠመንጃ ያነሱ ተቃዋሚዎችና የፕሬዚዳንቱ ታማኝ ኃይሎች እየተቆራቆሱ ሀገሪቱን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ ዘፍቀዋታል፤ የእነሱ ጦስም ለንፁሃኑ ተርፎ ከሞት የተረፉት ዕድለኛ ቁስለኞች ሰላም ከራቀው የትውልድ ቀያችን የማናውቀው የባዕድ ሀገር ይሻለናል ብለው የስደት ሲሳይ ሆነዋል፡፡

በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሃ ይጠጣል የሚለው አባባል የደረሰባቸው ቱርክ፣ ሶሪያና ዮርዳኖስ የመሳሰሉ የሶሪያ አጎራባች ሀገራት የሀገሪቱ ስደተኞችን በመቀበል ተጠምደው ከርመዋል፡፡ የቀጠናው ሰላም መናጋት ትኩሳት ለእነሱም ተርፏል፡፡ የፕሬዚዳንት አልአሳድ ታማኝ ኃይሎችና ተቃዋሚዎች ሜዳ የጠበባቸው እስኪመስል ድረስ የጦር አውድማውን አስፍተው በቱርክ ግዛትም ተዋግተዋል፡፡ ሂደቱ ዛሬም መቋጫ አላገኘም፡፡

ጦርነት ወይም ግጭት አማራጭ አይሆንም ሲባል በመጨረሻ አንደኛው ወገን የበላይነት አይዝም ማለት አይደየለም፡፡ ልክ ያልሆኑ አካሄዶችን ለማስተካከል ተብሎ የሚደረግ የኃይል እርምጃ ህዝብ ካላመነበት ይዞት የሚመጣው የመጨረሻ ውጤቱ ቀድሞ ከነበረው አካሄድ ቢብስ እንጂ የተሻለ አይሆንም በሚል የዚህ ሀሳብ አራማጆች ትንተና ይገለፃል፡፡ ወዳጆቼ ተቀምጠን የሰቀልነው ቆመን ለማውረድ እንዳያስቸግረን!

በጎ ተግባራቸው የድሆች እናት የሚል መልካም ስም ያተረፈላቸው እናት ትሬዛ ሰላም የሚጠፋው አንዳችን ለሌላችን አለኝታ፣ የአንዱ መኖር ለሌላው ህልውና መሆኑን ሙሉ በሙሉ ስንዘነጋው ነው በሚለው አባባላቸው ይታወቃሉ፡፡ የፍቅር ሀይል የበላይነት በያዘበት መንደር በሰላም መኖር አይቸግርም፡፡ እውነተኛ ፍቅር ካለ ልዩነት ሰላም እንዲጠፋ ምክንያት አይሆንም፡፡

ዊሊያም ጄ ክሊንተን የተባሉ ፀሐፊ በ1997 እ.ኤ.አ. ባሳተሙት መፅሐፋቸው ይህን ያስረዳሉ፡፡“በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ያለው ትክክለኛ ልዩነት በጂውሽና በአረቦች፣ በፕሮቴስታንትና በካቶሊክ፣ በሙስሊሞችና በክርስትና ወይም በሰርቦች መካከል አይደለም፡፡ እውነተኛው ልዩነት የሚገኘው ሰላምን በሚጠብቁና ሰላምን በሚያጠፉ፣ የወደፊቱን ሁኔታ ማየት በሚፈልጉና ወደኋላ ተመልሰው ያለፉ ክስተቶችን በሚመለከቱ መካከል፣ የጦር መሳሪያ በሚያነሱና በባዶ እጃቸው እንጂ በጦር መሣሪያ በማያምኑ ላይ ነው” ይላሉ ፀሀፊው፡፡

በዚህ ሀሳብ ድምዳሜ መሠረት የግጭት መንስዔው የማንነት ጥያቄ አይደለም፡፡ የሰላም መደፍረስ ዋናው ምክንያቱ በተቃራኒ ጎራ የቆሙና በመካከላቸው ሰፊ ርቀት ባላቸው የሀሳብ ልዩነቶች ነው፡፡ እርግጥ ነው ሰው ሁሉ ሀሳቡ ተጨምቆ አንድ ይሁን አይባልም፡፡ ሰው የፈለገውን ሀሳብ የማራመድና ባመነበት መንገድ አቋም መያዝ ይችላል፡፡ ይህ አካሄድ እንደ ግለሰብ ችግር አለው ተብሎ አይወሰድም፡፡ ይሁንና አንድ ግለሰብ የሚይዘው አቋምና የሚያራምደው ሀሳብ ሁሉም ወደ ጎጂ ውጤት ያመዝናል ወይም ሁሉም መልካም ፍሬ እንደማይኖረው የተሰወረ ሐቅ አይደለም፡፡

ስለ ሰላም በፃፉት መፅሀፍ የሚታወቁት ዊሊያም ክሊንተን ማንነት የሰላም መደፍረስ ሰበብ አይሆንም የሚል ብርቱ አቋም አላቸው፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል የሰዎች በጎሳ፣ በነገድ፣ በሃይማኖትና በብሔር መለያየት የግጭት መነሻ ምክንያት አይደለም፡፡በዓለማችን ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚነግሩን በሚደረጉ ዘመቻዎችና ቅስቀሳ በስሜት ተገፋፍቶ ካልሆነ በስተቀር የሰው አዕምሮአዊ ባህሪ ከሚከተለው ሃይማኖት ውጭ ሌላ እምነት ለሚከተሉ ሰዎች ተፈጥሮዓዊ ጥላቻ ወይም ቅራኔ የለውም፡፡ ችግሩ የሚፈጠረው የሌላ እምነት ተከታዮች እሱ በሚያመልክበት ሃይማኖት ከመጡበት ነው፡፡

ይህ የሚነግረን የግጭት መነሻ የሚሆነው የእምነት አቋም ልዩነት አለመሆኑን ነው፡፡ ሰው በባህሪው የሌሎችን እምነት የመጥላት ተፈጥሮ ከሌላው ፀሀፊው ዊልያም ክሊንተን እንዳሉት የሃይማኖት ልዩነት ሳይሆን የሌሎችን ዝቅ አድርጎ የማየት አካሄድ ነው የሰላም ቀበኛ ሊሆን የሚችለው፡፡

አልፎ አልፎ ደግሞ በውስጣቸው ሌላ ዓላማ ያላቸው ወገኖች የሃይማኖት ልዩነትን ሽፋን አድርገው ህዝብን ከጎናቸው በማሰለፍ ለፈለጉት ዘመቻ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

በብሔር ወይም በጎሳና በነገድ መካከል ያለው ልዩነትም፣ የሃይማኖት ልዩነት ከሰላም ጋር ከሚኖረው ዝምድና ጋር የተለየ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ሲወለድ በተፈጥሮ ያለውን የሰውነት ቅርጽ ይዞ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፡፡ እያንዳንዳችን አሁን ያለንን የቆዳ ቀለም፣ የአፍንጫና የጆሮ አቀማመጥ ወይም ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻችን መጠንና ቅርጽ ይዘን እንድንወለድ የኛ ምንም ዓይነት አስተዋፆ የለበትም፡፡ ስንወለድ በተፈጥሮ ያገኘነው እንጂ እኛ እንዲህ ቢሆን ይሻለናል ብለን ያገኘነው አይደለም፡፡ የብሔር ጉዳይም ሰው ፈልጎ የሚወስነው አይደለም፡፡ ማንም ከኦሮሞ ብሔር ብወለድ ይሻላል ብሎ የተወለደ የለም፡፡ የአጋጣሚ ጉዳይ እንጂ፤ ከአማራ ብሔር ነው መፈጠር የምፈልገው ብሎ የተወለደ ሰው የለም፡፡ በወላጆቹ የመኖሪያ አካባቢ ምክንያትና በሚናገሩት ቋንቋ የትግራይ ወይም የደቡብ ብሔር ተወላጅ የሚል  ስያሜ በወላጆቹ የተሰጠው ነው፡፡ ይህም ሆኖ በተሰጠው ስም መካከልና በሌላ ብሔር ከሚኖር ሰው ወይም ግለሰብ ጋር ምንም ዓይነት ሰዋዊ ባህሪ ልዩነት የለውም፡፡

አስተሳሰብ በተወሰነ ማኀበረሰብ የበላይነት ሊኖረው ቢችልም የሰው ማንነት ልኬታው በሚኖርበት ቦታ ይወሰናል ማለት ግን አይቻልም፡፡ የዚህ መንደር ሰዎች እንዲህ ናቸው የእንትና ሰፈር ሰዎች እንዲያ ናቸው ተብሎ የሰዎች አስተሳሰብን አንድ ስልቻ ውስጥ አስገብቶ መናገርም ተገቢ አይደለም፡፡ እንዲያውም የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚነግሩን እንዲህ ዓይነቱ የጅምላ ፍረጃ ሰዎች ቀድሞ የሌለባቸውን ባህሪያት አውቀውም ሆነ ሳይተዋወቁ ቀስ በቀስ በውስጣቸው እያሳደጉት እንዲሄዱ ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህም ራስን ከሌሎች የተለየን አድርጎ እስከመቁጠር ደረጃ የሚያደርስ መዘዝን ይዞ ይመጣል፡፡ እኛና እነሱ የሚል መልካም ያልሆነና እርስ በርስ በጥርጣሬ የመተያየት አካሄድን ይፈጥራል፡፡ እኛና እነሱ የሚለው ሀሳብ እየጎለበተ ከመጣና ሰዎች በችሎታቸውና በሰብዓዊ ክብራቸው ሳይሆን በማንነታቸው ዋጋ የሚሰጣቸው ከሆነ ደግሞ የእኛና እነሱ ምደባ ጥንስስ ወደለየለት የዘረኝነት አስተሳሰብ ማምራቱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች ወደውና ፈቅደው የአንድ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ይመስል ከዚያ ብሔር ስለተገኙ ብቻ ምንም ይሰሩ ምን አንድ ሰው ከነሱ ወገን ቢያጠፉ እንኳ “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረጥ ተወቀጥ” ዓይነት እርምጃ፣ ውግዘትና ጥላቻ ሊከተላቸው ይችላል፡፡

የሰላም ጥቅም ጎልቶ የሚከሰትልን ሰላም በራቀን ወቅት ወይም የሚያስፈራን ጫካ ውስጥ በድቅድቅ ጨለማ ስንጓዝ ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ ሰላም ከሌለ ሰው ያለበት ቦታም ጭር ያለ ባዶ ሜዳም ወይም የከተማ ውስጥ አስፓልት በራሱ አስፈሪ ድባብ ይኖረዋል፡፡ ሰላም ከሌለ የሕግ የበላይነት አምዱ ከሥሩ ተገርስሶ በመውደቅ የዜጎች ከለላ መሆኑ ይቀራል፡፡ በሕግ አምላክ መባልን ሰምቶ ከድርጊቱ የሚቆጠብ ባለጉልበትም አይኖርም፡፡ ግርግር በነገሰበት ቀጠና ከቤት ወጥቶ መግባት ብርቅ ይሆናል፡፡ የሁከት ዳፋው በዚህ ብቻ ተገድቦ አይቀርም፡፡ የማይተካውን ህይወት ያሳጣል፤ ለስደትና እንግልት ይዳርጋል፤ በአጭሩ ሰዎች ፍርሃት ተጭኗቸው የነገ ተስፋና ዕቅዳቸውን ውሃ በልቶት በሰቀቀን ህይወታቸውን እንዲገፉ ያስገድዳቸዋል፡፡

እንግዲህ የሰላም መጥፋት ጉዳት ጥጉ እስከዚህ ድረስ ከሆነ አማራጭ አጥቼ ነው ብሎ በየትኛውም መንገድ ወደ ግርግርና ሁከት መግባቱ ለማናችንም የሚበጅ አይደለም፡፡ ራልፍ ዋልዶ ኤምርሰን የተባሉት የዓለማችን ስመ ጥር ፀሃፊም በመፅሃፋቸው ይህንን ነው ያሉት፡፡ “ሰላም መቼም ቢሆን በአመፅ አይገኝም፤ ሰላም የሚመጣው በመግባባት ብቻ ነው”፡፡

የሰላማዊ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ (democratic peace theory) አራማጆች ማጠንጠኛም ይኸው መልዕክት ነው፡፡ እውነተኛ የዴሞክራዊ አራማጅ መሪዎች አማራጭ አጥተን ነው በሚል የሰላምን ጉዳይ ገደል ከተው ወደ ጦርነት መሄድን መቼም ቢሆን አማራጭ አያደርጉም የሚል ነው ፅንሰ ሀሳቡ፡፡

ከአፍሪካዊቷ ሀገር ሊቢያ የቅርብ ታሪክ ልንማር ይገባል፡፡

በቁጥር በርከት ባሉ የፊዚክስ ፅንሰ ሀሳቦቹ ዓለም የሚያውቀው አልበርት አንስታይን የሚታወቅባቸው ወርቃማ አባበሎች አንዱ ይህ ነው፡፡

“ችግርን በፈጠርክበት አስተሳሰብ መፍትሄ ማምጣት አትችልም”፡፡ በተመራማሪው አንስታይን አንደበት የተነገረው ይህ አባባል ዛሬም ድረስ እንደሚሰራ የሊቢያ የቅርብ ጊዜ አብዮት ከወለደው ውጤት መረዳት የሚቻል ይመስላል፡፡ ሊቢያ በአውሮፓውያኑ የጊዜ መስፈሪያ ከ2011 በፊት በአመዛኙ ሰላም የነበራት ሀገር ናት፡፡ በአመዛኙ ማለቴ በሰላም ፅንሰ ሀሳብ ትርጓሜ መሰረት የጦርነት አለመኖር ብቻውን በአንድ ሀገር ሰላም አለ ብሎ መናገርን ስለማይፈቀድ ነው፡፡ ውጥረቶች የሚፈቱበት መንገድ በመግባባት እንጂ ደካማው አፄ በጉልበቱን ፈርቶ ፀጥ የሚል ከሆነም ሰላም አለ አይባልም፡፡ ባለጊዜው ቀን የጎደለውን በኃይል አስገድዶና አንበርክኮ ምንም እንዳያደርግና እንዳይናገር አንደበቱን ሸብቦ አማራጭ በማሳጣት ለጊዜው ዝም ቢያሰኘውም በባለሙያዎቹ እይታ አሁንም ሰላም የለም፡፡

ወደ ሊቢያ ልመለስ፤ የሰላም ፅንሰ ሀሳብ ተንታኞች እይታ እንዳለ ሆኖ ይች ሀገር ከአብዮቱ በፊት አንድነቷ የጠነከረና ከአንፃራዊ መልኩ ሰላማዊ ሀገር ነበረች፤ አሁን ግን ያ የተረጋጋ ሁኔታ ከጠፋ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የሀገሪቱ የረጅም ጊዜ አምባገነናዊ መሪ ሙዓመር አል-ጋዳፊ ስርዓት አንገሸገሸን ብለው ጠመንጃ ያነሱ ኃይሎች በእርግጥ ሀሳባቸው ሰምሮ የፈለጉትን አድርገው ነበር፡፡ ይሁንና “ማምሻም ዕድሜ ነው” የሚል ትርጉም ካልተሰጠው በቀር በሀገሪቱ ጎደለ ያሉትን ሰላም እነሱ ሙሉ አድርገውት መቆየት አልሆነላቸውም፡፡ ይባስ ብሎ እነሱ ጉድለት አለበት ያሉትን የሀገሪቱን ሰላም ከነ አካቴው ገደል ከተው ሽባ አደረጉት፡፡

በአብዮቱ ማግስት ብጥብጥ ናላዋን ያዞራት ሊቢያ ራሳቸውን በ ናቸው እንደ መንግሥት በሚቆጥሩ ሁለት ቡድኖች እየተመራች ትገኛለች፡፡ የሀገሪቱ መንግሥት እኔ ነኝ የሚለው አንደኛው ቡድን ትሪፖሊንና አካባቢውን ተቆጣጥሯል፡፡ በሌላው የሀገሪቱ ክፍል መንግሥት እኔ ነኝ የሚል ሁለተኛው ቡድን አለ፡፡ በቀሪዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጠረውን የፀጥታ ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የሚያቆበቁቡ ስርዓት አልበኞች ተፈልፍለዋል፡፡ በእነዚህ መካከል በየጊዜው ግጭት ተከስቷል፡፡ ንፁሃን ሊቢያዋን ሰላም ብርቅ ሆኖባቸው ችግሮቻቸውን እንደታቀፉ ይኸው ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የሊቢያ አብዮተኞች ነን ያሉት አካላት “ችግር በተፈጠረበት አስተሳሰብ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም” ለሚለው የአልበርት አንስታይን አባባል መሰረት ትግላቸውን ያስቀጠሉት አይመስልም፡፡ ራሳቸው በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጋዳፊ ዘመን ተፈፀመ ብለው የኮነኑትን የኃይል እርምጃ እነሱው መልሰው ደገሙት፡፡ ሰው ያለፍርድ እንዴት ይገደላል ብለው በአደባባይ መፈክር ይዘው እንዳልወጡ ሁሉ ያንን ሁሉ ረስተው እነሱው መልሰው ሰው በአደባባይ- መግደልን ስራዬ ብለው ተያያዙት፡፡

የሊቢያ አብዮተኞች ቸግር በተፈጠረበት መንገድ ችግርን ማስወገድ አልቻሉም፡፡ ጦርነትን አማራጭ አድርገው እነሱ የፈለጓትን ሰላም ማምጣት አይደለም እንዲያውም አዳፈኑት፡፡

ሊቢያ እንደ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦችና የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች ሀገር አይደለችም፡፡ ይሁንና አመፅን መሰረት ያደረገው እንቅስቃሴ የሀገሪቱን የአንድነት ምሰሶ ገርስሶታል፡፡ እንግዲህ አንድነት የነበራት ሀገር ሊቢያን የበታተነ የአመፅ አማራጭ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ሃይማኖት መገኛ ለሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የአመፅ አማራጭ በሊቢያ ከተጋረጠው የተለየ ውጤት ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም፡፡

ሆኖም ሰላም ስለፈለግነው ብቻ እና ስለተዘመረለት የሚመጣ ክስተት አይደለም፡፡ ሰላምን የማቆየትም ሆነ የማጥፋት ስልጣን ግን በእያንዳንዳችን እጅ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው  ክስቶተች ወደ ቅራኔና ወደ ግጭት ከማምራታቸው በፊት ነው፡፡ አለመግባባት ደረጃዎቹ ከፍ ብለው የሰላም ሂደት ከተናጋ የእያንዳንዳችን የተናጠል ሙከራ እና የቀናት የዘመቻ ሥራም ለችግሩ መፍትሄ በቀላሉ ላያመጡ ይችላሉ፡፡

የእነሱና የእኛ የተቃራኒ ጎራ ክፍፍል መቼም ቢሆን ለሰላም በር አይከፍትም፡፡ በህዝብ መካከል የጥላቻ አስተሳሰብ እንዲስፋፋ ጉልበት የሚሆነው ደግሞ በስፋት የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና አሉባልታዎች ናቸው፡፡ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው የሚለው አባባል እንዲህ ዓይነቱን የጥፋት መንገድ ውጤት ለማሳየት የተነገረ ይመስላል፡፡ በተለይ የጥላቻ መልዕክቶች ለህዝብ በተመሳሳይ ሰዓት የሚደርሱበት ቀዳዳ ከተፈጠረ የጠፋ ሰላምን ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ ማጣፊያው ያጥራል፡፡  “ጦር ሜዳ አልፈራም አንዲት ትንሽ ሬዲዮ ጣቢያ ግን በእጅጉ ታስፈራኛለች” የሚለው የቀድሞው የፈረንሳይ ጦረኛ መሪ ናፖሊዮን ቦና ፓርቲ አባባል መልዕክት ይህን ስጋት የሚገልጽ ነው፡፡

“እኛ ከነሱ እንበልጣለን፤ የእነሱ ከእኛ ያንሳል፤ እኛ ታሪካችን ወዲህ ነው የእነሱ ታሪክ ወዲያ ነው” የሚሉ አስተሳሰቦች ህዝብን ለእልቂት ሲዳርጉ ሀገርንም ሲበታትኑ እንጂ አንድነት ሲፈጥሩ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ተዋህዶ እንጂ ተለያይቶ ወዳጅነትን የፈጠረ ሀገር እንዳለ ታሪክ አይነግረንም፡፡ አሜሪካ በፖለቲካውም በቴክኖሎጂውም ታላቅ ሀገር የሆነችው ከተዋሀደች በኋላ ነው፡፡ ጀርመንና ጣሊያንም እንዲሁ፡፡ ኮሪያ ሰሜንና ደቡብ ተብላ ከተከፈለች በኋላ ሁለቱ ሀገሮች በጦርነት ውድ የሆነውን የሰው ህይወትና ንብረት አጥተዋል፤ የወቅቱ የደቡብ ሱዳንና የሱዳን ክስተት ሩቅ ሳንሄድ ማየት እንችላለን፡፡

ጥላቻን በፍቅር በመተካት እንጂ ጥላቻን በጥላቻ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሰላምን በሚመለከት ከተናገራቸው መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፡፡

“ሰላምን በኃይል ማስጠበቅ አይቻልም፤ ሰላም የሚመጣው በመግባባት ብቻ ነው፤ ጨለማን በጨለማ ማስወገድ አይቻልም፤ ጨለማን የሚያስወግደው ብርሃን ብቻ ነው፤ ጥላቻን በጥላቻ ማስወገድ አይቻልም፤ ይህን ማድረግ የሚቻለው በፍቅር ብቻ ነው”፡፡

ስለሆነም በርካታ የጋራ የሚያደርጉን ባህሎች እና ወጎች ስላሉን እነዚህን መሰረት በማድረግ ሕገ መንግስታችን ላይ የተቀመጠውን አንድ ፖለቲካዊ፡ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት መስራት ይኖርብናል፡፡ ሰላሙን ያብዛልን!!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy